የካቲትን ደራሽ፤ ግንቦትን ደግሞ ተደራሽ አድርጎ በትርክቱ ፍሰት እንደ ወራጅ ውሃ አንባቢውን ይዞ የሚነጉደውን የዶ/ር ነገደ ጎበዜን የሃሳብ ሙላት የዋኘሁት በሁለት መልኩ ነበር። በታሪክ “መረጃነቱና” በስነ-ጽሁፍ ውበቱ። ትርክቱ እንደ ውሃ ሙላት እያሳሳቀ ይዞ ስለሚነጉድ ቆም ብሎ የድርጊቶችን ጊዜና ቦታ የትና መቼ? እንዴትና በማን? ብሎ ኩነቶችን ለማስታወስ አንባቢውን ፋታ ስለሚነሳ ዐይንና ገጽ ሳይነጣጠሉ እንዲተሙ ትንታኔው የማስገደድ ባህሪይ አለው። ድርሰቱ ሶስት ዓይነት ትውልድ አንባቢ ያለው መሰለኝ። የመጀመሪያው ትውልድ የደራሲው ጓደ- ዘመን ትውልድ ሲሆን ሁለተኛውና ሶስተኛው ደግሞ የየካቲቱና የድህረ-የካቲቱ ትውልዶች ናቸው። አዲሱ ትውልድ በትርክቱ መሳሂብ ተውጦ ከጫፍ እስከ ጫፍ ያለማቋረጥ በንባቡ ሊነጉድ ይችላል። ለየካቲቱ የታሪክ ኩነቶች ባዕዳ ስለሆነ ዕውነቱንና ውሸቱን ለመለየት መቼ? የት? ለምን? በማንና እንዴት? የሚሉ ጥያቄዎችን እንዲያነሳ አይጠበቅበትም። ቀዳሚዎቹ ሁለቱ ትውልዶች ግን የመጀመሪያን ክፍል አንብበው ከየካቲቱ ትርክት ላይ ሲደርሱ የኩነቶቹን ይዘትና ዕውነታ ከጊዜና ቦታ ጋር እያገናዘቡ መቼ? ለምን? እንዴትና በማን? ማለታቸው አይቀርም።
ትርክቱም እንደ አንባቢው በሶስት ክፍሎች የሚከፈል መሰለኝ። የመጀመሪያው ምዕራፍ የትርክቱ ታሪካዊ መንደርደሪያ ሲሆን የቅድመ-የካቲቱን የለውጥ እንቅስቃሴ ይዳስሳል። ሁለተኛው ክፍል ደግሞ የየካቲቱን ህዝባዊ ማዕበል አነሳስና አወዳደቅ ሲሸፍን ሶስተኛውና የመጨረሻው ክፍል ግን አብዮቱን በውርስ ይዞ የመረሸውን ግንቦትንና የግንቦትን ቅልበሳ ተረማምዶ የወደፊቱን የትግል ሂደት የሚዳስስ መሰለኝ። በመጀመሪያውና በመጨረሻው ሁለት ክፍሎች ላይ የሚጎረብጥ ውሸት ስላላየሁበት ተቃውሞ የለኝም። እውነትና ውሸት ተገለባብጠው ብዙ አክሮባት ተሰርቶ ያየሁበት በመሃለኛው ክፍል ነው። በዚህ ክፍል የዕውነት አፅም እንደ ጤፍ ቀርም ተልከስክሷል። ይሉኝታም በጥሬው ተቆርጥሞ ተበልቷል። መበላቱ ብቻ ሳይበቃ ዐይነ-ሞራ ገላጭና ሞራል አዳይ ባለስልጣን ሲሆንም ተስተውሏል ።
እንደ መነሾ
ዶ/ር ነገደ ጎበዜ የቀደምቱን ትውልድ የለውጥ እንቅስቃሴ አሻጋሪና ተሻጋሪ አድርገው ለየካቲቱ ህዝባዊ ማዕበል መፋለቂያ ምንጭነቱን ብቻ ሳይሆን ከዚያም አልፎ ወደ ግንቦት ተሻጋሪነቱን በስነ-ጽሁፍ ውበት እያኳሸሙ ግንቦት ላይ ያደርሱታል። ከግንቦትም ማግስት ቀጣይነቱን እውር በደበሳ ፈልጎ ያገኘው ዘንድ ስዕሉን ፍንትው አድርገው ያቀርቡታል። ከየካቲት ወደ ግንቦት የተሸጋገረው ህዝባዊ ማዕበል የዛሬዎቹን የአሜሪካንና የእንግሊዝን ጉዲፍቻዎች ጠራርጎ የመውሰድ ግዙፍ ሃይሉን ብቻ ሳይሆን የአወሳሰዱንም ስልት ታክቲኩንና ስትራቴጂውን ብልት ብልቱን ለያይተው የማዕበሉ ወጀብ ወደየት እንደሚወስደው በአብርሆት አመላክተዋል። የሆነ ሆኖ ግን መጭውን ትግልና ግበዓቱን በአብርሆት አሻግረው እንደተመለከቱት ሁሉ በህልፈት የሸኘነውን የካቲት ግን ዘወር ብሎ ለማየት አንገት ሲያጥራቸው ተስተውሏል።
የኩነቶች ተሻጋሪነት በሰዎች የመገንባትና የመናድ ሃይል እንደሚወሰን ያለፉት ታሪኮቻችን ያስገነዝቡናል። ዕውነትና ቅንነትም ተሻጋሪ ባህሪያቶቻቸው ህልው የሚሆኑት የሰዎች ስብዕና በየሚኖረው የመገንባትና የመናድ ሃይል ነው። ስለሆነም ደራሲው ከየካቲት ማግስት እስከ ግንቦት መባቻ የነበረውን ትርክት “የራስን ንጹህ ሰውነት” ለመፍጠር ሲሉ ትርክቱን ከዕውነት ጋር ሆድና ጀርባ አድርገውታል። በዚህም ህፀፃቸው መጽሃፉን ከጠቃሚ የታሪክ ሰነድነት አውርደውታል። በዚህ ድርጊታቸውም ቂመኛ ይሆኑና በቁርሾ ራሳቸውን ሲያቀጭጩ ይታያሉ። በበኩሌ የፊውዳሉ ባህላችን እርሳቸውንም እንደ ብዙዎቹ ልሂቃን የምሁር ወርዴ ሲያደርጋቸው መታዘብ አለመታደል ይመስለኛል።
በኋላ ቀሩ ባህላችን ተጠቂ ከመሆን ያላመለጡት እኒህ “ትልቅ” ሰው ከየካቲት ማግስትና ከዚያም በኋላ በቀጣዮቹ ቀናት፤ ወራትና ዓመታት የተከሰቱትን ፖለቲካዊ ስህተቶች ከፍ ሲል የኢህአፓ፤ ዝቅ ሲል ደግሞ የሰደድና የደርግ ጥፋቶች ያደርጓቸውና አብዮቱ ተቀለበሰ ይሉናል። በዚህም ክህደት የራሳቸውንና የመኢሶንን በደም የወየበ እጅ በትርክቱ ጎርፍ አጥበው “ያፀዱታል”። ስለሆነም ይህን በትርክቱ ሊያፀዱት የሞከሩትን ወንጀል የተፈበረኩትንም “ዕውነታዎች ”በወቅቱ መሬት ላይ ከነበረው ጭብጥ ጋር እያመሳከሩ እውነቱን ከውሸቱ አበራይቶ መለየት ተገቢ መሰለኝ። የክሳቸው መጀመሪያ የታህሳስ 4ቱ 1968 ዓ.ም “የገበሬ ማህበራትን ለማጠናከር”የወጣው አዋጅ ሲሆን ተከሳሹም ኢህአፓ ሆኗል።
“በኢህአፓ አመራር በኩል. . . በተለይ ዴሞክራሲያ ጳጉሜ 4 ቀን 1967 ዓ. ም “የገጠሩ ትግል” በሚል ርዕስ ለንባብ ባበቃው እትሙ በመካሄድ ላይ ያለው የገጠሩ ትግል ማንገብ ይኖርበታል ያለውን ዋና ዋና አጀንዳ ሲጠቁም ስልጣን ለገበሬ ማህበራት እንዲሰጥ፤ ድሃ ገበሬዎች እንዲታጠቁ . . . ወዘተ እያለ በተራማጅ የሚነሱትን ጥያቄዎች ያስተጋባ ነበር”። ሆኖም በዚህ አቋም ከመቀጠል በየካቲት የመሬት አዋጅ ወቅት እንደታየው አቋም ለውጥ ወይም መለሳለስ ያሳያሉ ተብሎ ሲጠበቅ የኢህአፓ መሪዎች አዲስ በተፈጠረው ሁኔታ ሳቢያ ከደርግ አንጻርየያዙትን የሙሉ ተቃውሞ አቋም በመቀጠል እንደገና ፈትሸው ለአዲሱ ሁኔታ የሚመጥን ስትራቴጂ ማውጣት አልቻሉም። አልፎ ተርፎ ይህንን በመኢሶን በኩል ስለ ሀገሪቱ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ተስፋችንን የጣልንበትን አዋጅ . . . . “በታወቁ አድርባይ ምሁራን ተረቆ ፍሽዝምን በገጠሩ ለማጠናከር የፀደቀና በህዝብ ትግል ተወጥሮ የተያዘውን ደርግ ለህዝብ ጥያቄ መልስ የሰጠ በመምሰል የአብዮቱን ሂደት ለመግታት የተጠነሰሰ ሴራ” በማለት በማያዳግም ሁኔታ ይኮንነዋል። (ገጽ 96) ሲሉ የተጠየቅ ፋይል ከፍተውበታል።
በመኢሶንና በኢህአፓ መሃከል የነበረውን ልዩነት የገበሬ ማህበርን በማጠናከርና ባለማጠናከር አዋጅ የተከሰተ ልዩነት አስመስሎ መመልከቱ ስህተት ነበር። ልዩነቱ የተፈጠረው ኢህአፓ ከመወለዱ በፊት በ1963 ዓ.ም በኃይሌ ፊዳና በብርሃነ መስቀል የአቋም ልዩነቶች ነበር። ወደ ልዩነቱ ስርዎ-መሰረት ከማምራታችን በፊት ግን በዚሁ በተናስው ገበሬ ነክ አዋጅ ዙሪያ የነበረውን ልዩነት መልክ አስይዘነው እንለፍ።
አብዮት ሲሉ አብዮት ስንል
ዶ/ር ነገደ ጎበዜና ጌታ ያደሩለት ደርግ አብዮት ሲሉ እነርሱ የማይነጠቅ ስልጣን የሚጨብጡበትን ሂደት ሲሆን፤ ኢህአፓ ግን አብዮት የሚለው ስልጣን የህዝብ የሚሆንበትን ሂደት ነበር። ይህም ማለት ደርግ ለጊዚያዊ ህዝባዊ የሽግግር መንግስት ስልጣኑን አስረክቦ ከሽግግሩ ማግስት ህዝብ የመረጠው አካል አገሪቱን የማስተዳደር ሃላፊነት የሚረከብበትን ሂደት ማመቻቸት ነው። መኢሶን ግን እርሱ ህዝቡን እንደ ካደው ኢህአፓም ከድቶ ደርግን በአዋጅ የተራማጅ ካባ እየደረበ አብዮታዊ በማስመሰል ግራዚያኒ መንግስቱን ከስልጣን ቆጥ ላይ የማይወርድ አውራ ዶሮ ለማደረግ ሳይተባበር ቀረ ብሎ ያማርራል። ኢህአፓና መኢሶን ድሮውንም የተለያዩት ቁርጠኝነት በመኖርና ባለመኖር ልዩነት ስለነበር ነገሩ የሚገርም አይሆንም። ትዝብቱ ግን ዶ/ር ነገደ ኢህአፓ አዋጁን የተቃወመው ደርግን ህጋዊ መንግስት ለማደረግ ያለመፈለግ እንጂ የገበሬዎችን በነጻ መደራጀትና መታጠቅ መቃወሙ እንዳልሆነ እያወቁ ነገሩን ገልብጠው “ተስፋችንን የጣልንበትን” አዋጅ አመከነው ብለውታል።
“ኢህአፓ አዋጁን ፋሽዝምን በገጠሩ ለማጠናከር የጸደቀ አዋጅ ነው” ያለው እንበለ ምክኒያት አልነበረም። ዝግየት ብሎ እንደ ተከሰተው የራዛ ዘመቻና በኋላም ኢህአፓ/ኢህአሠ በተንቀሳቀሰባቸው የገጠር አካባቢዎች በተለይም በፀለምት፤ በጃናሞራና በበለሳ አርሶ አደሮች ላይ የተፈጸሙትን ፋሽስታዊ ጭፍቸፋዎችና የመንደር ቃጠሎዎች፤ የተዘረፉትን የቀንድና የጋማ ከብቶች፤ ፍየሎችና በጎች፤ የቤት ውስጥ ቁሳቁሶችና አስገድዶ መድፈርን ጨምሮ የተፈፀሙትን ግፎችና በደሎች አሁን ላይ ሆነን ስናያቸው አዋጁን መቃወሙ በደርግ የገበሬ ማህበር ሚልሻ ይህ ግፍ እንደሚፈጸም ተንብዮ ኖሯል።
መኢሶን አዲስ አበባን ከኢህአፓ ለማጽዳት በመጋቢት ወር 1969 ዓ.ም ባካሄደው የመንጥር ዘመቻ ከፖሊስ ሠራዊት፤ ከካድሬዎችና ከቀበሌ ጥበቃ ጋር ተሰልፈው ፋሽስታዊ እርምጃ የወሰዱት የገፈርሳና የሱሉልታ ገበሬ ማህበራት ታጣቂዎች መሆናቸው ደግሞ ሌላው የኢህአፓን ስጋት ገላጭ ደርጊት ነበር። በኋላም ወጉ ደርሶት የመኢሶን አመራር በርሃ ሊወጣ መንገድ ሲጀምር አንገት አንገቱን እያነቁ ለፋሽስት ያስበሉት እኒሁ መኢሶን “ያደራጃቸው” የገበሬ ማህበራት መሆናቸው የኢህአፓን ስጋት ህልው አድርጎታል። ገበሬዎቹ በዚሁ ድርጊታቸው ሌላም ዕውነታ ያረጋገጡ መሰለኝ። የመኢሶንና የደርጉ ሽርክና የማታ ማታ
ዕድሜውን በሙሉ ሲያነባ ለፈጀው
የአጋም ጉርብትና ለቁልቋል ምን በጀው ?
እንዲሉ ሆኖ መደምደሙን።
ከዚሁ ከገበሬው አዋጅ ጋር በተያያዘ ዶ/ር ነገደ “ድሮውንም ስለገበሬው ደንታ ያልነበረው ኢህአፓ . . .” በማለት መኢሶንን ብቸኛው የገበሬ ተቆርቋሪና አብዮተኛ አስመስለውታል። ዶ/ር ነገደ አላወቁት እንደሁ እንጂ መናገርና መሆን ሁለት የተለያዩ ነገሮች ናቸው። “እንደ አርስጣጢለስ መናገር ላይቸግር ይችላል፤ እንደ ሶቅራጥስ ግን የተናገሩትን መኖር (ሆኖ መገኘት) በእጅጉ ይከብዳል” እንደተባለው በነጭ ሸሚዝ ላይ ቀይ ክራባት ሸብ አድርጎ በቤተ መንግሥት ግቢ የድሎት ህይዎት እየቀጩ በአዋጅ ላይ አዋጅ ማዥጎድጎድና በገበሬው መሃል ተገኝቶ የገበሬውን ኖሮ እየኖሩ ገበሬውን ማደራጀት የሰማይና የምድር ያክል ይራራቃሉ። ገበሬው የሚበላውን ጥሬ ቆርጥሞ፣ ገበሬው የሚጠጣውን ጥርኝ ውኃ ተጎንጭቶ፣ ገበሬው ከሚተኛበት መደብ ተኝቶ፣ እንደ ገበሬው ቀምሎ፣ ገበሬው የታረዘውን እርዛት ታርዞ፣ ርሃቡን ተርቦ፣ ችጋሩን ተቸግሮ ገበሬውን ያደራጀ ጸጋየ ገ/ መድህን (አበበ ደብተራው) እንጂ ዶ/ር ነገደ ጎበዜ አልነበረም። ፍቅሬ ዘርጋው እንጂ አንዳርጋቸው አሰግድ አልነበረም። መኢሶን አደራጀሁት የሚለው የገበሬ ማህበርም ኢህአፓ ካደራጀው የገበሬ ማህበር ጋር ከቶውን ሊወዳደር የሚችል አይሆንም። የመኢሶን የገበሬ ማህበር በአንድ ጥፊ የሚናደ የዕምቧይ ካብ ነበር። ኢህአፓ ያደራጀው የገበሬ ማህበር ግን ደርግን ከመፋለም ባሻገር ዛሬም ለወያኔ የጎን ውጋት መሆኑን ከሚገልጹት ትግብርቶቹ አንዷን ልጥቀስ።
ጊዜው የ97ቱ የምርጫ ወቅት ነበር። አዲሱ ለገሰ ወደ ጎንደር ድሮ ኢህአፓ/ኢህአሠ ይንቀሳቀስበት ወደነበረው በለሳ ወረዳ ጎራ ብሎ የምረጡኝ ዘመቻ ሲያካሂድ ልዩ ምልክታችን ንብ ነች ይልና እጁን ከሞላው ወረቀት አንዷን የንብ ስእል ከፍ አደርጎ ያሳያል። ገበሬዎቹም ከንግግሩ በኋላ ማስታወቂያው ሲታደላቸው አንደኛው ገበሬ “ልዩ ምልክታችን ንብ ነች አልከን? ሲል አዲሱን ይጠይቀዋል። አዲሱ ለገሰም አዎ ንብ ነች ብሎ ሲመልስለት፤ ገበሬው መልሶ ምልክታችሁ ንብ ሲሆን ሥራችሁ ግን የዝንብ ነው በማለት በነጻ የመደራጀት መብታቸውን ወያኔ እንደማያከብርላቸው ነግሮት መንግዱን ሲቀጥል ይህ ገበሬ አለቀለት ብየ ነበር። አዲሱ ግን ምንም ሳይለው ቀረ በማለት በቦታው ተገኝቶ ያየውን ሁኔታ ጓደኛየ አጫውቶኛል።
ልዩነቱ እንዴት ተጀመረ?
“የገበሬ ማህበራትን ለማጠናከር” ስለወጣው አዋጅ ይህን ካልን ዘንዳ ወደ ልዩነቱ መነሾ እንመለስና መቼና እንዴት እንደተጀመረ እንዳስሰው። እነ ብርሃነ መስቀል እረዳ ከባህር ዳር አውሮፕላን ጠልፈው መስከረም 1962 ዓ.ም ሱዳን ይገባሉ። ከዚያም ለደህንነታቸው ሱዳን አስተማማኝ ስላልነበር ወደ ሌላ አገር እንዲዛወሩ ጠየቁና ጠያቄያቸውን ወደ ተቀበለቻቸው ወደ አልጀሪያ ያቀናሉ። የነብርሃነ ቡድን አልጀሪያ በገባ ባመቱ ማለትም በ1963 ዓ. ም ኃይሌ ፊዳ ወደ አልጀሪያ ይሄደና መጠነኛ የገንዘብ እርዳታ አድርጎ ከብርሃነ መስቀል ጋር ውይይት ያካሂዳል። ብርሃነ መስቀልና ቡድኑ በውጭ የሚኖሩት ወንድሞቻቸው ድርጅት መስርተው ይሆናል የሚል ግምት ሰለነበራቸው ከኃይሌ ፊዳ በሰሙት የድርጅት አለመኖር ቅሬታ ይሰማቸዋል። አንገብጋቢነቱንም ለሃይሊ ፊዳ ብርሃነ መስቀል ሊያስረዳው ይሞክራል። ኃይሌ ፊዳ ግን በኢትዮጵያ አብዮት ለማካሄድ ጊዜው አሁን አይደለም፤ ጊዜው ገና ነው ሲል አቋሙን ይገልጻል። ብርሃነ መስቀልም በበኩሉ ትግሉ ተጀምሯል። ወደ ኋላ የቀረው ትግሉን መምራት የሚገባው ድርጀት አለመኖር ነው ሲል መሬት ላይ የነበረውን ጭብጥ ለኃይሌ ፊዳ ሊያስጨብጠው ይሞክራል። በዚህም ውይይቱ ተቋጭቶ ስምምነት ላይ ሳይደርሱ ይለያያሉ። ታህሳስ 1965 ዓ.ም በርሊን ላይ እንደገና ሲገናኙ በጨዋታቸው መሃል “አብዮት በኢትዮጵያ ለመፈንዳት ስንት ጊዜ የሚፈጅ ይመስልሃል?” ሲል ብርሃነ መስቀል ኃይሌ ፊዳን ይጠይቀዋል። ኃይሌ ፊዳም ሳያመነታ “ከሃያ አምስት ዓመት በፊት አብዮት በኢትዮጵያ ሲመጣ አይታየኝም” ሲል ይመልስለታል። (ክፍሉ ታደሰ ያ ትውልድ ገጽ 85) አብዮቱ ግን ሁለት ሳምንት ባልበለጠ ጊዜ ወስጥ ፈነዳ።
የአልጀሪያውንና የነኃይሌ ፊዳን ቡድን ከድርጅት ጉዳይ ባሻገር ሌሎችም ያላግባቧቸው ልዩነቶች ነበሯቸው። እነዚህም ልዩነቶች እየሰፉ ወደ ተማሪው ማህበራት ተሰራጭተው የሁለቱን ቡድኖች የሃሳብ ልዩነቶች በየበኩላቸው አጠጠሩት። እየጠጠሩ የመጡት ልዩነቶችም በተማሪው ጋዜጣ በ”ታጠቅ” ገጾች ላይ ጎልተው መታየት ጀመሩ። በታጠቅ መጽሔት ይወጡ የነበሩት የአልጀሪያው ቡድን መጣጥፎች ሽርሞ ነክ (polemical) ስለነበሩ የነኃይሌ ፊዳ ቡድንም ሽርሞውን በሽርሞ ለመመለሰ እስከተወሰነ ጊዜ ሲንገዳገድ ቆይቶ የብዕሩን መዶልዶም ሲገነዘብ የአልጀሪያውን ቡድን መጣጥፎች በመጽሄቱ ገጾች እንደማያስተናግድ አስታወቀና የራሱን ጽሁፎች ብቻ ማውጣት ጀመረ። በወቅቱ የመጽሄቱን ዝግጅት ይቆጣጠር የነበረው የነኃይሌ ፊዳ ቡድን ነበርና የአልጀሪያውን ቡድን መጣጥፎች እንደማያስተናግድ ሲገልጽ ልዩነቱ እየጦዘ ሄደ። በተጀመረው የብዕር ውረድ እንውረድ “ጦርነት” የነብርሃነ መስቀል ቡድን የአመዛኙን የተማሪ ድጋፍ ሲያገኝ የነኃይሌ ፊዳን ቡድን በአውሮፓ የተማሪዎች ማህበር ብቻ እንዲወሰን ማደረጉ አልቀረም።
የአልጀሪያው ቡድን የብዙሃኑን ተማሪ ድጋፍ ወደ ትግብርት መንዝሮ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነጻነት ግንባር (ኢሕአግ) የተሰኘ ድርጅት በ1964 ዓ.ም በርሊን ላይ መሰረተ። ምስረታውንም ተከትሎ ፖለቲካዊና ወታደራዊ ሥራዎች መቀላጠፍ ጀመሩ። ይህም ፈጣን እንቅስቃሴ ከአራት ዓመት በፊት በ1960 ዓ.ም ተመስርቶ ለነበረው መኢሶን የዳተኝነት ብቻ ሳይሆን የደካማነት ምልክት ሆኖ ታየ። መኢሶንም ይህንኑ ደካማነቱን አውቆ ገና ከጅምሩ እነዚህ ልጆች . . ማለት ጀመረ። ልዩነቶቹ እየሰፉ ሲሄዱና ኢሕአግም ድርጅታዊ ዕድገቱ እየጎላ ሲመጣ ሁኔታው መኢሶንን እያሳሰበው ይሄድ ጀመር። የተማሪው ማህበር የፈጠረው የኃይል ሚዛን ማጋደል እነብርሃነ መስቀልን ታላላቆቻቸውን የማያከብሩ ተደርገው እንዲታዩ የራሱን ተጽኖ አሳድረና በመኢሶን ጥርስ ውስጥ የገባች ባቄላ እንዲሆኑ አደረጋቸው። በዚሁ ላይ የብሔርና የትግል ስልት ( ያኔ ባሌ ውስጥ አመጽ ይካሄድ ስለነበር )ጥያቄ በቦሌና በባሌ ወደ አገር የመመለስ አቋም ታክሎበት ልዩነቱ ወደ ለየለት የጎራ ሽኩቻ ተሸጋገረና እናንተና እኛ መባባልን አስከተለ።
ከዚህ በኋላ ሁለቱም ቡድኖች የየራሳቸውን መንገድ ጠርገው ግስጋሴያቸውን ቀጠሉና መኢሶን አንድ የኤርትራ ተወላጅ አባሉን ጀብሃን ለትጥቅ ትግል የትብብር እርዳታ እንዲጠይቅ ወደ ሶሪያ ይልካል። ከዚሁ ልኡክ ጎን ለጎንም ሁለት አባላቱን (የከፋና የኢሉባቡር ተወላጆች) ለዚሁ ጉዳይ ወደ ሱዳን ይልካል። ሆኖም ጀብሃን ለመገናኘት ወደ ሶሪያ የተላከው የመኢሶን ልኡክ ጀብሃን ተቀላቅሎ በዚያው ሲቀር የሱዳኑም ልኡክ ተልኮው ይጨናገፍና የመኢሶንን በቦሌ መግባት ብቸኛው የትግል ስልት እንዲሆን ይደመድመዋል። ይህ በዚህ እንዳለ ደርግ የሚጓዝበትን አቅጣጫ የሚያመላክቱት ግራ ዘመም አመለካከት ያላቸውን ምሁራን ካገር ወስጥና ውጪ ማፈላግ ላይ እንዳለ የመኢሶን አመራር አጋጣሚውን ተጠቅሞ ከደርጉ ጋር ግንኙነት ይፈጥራል። ነገሩ ሰኔና ግንቦት ሲገጣጠሙ ሆነና ትኬት ተልኮለት የመኢሶን አመራር በቦሌ ወደ አገሩ ፊቱን አቀና።
በባሌ ለመግባት ቆርጦ የነበረው ኢሕአግ/ኢህአፓም በበኩሉ ለትጥቅ ትግሉ ዝግጅት ከሳላህ ሳቤ ቡድን ጋር ግንኙነት ፈጥሮ ወደ ሜዳ የሚልካቸውን አባላቱን በፍልስጤም ነጻ አውጭ ድርጅት እንዲሰለጥኑ ወደ ሶሪያ ላከ። ይህም ቡድን በደማስቆስ አካባቢ ወዲያ ወዲህ ሲል ድንገት ቤሩት ዩኒቨርሲቲ ተማሪ በነበረውና በመንግሥት ጆሮ ጠቢነት ይጠረጠር በነበረው በተስፋየ ታደሰ ዕይታ ውስጥ ይገባል። ተስፋየም ቡድኑን ተከታትሎ የሰበሰበውን የስም ዝርዝር ወደ አውሮፓ ተማሪዎች ማህበር (ወደ መኢሶን አመራር) ይልከዋል። ( ክፍሉ ታደሰ ያ ትውልድ ገጽ 104) የመኢሶን አመራር አገር ቤት እንደገባም ተስፋየ የኢህአፓን አባላት የስም ዝርዝር በጋዜጣ ያሳትመዋል። ይልቁንም የስም ዝርዝሩ ተባዝቶ ለደርግ ደጋፊዎችና ለፀጥታ ክፍሎች ጫፍ እስከ ጫፍ ተበትኖ ኢህአፓዎቹ እንዲታደኑ ተደረገ። ኢህአፓም ይህን የማጋለጥ ደባ በራሱ ላይ ጦርነት እንደታወጀበት ቆጥሮ በነሀሴ 1967 ዓ.ም በወጣው የዴምክራሲያ እትም “ጦርነቱ ታውጇል” ሲል የሰጠው የአጸፋ ምላሽ የመጠፋፋቱ ዋዜ ሆነ። የመዲናይቱ አየር በዚህ መልክ ተወጥሮ እያለ ደ/ች ብርሃነ መስቀል በወሎ፣ ቢትወደድ አዳነ መኮነንና ጀ/ል ነጋ ተገኝ በጎንደር፣ ደ/ች ስሜነህ በጎጃም፣ ራስ መንገሻ ስዩም በትግራይና ሁለቱ ወንድማማቾች የብሩ ልጆች ደግሞ በሰሜን ሸዋ ደርግን ተቃውመው ጦርነት ጀመሩ።
ባንድ በኩል በከተማ የገጠመው አለመረጋጋት በሌላ በኩል ደግሞ ባገሪቱ ገጠሮች የተጀመረው የጥጥቅ ተቃውሞ ደርግን እንቅልፍ ነስቶት ያድር ስለነበር በዕስር የነበሩትን የቀድሞ ባለስልጣናት የፍርድ ሂደት መጠበቅ በራስ ላይ እባብ መጠምጠም እንደሆነ ይመክሩት የነበሩት ምሁራን ባሳደሩበት ጫና ስድሳዎቹን አውጥቶ እረሸናቸው። ከነዚህ የድሮ ባለስልጣናት ጋር ሌሎች ሰባት ሰዎችም አብረው ተረሸኑ። ከነዚህ ውስጥ ሶስቱ የኢህአፓ አባላት ስለነበሩ ኢህአፓም የመኢሶን እጅ እንዳለበት መገመቱ አልቀረም። ከዚያም በጎር ጎራ ከተማ ሁለት የኢህአፓ አባላት መምህር ሽባባው ካሴና መምህር ታረቀኝ የጥምቀት ዕለት ታቦቱን አጅባችሁ ጸረ-ደርግ ግጥም ስትደረድሩ ውላችኋል ተብለው ታሰሩ። ብዙም ሳይቆዩ ተገደሉ። እነዚህን መምህራን ለማስያዝ ጥቆማውን ያካሄደው የመኢሶን ካድሬ ነበር። በጎጃም ክፍለ ሀገርም በቢቸና አውራጃ እንዲሁ ኢህአፓዎች ናችሁ ተብለው በጥርጣሬ ተይዘው ባልና ሚስት አርሶ አደሮች ተገደሉ። እነዚህንም ጠቁሞ ያስያዛቸው የመኢሶን ካደሬ ነበር። በጅማም እንዲሁ ተመሳሳይ እስራትና ግድያ በኢህአፓዎች ላይ ተፈፀመ። ከዚህ በኋላ መኢሶን ባቋራጭ ስልጣን ሊይዝ ሲጣድፍ ኢህአፓ ያደናቅፈኛል በሚል ፍርሃት የደርግን ትከሻ ተደግፎ ሊያጠፋው በስፋት ዘመተበት። ሀቁ ይህ ሆኖ ሳለ ዶ/ር ነገደ ግን አልሞት ባይ ተጋዳይ የነበረውን ኢህአፓን በጠብ አጫሪነት ገልብጠው ከሰውታል።
ቅልበሳና ቀይ ሽብር
ቀጥለን ዶ/ር ነገደ ጎበዜ በመጽሃፋቸው ብዙ ስፍራ ወደ ሰጡት ወደ ቅልበሳው ርዕስ እንሸጋገርና ቅልበሳው መቼና በማን እንደ ተከናወነ ተረገጡን እንፈልግ። “የቅልበሳው ዘር ሲዘራ” በሚል ንኡስ ርዕስ የጀመሩት ትንታኔ በውስጡ የሸሸጋቸው ዕውነታዎች ብዙ ስለሆኑ እኔም ዘርዘር አድርጌ ለማየት እሞክራለሁ።
“በርግጥም ከ1968 ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ በአዲስ አበባ የኃይል ሚዛን በተቀያየረ ቁጥር አብዮታችን አስደናቂ በሆነ ፍጥነት አንዴ እያጠቃ አንዴ እየተከላከለ ሲንገዳገድ ቆይቶ ከየካቲት/መጋቢት 1969 ዓ.ም በኃላ የአብዮታዊ ሰደድ ኃይሎች መሃከለኛውን መንግሥት በመቆጣጠራቸው መልሶ እንደማይነሳ ሆኖ ወደ ተከላካይነትና ወደ ሽንፈት አመራ። የዚህን የቅልበሳ ዘር መዝራት ሂደት መጀመሪያ ከ1968 ዓ.ም ከረምት አንስቶ እስከ ጥር 26 1969 ዓ.ም ድረስ በተካሄደው የደርግ አንጃዎች ፍልሚያና በነጭ ሽብር ሳቢያ በአብዮቱ ሃይሎች ላይ በወረደው ፈተና ዙሪያ መተንተን ይቻላል። ከዚያም በነዚህ በተያያዙ ሁለት አሉታዊ ክስተቶች ሳቢያ ለቅልበሳው በተመቻቸው ህብረተሰባችን በ1969 ዓ.ም ሁለትኛ አጋማሽ ጀምሮ ገና ከነጭ ሽብር ዘመቻ ባላገገሙት በአብዮት ሃይሎች ላይ በሰደድ ስውር ኮማንዶዎች የተከፈተው “ቀለም የለሽ” የሽብር ሂደት በ1970 ዓ.ም መጀመሪያ ወራት በቀይ ሽብር ዘመጃ ተተክቶ ሁኔታዎች ለለየለት ቅልበሳ እንዴት እንደ ተመቻቹና በተለይ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ለገበሬው መብትና ምርት ንጥቂያ ሂደት በሩ ተበርግዶ እንደተከፈተ እንመለከታለን።”(ገጽ 203-4)
በዚህ ጥቅስ ውስጥ የተካተቱት አንኳር ነጥቦች ሁለት ናቸው። ቅልበሳና ቀይ ሽበር። ማንኛችንም በዚያን ወቅት የነበርን ሰዎች አንድም በተቃዋሚው ወገን አለያም በደርግ ዙሪያ ከነበሩ “ህቡዕ” ድርጅቶች ጎን እንድንሰለፍ ሁኔታዎች አስገዳጅ እንደነበሩ እናስታውሳለን። ትውስታችን ካልካደን በቀር የነበረውን የፖለቲካ ሽኩቻና የስልጣን እሽቅድድም አሁን ላይ ሆነን ስናጤነው የትግል ሰካራሞች እንመስል እንደነበር ብዙዎቻችን አንክድም። ዛሬም ከአርባ ዓመት በኋላ ያንኑ የፖለቲካ ስካር እንዳንደግም ዕድሜአችንና ተመክሯችን ከበቂ በላይ ጫና ያደርግብናል የሚል ግምት የነበረው የሰው ቁጥር ቀላል አልመሰለኝም። በተለይ ዕድሜ ጠገብ የሆኑት “ገራም ገራም” ሰዎቻችን ለታችኞቹ ትውልዶች በአራያ ምኩራብነት እንዲታዩ የሚያደርጋቸውን ሃላፊነት አይስቱትም ብሎ የገመተው የጓህ ፖለቲከኛ በዶ/ር ነገደ ሥራ ተስፋውን ያሟጠጠ ይመስለኛል። መኢሶንና ኢህአፓ ትናንት ባደረጉት ትግል የአህያ ውድቆሽ የወደቁ ኃይሎች መሆናቸውን ተረድተው የትናንቱን ስህተት ለዛሬው መማሪያ የደርጉት ዘንድ ታሪካዊ ሃላፊነት አለባቸው። ሁለቱ ድርጅቶች ድርጅታዊ፤ ፖለቲካዊና ወታደራዊ ኃይላቸው ትናንት በነበረው ሁኔታ ላይ እንዳይደለ ሲያውቁት ዛሬ በሌለ ሁኔታ የጠብ ያለህ በዳቦ ለምን እንደሚሉ ሳስበው ያመኛል። ባለፈ ነገር መተነኳኮስ ላለፈው ነው ጭንቀቱ ወይስ ለወደፊቱ ፋይዳ? ማንንስ ጎድቶ ማንን ለመጥቀም ነው ይህ ሁሉ ክህደትና ውሸት?. . . የሚሉ ጥያቄዎችን ያጭራል። ትችቱም የተሰነዘረው እነዚህን ጥያቄዎች ታሳቢ አድርጎ ነው።
ደራሲው ሙሉውን አራት ዓመት የደርግ ካባ ቀዳጅ ሆነው ሲያገለግሉ እንዳልኖሩ ከቤተመንግሥት ሲባረሩ አብዮቱ ተቀለበሰ ይሉናል። አብዮቱ መቀልበስ የጀመረው የመኢሶን አመራር የጊዚያዊ ህዝባዊ መንግሥትን ጥያቄ ወደ ጎን ገፍቶ ሂሳዊ ድጋፍ ብሎ ለምርጥ መኮንኖች ጌታ ለማደር የአውሮፕላን ቲኬት ተገዝቶለት በቦሌ ሲገባና ደርግም መስከረም ሁለት 1967 ዓ.ም ኢትዮጵያ ትቅደም በሚል ማዘናጊያ መፈከር የንጉሡን ወንበር በውርስ የያዘ ዕለት ነበር። ከአብዮቱ ፍንዳታ እስከ ጥር 26 1969 ዓ.ም ድረስ ደርግን ከስልጣን ለማውረድ በተደረገው ትግል ከደርግ ጎን ተሰልፎ ታጋዮችን ሲያፍን፤ ሲገርፍና ሲረሽን ድፍን ሁለት ዓመታት ያስቆጠረው መኢሶን ራሱን ብቻ ታጋይ አድርጎ ትግሉ ተቀለበሰ ሲል ሀፍረቱን በጥሬው ቆርጥሞ የጨረሰው ይምስለኛል። ሀቁ ይህ ሆኖ ሳለ ደራሲው ግን የመኢሶንን ገመና ወደ ህዝቡ አዙረው “ለቅልበሳ በተመቻቸው ህብረተሰባችን” . . . አብዮቱ ማጅራቱን ተመትቶ ሂደቱን አቆመ ይላሉ። ዕውነታውን ለሚያውቀው ግን ይህ አባባላቸው መኢሶን ከፖለቲካው ጨዋታ ወጣ ማለታቸው እንደሆነ ግልጽ ነው። ሌላው አስገራሚ ፈጠራ ግን ቀይ ሽብር የተጀመረው በ1970 ዓ.ም መጀመርያ ወራት ላይ እንዲሆነ ተሰልቶ ቀይ ሽብር የተጀመረው ከመኢሶን ቤትመንግሥት መውጣት በኋላ እንዲመሰል ብዙ ውሸት ተዋሽቶ “እኛ የቀይ ሽብር ተጠቂዎች እንጂ አራማጆች አልነበርንም” ለማለት ተሞክሯል። ዕውነት ዕውነቱን እንነጋገር ከተባለ በወቅቱ በሁለቱም ወገን የተፈጸመውን ስህተት እንደየ ድርሻቸው ተቀብለው ያለፈውን ለወደፊቱ መማሪያ ማደረግ በቻሉ ነበር። ግን አልሆነም።
የሆነ ሆኖ ግን ቀይ ሽብር የተጀመረው ጥር 26 1969 ዓ.ም እነ ሻምበል ዓለማየሁ በተገደሉ ማግስት ነበር። “መፈንቅለ መንግሥቱን” አስመልክቶ በሻለቃ ደበላ ዲንሳ በተመራው በፓርላማ ውስጥ የቀበሌና የከፍተኛ ሊቀ መናብርት ስብሰባ ላይ ተሰብሳቢዎቹ አስታጥቁን! አታስጨርሱን! እያሉ ከፍተኛ ጩኸት አሰምተው ስለነበር ሻምበል ለገሠ አስፋው “ቀይ ሽብር እንዲፈፀም ተፈቅዷል። ነፃ እርምጃ መውሰድ ትችላላችሁ” ተብሎ ነበር ቀይ ሽበር የታወጀው። ቀጥሎም ቀይ ሽብሩን የሚመራ የቀይ ሽብር ኮሚቴም ተቋቋመ። ከአዋጁ በኋላም መኢሶን ያነሳው መፈክር ቀይ ሽብር ይፋፋም! ዕርቅ የለም! የሚል ነበር። ለቀይ ሽብር ደርግና መኢሶን ተጠያቂነት አለባቸው ሲሉ ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም የመሰከሩትም ይህንኑ ሀቅ ነበር።
ዶ/ር ነገደ ጎበዜ ቀደም ሲል ከዶ/ር ካሱ ጋር ሆነው በኢህአፓ አባላት ላይ እጅግ ብዙ ጭካኔ ፈጽመዋል። ከአሲምባ መጥተው የታሰሩ የኢህአፓ አባላትን ካላነጋገርን ብለው ሁለቱ ዶ/ሮች ከሹሙ ከኮ/ል ተክለ ሚካኤል አርምዴ ጋር ትልቅ አምባጓሮ ፈጥረው እንደነበር ዶ/ር ነገደ የሚረሱት አይመስለኝም። ኮለኔሉ ቢፈቅዱላቸው ኖሮ ምን ሊያደርጉ እንድሚችሉ መገመት አያዳግትም። ቀጥሎ የብ/ጀኔራል ተፈሪ ባንቲን የብሔራዊ ዕርቅ ጥሪ ለመቃወም በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ግቢ መኢሶን የጠራውን ስብሰባ ለማደናቀፍ በሞከሩት ኢህአፓዎች ላይ ቆራጥ እርምጃ ወስደናል ሲሉ አቶ ኃይሌ ፊዳ ለፖሊስ ምርመራ በሰጡት ቃል ቀይ ሽብር በመኢሶን መጀመሩን አስምረውበት አልፈዋል። ያን ጭፍጨፋም የፈጸሙትም በወቅቱ ስብሰባውን ይመሩ የነበሩት ራሳቸው ዶ/ር ነገደ ጎበዜ መሆናቸውን ህሊናቸው እያወቀው ቀይ ሽብር የተጀመረው በ1970 ዓ.ም ነው ሲሉ አንባቢውን ደግመው ዋሽተውታል። ቀይ ሽብር የመነጨው በቤተ መንግስቱ ግድያ ነበር እነዓለማየሁ በግፍ ሲረሸኑ።
የነመቶ አለቃ ዓለማየሁ “ወንጀል” ብሄራዊ ዕርቅ ይውረድ፤ የደርጉ ጽ/ቤት ችሎታ ባላቸው ሰዎች ይመራ፤ በአንድ ግለሰብ እጅ የወደቀው ስልጣን እንደየ ደረጃው ይከፋፈል፤ የደርጉ ሥራ በሥርዓት ይከናወን፤ በደርጉ ዙሪያ ባሉ ድርጅቶችና በኢህአፓ መካከል ግልጽ ውይይት ተካሂዶ የህዝቡ የስልጣን ጥያቄ በተገቢው መንገድ መልስ እንዲያገኝ ሁኔታዎች ተመቻችተው ህዝቡ ይምረጥ ማለታቸው ለመኢሶን አልተመቸም። ይህንኑ ሁኔታ የደርግ አባል የነበሩት በጋሻው አታላይ እንዲህ ያቀርቡታል። “መኢሶኖች የሚፈልጉትን ስልጣን በራሳቸው ጥረት ሳይሆን በሌሎች ከለላነት ነበር ለመያዝ ይታገሉ የነበሩት። በጥሪው መሰረት ኢህአፓ ወደ ብሔራዊ ዕርቅ መድረክ ከመጣ ባቋራጭ ስልጣን ለመንጠቅ ያቆጠቆጡት የመኢሶንና የወዝ ሊግ ምሁራን ከሳሪ መሆናቸውን ፈጥነው አወቁና በዳኔል አስፋውና በስዩም መኮንን አቀናባሪነትና በመንግሥቱ መሪነት፤ በኃይሌ ፊዳና በሰናይ ልኬ አማካሪነት እነተፈሪ ባንቲ በሀሰት ውንጀላ ተበሉ” በማለት ( በምስክርነት) ሀቁን አስቀምጠውታል።
በሃገሪቱ ዕስር ቤቶች ውስጥ ታጉረው ከነበሩት ብዙ እስረኞች መሃል መፈታት የነበረባቸውን እስረኞች ለይቶ በማውጣት ለደርግ ሊያቀርብ አንድ ኮሚቴ ተቋቁሞ ነበር። ‘ሊፈቱ ይገባቸዋል’ ያላቸውን የአንድ መቶ እስረኞች የስም ዝርዝር ዶ/ር ነገደ ጎበዜና ዶ/ር መስፍን ካሱ ከአባተ መርሻ ተቀብለው በሃምሳዎቹ እስረኞች ስም ፊት በቀይ ቀለም ( x ) ኤክስ አስቀመጡበት። ሁለቱ ዶ/ች ምልክት ያደረጉበት የስም ዝርዝርም ወደ ደርግ ጽ/ቤት ተልኮ እስረኞቹ ተገድለዋል።
ደርግና መኢሶን እስከ ሰኔ 10 ቀን 1969 ዓ.ም ድረስ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታ፣ አንድም ሁለትም ነበሩ። ስለዚህ ደርግና መኢሶን ከኢህአፓ ምልሶች አንጀኞች ጋር ሆነው ገድለዋል። አስገድለዋል። ዕስር ቤት የታሰሩትን በሰከሩ ጌዜ እያወጡ የተኩስ መለማመጃ ያደርጓቸው የነበረውን ግፍ የዶ/ር ነገደ ጎበዜ ህሊና ይስተዋል ተብሎ አይገመትም። የመኢሶን አሳፋሪ ሥራ ወደ ቀበሌዎች ወርዶ በህዝብ ላይ ስንትና ስንት ግፍ ፈጽሟል። አገር ወዳዶችንና ምሁራንን የአዳሃሪነት፣ የህአፓነት፣ የበራዥነት፣ ታርጋ እየለጠፉ አሰሩ። ስየል (torture) ፈጸሙባቸው። ገደሏቸው። አሰደዷቸው። የዶ/ር ነገደ ትርክት እነዚህንና ሌሎች በርካታ ግፎችን ተረማምዶ ነው ስለ ቅልበሳ ሊነግረን ብዙ አዙሪት የሚዞረው። ከአዙሪቱ ውስጥም የነ ብጀ/ል ተፈሪ ባንቲ አገዳደል ይገኝበታል። ዶ/ር ነገደ ጎበዜ ግን ስለነ ተፈሪ ባንቲ የግድያ ሴራ እኔም ሆንኩ ኃይሌ ፊዳ ምንም አናውቅም ሲሉ በትርክታቸው አንባቢውን ደግመኛ ዋሽተውታል።
ከወደ መግቢያየ እንደ ገለጽኩት የኩነቶችን ዕውነትነትና ውሸትነት ለማበጠር የጊዜ ሰፌድ ባለቤት ያልሆነው አዲሱ ትውልድ የንባቡን ግርድና ምርት እንደ ወረደ ወስዶ ሊማርበት አለማቻሉ ብቻ ሳይሆን ባልተገባደደው ትግል ላይም የሚኖረው አሉታዊ እንደምታ ጭምር ይመስለኛል የዚህን ትርክት አሳሳቢነት የሚያጎላው። የቀይ ሽብርን አነሳስና አወዳደቅ ከቅልበሳው ጋር እያጎዳኘን ከየካቲት መባቻ እስከ ጥር 26 1969 ዓ.ም የጀመርነውን ትንተና ስንቀጥል ጥር 26 1969 ዓ. ም በነተፈሪ ባንቴ የተጀመረው ግድያ እስከ ጳጉሜ 1ቀን 1969 ዓ.ም ዘልቋል።
ወሩ መጋቢት 1969 ዓ.ም ነበር። መኢሶን “አዲስ አብባን ከኢህአፓ ለማጽዳት” በሚል ሰበብ የመንጥር ዘመቻ አካሂደ። ስፍር ቁጥር የሌላቸውን የኢህአፓ አባላትና ደጋፊዎች አሰረ። ገደለ። በአንጃዎችና በመኢሶን ትብብር የኢህአፓ መዋቅር የተጎለጎለ ልቃቂት እስኪመስል ውሉ ጠፋ። በርካታ መሳሪያዎች በመኢሶን እጅ ወደቁ። ብርሃነ መስቀል ረዳ መዋቅር ጥሶ በሰጡው ትዕዛዝ ሳቢያ የኢህአፓ መከላከያ ሀይል ምንም አጸፋ ሊሰጥ ባለመቻሉ የመኢሶን ካደሪዎች ከጫፍ እስከ ጫፍ አዲስ አበባን ዋኝተው ተመለሱ። መኢሶንም ቀደም ሲል አንስቶት የነበረውን “ዴሞን በዲሞትፈር” መፈክር ወደ ደም መነዘረው። የኢህአፓ መሪዎችም ተስፋየ ደበሳይ፣ ዮሃንስ ብርሃኔ፣ ከፍሉ ተፈራ፣ ግርማቸው ለማ፣ ነጋ አየለና ሌሎቹም በአሰሳው ተገደሉ። ነጻ እርምጃና ቀይ ሽበር በኢህአፓዎች ጀርባ ላይ እየተለጠፉ “አብዮቱ ከተከላካይነት ወደ አጥቂነት” ተሸጋገረ ተባለ። በዚህ መልክ መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም በመኢሶንና በደርግ የተጀመረው ቅልበሳ ሂደቱን ጨርሶ ፋይሉ እንዲዘጋ የተደረገው ጥር 1969 ላይ ነበር። እነሻምበል ዓለማየሁን በግፍ በመግደል!!!
የማይነቅዘው በቀል
የመኢሶን ኢህአፓን የማጥፋት ዘመቻ ግን ከጥር 26 1969 በኋልም እስከ ሃምሌ 1970 ዓ.ም መዝለቅ ብቻ ሳይሆን ከዚያም ባሻገር ዛሬም ድረስ አላቆመም። ከቤተ መንግሥት ከወጣበት ከመስከረም 1970 ዓ.ም በኋላም በዚያው ዓመት ሃምሌ ወር ላይ ለንባብ ባበቃው የሰፊው ሕዝብ ድምጽ እንዲህ ብሎ ነበር፦
ለ. ቢሮክራሲውንና ኢደህን በሚመለከተው በኩል
- የታወቁ አድሃሪ የሲቭል/ሚሊታሪ ቢሮክራቶች ከስልጣን እንዲወገዱ፣
- የነፍስ ግድያ ተባባሪ በሆኑ አድሃሪ ቢሮክራቶች ላይ አብዮታዊ እርምጃ እንዲወሰድ፣
- የሲቪል/ ሚሊታሪ ቢሮክራሲ እንዲዘመትበት እንጂ እንዳያዘምት፣
- ሃቀኛና ተራማጅ የሲቪል/ሚሊታሪ ትስጋዮች በቢሮክራሲው ውስጥ እንዲገቡ፣
- በሰሜን ክፍለ ሀገር ትዕግስትና ብልህነት የተሞላበት ከፍተኛ የፖለቲካ ሥራ እንዲሰራ፣
ሐ. የኢህአፓን ነጭ ሽብር በሚመለከተው በኩል
- በሕዝባዊ ነፃ እርምጃዎች ላይ የተደረገው እገዳ እንዲነሳና ተፋፍሞ ያለማቋረጥ እንዲቀጥል እንዲደረግ፣
- የተቋረጠው የሰፊው ሕዝብ መታወቅ እንዲቀጥል፣
- በታወቁ የኢህአፓ ቅጥር ነፍሰገዳዮች ላይ አብዮታዊ እርምጃ እንዲወሰድ፣
- ቅጥር ነፍሰገዳዮችን እያሰሩ መልቀቅ እንዲቆም፣
መ. የኤርትራን ጥያቄ በሚመለከተው በኩል
- 1. በዚያ የተሰማራው ጦር በሰውና በትጥቅ እንዲጠናከር
- 2. በዚያ የሚገኙት አድሃሪ የሚሊታሪ ቢሮክራቶች እንዲወገዱና ለጦሩ የፖለቲካ ትምህርት እንዲሰጥ
- 3. በአስተዳደር በጸጥታውና በሌሎች የመንግሥት መ/ቤቶች የተሰበሰቡት ጉቦኛ ቢሮክራቶች እንዲመነጠሩ፣
- 4. የኤርትራ ኮሚሽን ሥራ እንዲፋጠን፣
- 5. በተጠናከረ የፖለቲካ ቅስቀሳና ማደራጀት የክ/ሀገሩን ህዝብ ድጋፍና ዕምነት ለማግኘት እንዲሰራ፣
- 6. ከኢ.ኤል.ኤፍ-ቲ.ፒ.ኤል.ኤፍ ጋር ተጀምሮ የነበረው “ውይይት” እንዲቀጥል፤
- 7. የአፋርን ሪጅናል አውቶኖሚ ጥያቄ በአስቸኳይ መመለስ፣ (የሰፊው ሕዝብ ድምጽ ቁ. 67 ሃምሌ 15/1970 ገጽ 22)
ይልና በ” ሠ” ና በ”ረ” ተራም እኮኖሚውንና ብሔራዊ ነጻነትን በተመለከተ. . . እያለ ይቀጥላል። መኢሶን ከቤተ መንግሥት ከወጣ በኋላም ቀይ ሽብርና ነጻ እርምጃ መቆም እንደሌለባቸው አገዛዙን ይወተውት እንደነበር ከፍ ብሎ የተጠቀሰው የሰፊው ሕዝብ ድምጽ ጉልህ መረጃ ነው። ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ እንዲሉ ትጥቁን ቢቀማም እንኳ መግደሉ እንዳይቆም ዘመቻውን አላቆመም። እዚህ ላይ አንባቢ ልብ ሊለው የሚገባ አንድ ቁም ነገር አለ። መኢሶንና ወያኔ ቀደም ሲል ሃምሌ/ነሃሴ 1968 ዓ.ም ፀረ-ኢህአፓ ውል ተፈጣጥመው ነበር። ሻለቃ ጌታቸው ሽበሺ የመራው የመኢሶን/ደርግ ቡድን መቀሌ ድረስ ሄዶ ነበር ውሉን የተዋዋለው። ወያኔ በገጠር፤ ደርግና መኢሶን ደግሞ በከተማ ኢህአፓን አጠራቅቆ ማጥፋት ነበር የውሉ ቋጠሮ። ከፍ ሲል በ”ለ” ክፍል ቁጥር አምስት ስር “በሰሜን ክፍለ ሀገር ትዕግስትና ብልህነት የተሞላበት ከፍተኛ የፖለቲካ ሥራ እንዲሠራ” የምትለዋ ቁምነገር መኢሶን ወዳጁን ወያኔን ጥቃት እንዳይደርስበት መከላከሉ ነበር። ይህንኑ የወያኔና የደርግ/መኢሶን ግንኙነት ኃይሌ ፊዳም ለፖሊስ በሰጠው ቃል አረጋግጦታል። ገብሩ አሥራትም “ተሓሕት ከውጊያ ውጭም ከደርግ ትጥቅ የሚገኝበትን መንገድ ያፈላልግ ነበር። በአመራሩ ውሳኔ ይሁን በግል ተነሳሽነት እስካሁን ድረስ ግልጽ ባልሆነልኝ መንገድ. . . በ1969 ዓ.ም በጋ ላይ አረጋዊ በርሀ ሽሬ እንዳስላሴ ገብቶ ከደርግ ባለስልጣናት ጋር እንደተነጋገረ በሕዝብ ግንኙነት ሠራተኝነቴ ሰምቼ ነበር። ከኢደህ ጋር በተደረገው ጦርነት ተሓሕት ውስጥ በደረሰው ከፍተኛ የትጥቅ ችግር የተነሳም ሽሬ እንዳስላሴ መሽጎ ወደ ነበረው የደርግ ጦር ሰፈር ተጉዞ በወቅቱ የማይታሰበውን ውይይት አድርጓል ይባላል” ይልና ወረድ ብሎም “ተሓሕት ይህን ከደርግ ጋር የተደረገውን ግንኙነት በይፋ ባለማመኑም ባዘጋጀው ድርጅታዊ ታሪክ “የመኢሶን ካድሬዎች መሳፍንቱን ለመግጠም ከህወሃት ጋ ተስማምተናል እያሉ ያደናግሩ ነበር” ሲል የሁለቱን ድርጅቶች ግንኙነት አስረግጦ ያልፈዋል። ( ገብሩ አሥራት ሉዓላዋላዊነትና ዴምክራሲ በኢትዮጵያ ገጽ 70-71 )
መኢሶን ከመነሻው ደርግን ከለላ አድርጎ ሊይዘው ያቀደው ስልጣን ሳይሳካለት ቢቀር በወያኔ ከለላ አገኘዋለሁ ብሎ ነበር ሁለት ባላ ተክሎ አንዱ ሲሰበር በሌላው ለመንጠልጠል እንዲችል እንቅፋት ይሆንብኛል ያለውን ኢህአፓን ከወያኔ ጋር ተባብሮ ለማጥፋት ውል የተዋዋለው። ዶ/ር ነገደ ጎበዜ ግን ይህን ዕውነታ በውሸት ጋርደው ከህዝብ ዕይታ ሊሰውሩት ቢሞክሩም ሳይሳካላቸው ቀርቷል። ክቡራትና ክቡራን ምን ያንከራተተናል አትብሉኝና ከዚህ የሴራ ጎዞ ወጥተን በህሊናችን ምናብ አዲስ አበባ እንመለስ። ወቅቱ መጋቢት ወር 1969 ዓ.ም ነበር;፡ አዲስ አበባ በመኢሶንና በደርግ ቀይ ሽበር ጎዳናዋ በሬሳ የተሞላበት ወቅት። ጠረኗ ደም ደም የከረፋበት ወቅት። እናቶች ልጆቻቸው የተገደሉበትን የጥይት ዋጋ እየከፈሉ እሬሳቸውን እንዲያነሱ የተገደዱበት ወቅት። መኢሶን የኢህአፓን አንጃዎች እገዛ አግኝቶ የጀግና ሱሪ ታጠኩ ያለበት ወቅት። ኢህአፓም በራሱ የድሮ አባላት ክህደት ህልውናው ጥያቄ ወስጥ የገባበት ጊዜ መጋቢት 1969 ዓ.ም ነበር።
በመጋቢቱ አሰሳ ከተገደሉት የኢህአፓ መሪዎች ዶ/ር ተስፋዬ ደበሳይ አንዱ ነበር። ዶ/ር ነገደ ጎበዜ ግን ግድያው ከአሰሳው ጋር የማይያያዝ መሆኑን በወ/ሮ ገነት መጽሀፍ ውስጥ የመንግስቱ ኃይለማርያምን ቃል ዋቤ አድርገው አገዳደሉን በኢህአፓ አንጃዎችና በዘመቻ መምሪያ ቅንብር የተከናወነ ግድያ አድርገውታል። አቶ አሰፋ ጫቦ ግን “ተስፋዬ ደበሳይ በዶ/ር ንግሥት አዳነ ጠቋሚነት ጠቅላይ ፖስታ ቤት አካባቢ ሊያዝ ሲል አምልጦ አምባሳደር የመጨረሻ ፎቅ ላይ ተወርውሮ ራሱን ገደለ” ( ጦቢያ መጽሄት 1991 ዓ. ም ገፅ 17-18) በማለት የዶ/ር ነገድን ሃሳብ አይጋሩም። የደህንነቱ ባልደረባ ሻ/ል ተስፋየኤ ረስቴም “ የመኢሶን ካድሬዎች ባይሳተፉ ተስፋየ ደበሳይን የደርግ ወታደሮችም ሆኑ የደህንነት አባላት መለየት አይችሉም። ዶ/ር ተስፋዬ ደበደሳይን ለአሳሹ ጦር ያሳየችና ከኪሱ መታወቂያውን አይተው ያረጋገጡ ዶ/ር ንግሥት አዳነ ሲሆኑ፤ የተስፋዬ ደበሳይን አስከሬን ከወደቀበት ቦታው ላይ እንዲነሳ ያስደረጉ ደግሞ ዶ/ር ነገደ ጎበዜ፣ ዶ/ር ንግሥት አዳነና ኮ/ል ስለሺ መኩሪያ ናቸው” ሲሉ የአሰፋ ጫቦን ሃሳብ ያጠናክሩታል።ይህ ማለት ግን አንጀኞቹ ጌታቸው ማሩና ብርሃነ መስቀል ረዳ ለዘመቻ መምሪያው ክፍል አልጠቆሙም ማለት አይደለም። በወቅቱ መኢሶን ሳያውቀው ምንም ነገር ስለማይደረግ ከመኢሶን ዕውቅና ውጭ በደርግ ኃይሎች ብቻ የተከናወነ ትግብርት ነበር የሚለው የደራሲው ሃሳብ ውኃ የሚቋጥር ዕውነት ሲሆን አይታይም ለማለት እንጂ አንጀኞቹ አልጠቆሙም ለማለት አይደለም። የዶ/ር ንግሥት አዳነና የዶ/ር ነገደ ጎበዜ ከማንም በፊት ቀድሞ በቦታው መገኘት በራሱ የሚነግረን ዕውነት አለው።
ግንቦትንና የካቲትን ተደራሽና ደራሽ አድርጎ የተነሳው የዶ/ር ነገደ ጎበዜ ትርክት ባመዛኙ የደራሲው የግል አስተያየት ሊሆን ይችላል። ለዚህ ግምቴ ያለኝ አመክንዮ የድርጅቱ “ ሂሳዊ ግምገማ” ከደራሲው ትርክት ፈጽሞ የተለየ መሆኑ ነው። ( ገጽ 296-303) የድርጅቱ “ ሂሳዊ ግምጋሜ” ዶ/ር ነገደ ጎበዜ የቆሙበትን መሬት ንዶታል። እርሳቸው ግን ዛሬም የሚኖሩት ትናንት የኖሩትን የቤተ መንግሥት ህይዎት ይመስላል። ለነገሩ በፖለቲካ ዓለም ውስጥ ያለፈው ቀድሞ የወደፊት ሁኔታ መሆኑ የተለመደ የታሪክ አዙሪት ስለሆነ የደራሲውን ትግብርት አዲስ አያደርገውም። ያለፈው ወደፊት ቀድሞ የግንቦቱ ቅልበሳ የየካቲቱን ስህተት ሲደግመው ታዝበናል። እኛም ካለፈው ተመክሮ ተለብመን
ዘመኑን ጨርሶ በጀመረው ፈሰስ
ታሪካችን ሁሉ ዳግም ላይመለስ
ይመስለናል እንጂ በሽኝት ተጉዟል
ተመልሶ መጭ ነው የነገን ቁልፍ ይዟል
እንዲሉ ያለፈው ቀድሞን ነገን ከመሆኑ በፊት እያንዳንዳችን ቀድመን ከራሳችን ህሊና ጋር እርቅ አውርደን የዕውነት ሰዎች መሆናችንን ለዚህች ዘማዊ ዓለም ማረጋገጥ የምንችለው ዕውነቱን ስንመሰክር ብቻ ነው። ለነገሩ ይህች ዓለም የዕውነት ዓለም እንዳይደለች እናውቃለን። ኢየሱስ ክርስቶስን በቢስማር ቸንክራ፣ ሶቅራጥስን በሲባጎ አንጠልጥላ፣ ዶ/ር ማርቲን ሉተር ኪንግን በጥይት ደብድባ የገደለች ዓለም ከቶውንም የዕውነት ዓለም ልትባል አትችልም። የሰው ልጆችም መርሆዋን አንድም ሲታገሉት አለያም በሽንፈት ተቀብለውት ኑሮዋን ሲኖሩት ኖረዋል። እኔም ስለኖርነውና ለወደፊቱም ስለምንኖረው ዕውነትና ውሸት ያለኝን እሳቤ በነዚህ ስንኞች ልቋጥርና ልሰናበታችሁ።
በቅቡል አንደበት በቃላት ሞሽሮ
ወይም በልብ ወለድ በማስመሰል ፈጥሮ
አመኔታ እሚቀርፅ ምንም ይሁን የትም
ዕውነት እንደ ውሸት ብዙ መልክ የላትም።
ታህሳስ 2006
No comments:
Post a Comment