Friday, December 26, 2014

ለሥልጣን ለውጥ ወይስ

ይድነቃቸው ከበደ
ይህን ለማለት የሚያስደፍረው በአገራችን የሚካሄደው ምርጫ፣ የፖለቲካ ወይም የዲሞክራሲ ቅንጦት ሣይሆን፣ የአገር እና የዜጎች የእልውና ጉዳይ መሆኑ የሚያረጋገጥ የበዛ ምክንያት በመኖሩ ነው፡፡
----------------------
የትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ እራሱን ለምርጫ በማቅረብ ያወዳድራል፤በምርጫም ካሻነፈ የመንግሥትነትን ሥልጣን ይይዛል፡፡በምርጫ ዕድል ካልቀናው የተቃዋሚውን ቦታ ይዞ መንግስት ለሚያቀርበው ፓሊስ እና ፕሮግራም ነቀፌታ ወይም አማራጭ አሳብ በማቅረብ የተለመደው የፖለቲካ ሥራ ይሰራል፡፡ እንዲህ አይነቱ የፓርቲዎች አደረጃጀት እና አሰራር በሰፊው የተለመደ ጤናማ አካሄድ ነው፡፡የፖለቲካ ሊቃውንት ከላይ የተገለፀውን አካሄድ ጤናማ ነው ሲሉ፣ዋንኛ መመዘኛቸው ያልተንዛዛ በዛ ቢባል ፣ከሁለት ዙር ያለፈ የስልጣን ዘመን እንደማይኖር ታሳቢ በማድረግ ነው፡፡በተለይ እንዲህ አይንቱ የፓርቲዎች እንቅስቃሴ ፣በከፍተኛ ዲሲፕሊን እና በተቀናጀ የሙሉ ጊዜ የፓርቲ ስራ ላይ በሚያሳልፉ ታጋዮች የሚከናወን ጥበባዊ ስራ ነው፡፡


በአገራችን በሰላማዊ መንገድ እየተንቀሳቁ የሚገኙ አገረ የአቀፍ እና የክልል ፓርቲዎች መኖራቸው የሚታወቅ ነው፡፡ከነዚህ መካከል ምን ያህሉ በሙሉ ጊዚያቸው የፖለቲካ ስራ እየሰሩ ይገኛሉ፣ለፓርቲያቸው ዲሲፕሊን ያላቸው ተቆርቋሪነት እና ታማኝነት እስከምን ድረሰ ነው ፣ብልህነት የተሞላበትና የማይጨናገፍ ለድል የሚያበቃ ዕቅድ የትኛው ፓርቲ ነው ያለው ፤በማለት ተጠያቂነትና ግልፅነት ያለው ጥያቄ ማንሳት አግባብነት ያለው ሃቅ ነው፡፡ይሁን እንጂ እነዚህን ጥያቄዎች ማንሳትና መልስ መስጠት የዚህ ጽሑፍ ዓለማ አይደለም፡፡ ሆኖም ግን በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ ለጹሑፊ መነሻ ለሆነኝ እርስ እንደ መነሻ አሳብ ልጠቀምበት ችያለው፡፡
የፊታችን ግንቦት ወር ለ5ኛ ጊዜ አገረ አቀፍ ምርጫ ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ምርጫውን አስመልክቶ የተለያየ አሳብ ሲንፀባረቅ እንደነበር እና አሁንም የቀጠለ መሆኖ ለማወቅ ተችሎአል፡፡በተለይ በማህበራዊ-ድረገፅ በጉዳዩ ዙሪያ ቅርበት ያላቸው ግለሰቦች፣ የተቃዋሚ ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች እና አባላት፣ ተቀራራቢ እና ፍፁም እርቀት ባለው አሳብ መካከል ክርክር እያካሄዱ ይገኛል፡፡ከዚህም አልፎ በባህር ማዶ በሚገኘው በቪኦኤ ራዲዮ መጠነኛ ዳሰሳ እና ክርክር ሲደረግበት ነበር፡፡ መስመሩን ሣይስት ከምረጡኝ ዘመቻ ባልተናነሰ አጠቃላይ ምርጫውን አስመልክቶ ከዚህም በበለጠ የአሳብ ክርክር ቢደረግ ቢጠቅም እንጂ አይጎዳም፡፡ይህን ለማለት የሚያስደፍረው በአገራችን የሚካሄደው ምርጫ፣ የፖለቲካ ወይም የዲሞክራሲ ቅንጦት ሣይሆን፣ የአገር እና የዜጎች የእልውና ጉዳይ መሆኑ የሚያረጋገጥ የበዛ ምክንያት በመኖሩ ነው፡፡
በተለይ ከሰሞኑ ከፍተኛ የሆነ ክርክር ያስነሳው በአንድነት ፓርቲ እና ሰማያዊ ፓርቲ በአቀፈው በዘጠኙ የትብብር ፓርቲዎች መካከል ያለው የምርጫ ዘዴ ነው፡፡ አንድነት ፓርቲ በማያሻማ መልኩ የትኛውንም ዓይነት ቅድመ ሁኔታ ሳያስቀምጥ እና ሳያሳውቅ፣ በምርጫው በመሳተፍ ውጤት አመጣለው፣የተዘጋውን በር በህዝብ ተሳትፎ አሰከፍታለው የሚል እምነት ላይ መድረሱ ነው፡፡ይህ አይነቱ እምነት ላይ እንዲደርስ ያደረገው የፓርቲው የራሱ የሆነ እስትራቴጂ እንዳለው ቢነገርም፣ነገር ግን የእስትራቴጂውን ባያሣውቅም ቅሉ ፡፡ 
በተቃራኒው ደግሞ የዘጠኙ ትብብር ፓርቲዎች ገና ከመነሻው “ ነፃነት ለፍትሐዊ ምርጫ” በማለት ከምርጫው በፊት ምላሽ ያስፈልጋቸዋል በማለት፣ ለምርጫ ቦርድ ከአስራምስት የማይበሉጡ ጥያቄዎችን ማቅረባቸው የሚታወቅ ነው፡፡ ከዚህም ባለፈ በ2007 አገር አቀፍ ምርጫ የጊዜ ሠሌዳ ይፋ ለማድረግ ምርጫ ቦርድ በጠራው ስብሳበ ላይ፣ በዘጠኙ ትብብር ውስጥ ያሉ ፓርቲዎች ከጊዜው ሠሌዳ በፊት መመለስ ያለባቸው ጥያቄዎች አሉ ፣ይህ ባልተመለሰበት በጊዜ ሠሌዳ ላይ መነጋገር እና መወስን እንቸገራለን፤በማለት በወቅቱ የጊዜ ሠሌዳውን ሳይቀበሉ ሰብሰባውን ረግጠው መውጣታቸው የቅርብ ጊዜ ትዛታ ነው፡፡ይህ በሆነ ከቀናቶች በኋላ በጊዜ ሠሌዳ ላይ አልወያይም ያሉ እንዲሁም የተወያዩ ፓርቲዎች ፣በምርጫ ቦርድ የጊዜ ሠሌዳ መሰረት ሁሉም የምርጫ መወዳደሪያ መልክት ማስገባታቸው ተገልፆል፡፡ 
ከዚህ በላይ ግን የትኛውም ፓርቲ እስካሁን ባለው መረጃ ምርጫ አልሳተፍም ያለ የለም፡፡ሰማያዊ ፓርቲ በአቀፈው የዘጠኙ የትብብር ፓርቲዎች ምርጫ አንሳትፍም አላሉም፡፡ነገር ግን ከሰሞኑ መነሻው ከኢሕአዴግ ፅ/ቤት አድርጎ በሌሎች የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት አጥር ተንጠላጥሎ “ሰማያዊ ፓርቲ ከምርጫው እርሱን አግልሎ እንዴት የመወዳደሪያ ምልክት ያስገባል” የሚል ወሬ እየተናፈሰ ነው፡፡ይሁን አንጂ ሰማያዊ ፓርቲ እንዲህም ትብብሩ በምርጫ ተሳታፊ መሆናቸው ቀድሞም የሚታወቅ ፣አሁንም የተለወጠ ነገር አለመኖሮ ከፓርቲዎች አቋም ለማረጋገጥ ተችሎአል፡፡
በተለይ የዘጠኙ ትብብር ፓርቲዎች ገና ከመነሻው የያዙት አቋም የሚደግፍ እና የሚበረታታ ነው፡፡ነግር ግን ቀድሞ ከያዙት አጠቃላይ የምርጫ ስትራቴጂ አቋማቸው ለየት ያለ አንድ አንድ አካሄዶች አሁን ላይ እየተከተሉ አንደሆነ ለማወቅ ብዙ እርቀት መሄድን የሚጠይቅ አይደለም፡፡ምን አልባትም ሙሉ ለሙሉ ለማላት የማያስደፍር፣ ነገር ግን ጥገናዊ የአቋም ለውጥ ለማድረግ የተገደዱበት በቂ ምክንያቶች ሊኖራቸው ይችል ይሆናል፡፡ይሄኛው ምክንያት የቀደመውን ምክንያት ያስቀረበት ውጤቱ ሊለካ የሚችል፣ በትብብሩ ፓርቲዎች የምንጠብቀው የፖለቲካ ሥራ መኖሩ ሲረጋገጥ ብቻ ነው፡፡
የ2007 አገር አቀፍ ምርጫ አስመልክቶ ምርጫው ከመካሄዱ በፊት፤በቅድም ምርጫ፣በምርጫ እና ከምርጫ በኋላ ነጻ፣ፍትሃዊ፣ ተኣማኒና አሳታፊ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ መኖሩ መረጋገጥ አለበት፡፡ለዚህም ቅደመ ሁኔታዎች ሊሞሉ ይገባል፣ የሚል አቋም በመያዝ እና ምላሽ ሳያገኙ ፓርቲዎች በቀጥታ በምርጫ መሳተፋቸው ተገቢነት እንደሌለው የአብዛኛው ሰው እምነት ነው፡፡ እኔም በግሌ ከዚህ የተለየ በምርጫው ላይ እምነት የለኝም፡፡ሆኖም ግን ከዚህ በኋላ ሁሉም የተቃዋሚ ፓርቲዎች ያለምንም ቅድም ሁኔታ በምርጫ ለመሳተፍ መወሰናቸው፣ የሚለወጥ ነገር እስከሌለ ድረስ እርግጥ እየሆነ መጥቷአል፡፡ በዚህ አጋጣሚ ግራ-አጋቢ የቃላት ንትርኮች ከሰሞኑ ለመታዘብ ችያለው፣ እሱም “በምርጫው ሂደት ላይ እንጂ በመርጫ ላይ ቅድመ ሁኔታ አላስቀመጥንም”፤ አቸነፍን እና አሸነፍን እንደማላት ይሆን ? 
ለማንኛውም በምርጫ ሂደቱ ላይ ሆነ በምርጫ ላይ እስካሁን ባለው መረጃ የትኛውም ፓርቲ ቅድመ ሁኔታ ያስቀመጠ የለም፡፡የዘጠኙ ፓርቲዎች ትብብር አስቀምጠውት የነበረው ቅድም ሁኔታ ከመንግስትም ሆነ ከምርጫ ቦርድ ለመዳራደርም ሆነ ምላሽ ለማገኝት አልተቻላቸውም፡፡ይህ በሆነበት ሁኔታ ቅድመ ድርድ አለ ለማለት አያስችልም፡፡በቅድመ ሁኔታ ወይም ድርድር ሂደት ውስጥ መቀበል እንዲሁም መስጠት የሚባል የቅድም ሁኔታ ማሳያ የሆነ የሚለካ ውጤት ያስፈልጋል፡፡ምን አልባት አሁን ላይ እዚህ ድምዳሜ ላይ መድረስ አይቻልም ከተባል በሂደት የሚታ ይሆናል፡፡ ሆኖም ግን የምርጫ መወዳደሪያ ምልክት መውሰድ፣ ከመንግሰት ወይም ከምርጫ ቦርድ ጋር ቅድመ ሁኔታ በማስቀመጥ ከመደራደር የሚያግድ አንዳችም ነገር የለም፡፡ይሁን እንጂ የመደራደሪያ ነጥቦች ጊዜን ታሳቢ ያደረጉ መሆናቸው ግድ ነው፡፡
በመሆኑም ከዚህ በኋላ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በምርጫ የሚሳተፉት ለሥርዓት ለውጥ ወይስ ለፓርላማ ውክልና የሚለውን ዋና አሳብ በመያዝ፣ እልህ እስጨራሽ ነገር ግን ጤነኛ የሆነ ክርክር ሊካሄድ ይገባል፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲዎች በምርጫው የሚሳተፉት ለምንድነው ? በፓርላማ የፓርቲ ውክልና ወንበር ለማግኘት ውይስ የመንግሰትነት ሥልጣን ለመያዝ ? የትኛው ነው ለተገፋው ለተጨቆነው ኢትዮጵያዊ እውነተኛ መፍትሔ ሊሰጥ የምችለው ? የሚለውን ጥያቄ በመመለስ፣ ፓርቲዎች በምርጫ የሚሳተፉበት ዋንኛ ምክንያት ማወቅ እና መመርምር አስፈላጊ ነው፡፡ይህን ማወቅ የተቃዋሚ ፓርቲዎች በምርጫ ላይ ሊኖራቸው የሚችለው የቅድም ሁኔታ እና ደረጃቸውን በግልፅ እንዲያውቁ ይረዳቸዋል፡፡
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር !

No comments:

Post a Comment