ገብረመድህን አርአያ፣ አውስትራሊያ
ኢትዮጵያ ሃገራችን ትልቁ እድሏ ከጥንት ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ብዙ የታሪክ ሊቃውንትና ጸሓፍት ያፈራች ሃገር መሆኗ ነው።
በጥንቱ ዘመን በኢትዮጵያ መቀመጫቸውን አክሱም ያደረጉት ነገሥታት ታሪካቸውን እና ጥበባቸውን በሳብኛና በግእዝ እያጻፉ አዘጋጀተዋል። በመቀጠልም መቀመጫቸውን ወደ ዛጔ፣ ላስታ ላሊበላ፣ ወሎ ሲተላለፍ በዚያ የነገሡ ነገሥታትም ታሪካቸውን እና ጥበባቸውን በግእዝና በአማርኛ እያዘጋጁ አልፈዋል። የነገሥታቱ መቀመጫ ከወሎ ወደ ሸዋ፤ ከዛም ወደ ጎንደር ሲሸጋገር፣ የነበረው ታሪክ፣ ጥበብና የነገሥታቱ ዝርዝር ሁኔታ ተዘጋጅተው ተመዝግበዋል።
የታሪክ ሊቃውንት የነጋሥታቱን ብርቱና ደካማ ጎኖቻቸውን እና የሰሩትን ታሪክና ገድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ በማሳወቅ፣ ሕዝቡም በተራው ያለፉት ነገሥታት የጣሉበትን የጀግንነት አደራ እንዲጠብቅ አድርጎታል። የኢትዮጵያን ሉአላዊነት፣ ዝና እና ክብር እንዲሁም ታሪክና የታሪክ ቅርሶቿ በክብር እንዲንከባከባቸው በሰጡት አደራ መሰረት ኢትዮጵያ ለማንም ቅኝ ገዢ ሳትንበረከክ በዓለም ደረጃ ዝነኛ ሆና የወጣች ሃገር እንድትሆን አድርገዋታል።
የታሪክ ሊቃውንት በ845 በኢትዮጵያ አክሱም ዘመነ መንግሥት በኢትዮጵያ ንጉሥ አንበሳ ውድም ልታወድም የተነሳችው ዮዲት ጉዲት ዙፋኑን ገልብጣ፣ አብያተ ክርስቲያናቱን በማቃጠል፣ ሃውልቶችን እያፈረሰች ታሪካዊ ቅርሶችን በማውደም፣ ክርስቲያኖችን በመጨፍጨፍ ብዙ ከባድ ግፎችን ፈጽማለች። ቀጥሎም በ1515 በአፄ ልብነ ድንግል ዘመን መንግሥት ግራኝ አህመድ የተባለ ጠላት ተነስቶ ብዙ አብያተ ክርስቲያናትን፣ ታሪካዊ ገዳማትን እና ታሪካዊ መዛግብትን ከማውደሙም በላይ፣ ክርስቲያኖችንም አንገታቸውን በሰይፍ እየቀላ ሕዝብ ጨርሷል። ታሪክ ጸሐፊዎችም በዮዲት ጉዲትና በግራኝ አህመድ የተፈጸመውን ግፍ በጥቁር ታሪክነቱ ከትበው ለትውልደ ኢትዮጵያውያን አስተላልፈዋል።
አሁን ባለንበት ዘመን ከሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ የመጣው ገዢ፣ ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ኢትዮጵያን እና ሕዝቧን ከላይ ከተጠቀሱት የኢትዮጵያ ጠላቶች እጅግ በጣም ተወዳዳሪ የማይገኝለት፣ በክፉ መልኩ ኢትዮጵያን እና ሕዝቧን ያወደመ፣ የሃገር ሉአላዊነትን ያፈረሰ፣ ሃገር የሸጠ፣ ወጣት ሴቶችን እና ወንዶችን ለባርነትና ለስደት የዳረገ ነው። ከየት መጣ ሳይባል ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት በመቆጣጠር ሃገር በማፍረስ፣ ሕዝብን ከተወለደበት በማፈናቀል የሚፈጽመውን ፋሽስታዊ ተግባራቱን የታሪክ ጸሐፊዎችና የኢኮኖሚ ሊቃውንት ኢትዮጵያውያን እየጻፉት ነው።
በህዳር 2006 መጨረሻ አስደንጋጭ ዜና በዓለም ሚዲያዎች ተነገረ። የደቡብ አፍሪካው የነፃነት አባት ኔልሰን ማንዴላ ከዚች ዓለም በሞት እንደተለየ ተገለጸ። የዓለም ሕዝብና መሪዎቹ የተሰማቸውን ጥልቅ ሃዘን በማስተላለፍ የኔልሰን ማንዴላን አንጸባራቂ ታሪክና ኤ.ኤን.ሲን በመምራት የከፈሉትን መስዋእትነት፣ በተካሄደው መራራ ትግል ደቡብ አፍሪካን ከአፓርታይድ ስርዓት አላቀው ሃገሪቷን እና ሕዝቧን ነፃ ምውጣታቸውን፣ እስከ ግባተ መሬታቸው ድረስ በትግል የፈጸሙትን አኩሪ ታሪካቸውን እና ገድላቸውን ካለምንም ማቋረጥ በዓለም ዙሪያ ነግሮላቸዋል፣ የሰላምና የእርቅ አባትም ተብለዋል።
በቀብራቸው እለትም ከ100 በላይ የዓለም መሪዎች ደቡብ አፍሪካ ድረስ በመጓዝ ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለም ያልታየ እጅግ የደመቀ የቀብር ስነስርዓት ተፈጽሞላቸዋል። የዚህ ሁሉ ድምር ውጤት ማንዴላ የፈጸሙት የትግል ድልና ታሪክ ነው። ስለሆነም ታሪክ ለባለ ታሪኩ እንደሆነና እንደሚገባ በኔልሰን ማንዴላ ታይቷል። ጥቁር ታሪክ የተሸከመው ወያኔ ህወሓት ደግሞ ከትወልድ ወደ ትውልድ እየተላለፈ፣ እየተረገመና እየተወገዘ ልክ እንደ ዮዲት ጉዲት በሳጥናኤል ምስል እየታወሰ ይኖራል።
የኔልሰን ማንዴላን ህልፈት ተከትሎ የዓለም መሪዎች የተሰማቸውን ሃዘን ሲገልጹ፣ የዓለም ብዙሃን መገናኛዎችም ለሶስት ሳማንታት የቆየ ሰፊ ሽፋን ሰጥተውታል። በዚህም የተነሳ ለህወሓት አመራርና ካድሬዎቹ፣ እንዲሁም የፋሽስቱ ስርዓት መሳሪያ በመሆን የሚያገለግሉት ብአዴን፣ ኦህዴድ፣ ደቡብ ህዝቦች ተብለው በሚታወቁት የገዢው አጎብዳጆች ላይ የራስ ምታት ለቆባቸው ሰንብቷል። ምክንያቱም የህወሓት መሪ ከዚህ ዓለም በሞት ሲቀጠፍ ማንም የዓለም መሪም ሆነ ሕዝብ ከግምት ውስጥ ስለአላስገባው። ሚዲያውን በተመለከተ አልጀዚራና ቢቢሲ ከ2 ደቂቃ ባነሰ ጊዜ መለስ ዜናዊ የኢትዮጵያው አምባገነን መሪ ሞተ ብለው ከመናገር የዘለለ ምንም አልጨመሩም።
በ24/12/2013 በአይጋ ፎረም ርእሰ አንቀጽ “ማንዴላን በማሳበጥ የመለስ ራእይ አይሟሽሽም”!! በሚል ርእስ ስር የተጻፈውን አንኳር አንኳሩን ልዳስስ፤
ከመነሻው ጀምሮ ኔልሰን ማንዴላን በመጥፎ ስምና ተግባር እያብጠለጠለ የመለስ ራይእይን እና ጀግንነት፤ ሀገር ወዳድነት ወዘተ. እያለ ሙግስናውን ይቀጥላል፤
- ጀግናው መለስ ዜናዊ ጦርነት ሳይንስ እንጂ በእድል የሚገኝ አይደለም ብሎ የተነተነ ምሁር ሲሆን፣ ፋሽስት በሆነው ደርግ ላይ ያረጋገጠ ጀግናና የብዙ ጀግኖች ፈጣሪ ነው ይላል፤
በመሰረቱ የዚህ ርእሰ አንቀጽ ጸሐፊ የመለስ ዜናዊን ማንነት የማያውቅ፣ ለጥቅሙ ብሎ በአየር ላይ የሚንሳፈፍ ፊኛ ፍጡር ነው። መለስ ዜናዊ ከተሓህት/ህወሓት ለትግል ከተደባለቀበት ጊዜ አንስቶ በጦርነት ተሳተፍ ተብሎ በግዴታ በተሰለፈባቸው ጦርነቶች ገና የመጀመሪያዋ ጥይት ስትተኮስ ፈርቶ የሸሸ ለመሆኑ በጊዜው የነበሩ የተሓህት ታጋዮች በሚገባ እናውቃለን። በተሓህት ህግና ስነሥርአት መሰረት ከጦርነት ያፈገፈገ ሞት ይፈረድበታል። መለስ ዜናዊ በአደዋ፣ ፈረሰማይ፣ አዲደእሮ፣ ማይቅንጣል፣ ሃገረሰላም፣ አዲ-ኮኸብ፣ ገለበዳ ወዘተ. በተደረጉት ጦርነቶች ፈርቶ የሸሸና ያፈገፈገ ግለሰብ ነው። ለምን እንደሌሎቹ አፈገፈጋችሁ ተብለው እንደተገደሉት መለስ ዜናዊ ስላልተገደለበት ምክንያት በቀዳሚነት የሚጠየቅበትና መልስ የሚሰጠው አረጋዊ በርሄ ነው። ጀግኖች የፈጠረ ማለት ቀልድና ቧልት ነው። ሌቦችን እና ዘራፊዎችን የፈጠረና ራሱም ቀንደኛ ዘራፊ የሆነ ሰው ጀግኖች ሊፈጥር አይችልም። መለስ ዜናዊ ምንም የጦርነት ሳይንስም ሆነ ወታደራዊ ጥበብ የለውም።
- የባለ ራእይነትና አርባኝነት ትልቁ ዓላማው ኢትዮጵያን በአጭር ጊዜ ከበለጽጉት ሃገሮች ጋር እንድትቀላቀል ማድረግ ነው። የትራንስፎርሜሽን እቅዱም የዚሁ ራእይ አካል ነው ይላል። ቀጠል በማድረግም፣ የታላቁ መሪ ራእይ ስኬታማ እየሆኑ መምጣታቸውን እየተመለከትን ነው። የኢትዮጵያን ሕዝብ ከጭቆና በማላቀቅ የኢኮኖሚ ባለቤትነቱን ያረጋገጠ ጀግና ነው ብሎም ያትታል።
ባለርእሰ አንቀጹ ይህን ሲጽፍ ከጠባብ አስተሳሰብ በመነሳት ነው። ህወሓት ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት ከተቆጣጠረበት ከግንቦት 1983 እስከ አሁን ድረስ በሃገሪቱና በሕዝቧ የወረደው ፋሽስታዊ አገዛዝ ረሃብ፣ በሽታ፣ እንክርት፣ መፈናቀል፣ እስራት፣ የሃገር መሬትና ድነበር ለባእዳን መሸጥ፣ ሰቆቃ፣ አፍኖ ማጥፋት ወዘተ. እየተፈጸሙ ያሉት የመለስ ዜናዊ ራእይና የህወሓት አመራሮች እቅድ መሆኑን ማወቅና መገንዘብ መቻል ያለበት ይመስለኛል። በመሰረቱ የርእሰ አንቀጹ ጸሐፊ ህወሓት ማነው? ሲፈጥርስ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት ሆኖ የተፈጠረ ነው ወይ? የሕዝብ ፍቅርና ስሜት መስፈርቱ ነበር ወይ? በኢትዮጵያ ሉአላዊነት ያምን ነበር ወይ? የሚሉትን ጥያቄዎች ያላገናዘበ ከጠባብ ዘርኝነት ስሜት የመነጨ ነው። ውሸት በመደርደር መለስንም ሆነ የህወሓት አመራርን ለልማት የቆሙ አስመስሎ መጻፍ የጸሐፊው አባላት ሳይቀሩ ይታዘቡታል፣ ይንቁታል። ለምን ቢባል፣ ጸረ-ሕዝብና ጸረ-ሃገር የሆነውን የህወሓትን ጥቁር ታሪክ በወርቃማ ቀለም መለወጥ አይቻልምና። ኢትዮጵያን ለማፍረስ ትልእኮው አድርጎ የተነሳ ድርጅት ነው። ከላይ የተጠቀሱትን ኢትዮጵያን ወሮ ከተቆጣጠረ ጀምሮ በተግባር ታይተዋል። ስለሆነም የመለስ ራእይ ለእድገትና ትራንስፎርሜሽን የሚበጅ ሊሆን አይችለም። የመለስና ግብረአበሮቹ ባህሪና የፖሊሲ አቋመቸው ጸረ-ዲሞክራሲ፣ ጸረ-ሃገርና ሕዝብ ነው። በቅጽበት ተለውጠው ለሕዝብና ለሃገር ተቆርቋሪ ሊሆኑ አይችሉም። ዲሞክራሲ ገና ከጅምሩ አንድ ድርጅት ሲፈጠር መሰረታዊ የዲሞክራሲ መሰሶዎች አበጅቶ የሚዳሰስ፣ የሚታይ ጠንካራ የህንጻ ብረት መሳሪያ መሰረቱን የጣለ ከሆነ ነው። ህወሓት ግን ከዚህ ያፈነገጠ ጠባብና ዘረኛ ፋሽስት ድርጅት የዲሞክራሲ መድረኩ አይፈቅድለትም። ስለዚህ፣ የኢኮኖሚ ባለቤትነትን ያረጋገጠ የመለስ ዜናዊ የጀግንነት መግለጫ ነው የሚለው አባባል ከእውነት የራቀ የጠባብ ዘረኝነት አስተሳሰብ ነው። ውሃ የማይቋጥር ቀዳዳ ጣሳ እንበለው።
- መለስ ዜናዊ ከድህነት በላይ አዋራጅ ከድህነት በላይ ክፉ ጠላት የለም የሚለው ራእይ በወሰደው ቆራጥ አመራር የከተማና የገጠር ልማት ፖሊሲዎችና የአፈጻጸም ስልቶች የመለስን የልማት አርበኝነትና ጀግንነት በትክክል የሚያሳይና የሚያርጋግጡ ናቸው ይላል።
የመለስ ዜናዊ የልማት፣ የእድገት አርበኝነት እያሉ በየቀኑ ሕዝብን የሚያደነቁሩ የህወሓት ካድሬዎች ብአዴን፣ ኦህዴድ፣ ደቡብ ህዝቦች ናቸው። ህወሓት የፈጠራቸው ቅጥረኛ ድርጅቶች ሃገር እያፈረሱ፣ ሕዝብን እየጨፈጨፉ ሲሆን፣ መሪያቸው የህወሓት አመራር ድህነትን የተዋጋ፣ ሰፊ የልማት አውታር በመዘርጋት ኢትዮጵያን የለወጠ ብሎ መናገር ከሃዲነት ነው። ወያኔ ህወሓት በ1983 ሃገር ወሮ በቅኝ ግዘቱ ስር ባደረጋት ማግስት የኢትዮጵያ ሁኔታ ሙሉ በሙሉ ተለዋወጠ። ሕዝቡ በርካሽ እየገዛ የሚጠቀምባቸው የምግብ አይነቶች ጤፍ፣ ስንዴ፣ ቅቤ፣ ሥጋ ወዘተ. ዋጋ የሰማይ ጣራ ነካ። እስከ ደርግ ዘመን ፍጻሜ ድረስ ጤፍ በኩንታል ብር 45-60 ይሸጥ ነበር። ቅቤ፣ ዘይት፣ ስጋ ወዘተ. በተመጣጣኝ ዋጋ ይገበይ ነበር። በወያኔ ህወሓት አገዛዝ ቅቤ፣ ዘይት ወዘተ. ከገበያ ጠፍቷል። ጤፍ በኩንታል ብር 1500-1800 ደርሷል። ከአፄ ኃ/ሥላሴ እስከ ደርግ ዘመን ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በቀን ሶስት ጊዜ መብላት ይችል ነበር። በአሁኑ ስርዓት ግን በቀን አንድ ጊዜ ለመብላት የሚታገለው ሕዝብ ቁጥሩ በርካታ ሆኗል። የኢትዮጵያ ሕዝብ በታሪክ አይቶት ለማያውቀው ድህነት ከተዳረገ 23 ዓመት አስቆጥሯል። መራሹ ገዢ ህወሓት የኢትዮጵያን ሕዝብ ለከፋ ረሃብ፣ በሽታና ስደት ዳርጓል። “እንኳንስ ዘንቦብሽ ዱሮውንም ጤዛ ነሽ” እንደሚባለው፣ ከትግሉ መነሻ ጀምሮ እስከ መጨረሻው ወያኔ ህወሓት ለኢትዮጵያና ህዝቧ ጠላት ሆኖ የተፈጠረ ድርጅት ነው። ከ1967 ጀምሮ ሕዝቧን በጎሳና በዘር ከፋፍዬ አጠፋታለሁ ብሎ የተነሳ ድርጅት ነው። ይህንን ከመጠን ያለፈ ጥላቻ ከትግሉ መነሻ ጀምሮ ሲያራምደው የመጣና ዛሬ በተግባር እያሳየው ነው። ምክንያቱ፣ ህወሓት ኢትዮጵያዊ አይደለምና።
የህወሓት ካድሬዎችና ደጋፊዎች የምትናገሩትና የምትጽፉት ገደብ የለሽ ውሸት፣ በሙስና እና በዝርፊያ ባገኛችሁት ንብረት ከነቤተሰባችሁ እየተንደላቀቃችሁ ጠግባችሁ ብታድሩም፣ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የምትነግሩትና የምትጎስሙትን የውሸት ነጋሪት ውድቅ ካደረገው ዓመታት አልፈዋል። ህወሓት፣ ብአዴን፣ ኦህዴድ፣ ደቡብ ህዝቦች በሕዝብ ፊት ቀርባችሁ ፍርዳችሁን የምታገኙበት ጊዜ ተቃርባለች።
ህወሓት ኢትዮጵያን ሲቆጣጠር ተሸክሞት የመጣውን በቀል አማራው፣ ኦሮሞው፣ ጋምቤላው፣ አፋሩ፣ ኦጋዴኑ ወዘተ. ዘር የማጥፋት ተግባሩን ፈጽሞታል። አሁንም እያጠፋ፣ እየገደለ በየወህኒ ቤቶቹ እየማገደው ነው። ይዞት የመጣው ድህነትና በሽታን ብቻ ነው። ፖሊሲው የኢትዮጵያን ሕዝብ ከዓለም ሃገሮች በድህነት ከወለል በታች ያደረገ ስርዓት ነው። የኢትዮጵያ ገበሬ የመሬቱ ባለቤት በነበረበት ወቅት እራሱን እና ቤተሰቡን አብልቶ ቀሪውን ለገበያ በማቅረብ ሕዝቧ እንደአቅሙ በልቶና ጠጥቶ ያድር ነበር። የህወሓት አስተዳደር መሬት የመንግሥት ነው ብሎ በማወጁ የኢትዮጵያ ሕዝብ በገጠሩም በከተማም መሬት አልባ ሆኗል። የኢትዮጵያ ሕዝብ በገዛ ሃገሩ ሁለተኛ ዜጋ ከመሆኑ የተነሳ ሲሞት እንኳን የሚቀበርበት ቦታ ያጣ ሕዝብ ሆኗል። የመለስ ራእይ እድገትና ልማት ነው ተብሎ የተጻፈው፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ በዚህ ሁኔታ ይቀጥላል የሚል አመለካከት ካለው ፈጽሞ ተሳስቷል። የኢትዮጵያ ሕዝብ ለገዢው ስርዓት መቃብር ቆፍሮ እየጠበቃቸው ነው። የሚተርፋቸው ጥቁር ታሪካቸው ከትውልድ ትውልድ መተለለፉ ብቻ ይሆናል።
ይህንን በዚሁ ላብቃ። በሌላ መልኩ ደግሞ መልስ ልስጥህ። “ማንዴላን በማሳበጥ የመለስ ዜናዊ ራእይ አይሟሽሽም” ያልከው ጸሐፊ ይህንን አንብብ።
ለመለስ ዜናዊ ከድህነት በላይ ክፉ ጠላት የለውም ብሎ መጻፉ ትክክል ነው፣ እስማማበታለሁ። መለስ ዜናዊ የድሃ ቤተስብ ልጅ መሆኑ እንዳይታወቅበት ብዙ ጊዜ ሲከላከል እንደነበር የምናውቀ ሃቅ ነው። መለስ ዜናዊ የሹምባሽ አስረስ ተሰማ የልጅ ልጅ ነው። የሴት አያቱም ወ/ሮ ዘውዲቱ መንገሻ ይባላሉ። አድዋ አውራጃ የተወለደው አስረስ ተሰማ ደግሞ ኤርትራዊ ሲሆን፣ መለስ ዜናዊ በትግራይ ያለው ትውልድ በሴት አያቱ ብቻ ነው። ወራሪው ጣልያን ለሁለተኛ ጊዜ በአፄ ኃ/ሥላሴ ዘመነ መንግሥት በተሸነፈበት ጊዜ የጣልያን ባንዳው ሹምባሽ አስረስ ተሰማ በግዞት አድዋ ውስጥ ነበር። በ6 ወራት ጣልያን ሙሉ በሙሉ ተሸንፎ ኢትዮጵያ ነጻነቷን ስትቀዳጅ አስራስ ተሰማ በደረሰበት ድንጋጤ ታሞ ሞተ። ዜናዊ አስረስም ከአድዋ ከተማ ወደ ኤርትራ አልተመለሰም። ቀደም ብሎ በጣሊያን ጊዜ ያገባቺው ሚስቱም አንዴ አድዋ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ አዲኳላ እየተመላለሱ ኖረዋል። ዜናዊ አስረስ ከወ/ሮ አለማሽ ወ/ልኡል መለስ ዜናዊን ጨምሮ 5 ልጆች ወልደዋል። ሌሎች ሁለት ኤርትራውያን ሴቶች ስለነበሩት በጠቅላላው 13 ልጆች አሉት። ዜናዊ አስረስ ጣልያንኛ በመጠኑ ይናገራል፣ ግን አይጽፍም። ዜናዊ አስረስ ሥራ ያልነበረው ድሃ ስለነበር ማመልከቻ ጸሐፊ በመሆን ኑሮውን ይገፋ ነበር። በኤርትራዊነቱ ስለሚታወቅ በአድዋ አውራጃ ውስጥ የእርሻ መሬት አልነበረውም። አባቱ ሹምባሽ አስረስ ተሰማ በሕዝብ ላይ ብዙ ግፍ የፈጸመና በጣሊያን ባንደነቱ የተነሳ አድዋ ውስጥ በጣም የተጠላና የተገለለ ነበር። ይህንን ሁሉም የአድዋ ሰው የሚያውቀው ሃቅ ነው። ድህነት የሚያሳፍርና የሚያሸማቅቅ አይደለም። የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ የድሃ ልጅ ነኝ፣ ስለሆነም አላፍርበትም። በድህነቴ እኮራለሁ እንጂ የሌለኝን አለኝ ብዬ አልመጻደቅም።
መለስ ዜናዊ ግን ይህን አይቀበልም፣ ቤተሰቦቹም ይህን አይቀበሉም። ወንድሞቹ በክፉ ድህነት ያደጉ፣ እህቶቹ እነ ገርግስ ዜናዊ በአሁኑ ጊዜ ሚሊየነር ብትሆንም እንጀራ እየሸጠች ያደገች፣ ኒቆዲሞስ ዜናዊም እንቁላል እየቀቀለና እንጀራ በየጠላ ቤቱ ማታ ማታ እየሸጠ ያደገ ነው። ይህ ሁሉም ሥራ ነው፣ የሚያስከብር እንጂ የሚያሳፈር አይደለም። ዜናዊ አስረስ በአፄ ኃ/ሥላሴ ዘመን የአድዋ አውራጃ ገዢ ነበር ብሎ ዋሸ። የተናገረውን ሁሉ ረስቶ ለሞቱ በተቃረበ ጊዜ አፄ ኃ/ሥላሴ አዲስ አበባ ድረስ አስጠርተው የአባትህን ሥራ ልስጥህ፣ በአታሼ ድረጃ ሥራ ልመድብህ ሲሉኝ አልቀበልም አልኩ በማለት ተናግሯል። የወላጅ አባቴን ሃብትና ንብረት ጠብቄ ለልጆቼ አወርሳለሁ ብዬ ወደ አድዋ ተመልስኩ ብሎ የተናግረውን በድረ ገጾች አይቸዋልሁ። ይህ ሁሉ ደረቅ ውሸት ነው። የሚኖረው ተወልደን ባደግንበት አድዋ ከተማ ነው። እስከምናውቅ ድረስ ምንም አይነት ሃብት የሌለው፣ በማመልከቻ ጸሐፊነት የሚተዳደር ደሃ መሆኑን የወቅቱ የአድዋ ከተማ ሕዝብ ያውቀዋል። መለስም ሥልጣን እንደጨበጠ የደሃ ልጅ እንዳይባል በተክለ ሰውነቱ እንዳትጠጋው አደረጋት። ድህነት አያሳፍርም። በዚህ ዓለም አሳፋሪ ነገር ውሸት፣ ዝርፊያ፣ ሙስና፤ የንጹሃን ደም ማፈሰስ፣ ባጠቃላይ ወንጀል ናቸው። መለስ ዜናዊ የዚህ ሁሉ ቀንደኛ ተዋናይ ነው።
አንድ እውነተኛ ታሪክ ላቅርብ። የታሪኩ ባለቤት የአድዋ ሰው ሲሆኑ አሁን ግን አልፈዋል። ታሪኩን በጊዜው የነበሩ የአድዋ ከተማ ኗሪ የሚያውቁት ትክክለኛ የታሪክ ሃቅ ነው። አባቶቻችን ለኛ ለልጆቻቸው ነግረውና አስተምረው አልፈዋል።
አስረስ ተሰማ የታወቀ የጣሊያን ባንዳ ነበር። ጣሊያን ኢትዮጵያን እንደወረረ አስረስ ተሰማ የጣሊያኖች ታማኝ አሽከር ነበር። በጣሊያኖች የተሰጠው ማእረግ መጀመሪያ ኮማንዳቶሪ ሲሆን፣ ቀጥሎም ካባሌሪ ሆነ። ትንሽ እንደቆየም ሹምባሽ አስረስ ተብሎ ይጠራ ነበር። በአድዋ፣ አዲግራትና አክሱም በርካታ ግፎችን ፈጽሟል። ግለሰቦችን ሁለት እግራቸውን፤ እጆቻቸውን እና ጆሯቸውን በመቁረጥ እስከግድያ በሚደርስ ድርጊት አስቃይቷል። በገበያ ቀን ኢትዮጵያውያንን ሰላይ እያለ ሴት ከወንድ ሳይለይ ለገበያ በወጣው ሕዝብ ፊት አርባ አርባ ጅራፍ በመግረፍ ስፍር ቁጥር በሌለው ሕዝብ ላይ ስቃይ አድርሷል። በዚህ መጥፎ ተግባሩ የታወቀው ሹምባሽ አስረስ ተሰማ ለዓመታት በዚህ አይነት ሲቀጥል፣ የሕዝቡ አቤቱታ ለራስ ስዩም መንገሻ ይደርስ ነበር። ጣልያን ውድቀቱ በተቃረበበት ወቅት፣ ራስ ሥዩም ደጃዝማች ገ/ህይወት መሸሻን ይህንን ሰው እንደምንም ብለህ ይዘህ አምጣልኝ የሚል ትእዛዝ ሰጥተዋቸው ነበር። ደጃዝማቹ አካባቢውን ስለሚያውቁት በሶስት ሳምንት ክትትል አዲኳላ በምትገኘው ማይጫአት፣ ልዩ ስሟ አዲአዝማቲ ከምትባል ቦታ በሌሊት ተከታትለው ሹምባሽ አስረስ ተሰማን ከልጃቸው ዜናዊ አስረስ ጋር ማርከው ያዟቸው። በሌሊት ወደ አድዋ አሸጋግረው ለፊታውራሪ ገ/አምላክ ከነልጁ በግዞት እንዲቆይና ለፍርድ እንዲቀርብ አደረጉ። ፊታውራሪ ገ/አምላክ ማለት የወያኔ ህወሓት መሪ የነበረው በ1993 ከነስየ አብርሃ ጋር የተባረረው የአለምሰገድ ገ/አምላክ ወላጅ አባት ናቸው። አስረስ ተሰማ ለጥቂት ወራት በግዞት ላይ እንዳለ ኢትዮጵያ ጣልያንን አሸንፋ ነጻነቷን ተቀዳጀች። አስረስ ተሳማና ዜናዊ አስረስን የራስ ሥዩም አሽከሮች ይኖሩበት ወደነበረው አድዋ እንዳሥላሴ አዘዋወሯቸው። የጣልያንን ሽንፈት በሰማ ጊዜ ታሞ ከትንሽ ጊዜ በኋላ ሞተ። ሹምባሽ አስረስ በሞተ ጊዜ የሚቀበርበት ቦታ ታጥቶለት ነበር። ጥቂት የሆኑት ቀባሪዎቹ እንዳሥላሴ ቤተ ክርስቲያን በመሄድ በቦታው እንዲቀበር ቢማጸኑም፣ ንብሰ ገዳይና የጣልያን አሽከር በቤተ ክርስቲያናችን አናስቀብርም ብለው ከለከሉ። አስረስ ተሰማ ከቆየባት ቤቱ በግመት 300 ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው እንዳጽዮን ቤተ ክርስቲያን ሂደው ሲጠይቁ፣ ለምን እንዳሥላሴ አትቀብሩትም፣ የቤተ ክርስቲያኑ አለቃ አስረስ ተሰማ በዚች ቅድስት ማርያም ቦታ፣ ገዳይና ከሃዲ የጣልያን አሽከር አናስቀብርም የሚል መልስ ሰጥተው አሰናበቷቸው። በቀሪዎቹ ቤተ ክርስቲያናት እንደ እንዳ መድሃኔዓለም፣ እንዳ ገብርኤል፣ እንዳ ሚካኤል ፈጽሞ የማይታሰብ ሆነ። ያላቸው አማራጭ በረሃ ውስጥ ጉድጓድ ቆፍረው ምቅበር ብቻ ነበር። ማይ ምድማር ውሰዱ ተባሉ። ይህ ቦታ ደግሞ የወንድሞቻችን እስላሞች መካነ መቃብር ነው። በአጥር የተከለለ በጣም ሰፊ ሜዳ ነው። ቦታው በክብር የሚጠበቅ ስለሆነ ማንም ዝር አይልበትም። ስለሆነም እዛም አልተቻለም። እንደ አማራጭ ብለው ያሰቡት ማይ ምድማርን ተሻግሮ በሚገኝ ቦታ ላይ ሆነ። ማይ ምድማር ማለት፣ ከሰሜን በኩል ማይጓጓ ወንዝ፤ በፀሃይ መውጫ በኩል አሰብ ወንዝ የአድዋን ከተማ ለሁለት ሰንጥቆ የሚያልፍ ሲሆን፣ ሁለቱ የሚገናኙበት ቦታ ማይምድማር ተብሎ ይጠራል። አንዳንድ ጊዜም ጉራንጉር ተብሎ ይጠራል። ከማይምድማር ተሻግሮ የሚገኘው ቦታ ደግሞ የእንዳ ጊዮርጊስ መሬት ነው። ብዙ የመስኖ እርሻ ስላለበት ቀባሪዎቹ እዚያ ማድረግ እንደማይችሉ ስለተገነዘቡ፣ ሬሳውን ተሸክመው ወደ ተምቤን በሚያቀና መንገድ ተጉዘው አንድ በማይታወቅ ቦታ ቀበሩት። ከቀባሪዎቹ ከማስታውሳቸው መካከል አቶ ግብረቱ፣ አቶ ገብሩ፤ ልጃቸው ዜናዊ አስረስ ሲሆኑ ቀሪዎቹን ማስታውስ አልቻልኩም። የሹምባሽ አስረስ ተሰማ ሬሳ በረሃ እንደተጣለ አባቶቻን ነግረውናል። ይህንንም በወቅቱ የነበረው የአድዋ ሕዝብ በግልጽ የሚያውቀው ነው። ዜናዊ አስረስ ከሕዝብ የተገለለ፣ ልጆቹም ከሰው ተገልለው ማደጋቸው ሁሉም የሚያውቀው ሃቅ ነው።
መለስ ዜናዊ በቤልጂየም ሆስፒታል መሞቱን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያበሰረው ኢሳት ነበር። ሕይወቱ ያለፈችው ከብዙ ስቃይ ብኋላ ነው። ነብስ ይማር ያለው ኢትዮጵያዊ አልነበረም፣ እሰይ አምላክ ፍርድህን ሰጠህ ከማለት በስተቀር። ሬሳው ኢትዮጵያ ውስጥ ይቀበር አይቀበር አይታወቅም። የአያቱ ሹምባሽ አስረስ ተሰማ ሬሳ የገጠመው አይነት እድል እንደገጠመው እገምታለሁ። የማይቀረው ጊዜ ሲደርስ ስላሴ የተቀበረው ባዶ ሳጥን የአያቱን አይነት እድል እንዲሚያገኝ አልጠራጠርም። መለስ ዜናዊና ግብረ አበሮቹ ኢትዮጵያን ሲቆጣጠሩ በእናቱም በአባቱም የደጃዝማች ልጅ ነው ብለው በድረ ገጽ ተጽፎ አንብቤአለሁ። ከላይ እንደዘረዘርኩት ከእውነት የራቀ ነው። ባንዳዎቹ ኢትዮጵያ ወደ ነፃነቷ እያመራች በነበረችበት ጊዜ አስመራ ለነበረው ጄነራል ደቦኖ አቤቱታ አቅርበው ነበር። የኢትዮጵያ መንግሥት ለራሱ ሰዎች ራስ፣ ደጃዝማች፣ ፊታውራሪ ወዘተ. እያለ ማእረግ ሰጥቷቸዋል። እኛ የጣሊያን አሽከሮች ግን ምንም አይነት ማእረግ አልተሰጠንም። እኛም ልክ እንደ ኢትዮጵያውያኖቹ አይነት ማእረግ እንዲሰጠን እንፈልጋለን ብለው አቤት ብለው ነበር። አቤቱታቸውን ግራዚያኒ ወደ ሮም መንግሥት በማስተላለፍ ሹመቱን እንዲሰጥ ተፈቀደለት። በዚያም መሰረት የጣሊያኑ ባለሥልጣን ለባንዳዎቹ ደጃዝማች፣ ፊታውራሪ ወዘተ. እያለ አምበሸበሻቸው። ለአጭር ጊዜም ቢሆን፣ የዚህ ተጠቃሚ የሆኑት፣ የዜናዊ አስረስ ባለቤት የነበረች አለማሽ ገ/ልኡል፣ አባቷ ደጃዝማች ገ/ልኡል ሲሆኑ፣ ሹምባሽ አስረስም ደጃዝማችነት ተችሮት ነበር። ይሁንና ሳይጠራበት በኢትዮጵያ ጀግኖች ተይዞ ግዞት ገባ። ሌላው የዚህ ተጠቃሚ የነበሩት የስብሃት ነጋ አባት ፍታውራሪ ነጋ ነበሩ። ማእረጉን ባገኙ በጥቂት ወራት ጣልያን ተሸንፎ ሲወጣ፣ እስከ እለተ ሞታቸው ድረስ የአድዋ ሕዝብ በጣልያን የተሰጠውን ፊታውራሪነት አልተቀበለላቸውም። አብዛኛው ኗሪ አቶ ነጋ ሲላቸው፣ ጥቂት የቅርብ ጓደኞቻቸውና ዘመዶቻቸው በጣልያኑ ሹመት ፊታውራሪ ነጋ እያሉ ሲጠሯቸው አውቃለሁ።
ይድረስ ለህወሓት አመራር አባላት፣ ለብአዴን እና የደቡብ ኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ዲሞክራሲይዊ ንቅናቄ
የደቡብ አፍሪካው መሪ ኔልሰን ማንዴላ በሞቱ ጊዜ የዓለም ሕዝብና መሪዎቻቸው መራራ ሃዘናቸውን ገልጸዋል። የዓለም ብዙሃን መገናኛዎችም ሶስት ሳምንታት ሙሉ የኔልሰን ማንዴላን አርበኝነት፣ የንፃነት መሪነታቸውን፣ የሰላምና የፍቅር አባትነታቸውን እና አንጸባራቂ ታሪካቸውን በስፋት ዘግበዋል። ይህ ነው እንግዲህ ታሪክ ለሰሪው፣ ታሪክ ለባለታሪኩ የሚባለው።
መለስ በሞተበት ጊዜ ሕዝብ በቀበሌ ተገዶና ብር 100 የውሎ አበል እየተሰጠው ነው ለቀብር የወጣው። ከዓለም መሪዎች መካከል የተገኙትም ጥቂቶች ናቸው። አብዛኛዎቹም ከነአካቴው የሃዘን መግለጫ እንኳን አልላኩም። ሚዲያውም ቢሆን፣ በጣም ጥቂቶቹ፣ አምባገነኑ መሪ መለስ ዜናዊ ሞተ ብለው ከመዘብ ያለፈ አላደረጉም። የኢትዮጵያ ገዢው መደብ ግን በዚህ ተናዷል። በዚህ የተነሳ፣ “ማንዴላን በማሳበጥ የመለስ ራእይ አይሟሽሽም” ብለው ጽፈዋል። እናንተ በየጊዜው የነበራችሁ የህወሓት አመራር አብሎችና አባላት ሆይ፣ መሪዎቻችሁ የፈጸሙት ግፍና ግድያ ለናንተ ደስታ ይሰጣችኋል። በትግልና በአመራር ዘመናቸው ዘርፈዋል፣ በሙስና ተጨማልቀዋል፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ ለስደት፣ ለረሃብና ለሰቆቃ ዳርገዋል። እናንተም የዚህ ሁሉ ግፍ ተሳታፊዎች ናችሁ። ድርጊታችሁና ታሪካችሁ በደም የተጨማለቀ መሆኑን ዘንግታችሁ መለስ ዜናዊን ከኔልሰን ማንዴላ ጋር ማወዳደራችሁ በጣም አሳፋሪ ነው። በሁለቱ መካከል ያለው ልዩነት የሰማይና የምድርን ያክል ነው። ባለፉት ጽሑፎቼ እንደገለጽኩት፣ አጠር ባለ መልኩ፣ ሕወሓት ኢትዮጵያን ተቆጣጥሮ ያለ ድርጅት ነው። ስርዓቱም ፋሽስት፣ አምባገነን፣ ጠባብ ዘረኛ፣ ሽብርተኛ፣ ጸረ-ኢትዮጵያ ሉዓላዊነት፣ ጸረ-ኢትዮጵያ ሕዝብና የባእዳን ቅጥረኛ ነው።
ከ1969 መጀመሪያ ጀምሮ በትግራይ ሰላማዊ ዜጋ ላይ ግድያውን አቀጣጠለው። ግድያው ሳያንሰው ሃብትና ንብረቱም ተወረሰ። ከደደቢት በረሃ የጀመረውን አማራ የትግራይ ሕዝብ ጠላት ነው በማለት በተለያዩ ጊዜያትና ቦታዎች አማራውን በመጨፍጨፍ የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈጽመዋል። ለሴቶች በግዳጅ የማምከኛ መድሃኒት በመስጠት የአማራው ቁጥር እንዳይጨመር አድርገዋል። ከኖርበት ቀየውና መሬቱ በግዳጅ እንዲፈናቀል አድርገዋል።
ህወሓት ኢትዮጵያን እንደተቆጣጠረ ከ1985 መጀመሪያ ጀምሮ በኦሮሞ ሕዝብ ላይ ሰፊ የጥቃት ዘመቻ በመክፈት የግድያ፣ የቤት ማቃጠል፣ ንብረቱን መዝረፍና ከፍ ያለ ሰቆቃ አድርሶባቸዋል። እንደ አማራው ሁሉ ከመኖሪያ ቦታውና ከመሬቱ ላይ ተፈናቅሏል። የኦነግ አባል ናችሁ እየተባሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ያለምንም የፍርድ ውሳኔ ወደ ወህኒ ወርደዋል። በየቦታው በከፍተኛ ትምህርት ተቋሟት የሚማሩት የኦሮም ልጆች ከትምህርታቸው ተባረዋል። የተባረሩትም፣ መባረራቸው አልበቃ ብሎ ለእስር ተዳርገዋል። ደጉና ሩህሩሁ የኦሮሞ ሕዝብ ከእርሻው ተፈናቅሎ የረሃብና የበሽታ ሰለባ ሆኗል።
ህወሃት በጋምቤላ አኝዋኮች ላይ በፈጸመው የዘር ማጥፋት ወንጀል ተጠያቂ ነው። ሕዝቡ ከመሬቱ ተፈናቅሎ አብዛኛው በጎረቤት ሃገሮች ስደተኛ ሆነው በየሃገሩ እየተንከራተተ በችግር ላይ ነው።
የኦጋዴን ሕዝብም የዘር ማጥፋት ወንጀል ተፈጽሞበታል። ቤት ንብረቱ በህወሓት ወታደሮች ተቃጥሎበታል። ሴት ልጆቹና ሚስቶቹ ተደፍረውበታል። በተጨማሪም ከመሬቱ ላይ ተፈናቅሎ ለስደት ተዳርጓል።
የአፋር ሕዝብም በሌሎቹ የኢትዮጵያ ጎሳዎች የደረሰው ደርሶበታል፣ እየደረሰበትም ነው። የኢትዮጵያን ሕዝብ ከማሰቃየት ባለፈ ደግሞ የኢትዮጵያን ዳር ድንበር ለሱዳን መንግሥት ሸጠዋል። ሃገሪቱን ካለባህር በር አስቀርተዋል። የሃገር ሃብትና ታሪካዊ ቅርሶችን አውደመዋል፣ ሸጠዋል። ጊዜው ሲደርስ በኢትዮጵያ ሕዝብና በሃገሪቱ ላይ ለፈጸማችሁት ወንጀል ለፍርድ ያቀርባችኋል።
ይድረስ ለትግራይ ሕዝብ
ውድ የትግራይ ሕዝብ ሆይ!! ተሓህት ደደቢት በረሃ እንደወረደ በየሰበብ አስባቡ በየቤተ ክርስቲያናት እየመጡ፣ የትግራይ ሕዝብ በደመኛ ጠላትህ በአማራው የተጠቃህ ነህ። ነፃ የነበረችው ትግራይ ሃገርህ ወድቃልችና ተነስ። ከመሪ ድርጅተህ ተሓህት ጎን ተሰልፈህ አማራው ጠላትህን ደምስስ፣ ሲሉህ የሰጠኸው መልስ፣ አማራ የትግራይ ሕዝብ ጠላት አይደለም፣ ሆኖም አያውቅም፤ አብረን ተባብረን እና ጎን ለጎን ተሰልፈን፣ በአድዋና በማይጨው ጦርነት ጠላት የደመሰስን እና በደማችን አንድ የሆንን ኢትዮጵያውያን ነን። የአማራ ጠላት የሚባል አናውቅም። ትግራይ ኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያም ትግራይ ናት፣ የቅኝ ግዛት አይደለችም። ስለዚህ ኢትዮጵያዊነታችንን የሚነፍገን ምንም ሃይል አይኖርም። ድርጅታችሁ ትሓህት የምትሉትንም አናውቀውም፣ አንቀበለውም ብለህ መልሰሃል።
ይህንን ዓላማቸውን ለማዛመት በየቦታው የተንቀሳቀሱት የተሓህት መሪዎች በሁሉም ቦታ ተመሳሳይ ተቃውሞ ገጠማቸው። ተቃውሞው በሁሉም ከተሞች ሲበዛባቸው በብስራት አማረ የሚመራው የፈዳያን ቡድን በጠራራ ፀሃይ ሕዝቡን ፈጀው። ከየከተማው ሰዎችን እያጋዙ በየእስር ቤቱ እያጎሩ ገደሉት። የገጠሩን ሕዝብ ደግሞ ‘ትግራዋይ ሸዋዊ’ (የትግራይ ሸዋ)፣ ፊውዳል፣ ጸረ-ትሓህት፣ ጸረ-ኤርትራ ትግል ወዘተ. በማለት በውሽት በመወንጀል በቀንና በሌሊት በአፋኝ ቡድን እየተያዘ፤ ሃብት ንብረቱ እየተወረሰ ሃለዋ 06 ተወረወረ። እዚያም ገብቶ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩት እንደተገደሉ አንተው እራስህ የምታውቀው ሃቅ ስለሆነ ምስክር አያስፈልግህም። ልጆችህ በተሓህት እየታፈኑ ወደ ሜዳ ወጥታችሁ ታገሉ እየተባሉ ብዙ ሺዎች ወንድና ሴት ልጆችህን ለሻእቢያ አሻግሮ ሸጠብህ። በቀይ ኮከብና በተለያዩ ዘመቻዎች ለሻእቢያ ተሰልፈው በማያውቁት የኤርትራ በረሃ ማለትም በሳህል፣ አቁርደት፣ ከርከበት፣ ናቅፋ፣ ሰሎሞና ወድቀው ቀሩብህ። በወቅቱ አንተው የትግራይ ሕዝብ ተሓህት/ህወሓትን በግለጽ የተቃወምከውና ያወገዝከው ስለነበረ መስካሪ አያሻህም። ኢትዮጵያዊነትህን እና ለሰንደቅዓላማዋ ያለህን ፍቅር አስመስክረሃል፣ ታሪክም ዘግቦታል።
ውድ የትግራይ ሕዝብ ሆይ፤ የህወሓት አመራሮችን ማንነት ጠንቅቀህ ታውቃለህ። ዛሬ ኢትዮጵያ ሃገራችን በሰቆቃና በችግር ውቅያኖስ ውስጥ ሰምጣለች። ይህ የሆነበት ምክንያት የህወሓት መሪዎች ኤርትራውያን እና የትግራይ ባናዳዎች ተሰባስበው በህወሓት ስም ሃገር አውድመዋል። ባንተ ስም ብዙ ሸቅጠዋል። በስምህ የመጣውን ሰፊ እርዳታ የህወሓት መሪዎች ዘርፈው ሸጠዋል። ይህም ካንተ የተደበቀ አይደለም። ወያኔ በጠነሰሰው ተንኮል በጠራራ ፀሃይ ያለረህራሄ በቦምብ ተደብድበሃል፣ ይህ ነው የማይባል የሰውና የንብረት ውድመት ደርሶብሃል። ከኢትዮጵያውያን ወገኖችህ ጋር ቅራኔ ውስጥ ሊከቱህም ብዙ ጥረዋል። በቆራጥ ኢትዮጵያዊነትህ ቁጣህን በማሳየት የወያኔ መሪዎችን አሳፍረሃቸዋል፣ አሁንም በርታበት፣ ቀጥልበት። የህወሓት መሪዎች 40 ዓመት ሙሉ አሰቃይተውሃል፣ አሁን በቃኝ በል። ከኢትዮጵያዊ ወገነህ ጎን ተሰልፈህ ግንባር ቀደም በመሆን ይህንን የህወሓት ገዳይና ሽብርተኛ ቅጥረኛ ፋሽስት ስርዓት በተበባረው ሕዝባዊ አመጽ መቃብር አስገብተን የኢትዮጵያን ሉአላዊነት፣ አንድነታችንን እና ነፃነታችንን እንጎናጸፍ።
የተከበርክ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ፤ ሰላማዊ ትግል እያልን ጊዜ አንስጠው። የተጀመረውን ሕዝባዊ ቁጣ በማቀጣጠል እጅ ለእጅ ተያይዘን በሕዝባዊ ማእበል ወያኔን ደምስሰን ሃገራችን ኢትዮጵያን ነፃ እናውጣት።
የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ለመስዋእትነት ቁርጠኛ ሁናችሁ ውጡ፣ ሕዝቡን ምሩት። በውጭ ሃገር ያለህ ኢትዮጵያዊም የትግሉ የጀርባ አጥንት ስለሆንክ አስፈላጊውን ሁሉ ለማቅረብ ተዘጋጅ።
በበረሃ ያላችሁ የትጥቅ ታጋዮችም ውጡ፣ የፋሽስቱን የወያኔ ሰራዊት በምታውቁት የውጊያ ስልት አጥቁት። የኢትዮጵያ ሕዝብ ያልተቆጠበ ድጋፉን ይሰጣችኋል። ጊዜው አሁን ነው፣ ሕዝቡም የናንተው ነው።
ድል ሊትዮጵያ እናታችን!!
ጥር 2006
ጥር 2006
No comments:
Post a Comment