Sunday, August 31, 2014

ጋዜጠኛ ብስራት ወ/ሚካኤል ተሰደደ

በጌታቸው ሺፈራው
ብስራት ወ/ሚካኤል
ብስራት ወ/ሚካኤል
በተለያዩ ጋዜጦች፣ መፅሔቶች የራሱ “አዲስሚዲያ” ብሎግን ጨምሮ በተለያዩ ድህረ-ገፆች አዘጋጅ እና ፀሐፊ ጋዜጠኛ ብስራት ወ/ሚካኤል መሰደዱ ታወቀ፡፡ ጋዜጠኛው ቀደም ሲል የፍኖተ-ነፃነት ጋዜጣ አዘጋጅ፣የኢቦኒ መፅሔት ዋና አዘጋጅ፣ በደቡብ አፍሪካ የሚገኘው ኢሳው መፅሔት ባልደረባና አምደኛ፤ በኢትዮ-ምህዳር ጋዜጣና በቅርቡ ወደህትመት የገባው ቀዳሚ ገፅ ጋዜጣ ላይም የተለያዩ የፖለቲካ፣ ሰብዓዊ መብት ጥሰትና ማኀበራዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ በራሱና በብዕር ስም እንደሚፅፍ ይወቃል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የተመሰረተውና በመንግስት ከፍተኛ ቁጥጥርና ጫና ላይ የወደቀው የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች መድረክ (ኢጋመ) መስራች አባል፤ በኋላም የማኀበሩ ትምህርትና ስልጠና ኃላፊ በመሆን እያገለገለ እንደነበር ይታወቃል፡፡ 


ጋዜጠኛው ከዚህ በፊትም በመንግስት ደህንነት ኃይሎች በምሽት እገታ እንደገጠመው፣ ከስልክ ጠለፋ እስከ ዛቻና ማስፈራራት ይደርስበት እንደነበር ከዚህ ቀደም የወጡ መረጃዎች ቢያመለክቱም፤በተለይ ከጥቅምት 2006 ዓ.ም. ከአዲሱ ጋዜጠኞች ማኀበር መመስረት ሂደት ጀምሮ እና በሚያዚያ ወር 2006 ዓ.ም. 3 ጋዜጠኞችን እና 6 የዞን 9 ብሎገሮች በመንግስት ከታሰሩ በኋላ የመንግስት ደህንነቶች ክትትል ከበፊቱ በበለጠ ሁኔታ ተጠናክሮ መቀጠሉንና ቀጣዩ እስር እሱ ላይም ሊፈፀም እንደሚችል በመረዳት ለቅርብ ጓደኞቹ አሳውቆ ነበር፡፡ 

ብስራት ባለፈው ነሐሴ 16 ቀን 2006 ዓ.ም. አርብ ጠዋት አዲስ ባወጣው የስልክ መስመር የማዕከላዊ ስልክ ጥሪ ካስተናገደ በኋላ ለጊዜው ከአዲስ አበባ ውጭ መሆኑን በማሳወቅ ለሰኞ እንደሚቀርብ ምላሽ ከሰጠ በኋላ ባለፈው እሁድ ድንገት ሀገር ጥሎ መሰደዱ ታውቋል፡፡ 

በቅርቡ ከታሰሩት ጋዜጠኞችና ብሎገሮች የእስር ስም ዝርዝር ውስጥ የማኀበሩ አመራሮች መኖራቸውና በቀጣይም መንግስት በአመራሮቹ ዙሪያ መረጃ እየሰበሰበ መሆኑ ምንጮች አረጋግጠው እንደነበረ ይታወቃል፡፡ ቀደም ሲል የማኀበሩ ፕሬዘዳንት ጋዜጠኛ በትረ ያዕቆብ፣ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው ጋዜጠኛ ዘሪሁን ሙሉጌታ፣ ገንዘብ ያዥ ጋዜጠኛ ሃብታሙ ስዩም እና መስራች አባል ጋዜጠኛ ተሰማ ደሳለኝ መሰደዳቸው አይዘነጋም፡፡ በአጠቃላይ ጋዜጠኛ ብስራት ወ/ሚካኤልን ጨምሮ በ2006 ዓ.ም. ብቻ 25 የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ሲሰደዱ፤3 የውጭ ዜጎች ጋዜጠኞችን ጨምሮ 20 ጋዜጠኞችና ብሎገሮች ደግሞ በእስር ላይ እንደሚገኙ ታውቋል፡፡

No comments:

Post a Comment