Friday, June 20, 2014

ነገን ለማስተካካል ዛሬ ላይ መነጋገር…

ፈረንጆቹ ፣ “አንድ ክፉ ነገር አሸንፎ የሚወጣው በጥቂት ሰዎች ዝምታ ምክንያት ነው” የሚል አባባል አላቸው፡፡ በዚህ ድሀ ሕዝብ ጫንቃ ተምረው፣ ኑሮአቸውን ካደላደሉ በኋላ አገር አማን ነው ብለው ዝምታን መርጠው የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን፤ ቢያንስ የሕሊና ወቀሳ እንደሚነዘንዛቸው ሊክዱ አይችሉም፡፡ በዚህ አደገኛ ጊዜ ዝምታ ወርቅ ሳይሆን ክህደት ነው፡፡
--------
የችግራችን መፍትሄው ሁሉም ሊገባው በሚችልበት፣ በሁለት ቃላት ማስቀመጥ ይቻላል፡፡ ይህን ያህል የዘር ጥላቻ ተካርሮ ወደ ግጭት ባላመራባት ኢትዮጵያ ቀርቶ፤ በዚያ በጥቂት ቀናት ውስጥ በዓለም ተወዳዳሪ ያልተገኘለት እልቂት በተፈጸመባት ሩዋንዳ እንኳን፤ ዛሬ በህዝቡ መሀከል እርቅ ወርዶ ሩዋንዳ በአፍሪቃ የሰላምና የእኩልነት ተምሳሌት ለመሆን ችላለች፡፡ ዛሬ ሩዋንዳ እንጂ እከሌ ሁቱ ነው እገሌ ቱትሲ ነው ማለት አጸያፊ ሆኗል፡፡ ስለዚህ፤ ምንም እንኳን መጪዎቹ ጊዜያት አስፈሪ ቢሆኑም ቅሉ፤ ብሄራዊ እርቅ በሚሉ ሁለት ቃላት፣ መፍትሄ ማስቀመጥ ይቻላል፡፡

በአገራችን የኢህአዴግ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የሕዝባዊ ድርጅቶች ፈቃደኝነት እስካለ ድረስ በቀላሉ እርቅ ወርዶ; ለዘር ጥላቻ መንስኤ የሆኑ ነገሮች ታርመው፤ አገራችን ፍቅርና ዴሞክራሲ የሰፈነባት ከመሆን ምንም የሚያግዳት ነገር አይኖርም፡፡ ብሄራዊ እርቅ ይውረድ ሲባል፣ ‹” ማን ከማን ጋር ተጣልቷል?” ብሎ መቀለድ፤ በኋላ መሪር ዋጋ ሊያስከፍል ይችላል፡፡
ብሄራዊ መግባባት እንዴት ይመጣል የሚለው፤( እኔም የማምንበት) በአገሪቷ እኩልነት፣ ዴሞክራሲያዊ እና ፍትህ ያለመ በአገር ደረጃ የሚወሰን ሲሆን ለመነሻነት ያህል ቀጥሎ በተዘረዘሩት መጀመር ይቻላል…
ሀ) ጋዜጠኞች፣ የፖለቲካ ፓርቲና የሃይማኖት መሪዎችና አባላት በጠቅላላው ከፖለቲካና ከሃይማኖት ጋር በተያያዘ የታሰሩ ሰዎችን በሙሉ መፍታት፡፡
ለ) የጸረ ሽብር አዋጅ መሰረዝ፤ እና
ሐ) በአገር ውስጥ እና በውጭ አገራት የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የህዝባዊ ድርጅቶች አባላት እና መሪዎች በሽብርተኛነት የተፈረጁትንም አጠቃሎ የያዘ አንድ ጉባዔ በአዲስ አበባ ማካሄድ
የሚሉት መነሻ ሊሆኑን ይችላል ብዬ አምናለሁ፡፡
******************************************ዶ/ር ያዕቆብ ኃይለማርያም ፋክት መጽሄት ላይ…

No comments:

Post a Comment