Wednesday, November 12, 2014

በፋይናንስ ችግርና በአንድነት ጉዳይ የሚፈተነው መድረክ

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ሒደት ውስጥ ብልጭ በማለት ለብዙዎች የተስፋ ስንቅ አስይዞ የነበረው ምርጫ 97 በአወዛጋቢ ሁኔታ ከተጠናቀቀ በኋላ በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ግለሰቦች የአገሪቱ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ወደኋላ እየተንሸራተተ ነው በማለት ይተቻሉ፡፡ ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ደግሞ አገሪቱ ለመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ግንባታና አጠቃላይ ለአገሪቱ ዕድገት ወሳኝ የሚባሉ ውሳኔዎችንና አሠራሮችን መዘርጋቱን ይሞግታል፡፡
የ97 ምርጫን ተከትሎ የፖለቲካ ምህዳሩ ከምን ጊዜውም በላይ ጠቧል፣ ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግም በ97 የተፈጠረው ዓይነት የሕዝብ እንቅስቃሴ እንዳይኖር ተግቶ እየሠራ ነው በማለት የሚተቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች በርካታ ናቸው፡፡ ከእነዚህ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ደግሞ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) በአሁን ወቅት አራት ፓርቱዎችን በአባልነት ያቀፈ ሲሆን፣ የመድረኩ አባል ከነበረው አንድነት ጋር ያለው ውዝግብ ባለመቋጨቱ እስካሁን ድረስ የሁለቱ ፓርቲዎች ግንኙነት አልለየለትም፡፡
በአገሪቱ የፖለቲካ ምህዳር እንደተስተዋለው የተለያዩ ስብስቦች በጋራ ለመሥራት የተፈራረሙዋቸው ስምምነቶች በርካታ ሲሆኑ፣ አብዛኛዎቹ ስምምነቶች የሚፈጸሙት በአብዛኛው አገር አቀፍ ምርጫ ሲደርስ በጋራ በመሆን ገዥውን ፓርቲ ለመታገልና በተበጣጠሰ መልኩ የሚገኘውን ድምፅ ከገዥው ፓርቲ ለመንጠቅ በማለም እንደሆነ የፖለቲካ ተንታኞች ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን የምርጫዎቹን መጠናቀቅ ተከትሎ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ወይ ሲፈርሱ አልያም ደግሞ ሲከስሙ ባስ ሲል ደግሞ ለአንድ ዓላማ ተሰልፈው የነበሩት ግለሰቦችና በትብብር ወይም በጋራ ለመሥራት የተስማሙት ፓርቲዎች አመራሮች ሲዘላለፉና ሲወነጃጀሉ መመልከት የተለመደ ክስተት ሆኗል፡፡
ምንም እንኳን እንዲህ ዓይነት ክስተቶች በኢትዮጵያ የተቃውሞ ፖለቲካ የተለመዱ ቢሆንም፣ በቅድመ ምርጫ 2002 የተመሠረተው መድረክ ብዙ ፈተናዎችን እያለፈና እየተቋቋመ እዚህ መድረሱን ቅዳሜ ጥቅምት 29 ቀን 2007 ዓ.ም. በተካሄደው የፓርቲው 10ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ ወቅት ተገልጿል፡፡
ፓርቲው ስድስት ኪሎ አካባቢ በሚገኘው ዋና ጽሕፈት ቤቱ ቅዳሜ ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ሰባት የሚሆኑ የመወያያ አጀንዳዎችን ለአባላቱ ያቀረበ ሲሆን፣ በዚህም መሠረት ሙሉ ቀን በፈጀ ውሎው በተቀመጡት አጀንዳዎች ላይ ከፍተኛ ውይይት ማካሄዱን ለሪፖርተር በተላከው መግለጫ ተጠቅሷል፡፡
በአጀንዳነት ቀርበው ከነበሩት ሐሳቦች መካከል ያለፉትን ስድስት ወራት የክንውን ሪፖርት ማዳመጥና ማፅደቅ፣ የአንድነትን እገዳ በተመለከተ መወያየትና ውሳኔ መስጠት፣ የገንዘብ ችግርን መፍታት ስለሚቻልበት ሁኔታ መወያየትና በዘንድሮው አገር አቀፍ ምርጫ ላይ ተወያይቶ አቅጣጫ ማስቀመጥ የሚሉት ይገኙበታል፡፡
ከጉባዔው መጠናቀቅ በኋላ የወጣው የአቋም መግለጫ ‹‹መድረክ ባሳለፋቸው የትግል ዓመታት ከገዥው ፓርቲ በአባላቱና በደጋፊዎቹ ላይ የደረሰውና እየደረሰ ያለው አፈና፣ ወከባ፣ እስርና ግድያ ሳይበግረው ይበልጥ እየተጠናከረ መጥቶ፣ እነሆ ዛሬም አሥረኛ ጠቅላላ ጉባዔውን በተሳካ ሁኔታ አካሂዶ በአገራችን ወቅታዊ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ በስፋትና በጥልቀት ከመከረ በኋላ ማኒፌስቶ በማፅደቅ አጠናቋል፤›› በማለት አትቷል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ፓርቲውን በፕሬዚዳንትነት ሲመሩ የነበሩትን አቶ መረራ ጉዲናን (ዶ/ር) የውጭ ጉዳይ ኃላፊ አድርጐ የመረጠ ሲሆን፣ አቶ በየነ ጴጥሮስን (ፕሮፌሰር) በፕሬዚዳንትነት መርጧል፡፡
የመድረክ መንገድ
ፓርቲውን በፕሬዚዳንትነት እንዲመሩ ዳግም የተመረጡት አቶ በየነ ጴጥሮስ ምርጫውን ተከትሎ ባሰሙት ንግግር ላይ እንደገለጹት፣ መድረክ ሁሉን አቀፍ ውይይት ከገዥው ፓርቲ ጋር በማድረግ ለአገሪቱ የሚበጅ አቅጣጫ ለማስቀመጥ የሚሠራ ፓርቲ ነው፡፡ ‹‹ኢሕአዴግ ግን ውይይቶችን ወደ ጐን በመግፋት የተያያዘውን መንገድ ለብቻው ቀጥሎበታል፤›› በማለት ተችተዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ‹‹ቀደም ሲል መድረክ በተደጋጋሚ ስለአገር ጉዳይ ከገዥው ፓርቲ ጋር ለመወያየት ያቀረባቸው ጥያቄዎች ተገቢና ዛሬም ወቅታዊ በመሆናቸው፣ ኢሕአዴግ ይህንን ጥያቄ በአገራዊና ንፁህ ህሊና ተመልክቶ ውይይቱ እንዲካሄድ እንዲደረግ፤›› በመግለጫው ጠይቋል፡፡
አዲሱ ተመራጭ ፕሬዚዳንት መድረክና ኢሕአዴግ የመርህ ልዩነት እንዳላቸው የገለጹ ሲሆን፣ ‹‹ይህንን ይዘን እንጂ የምንንቀሳቀሰው የጥላቻ ወይም የቂም በቀል ፖለቲከኞች አይደለንም፤›› በማለት ከኢሕአዴግ ጋር ያላቸው ልዩነት በጥላቻ ወይም በቂም በቀል አለመመሥረቱን በመግለጽ ልዩነቱ የሚያጠነጥነው መርህ ላይ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
‹‹በአገራችን ተስፋ አንቆርጥም›› ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ መድረክም ተስፋ ባለመቁረጥ እየተንቀሳቀሰ እንደሆነና የተሻለች ኢትዮጵያን ለማየት በሚያልሙ አመራሮችና የአገራችን ጉዳይ ያገባናል ባሉ ኢትዮጵያውያን መዋቀሩን አውስተዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ ገዥው ፓርቲ ለአገሪቱ ይሠራል ብሎ ያለው ሞዴል እንደማይሠራም ገልጸዋል፡፡ ልማትና ዕድገት በኢትዮጵያ እንደመጣ በከፍተኛ ደረጃ የዓለም መገናኛ ብዙኃን እየዘገቡ ቢሆንም፣ በሒደት ሕዝብን ተጠቃሚ የማያደርግ አሳታፊ ያልሆነ ልማት እንደሆነ በመግለጽ ተከራክረዋል፡፡
በዕለቱ ፓርቲው በመጪዎቹ አምስት ዓመታት የሚገለገልበት ማኒፌስቶ ይፋ የተደረገ ሲሆን፣ አጠቃላይ የአገሪቱን ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች በስፋት የተመለከተ፣ የተነተነና የመፍትሔ አቅጣጫ ያስቀመጠ እንደሆነ የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጥላሁን እንደሻው ገልጸዋል፡፡
ምንም እንኳን የማኒፌስቶውን ሙሉ መረጃ ለጋዜጠኞች መስጠት ‹‹ምርጫ ቦርድ ካስቀመጠው የቅስቀሳ የጊዜ ሰሌዳ ጋር የሚቃረን በመሆኑ ጊዜው ሲደርስ ለሕዝቡ ይፋ እናደርጋለን፤›› በማለት የገለጹ ቢሆንም፣ አባላቱ ግን ተወያይተውበት መፅደቁ ተገልጿል፡፡
መድረክ ውስጥ የሚገኙት አራት ፓርቲዎች የኢትዮጵያ ማኅበረ ዴሞክራሲ የደቡብ ኅብረት (ኢማዴደህ)፣ የሲዳማ አርነት ንቅናቄ (ሲአን)፣ ኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) እና ዓረና ትግራይ ለዲሞክራሲና ሉዓላዊነት (ዓረና) ሲሆኑ በዘጠነኛው የፓርቲው ጠቅላላ ጉባዔ ወቅት እገዳ የተጣለበት የአንድነት ፓርቲ ጉዳይ በአሥረኛው ጠቅላላ ጉባዔ ወቅትም መፍትሔ አላገኘም፡፡
መድረክና አንድነት
አንድነትና መድረክ የቀድሞው የአንድነት ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ ግዛቸው ሽፈራው (ኢንጂነር) ሰጡት በተባለው መግለጫ የተነሳ ውዝግብ ውስጥ ገብተው የነበረ ሲሆን፣ መግለጫውን ተከትሎም አንድነት የተሰጠውን መግለጫ እስካላስተባበለ ድረስ ከመድረክ አባልነት ታግዶ ይቆይ የሚል ውሳኔ መተላለፉ ይታወሳል፡፡
የቀድሞው የአንድነት ፕሬዚዳንት በሰጡት አስተያየት ‹‹ከዚህ ወዲህ ቅንጅት/ግንባር ማለት ጊዜ ማጥፋት ነው፤›› ያሉ ሲሆን፣ መድረክ ይህ አስተያየት ተገቢ ስላልሆነ ፓርቲው እንዲያስተባብል ጠይቋል፡፡ አንድነት በበኩሉ በሰጠው ምላሽ ‹‹መግለጫውን የሰጡት በግለሰብ ደረጃ እንጂ የፓርቲው አቋም አይደለም፤›› በማለት ለማስተባበል ፍቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል፡፡ ይህ ውዝግብ ያለ መፍትሔ እስካሁን እየተንከባለለ የሁለቱ ልዩነትም ወደ መፍትሔ ከመጠጋት ይልቅ እየሰፋ ወደ መለያየት የተቃረቡ ይመስላል፡፡
ከዚህ አንፃር አዲስ የተመረጡት የመድረክ ፕሬዚዳንት ‹‹ለአንድነቶች እስከ ህዳር 16 ድረስ ጊዜ ሰጥተናቸዋል፤›› በማለት ከአንድነት ጋር ያለውን ልዩነት ለመፍታት ማለማቸውን የገለጹ ቢሆንም፣ አሁንም ቢሆን ግን ከመድረክ በኩል የአቋም ለውጥ አለመደረጉን አውስተዋል፡፡
ከዚህ በፊት የተሰጣቸውን ምክር አዳምጠው ወደ መድረኩ መጥተው አብረው መንቀሳቀስ ፍላጎት እንዳላቸው የገለጹት አቶ በየነ፣ ከዚህ ቀደም የተሰጡት ምክሮች እስካልተፈጸሙ ድረስ እገዳው እንደሚቀጥል ግን ከማሳሰብ አልተቆጠቡም፡፡ የአንድነት ብሔራዊ ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ አበበ አካሉ በበኩላቸው፣ ‹‹እኛ መድረክን በተመለከተ የምናደርገው ምንም አዲስ ነገር የለም፤›› በማለት ፓርቲው በተደጋጋሚ አብሮ ለመሥራት ጥሪ ቢያቀርብም፣ ከመድረክ በኩል ቀና ምላሽ ባለመገኘቱ እዚህ ዓይነት ውሳኔ ላይ መድረሳቸውን ጨምረው ገልጸዋል፡፡
ቅዳሜ የተካሄደው የመድረክ ጠቅላላ ጉባዔ እግዱን አንስቶ አንድነትን ይጠራል የሚል ተስፋ እንደነበራቸው የገለጹት አቶ አበበ፣ መድረክ ግን ይህን ባለማድረጉ ‹‹ታሪካዊ የሆነ አሳፋሪ ውሳኔ ወስኗል፤›› ማለታቸው በሁለቱ ፓርቲዎች መካከል ያለው ልዩነት ከመስፋት አልፎ ሁለቱም ፓርቲዎች በውይይት የማይፈቱት ደረጃ ላይ መድረሱን አመላካች ሆኗል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የመድረክ ፕሬዚዳንትም ሆነ የአንድነት ብሔራዊ ምክር ቤት አፈ ጉባዔ በንግግራቸው ወቅት ወደ መለያየት መቃረባቸውን የሚገልጽ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ ‹‹ከህዳር 16 በኋላ የሕጋዊነት ጥያቄ ይመጣል፡፡ እኛ የምርጫ ምልክታችንን መውሰድ አለብን፡፡ አንድነትም አሁንም አባል ነኝ እያለ መቆየት የለበትም፡፡ ይህንን ጊዜ ሰጥተናል፡፡ ከዚያ በኋላ ግን መድረኩ አንድነትን ለማሰናበት  ይገደዳል ማለት ነው፤›› በማለት የመድረክ ፕሬዚዳንት አስተያየታቸውን የሰጡ ሲሆን፣ አቶ አበበ በበኩላቸው ‹‹አቶ ግዛቸው ፕሬዚዳንት በነበሩበት ወቅት እግዱን አንሱልንና ተቀራርበን እንሥራ ብለናል፡፡ ነገር ግን ምንም ምላሽ አላገኘንም ነበር፡፡ የቅዳሜው ጠቅላላ ጉባዔም እግዱን ያነሳልናል የሚል እምነት ነበረን፡፡ ነገር ግን ስላላነሱት በፍቅር መለያየት ነው ያለው አማራጭ፤›› በማለት ሁለቱም ፓርቲዎች ደጅ ደጁን እየተመለከቱ እንደሆነ ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡
መድረክ ለአንድነት እስከ ህዳር 16 ድረስ በሩን ክፍት ማድረጉን የገለጸ ሲሆን፣ ይህን ያደረገበት ዋነኛ ምክንያት ከህዳር 16 ጀምሮ ፓርቲዎች የምርጫ መወዳደሪያ ምልክታቸውን ከምርጫ ቦርድ የሚወስዱበት ጊዜ በመሆኑና ከዚያ በኋላ የሚደረግ ማንኛውም ግንኙነት ፍሬ እንደማይኖረው በማሰብ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
በዚህ ረገድ አቶ አበበ ‹‹እኛ ከዚህ በኋላ እንኳን ደብዳቤ ብንጽፍ ስድስት ወር ጠብቆ ነው እንደገና የመድረክ ጉባዔ የእኛን ደብዳቤ ተመልክቶ ውሳኔ የሚሰጠው፡፡ ስለዚህ ምርጫ በደረሰበት ወቅት እኛ ከመድረክ ጋር እንደገና ደብዳቤ ጽፈን ስድስት ወር ጠብቁን የምንልበት ምንም ምክንያት የለም፤›› በማለት ደብዳቤ መጻጻፉም ሆነ የጊዜ ቀነ ገደብ ማስቀመጡ ፋይዳ ቢስ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
መድረክ የገጠሙት ችግሮች
የቀድሞ የፓርቲው ፕሬዚዳንት አቶ መረራ ጉዲና የፓርቲውን ያለፈውን ስድስት ወር ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት ፓርቲው ያከናወናቸውን አበይት ተግባራት በማስታወስ የተሠሩትን ሥራዎችና የተወሰዱ ውሳኔዎችን የገለጹ ከመሆናቸው በተጨማሪ መድረኩ ባለፉት ስድስት ወራት ያጋጠሙትን አበይት ችግሮችም ጠቅሰዋል፡፡
በዚህም መሠረት መድረክ ካጋጠሙት ችግሮች በዋናነት ሊጠቀሱ የሚችሉት ሁለት ሲሆኑ፣ እነዚህም የፖለቲካ ምህዳሩ መጥበብና የፋይናንስ ችግሮች ናቸው፡፡
‹‹ከምርጫ 97 ትምህርት የወሰደው ገዥው ፓርቲ  ኢሕአዴግ ሰላማዊ ትግሉ ተጠናክሮ ከቀጠለ በሕዝብ ድምፅ ሥልጣን ላይ መቆየት እንደማይችል በማረጋገጡ፣ የፖለቲካ ምህዳሩን ከመቼውም ጊዜ በላይ እየጠበበ መጥቶ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሕዝብ ውስጥ ገብተው እንዳይንቀሳቀሱ ሁለንተናዊ አፈና ተዘርግቷል፤›› በማለት የገለጹት አቶ መረራ፣ ይህም ለመድረክ አጠቃላይ ሥራዎች ከፍተኛ ችግር መፍጠሩን ጠቁመዋል፡፡ ይህ ችግር ክፉኛ ለመባባሱም ከ2005 የማሟያ ምርጫ መድረክ ራሱን ከምርጫ ውድድር ውጪ ማድረጉን እንደ አብነት ጠቅሰዋል፡፡ ዘንድሮ የሚካሄደውን አምስተኛ ዙር አገር አቀፍ ምርጫን በተመለከተም ከጊዜ ሰሌዳው ውይይት በፊት በምርጫ ችግሮች ላይ ውይይት እንዲደረግ ለምርጫ ቦርድ መድረክ ያቀረበው ጥያቄ፣ እስከዛሬ ምላሽ አለማግኘቱ ከፖለቲካ ምህዳሩ መጥበብ ጋር የተፈጠሩት ችግሮች አሁንም ምላሽ እንዳልተሰጣቸው ጠቋሚ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የፋይናንስ ችግርን በተመለከተ ደግሞ መድረክ በፋይናንስና በሰው ኃይል ተጠናክሮ ከተገኘ የኢትዮጵያ ሕዝብ የፖለቲካ ሥልጣን ባለቤት የተሻለ አማራጭ ሆኖ በመገኘቱና ‹‹ይህን የተገነዘቡት ኃይሎች በተለይም በውጭ አገር የሚኖሩ የቀኝ ኃይሎች (ዳያስፖራዎች) መድረክ የጐሳ ድርጅቶች ስብስብ ስለሆነ መረዳት የለበትም የሚል ዘመቻ በመክፈታቸውና ውዥንብር በመፍጠራቸው መድረክ የፋይናንስ ችግር ገጥሞታል፤›› በማለት ፓርቲው የደረሰበትን አሳሳቢ የፋይናንስ ችግር አስረድተዋል፡፡
ፓርቲው እነዚህን ሁሉ ችግሮች ተቋቁሞ እየሠራ መሆኑን ጠቁሞ ያለው ነባራዊ ሁኔታ ግን እጅግ አሳሳቢ መሆኑን ያሰምርበታል፡፡ ምንም እንኳን ፓርቲው መጪው ምርጫን የተመለከተ መስመር ማስቀመጡንና የመጪው አምስት ዓመታት አማራጭ ለመሆን የሚያስችለውን ማኒፌስቶ ማዘጋጀቱን ቢገልጽም፣ ካለበት ከፍተኛ የሆነ የፋይናንስ ችግርና ከአንድነት ጋር ያለው ያለመግባባት ጉዳይ የፓርቲው ቀጣይ ፈተናዎች ይሆናሉ፡፡
reporter

No comments:

Post a Comment