አይ ‘ልማት’ ¡
ክፍል – 1
——————
ስለተከሰስኩበት ክስናና ይህንንም ተከትሎ ከእስር ጋር በተገናኘ ሥለነበረው ሁነት አንድ ሁለት በማለት ዛሬ ማውጋት ልጀምር፡፡ ከጽሑፍ ጋር በተያያዘ ፍርድ ቤት ስቀርብ ለሶስተኛ ጊዜ ነበር፡፡ የመጀመሪያው ‹‹አውራምባ ታይምስ›› ጋዜጣ ላይ በሪፖርተርነት ሥራ በጀመርኩ በወራቶች ውስጥ ነበር፡፡ የግንቦት ሰባት አመራሮች በሌሉበትና እነብርጋዲየር ጄነራል ተፈራ ማሞ ታስረው ባሉበት (46 ተከሳሾች) ‹‹ሕገ-መንግሥቱን በሃይል ለመናድ፣ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ለመግደል በማሴር …ወዘተ›› በሚል የቀረበውን ክስ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተገኝቼ የችሎት ሂደቱን የምዘግበው እኔ ነበርኩ፡፡
ክፍል – 1
——————
ስለተከሰስኩበት ክስናና ይህንንም ተከትሎ ከእስር ጋር በተገናኘ ሥለነበረው ሁነት አንድ ሁለት በማለት ዛሬ ማውጋት ልጀምር፡፡ ከጽሑፍ ጋር በተያያዘ ፍርድ ቤት ስቀርብ ለሶስተኛ ጊዜ ነበር፡፡ የመጀመሪያው ‹‹አውራምባ ታይምስ›› ጋዜጣ ላይ በሪፖርተርነት ሥራ በጀመርኩ በወራቶች ውስጥ ነበር፡፡ የግንቦት ሰባት አመራሮች በሌሉበትና እነብርጋዲየር ጄነራል ተፈራ ማሞ ታስረው ባሉበት (46 ተከሳሾች) ‹‹ሕገ-መንግሥቱን በሃይል ለመናድ፣ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ለመግደል በማሴር …ወዘተ›› በሚል የቀረበውን ክስ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተገኝቼ የችሎት ሂደቱን የምዘግበው እኔ ነበርኩ፡፡
ክሱ ቀርቦ አቃቤ ሕግ ምስክሮችን ሲያሰማ የሰራሁት ሰፊ የዜና ዘገባ ‹‹የምስክሮችን ስም ጠቅሷል …›› በሚል ከሳሽ ባቀረበው አቤቱታ እና ክስ ከጋዜጣው ዋና አዘጋጁ ፍጹም ማሞ ጋር ማዕከላዊ ቀርበን እያንዳንዳችን የ5000 ብር ሺህ ብር ዋስትና ፈርመን ከተለቀቅን በኋላ ፍርድ ቤት ሁለቴ በመቅረብ በመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ተለቅቀናል፡፡ ሁለተኛው፣ ባለፈው ዓመት፣ 2006 ዓ.ም በ‹‹ዕንቁ›› መጽሔት ላይ በተጻፈ የአምደኛ አምሳሉ ገ/ኪዳን ጽሑፍ ለምርመራ ማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ ተጠርቼ በህገ-ወጥ መንገድ ለአራት ቀናት እስር ከተዳረኩበት በኋላ ተከስሼ ለሁለተኛ ጊዜ ፍርድ ቤት ቀርቤ ነበር፡፡ ከዚያም በኋላ፣ ግልጽ ባልሆነ ሁኔታ ክሱ ተቋርጦ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ይህ ክስ ዳግም ተቀስቅሶ ለሶስተኛ ጊዜ ፍርድ ቤት ለመቅረብ ተገድጃለሁ፡፡
ሕዳር 2 ቀን 2007 ዓ.ም፣ እኔ እና አምሳሉ ገ/ኪዳን 1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች ሆነን በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ሁለተኛ ችሎት ለመቅረብ ተቀጥረን ነበር፡፡ በዕለቱ ጥዋት ተነስቼ ከጠበቃ ተማም አባቡልጉ ጋር ያዘጋጀነውን የክስ መቃመሚያ ፕሪንት ካደረኩኝ በኋላ ከወዳጄ እዩኤል ፍስሐ ጋር ፒያሳ ተገናንተን ዩሐንስ ቤተ-ክርስትን አቅራቢያ ወደሆነው ፍርድ ቤት አመራን፡፡ ፍርድ ቤቴን እኔም ሆኑኩ ጓደኞቼ ከዚህ ቀደም አናውቀውም ነበር፡፡ በዕለቱ ጓደኞቼ አቤል አለማየሁ፣ አሸናፊ አስማማው፣ ንዋይ ገበየሁ፣ አብነት ረጋሳ፣ ዳንኤል ሙላት፣ አናንያ ሶሪና መኳንንት በቀለ ከእኔ ጋር ተገኝተው ነበር፡፡ የመጽሔቷ ማኔጂንግ ዳይሬክተር እና የሥራ ባልደረባዬ አቶ ፍቃዱ ማህተመወርቅ (ባሪያው) ትንሽ ተግየት ብሎ መጥቶ ነበር፡፡
በሁለተኛ ወንጀል ችሎት የብዙ ሰዎች ጉዳይ እየታየ ስለነበረ ሁለተኛ ፎቅ በሰዎች ተጨናንቋል፡፡ ከቀኑ 5፡30 ሰዓት ገደማ ወደችሎት ውስጥ ገባን፡፡ ቀትር ላይ እኔና አምሳሉ ስማችን በዕለቱ ዳኛ ተጠራና ከጠበቃችን ጋር ችሎት ፊት ቆምን፡፡ ክሱ በዳኛው ተነበበልን፡፡ ክሱን በመቃመም ያዘጋጀነው መቃመሚያ መኖሩን ተማም ለችሎቱ ገለጸ፡፡ ዳኛው ‹‹እሺ ያንብቡት›› በማለት ለተማም ገለጹ፡፡ ተማምም ‹‹መቃወሚያው ዘጠኝ ገጽ ስለሆነ አሳጥሬ ፍሬ ፍሬ ነገሩን ልናገር›› ብሎ የክሱን ተቃውሞ ሰፋና ዘርዘር አድርጎ ገለጸ፡፡ ‹‹ክስ ሆኖ የቀረበው ጽሑፍ የአንድ ሰው አመለካከት ወይም ነጻ አስተያየት (opinion) መሆኑን፣ የቀረበው ክስ፣ ክስ ሆኖ መቅረብ እንደሌለበት ከተናገረ በኋላ ‹‹ደንበኞቼ በነጻ ይሰናበቱልኝ›› አለ፡፡ ተማም ሲናገር ችሎቱ በዝምታ ተውጦ ነበር፡፡ የሰዎች ትኩረት ወደተማም መሆኑን ታዘብኩ፡፡ የዕለቱ ዳኛም ትኩረት ሰጥቶ መቃወሚያውን አደመጡት፡፡ ከተማም በኋላ ሰዓሊ አምሳሉ ሃሳቡን አሰማ፡፡ ማስረጃ ላይ ተንተርሶ ጽሑፉን ማቅረቡን ለፍርድ ቤቱ ተናገረ፡፡ እኔም ቀጠልኩ፡፡ የህገ-መንግሥቱ አንቀጽ 29ን መሰረት በማድረግ ጽሑፉ መስተናገዱን፣ ሌሎች መሰል ሀሳቦች በተለያዩ ጊዜያት በመጽሄቷ ላይ በማስተናገድ የዜጎች ተለያየ ሃሳብ ማንሸራሸራችንን በመጥቀስ ክሱ ውድቅ እንዲሆን ተናገርኩ፡፡
ወጣቱ ከሳሽ አቃቤ ሕግም በመቃሚያችን ላይ የተነሱትን ነጥቦች በመንተራስ የተቃውሞ ሃሳቡን ሰፋ አድርጎ አቀረበ፡፡ ‹‹ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ላይ የሚጣሉ ገደቦች አሉ›› በማለት የሕገ-መንግሥቱን አንቀጽ 29/6ን በማጣቀስ ተናገረ፡፡ አያይዞም፣ ‹‹የግለሰብ መብት የቡድን መብትን መደፍጠጥ የለበትም፤ ጽሑፉ ውስጥ ምንጭ ቢገለጽ ጥሩ ነበር …ጽሑፉን ተከትሎ የወደመ ንብረት እና የተጎዱ ሰዎች አሉ፣ …ወዘተ›› አለ፡፡
ፍርድ ቤቱም የግራ ቀኙን ክርክር ካደመጠ በኋላ የምስከሮችን ቃል ለማድመጥ ለታህሳስ 6 ቀን 2006 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጠ፡፡ እያንዳንዳችን በ20 ሺህ ብር ዋስትና እንድንወጣም አዘዘ፡፡ በዕለቱ ከጅማ ድረስ ለመጡ አራት ምስክሮች (ፖሊሶች) የክርክሩ ቃል መገልበጥ ስለሚኖርበት ተለዋጭ ቀጠሮ በተሰጠው ቀን እንዲመጡ በትህትና ነገራቸው፡፡ ምስክቹም ከኪሳቸው ገንዘብ በመጠቀም መምጣታቸውን ጠቁመው አበል እንዲሰጣቸው ለፍርድ ቤቱ ጠየቁ፡፡ በሕጋዊ አሰራር መሰረት ምስክርነት የሚሰጡ ከሆነ አበል እንደሚሰጣቸው ተነገራቸው፡፡ በተለይ አንደኛው ምስክር ቅር መሰኘታቸው ፊታቸው ላይ በግልጽ ይነበብ ነበር፡፡ …የክሱን መዝገብ ከተዘጋ በኋላ እና እና አምሳሉን ፖሊሶች በችሎቱ በአንደኛው ጥግ ዋስትና ከተጠየቀባቸው ተጠርጣሪዎች ጋር እንድንቀመጥ አደረጉን፡፡
ጠበቃ ተማም ከችሎት ወዲያው ወጣ፡፡ ፍቃዱም ተከተለ፡፡ ሌሎች ጓደኞቼም ስለዋስትና ጉዳይ ለመነጋገር ተከታትለው ከችሎት ወጡ፡፡ በዕለቱ ችሎቱ የተጠናቀቀው ከቀኑ 8፡00 ሰዓት ላይ ነበር፡፡ እኔ እና አምሳሉ ወደዳኛው ቢሮ በመሄድ ልናነጋራቸው እንደፈለግን ገለጽልናቸው፡፡ ዳኛው በትህትና ‹‹ግቡ ና ተቀመጡ›› አሉን፡፡ ሰላምታ ከሰጠናቸው በኋላ ‹‹ዋስትናው ስለበዛ እንዲቀነስልን›› ጠየቅን፡፡ ዳኛውም እንደማይቀነስ፣ ነገር ግን 10 ወይም 15 ሺህ ብር የሚደርስ የመንግሥት ደመወዝተኛ የደመወዙን መጠን በመግለጽ ዋስትና ሊሆነን እንደሚችል ነገሩን፡፡ በአንድ ወቅት የቀድሞ ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጋዜጣዊ መግለጫ በጽ/ቤታቸው ሲሠጡ የ‹‹ቁምነገር›› መጽሄት ዋና አዘጋጅ የሆነው ጋዜጠኛ ታምራት ኃይሉ ደመወዛቸው ስንት እንደሆነ ሲጠይቃቸው 6000 ብር መሆኑን የገለጹት ትዝ አለኝና በውስጤ ፈገግ አልኩ፡፡ በወቅቱ ከ10000-15000 ሺህ ብር የሚከፈለው የመንግሥት ሠራተኛ በሀሳቤ ሊመጣልኝ አልቻለም፡፡ በወቅቱ ከዚህ ውጭ ምንም አማራጭ አመኖሩን ተገንዝበን ‹‹እናመሰግናለን›› በማለት ዳኛውን ተሰናብተን ወጣን፡፡
ከ30 ደቂቃ በኋላ እዩኤል እና መኳንንት ወጡ፡፡ በአቤልና በፍቃዱ መካከል አለመግባባት እንደተፈጠረ ነገሩኝ፡፡ ፍቃዱ ‹‹ሊብሬዬን ካስያዝኩ መኪናዬን መሸጥ መለወጥ አልችልም›› የሚል ሃሳብ መንሳቱን፣ አቤል ደግሞ ‹‹ይህ የዋስትና ጉዳይ የአንተ ኃላፊነት ነበር›› [በዚህ ጉዳይ ላይ የእኔን ሃሳብ በቀጣዩ ጽሑፍ ላይ እጠቅሳለሁ] በማለት የቃላት ልውውጥ ማድረጋቸውንና ፍቃዱም አቤልን ‹‹ከአንተ በላይ ተቆርቋሪና አሳቢ እንደሌለ ለማስመሰል አትሞክር›› በማለት መኪናውን አስነስቶ መሄዱን ነገሩኝ፡፡ አቤልም አፍታ ሳይቆይ ወደ ችሎት መጣ፡፡ አቤል መናደዱ ፊቱ ላይ ያስታውቃል፡፡ ተረጋጋ አልኩት፡፡ ሌሎች ሰዎች ስለእኔ በማሰብ ስልኬ ላይ ሲደውሉ ችሎት ቁጭ ብዬ በሞባይል መልዕክት ስለነበረው ነገር ነገርኳቸው፡፡
አንድ ሴት ፖሊስ አንገቴ ላይ ያደረኩትን የኢትዮጵያ ሰንደቅ (አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ) ስከርፍ ‹‹አውልቅ በለው›› እንዳለችው እዩኤል ነገረኝና አውልቄ ስከርፌን፣ ላፕቶፔን፣ ሞባይሌንና የቤቴን ቁልፍ ሰጠሁት፡፡ እስር የግድ መሆኑ ገባኝ፡፡ በዝምታ ከውስጤ ጋር ማውራት ጀመርኩ፡፡ ነገሮችን እንዳመጣጣቸው በእርጋታ የመቀበል ባህሪዬን ተጠቅሜ ራሴን በማረጋጋት አምሳሉን ተረጋጋ አልኩት፡፡ አልፎ አልፎ ስለተለያዩ ነገሮች ማውራታቸንን ቀጠልን፡፡ በመስኮቱ አሾልኬ እየተመለከትኩ በአዲስ አበባ ከተማ ለልማት ተብሎ በሚካሄደው ድሆችን ጥግ-የማስያዝ ዘመቻ ሲተራመስ ተመለከትኩ፡፡ ለ ‹‹መልሶ ማልማት›› ይሉታል¡ ቀየው ላይ ተመልሶ ሲለማ የታየ ግን የለም፡፡ አራት ኪሎ ይኖሩ የነበሩ ጀሞ፣ ካዛንቺሶች ደግሞ ሰሚት ሲሄዱ እንጂ መልሰው ሲለሙ አላየንም፡፡ አያሌ ሚዲያዎችም ለልማት ተነሺ እንዲሆኑ ተፈርዶባቸዋል፡፡ እነሱ ግን ‹‹ለልማት – ተነሺ›› እንጂ ‹‹መልሶ – ለሚ›› አይደሉም! አይ ‘ልማት’ ¡
ክፍል – 2 ይቀጥላል
ክፍል – 2 ይቀጥላል
No comments:
Post a Comment