Tuesday, December 9, 2014

”ኢትዮጵያ ብዙ የተደከመባት እና ብዙ ትላልቅ ሰዎች የተሰዉባት ሀገር ነች!” – ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት (የጉዳያችን ማስታወሻ)

እናት አርበኞች
”ኢትዮጵያ ብዙ የተደከመባት እና ብዙ ትላልቅ ሰዎች የተሰዉባት ሀገር ነች” ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ሰሞኑን ፓርቲው እና ዘጠኙ አጋር ፓርቲዎች በጋራ በጠሩት በመጪው ቅዳሜ እና ዕሁድ (ህዳር 26 እና 27/2007 ዓም) በአዲስ አበባ የተጠራውን የ 24 ሰዓት የተቃውሞ ሰልፍ አስመልክተው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የተናገሩት ንግግር ነው።
ይህ ንግግር አሁን ላለው ትውልድም ሆነ በኢትዮጵያዊነቱ ለሚያምነው ሁሉ ከሰማይ የገዘፈ፣ ሲያስቡት በትንሿ አእምሯችን ልንሸከመው የሚከብድ ግን ከእውነትም በላይ የሆነ እውነት ነው።
arebegnoch
ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ካቆሟት ነገሮች ውስጥ አንዱ ለዘመናት የኖረው ሕግ ነው።ዓለም እንደ ዛሬው ስለ ሕግ ብዙ ሳይናገር በቤተ መንግስቱ እና በሕዝቡ መካከል የሚያገናኙ ሕጎች ነበሩ።የተበደለ ፍትህ የሚያገኝበት፣አቤት የሚልበት ቦታ ነበረው።በዳኝነት የተቀመጠውም ህሊናውን እና አምላኩን የሚፈራበት መመዘኛ ነበረው።ፍፁምነት በእራሱ ከሰው ልጅ ባይጠበቅም እንደ ማህበረሰብ፣እንደ ሕዝብ እና እንደ መንግስት ኢትዮጵያ እና ህዝቧ ለሺህ ዓመታት ሲዳኝ የኖረው ከፈረንሳይ ሀገር በመጣ ወይንም ከእንግሊዝ በመጣ ሕግ አይደለም። ሃይማኖታዊ መሰረቱን በያዘ፣ህሊናን እና ህዝብን ታሳቢ ያደረገ ሕግ እና ፍርድ ለዘመናት አኑረውናል።
ይህንን ሕግ እና በነፃነት የመኖር ፀጋን አባቶቻችን በነፃ አላገኙትም።ወጥተው እና ወርደው ደምተው እና ቆስለው ያቆዩት እኛነታችን ነው።ለእዚህ ነው ዛሬ ላይ ሆነን ለነገ ለማስተካከልም ሆነ የምናወራው ስለ ምን ዓይነቷ ኢትዮጵያ እንደሆነ ለማስታወስ ኢትዮጵያ ብዙ የተደከመባት ሀገር መሆኗን ለአፍታም አለመርሳቱ ተገቢ የሚያደርገው።ብዙ የተደከመባት ብቻ አይደለም ብዙ ታላልቅ ሰዎች የተሰዉላት ሀገር ነች።ኢንጅነር ይልቃል ያስታወሱን እኔም በአምሮዬ ሲመላለስ የከረመው አረፍተነገር ይህ ነው።

ኢትዮጵያ ብዙ የተደከመባት እና ብዙ ትላልቅ ሰዎች የተሰዉባት ሀገር ነች
ኢትዮጵያ ንግስት ሳባ በሴት አቅሟ በረሃ ለበረሃ ተንከራታ ኢየሩሳሌም ድረስ ሄዳ ታቦተ ፅዮንን ያመጣችላት ሀገር ነች።ኢትዮጵያ ብዙ የተደከመባት እና ብዙ ትላልቅ ሰዎች የተሰዉባት ሀገር ነች።
ኢትዮጵያ ንጉስ ካሌብ እስከ የመን የሀገሩን ስም ይዞ ሄዶ በባርነት የተያዙትን ናግራውያንን ነፃ ያወጣባት ሀገር ነች።ኢትዮጵያ ብዙ የተደከመባት እና ብዙ ትላልቅ ሰዎች የተሰዉባት ሀገር ነች።
ኢትዮጵያ የመሐመድ ቤተሰቦች ተሰደው በክብር ተቀብላ መጠለያ ሰጥታ እስልምና ሃይማኖትን ለዛሬ አማኝ የሰው ልጆች በሙሉ ከመጥፋቱ በፊት የታደገች ሀገር ነች።ኢትዮጵያ ብዙ የተደከመባት እና ብዙ ትላልቅ ሰዎች የተሰዉባት ሀገር ነች።
ኢትዮጵያ በዘመነ ዮዲት (ጉዲት) ለአርባ ዓመት የመከራ ዶፍ ሲወርድባት ከመከራው ጋር የነደዱ፣በእሳት የተቃጠሉ፣በጦር የተወጉ ለሀገራቸው እና ለህዝባቸው ክብር በሰይፍ የተቀሉ ጀግኖች የሞቱባት ሀገር ነች።ኢትዮጵያ ብዙ የተደከመባት እና ብዙ ትላልቅ ሰዎች የተሰዉባት ሀገር ነች።
ኢትዮጵያ ለኢትዮጵያ ክብር ፣ለሌሎች ነፃነት እና ለእምነታቸው ፅናት የተጉ እነ አፄ ዳዊት፣ነገስታቷ ግብፅ ያሉ ህዝቦች ተጨቆኑ ብለው በሱዳን በረሃ ተንከራተው የግብፅን ሕዝብ ከመከራ የታደጉ ሲመለሱም የክርስቶስን መስቀል ይዘው የተመለሱ በመንገዳቸው መከራ ህመምን ታቅፈው ሀገራቸው ድንበር ላይ የሞቱባት ሀገር ነች።ኢትዮጵያ ብዙ የተደከመባት እና ብዙ ትላልቅ ሰዎች የተሰዉባት ሀገር ነች።
ኢትዮጵያ ባዕዳን እንግሊዞች ሀገራችውን እና ወገናቸውን በከዱ ባንዳዎች እየተመሩ ሲመጡ እጅ አልሰጥም፣ኢትዮጵያን መሳቅያ አላደርግም ብለው የገዛ ሽጉጣቸውን ጠጥተው የሞቱባት አፄ ቴዎድሮስ የተሰዉላት ሀገር ነች።ኢትዮጵያ ብዙ የተደከመባት እና ብዙ ትላልቅ ሰዎች የተሰዉባት ሀገር ነች።
ኢትዮጵያ ራስ አሉላ ”ፈረሴ የቀይ ባህርን ውሃ ሳይጠጣ አይመለስም” ብለው በባህረ ነጋሽ በረሃዎች ተንከራተው የሀገራቸውን ክብር ያስጠበቁ የተሰዉላት ሀገር ነች።ኢትዮጵያ ብዙ የተደከመባት እና ብዙ ትላልቅ ሰዎች የተሰዉባት ሀገር ነች።
ኢትዮጵያ አፍሪካን በጠረንጴዛ ዙርያ ተሰብስበው ለመቀራመት ከተስማሙ በኃላ ሊወራት የመጣውን ጣልያንን ለመዋጋት ለወራት በእግራቸው እስከ አድዋ ድረስ ተጉዘው መስዋዕት የተቀበሉባት ሀገር ነች።ኢትዮጵያ ብዙ የተደከመባት እና ብዙ ትላልቅ ሰዎች የተሰዉባት ሀገር ነች።
ኢትዮጵያ ኢጣልያ ዳግም በ1928 ዓም ሲወራት ከሊቅ እስከ ደቂቅ በረሃ ለበርሃ ተንከራተው ከውስጥ አርበኛ እስከ ዓለም አቀፍ ሙግት ገብተው፣ከጳጳሳቷ እስከ ሕፃን ሰማዕት የሆኑባት፣በአዲስ አበባ በየካቲት 12 ቀን ብቻ ከአስር ሺህ በላይ የንፁሃን ደም በአካፋ እና በዶማ ጭምር የፈሰሰባት ሀገር ነች።ኢትዮጵያ ብዙ የተደከመባት እና ብዙ ትላልቅ ሰዎች የተሰዉባት ሀገር ነች።
ኢትዮጵያ እነ ሞገስ አስገዶም እና አብርሃም ደቦጭ በአርበኝነታቸው ተይዘው ጥፍራቸው እየተነቀለ ተሰቃይተው የሞቱላት ሀገር ነች ኢትዮጵያ።ኢትዮጵያ ብዙ የተደከመባት እና ብዙ ትላልቅ ሰዎች የተሰዉባት ሀገር ነች።
Ethiopians on Sunday celebrated the 118th anniversary of the Adowa battle when an untrained Ethiopian army routed a better equipped Italian invasion army. Photo Credit: Turkish Press
Ethiopians on Sunday celebrated the 118th anniversary of the Adowa battle when an untrained Ethiopian army routed a better equipped Italian invasion army.
Photo Credit: Turkish Press

ኢትዮጵያ በሮም ጣልያን አደባባይ ጎራዴ መዘው የጣልያንን ፋሽትትን የቀሉ በመጨረሻም ለሞት ሰማዕት የሆነላት ዘርአይ ድረስን ያበቀለች ሀገር ነች።ኢትዮጵያ ብዙ የተደከመባት እና ብዙ ትላልቅ ሰዎች የተሰዉባት ሀገር ነች።

ኢትዮጵያ ከጣልያን እስር ቤት አምልጦ በገዛ የጣልያን በረሃ ሸፍቶ ፋሽትን ያርበደበደ በመጨረሻም በድል የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ እያውለበለበ ሮም የገባ እና ከአዲሱ የጣልያን ፕሬዝዳንት የገዛ የእጅ ሰዓታቸውን አውልቀው የሸለሙት ጀግና አብዲሳ አጋን ያፈራች ሀገር ነች።ኢትዮጵያ ብዙ የተደከመባት እና ብዙ ትላልቅ ሰዎች የተሰዉባት ሀገር ነች።
ኢትዮጵያ የተሻለ አስተዳደር ያስፈልጋታል።ብለው እራሳቸውን የሰጡ ጀግና የጦር ኃይል አባላት እነ ጀኔራል መንግስቱ ንዋይ እና ገርማሜ ንዋይ በስቅላት አንገታቸውን ለገመድ የሰጡላት ሀገር ነች።ኢትዮጵያ ብዙ የተደከመባት እና ብዙ ትላልቅ ሰዎች የተሰዉባት ሀገር ነች።
ኢትዮጵያ አሁንም የተሻለ አስተዳደር ያስፈልጋታል፣”ሕዝባዊ መንግስት አሁኑኑ!” ያሉ በሺህ የሚቆጠሩ ወጣቶች ለሞት እራሳቸውን የሰጡባት ሀገር ነች።ኢትዮጵያ ብዙ የተደከመባት እና ብዙ ትላልቅ ሰዎች የተሰዉባት ሀገር ነች።
ኢትዮጵያ የዚያድባሬ ሱማልያ ”ቁርስ ድሬዳዋ፣ምሳ አዲስ አበባ” ብላ በምትፎክርበት ወቅት ከሶስት መቶ ሺህ በላይ ወዶ ዘማች ባጭር ጊዜ ለኢትዮጵያ እሞትላታለሁ ብለው የተሰለፉላት እና ሺዎች በፈንጅ ላይ እየተራመዱ ሞተው ሀገራቸውን ለክብር ያበቁ ዜጎች የወለደች ሀገር ነች።ኢትዮጵያ ብዙ የተደከመባት እና ብዙ ትላልቅ ሰዎች የተሰዉባት ሀገር ነች።
ኢትዮጵያ አንድነቷ አይናጋም፣አትቆራረስም፣በጎሳ እና በዘር አትከፋፈልም ብለው ሰማዕት የሆኑላት እንደ ምፅዋ በነበረው የእርስ በርስ ውግያ ሳንጃ በሳንጃ እየተሞሻለቁ ከአፈር የተደባለቁላት ሀገር ነች።ኢትዮጵያ ብዙ የተደከመባት እና ብዙ ትላልቅ ሰዎች የተሰዉባት ሀገር ነች።
ኢትዮጵያ አሁንም ከአምባገነናዊ አገዛዝ ትላቀቅ ብለው ተነስተው በመጨረሻ ሰንደቅ አላማዋን ተጠቅልለው በመከላከያ ሚኒስትር ቢሮ ውስጥ የተሰዉላት እነ ጀነራል መርድን፣በሰሜን እኔ ብ/ጄነራል ደምሴ ቡልቱን፣ኮለኔል ታሪኩን ያፈራች መሬት ነች።ኢትዮጵያ ብዙ የተደከመባት እና ብዙ ትላልቅ ሰዎች የተሰዉባት ሀገር ነች።
አዎን ! ዛሬ በጎሳ እና በከፋፋይ አገዛዝ እጅ ወድቃ ብትቆስልም ኢትዮጵያ ብዙ ደም የፈሰሰላት፣ብዙዎች የደከሙላት ወደፊትም የሚደክሙላት ሀገር ነች።ዛሬ ኢትዮጵያን ስናስብ ይህንን ሁሉ ድካም እና እንደጎርፍ የፈሰሰው ደም ሊታወሰን ይገባል።
ይህንን ሁሉ ነው የኢንጅነር ይልቃል ንግግር ያስታወሰኝ።ይህንን ስናስብ ነው በሀገራችን ምን ያህል እንደቀለድን ሀገራችንን ለአልባሌ እዚህ ግባ ለማይባል ዘረኛ ቡድን ሰጥተን ግማሾቻችን ለስደት የቀረነው ለህሊና እስረኝነት መዳረጋችን የሚያንገበግበው።
አዎ እያወራን ያለነው ስለ ኢትዮጵያ ብዙ ስለተደከመላት እና ብዙ ትላልቅ ሰዎች ስለተሰዉላት ሀገር ነው።አዎን!! ኢትዮጵያ ብዙ የተደከመባት እና ብዙ ትላልቅ ሰዎች የተሰዉባት ሀገር ነች! ይህ ትውልድ የሀገሩን ክብር ማስመለስ ያለበት ወሳኝ ጊዜ ላይ ነው።ሁሉ እንጀራ ጋጋሪ አይሆንም።ሁሉም ወጥ አይሰራም።ባለን በችሎታችን ለሀገራችን ካልሰራን ከሞቱት አንሰናል።ብዙዎች የደከሙላት እና የሞቱላት ሀገር ላይ ቸል የማለት መብት የለንም።
ጉዳያችን
ህዳር 24/2007 ዓም (ደሴምበር 3/2014)

No comments:

Post a Comment