Tuesday, December 2, 2014

ማመን፣መታገል

መደማመጥና መነጋገር ከቻልን የማንፈታቸው ልዩነቶች የሉም!!!
አገራችን እና ሕዝቧ በአንድ ጠባብ ዘረኛ ቡድን መዳፍ ውስጥ ናቸው። በአገራችን የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች የግለሰብም ሆነ የቡድን መብቶቻቸው ተረግጠው በባርነት እየተገዙ፤ ጉልበታቸውና ሃብታቸው እየተመዘበረ ነው።
ኢትዮጵያ ውስጥ የምገኝ ዜጎችና ማኅበረሰቦች ሁሉ እጣ ፈንታችን ተሳስሯል። ሁላችንም ነፃ ካልወጣን በስተቀር ማናችንም በተናጠል የነፃነት አየር መተንፈስ አይቻለንም። ስለሆነም ለራሳችን የግልም የሆነ የቡድን ጥቅም ስንል እያንዳንዳችን ስለሁላችን ማሰብና መጨነቅ ግዴታችን ነው።
ከሁሉም የዲሞክራሲና የነፃነት ኃይሎች ጋር ተባብሮ ለመሥራት የሚያደርገው ጥረት ፍሬ እያፈራ ቢሆንም አሁንም የንቅናቄ አቋም በትክክል ያልተገነዘቡ ወገኖች እንዳሉ መገገንዘብ አያዳግትም።

ስለሆነም ኢትዮጵያዊ የሆንን በመሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ያለንን አቋም ደጋግመን ግልጽ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ መታየት ያስፈልጋል
1. ሥልጣንን በተመለከተ
የኢትዮጵያ መንግሥት የሥልጣን ምንጭ የኢትዮጵያ ሕዝብ መሆን ይገባዋል ብሎ ማመን፤ ለዚህም መታገል። ሁሉም የአስተዳደር እርከኖች አንድ ዜጋ አንድ ድምጽ ኖሮት በሚካሄድ ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ ብቻ የሚሾሙ መሆን ይኖርባቸዋል ብሎ ማመን፤ ለዚህም መታገል
ኢትዮጵያ የተለያዩ ማኅበረሰቦችና የተለያዩ እምነቶች ተከታዮች አገር መሆኗን ማወቅ። ለእንዲህ ዓይነቱ አገር ያልተማከለ ፌደራላዊ የመንግሥት አወቃቀር የተሻለ ነው ብሎ ማመን። በእያንዳንዱ ፌደራላዊ መንግሥት ውስጥም የዲሞክራሲ መሠረት የሆነው የአንድ ሰው አንድ ድምጽ መርህ መከበር አለበት ብሎ ማመን
ይህ መንገድ ነው በብዙሃን የሚደገፉ መሪዎችን ወደ ሥልጣን የሚያወጣልን።
2. መብቶችን በተመለከተ
የግለሰብና የቡድን መብቶች መከበር ይኖርባቸዋል ብሎ ማመን፤ ለዚህም መታገል።
የቡድን መብቶችን ሰጥቶ የግለሰብ መብቶችን መንሳት ምንም አለመስጠት መሆኑ በተግባር ከህውሃት አገዛዝ የምናየው ነው።ህውሃት ለብሄር፣ ብሄረሰቦች የክልል መንግሥታዊ መዋቅርን፣ አርማን፣ መዝሙርን፤ በቋንቋ መማርና መዳኘትን እና የመሳሰሉትን መስጠቱ ዘወትር የሚነግረን ጉዳይ ነው። እነዚህ ሁሉ ዋጋ ያላቸው ነገሮች የሚሆኑት ከግለሰብ ነፃነት መከበር ሆነው ቢሆን ነበር። ሰው የሰውነት ብሎም የዜግነት መብቱ ካልተከበረ የቡድን መብቱ መከበሩ ምን ትርጉም ይሰጠዋል? ፍትህ ሳይኖር በቋንቋው መዳኘቱ ተበዳይን ምን ይጠቅመዋል? የመረጠውን ሰው መሾም፤ የማይስማማውን መሻር የማይችል ከሆነ በስሙ የሚጠራ መንግሥት መኖሩ ምን ይፈይድለታል?
በሌላ በኩል ደግሞ የግለሰብ መብቶች ብቻቸው በቂ ናቸው ብዬ አላምንም። እንደ ኢትዮጵያ ላለ ውስብስብ ታሪክ ላላት አገር የቡድን ፍላጎቶችና ስሜቶች በቸልታ ማለፍ አይቻልም። በግለሰብ ነፃነት ሥም የቡድን መብቶችን መደፍጠጥም ኢፍትሃዊ ነው ብሎ ማመን። በተለያዩ ደረጃዎች ያሉ የማኅበረሰብ ክፍሎች እና ሃይማኖቶች ጠንካራ የቡድን ስሜትና ፍላጎት ሊኖራቸው እንደሚችል መገንዘብ
በዚህም ምክንያት ለሁለቱም የመብት ዓይነቶች እውቅና የሚሰጥ መንግስት ያስፈልጋል
3. ትብብርን በተመለከተ
የትብብር ጥሪ ሲደግ ሁላችንም በአገር ማዳን ስሜት እንነሳ በሚል ብቻ አይደለም። የተለያዩ ርዕዮቶች እና አስተሳሰቦች ባላቸው ቡድኖች መካከልም ትብብር ሊኖር እንሚችል ማመን። በአንድ ድርጅት ውስጥ እንኳን የተለያዩ አስተሳሰቦችን የሚያራምዱ ቡድኖች ቢኖሩ ከእያንዳንዱ ጋር መተባበር ይቻላል ብሎ ማመን
የአንድ ወገን እውነት የሁሉም ወገን እውነት ላይሆን እንደሚችል መገንዘብ። ለመደማመጥ ዝግጁዎች ከሆንን የጋራ ችግሮቻችን በርካታ ናቸውና በሚያስማሙን ጉዳዮች ላይ ተመርኩዘን ትግላችን ማጎልበት ይገባል ብሎ በጽኑ ማመን፤ ለዚህም መታገል
ከአገር ቤት ወይም ከውጪ ካሉ ኢትዮጵያዊያን ከዲሞክራሲና የነፃነት ኃይሎች ጋር መተባበር የሚፈልገው ዛሬ ተባብረን መታገላችን ለዘላቂው አብሮነታችን መሠረት ይጥላል ብሎ ማመን ነው።
መደማመጥ፣ መሰማማትና መነጋገር ከቻልን የማንፈታቸው ልዩነቶች የሉም።

ከሰብኣዊ

No comments:

Post a Comment