በአንድ ወቅት የኢትዮ-ቻናል ጋዜጣ ዘጋቢ ጋዜጠኛ፣ ወደ ሕዳሴ ግድብ በተደረገ ጉዞ ጋዜጠኞች ላይ የደረሰውን እንግልት አስመልክቶ “የጋዜጠኛ ዋጋው ስንት ነው” በሚል ርዕስ አንድ ጹሁፍ አስነብቦ ነበር። ይህን ጽሁፍ ከመፃፉ በፊት በጉዞው ላይ የነበርነውን ጋዜጠኞች ብዙ አነጋግሯል። ችግሩ የተፈጠረው ወደ ሕዳሴ ግድብ ጉዞ እያደረግን በነበረበት ጊዜ ነበር። የጹሁፉ ይዘት ከሕዳሴው ግድብ ጋር እንዳይያያዝ ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት ምክረ ሃሳብ እንዳስቀመጥን አስታውሳለሁ። አንዳንዶቻችን ከዚህም በላይ ርቀን ሄደን፣ ሊፃፍ የታሰበው ጽሁፉ ቀርቶ ቅሬታውን ለሚመለከተው አካል ሪፖርት ማድረግ በአማራጭነት አቅርበንም ነበር። በመጨረሻ ግን መፃፍ ወይንም አለመፃፉ የሚዲያ ተቋሙ ውሳኔ እንዲሆን ተስማማን።
ይህን መጥፎ የጉዞ ትዝታ ማስታወስ ባንፈልግም ፌዴሬሽን ም/ቤት ጽ/ቤት ከቤንሻንጉል ጉምዝ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ጋር በመተባበር ባዘጋጀው ዘጠነኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል ላይ ዳግም የተዝረከረከ አሰራር መደገሙ፣ ለዚህ ጽሁፍ መነሻ ሆኗል። መሠረታዊ ችግሩ የፌዴሬሽንም ምክር ቤት አፈ-ጉባኤና ጽ/ቤታቸው በ“አርቲስቶች” እና በሚዲያ ባለሙያዎች መካከል ያላቸው የተንሸዋረረ አመለካከት ነው። ይህ የተንሸዋረረ አመለካከት ግለሰባዊ ወይም ተቋማዊ ይሁን ለጊዜው እንተወው። በእርግጠኝነት ግን ተቋማዊ አመለካከት እንደማይሆን እምነቱ አለኝ። ለማንኛውም መታረም ስላለባቸው አግባቦች ግን የተወሰነ ማለቱ ለሁሉም የሚበጅ ነው። የፌዴሬሽን ም/ቤት ጽ/ቤትም ይህንን አስተያየት በቀናነት ተመልክቶ ለቀጣይ ሥራው በግብአትነት ይወስደዋል ብዬም አምናለሁ።
ወደ ሁነኛው የጽሁፌ ጭብጥ ከመንደርደሬ በፊት በኪነጥበብ ላይ በተሰጡት የትርጓሜና የፍቺ ብያኔዎች ላይ አንድ ሁለት ኀሳቦችን መሰንዘር እሻለሁ። ኪነ ጥበብ (Art) ከሚያካትታቸው ዘርፎች በስፋት የሚጠቀሱት ሥነ-ጽሁፍ፣ ሥዕል፣ ቅርፃቅርጽ፣ ሙዚቃ፣ ቲያትር እንዲሁም ሲኒማ ናቸው። ኪነ ጥበብ ተጨባጭ እውነታዎችን የሚያንጸባርቀው በኪነ ጥበባዊ ምስሎች ሲሆን ምስሎቹን የሚገልጽበት መንገድና የሕውስታ (sensation)፣ እና የሥነ አመክንዮ (Logic)፣ የጭብጥ (concept)ና የረቂቅ (abstract)፣ የግላዊ (individual) እና የሁለንተናዊ (universal) ውህደትን በማጣመር ነው። ይህም በመሆኑ ኪነ ጥበብ የማሕበራዊ ንቃተ ሕሊናን ከማስፋቱም ባሻገር፣ መሬት የወረደውን እውነታ በምስል የሚያንፀባርቅ እና ሰዎች ስለነባራዊው ዓለም ያላቸውን ሥነ ውበታዊ ግንዛቤን የሚገልጽ የሚያስጨብጥ ወይም የሚያሳይ ነው።
ኪነ ጥበብ የአንድ ሕብረተሰብን ፖለቲካዊ፣ ማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕሴቶችን በማስተጋበር በጥበብ ከማንፀባረቁ በላይ ሕብረተሰቡ ስለዓለም ያለውን አተያየት መለወጥም ማስተካከልም የሚያስችል ሁለንተናዊ አቅም አለው። ይህን የኪነ ጥበብ አቅም በትክክል መረዳት እና መዋቅራዊ አደረጃጀት መዘርጋት የቻለ ማንኛውም አካል፣ ያነገበውን ርዕዮተዓለም ማስረፅ እና አሸናፊ አድርጎ በአንድ ሕብረተሰብ ውስጥ ማውጣት ይችላል። በዚህ መልኩ ኪነ ጥበብን ለመጠቀም ግን ከፍተኛ የሆነ ዋጋ ያስከፍላል።
ይህም ሲባል፣ ለሁሉም ኅብረተሰብ የሚሆኑ የኪነ ጥበብ ስራዎች እና የመደብ ውክልና ያላቸው የኪነ ጥበብ እሴቶች ለየቅል ናቸው። የመደብ ውክልና ያላቸው የኪነ ጥበብ ስራዎች ስለወከሉት መደብ ምንነት ማንነት በትክክል አበጥረው ሊያውቁትና ግንዛቤ ሊጨብጡ ይገባል። የመደብ ውክልና የሰጣቸውም አካል በይፋ ለኪነ ጥበብ ሰዎቹ እና ስራዎቻቸው እውቅና መስጠት ይጠበቅበታል። ከዚህ ውጪ ወካይ እና ተወካይ የሌለበት የጥበብ ድግስ ከተራ የምሽት መዝናኛ የተለየ ትርጉም አይኖረውም።
የኪነጥበብ የመደብ ውክልና ሲባል፣ ኪነጥበብ ከደሃው፣ ከተጨቆነው፣ ከሚጨቁነው፣ ለመብቱ ከሚታገለው፣ ነፃ ካልወጣው፣ ማንነቱን ከተቀማው፣ ማንነቱ ከተገፈፈው፣ ለብሔሮችና ለግለሰቦች መብት መከበር ብሎም ለሌሎችም መደቦች አርነት ኪነ ጥበብ ውግንና ሊይዝ ይችላል። በአንፃሩም ኪነ ጥበብ የተንሸራታች (opportunism) መደብ ውግንናንም አንግቦ ሊቆም ይችላል። ይህን ዓይነት የመደብ ውክልና የሚይዝ ኪነ ጥበብ በብዙ መልኩ የሚያደርሳቸው ጉዳቶች ምትክ አልባ ናቸው። ይህም ሲባል እያንዳንዱን የመደብ ውክልና እንቅስቃሴን ለራሱ በሚያዋጣው ኪናዊ ዘዴ ይቀለብሰዋል። ድምር ውጤቱም፣ ወደ የሚያዋጣው የመደብ ውክልና መንሸራተት ይሆናል። ይህ ዓይነት የኪነጥበብ ውክልና በዚህች ሀገር በስፋት የተለመደ ነው። በአንፃሩም ለኪነጥበብ ልዕልና ኖረው ውድ ሕይወታቸውን ከፍለው ያለፉም ያሉም ባለሙያዎች መኖራቸውንም ፀሐፊው በዚህ ፅሁፍ አልዘነጋውም፡፡
እነሆ ስለ ኪነ-ጥበብ ሁለንተናዊ ፋይዳ ይህን ያህል ካልን፤ ጥያቄ ወደ ማንሳቱ እንግባ። የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ካሳ ተክለብርሃን እና ጽ/ቤታቸው “አርቲስቶችን” ከብሔር ብሔረሰቦች በዓል ጋር በተቀናጀ መልኩ የሚጠቀሙበት አግባብ እንዴት የሚገለፅ ነው? በበዓሉ ላይ የሚሳተፉ አርቲስቶችን በምን መመዘኛ ነው የሚመርጧቸው? በዚህ በዓል ላይ አርቲስቶቹን ሲጋብዙ፣ የበዓሉን ዓላማ በማስጨበጥና በማሰለፍ ነው? ወይንስ በበዓሉ ላይ እንዲዘፍኑ ክፍያ ለመፈጸም ነው? በዓሉን የሚደግፉ እና የሚደገፉትን አርቲስቶችን አፈጉባኤውና ጽ/ቤታቸው የመለየትስ አቅሙ ምን ያህል ነው? በሀገሪቷ ውስጥ የሚገኙ አርቲስቶችስ በበዓሉ ላይ በእኩል ሚዛን የመገኘት ዕድላቸውስ ምን ያህል ግልፅ አሰራርን የተከተለ ነው? አፅንኦት ሊሰጠው የሚገባው ጥያቄ ግን የመደብ ውክልናቸው ከማን ጋር ነው የሚለው መጠይቅ ነው። የፀና ወይንስ ተንሸራታች ነው?! እነኚህን ድምር ጥያቄዎች የመመለስ አግባብ የቀጣዩ አፈ ጉባኤ የቤት ሥራ ነው!
ለጋዜጠኞች ክብር የሌለው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ጽ/ቤት
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ካሳ ተክለብርሃን እና ጽ/ቤታቸው ያዘጋጁት በዓል ጥሩም ይሁን መጥፎ ከሕዝብ ፍርዱን እንዲያገኝ የሚያደርገው ጋዜጠኛው ነው። ጋዜጠኛው በቤንሻንጉል ጉሙዝ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ግዛት ውስጥ ባይደርስ ዝግጅቱ ሁሉ የአዘጋጆቹ ብቻ ሆኖ ይቀር እንደነበር እሙን ነው። ይህን እውነት በአደባባይ የደፈጠጡት አፈጉባኤ እና ጽ/ቤታቸው በጋዜጠኛው ላይ የፈጸሙትን ዘግናኝ ድርጊቶች እንመልከታቸው።
በመጀመሪያው ቀን አሶሳ ከተማ የደረሰው የጋዜጠኛ ቡድን የተዘጋጀለት አልጋም ሆነ የተለየ ማረፊያ ድንኳን እንደሌለው ተነገረ። በሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ውስጥ ተዘጋጅቶ ነበር የተባለው አልጋ የውሃ ሽታ ሆነ። የነበረው አማራጭ የተረፈ አልጋ ካለ በየተለያየ ሆቴሎች ውስጥ ገብተው ይደሩ ተባለ። ተራ በተራ ስም እየተጠራ በየሆቴሉ ብተና ተጀመረ።
ወደ ሰባት ጋዜጠኞች አንድ ሆቴል ውስጥ ተደልድለን ሄድን። የበር መቀርቀሪያ የሌላቸው፣ የቀን ጨዋታ የሚሰራባቸው ክፍሎች ታደለን። ሁሉም ተቃወመ። የክፍሎቹ ሽታ አያድርስ ነው። ብዙ ርቀት ተጉዘን ከመምጣታችን አንፃር ሁሉም ሻወር መውሰድ ይፈልግ ነበር። ድንቄም ሻወር፣ መኝታ እንኳን የለም። የሚገርመው የከተሞቹ አልጋዎች በጽ/ቤቱ ቁጥጥር ስር በመዋላቸው ከፍሎም መተኛት እንኳን አይቻልም። ምክንያቱም ሁሉም አልጋዎች ስለተያዙ ነው። የነበረው አማራጭ ለበዓል ዝግጅት ኮሚቴ አቤቱታ ማሰማት ነበር።
ተሰብስበን ሄደን ለማስረዳት ሞከርን፤ ግን ምን ያደርጋል ሰሚ የለም። ሁሉም ጆሮ የጽ/ቤቱን ትዕዛዝ ሰሚ ብቻ ነው የነበረው። በግልፅ ጋዜጠኛው ተቃውሞ አስነሳ። ከአስተናጋጆቹ መካከል አንዱ የእንግዶች መመዝገቢያ ቅጽ አውጥቶ አሳየን። “የመንግስት ባለስልጣኖች፣ ባለሃብቶች እና አርቲስቶች ብቻ ናቸው፤ አልጋ የተያዘላቸው” አለን። እውነትም በሆቴሉ ግራና ቀኝ ዞር ዞር ብለን ስንመለከት የፌደሬሽን ምክር ቤት ሰዎችና “አርቲስቶች” ሻወር ወስደው የደረቀ ጉሮራቸውን ማርጠቡን ተያይዘውታል። የጽ/ቤቱን ሚዛን ለታሪክ አስቀምጠን፣ ወደ ተመደብነው ሆቴሎች ጉዞ ቀጠልን። ከዚያም ስንደርስ፣ በስንት ጩኸት በወሰድነው ሁለት የመኝታ ክፍል ውስጥ ተራ በተራ ሻዎር ወሰድን። ወደ ማይቀረውም የሙታን ክፍል ሁሉም ተበተነ።
ወደ ማረፊያ ክፍላችን ገብተን ትንሽ ሳንቆይ በሞባይል ስልካችን መልዕክት ደረሰን። ከለሊቱ አስር ሰዓት “ወደ ሕዳሴው ግድብ ጉዞ ስለሚደረግ ተዘጋጁ!” የሚል ነበር። ለአልጋ ስንጨቃጨቅ እራት አምልጦን፣ እንቅልፍ የሚነሳ አልጋ አቅርበውልን ከለሊቱ አስር ሰዓት ተነሱ ሲባል፣ ከመካከላችን “ምነው አርቲስት ባረገኝ!” ብሎ ያልጸለየ ጋዜጠኛ አልነበረም። ዕድሜ ለአፈጉባኤው፣ በአውሮፕላን መጥተው፣ ቪአይፒ ባጅ ተስጥቷቸው፣ ደረጃ አንድ አልጋ ላይ ተኝተው፣ የሚፈልጉትን በልተውና ጠጥተው፣ በእነሱ ያልተቀና በማን ሊቀና?! እንኳንም ተመቻችሁ አቦ!
ከለሊቱ አስር ሰዓት ጉዞ ወደ ሕዳሴው ግድብ ተጀመረ። መንገዱ ፒስታ ከመሆኑም በላይ እርቀቱም የዋዛ የሚባል አይደለም። ከአድካሚ ጉዞ በኋላ ከቀኑ ስምንት ሰዓት አካባቢ ሕዳሴው ግድብ ደረስን። ሁሉም በረሃውን አቋርጦ ስለገባ ውሃ ቁጥር አንድ ጥያቄ ሆነ። ቁርስ ተረስቷል። ውሃ ከወዴት ይምጣ?! በቀጥታ ወደ ጉብኝት እንድንገባ ትዕዛዝ ተሰጠ። አማራጭ የለም፤ ውሃ! ውሃ! እያልን ጉብኝቱን ጀመርን።
በፌዴሬሽን ጽ/ቤት የተንሸዋረረ አመለካከት የተጎዳው ማንነታችን፣ የህዳሴውን ግድብ ግንባታ ሥራዎች ስንመለከት ሁሉንም ነገር ረሳነው። ደስታ፣ ፈንጠዝያ፣ የኩራት እንባ ውስጣችንን አመሰው። የግድቡ ግንባታዎች ሁላችንንም በእኩልነት ሲመለከቱን፣ የፌዴሬሽን ጽ/ቤትን ትንሽነት መመልከት ተገቢ አለመሆኑን ለመረዳት አልዘገየንም። ሁላችንም ወደ መደበኛ ሥራችን ገባን። ታሪካዊው የህዳሴው፣ ግድባችን ሁሉንም ነገር ታሪክ አደረገው። በአዲስ ጉልበት ሁሉንም የግንባታ ሥራዎች ጎበኘን። የምንችለውን ያህል ፎቶግራፎችንም አነሳን። ምርጥ ገለፃ አደመጥን። ጉብኝታችንም ጨርሰን ወደ ተዘጋጀልን ማረፊያ አመራን።
ያረፍነው በሕዳሴው ግድብ ዙሪያ በተሰሩ መጠለያ ቤቶች ውስጥ ነበር። አብዛኛው ጋዜጠኛም ተሰባስበን አንድ ክፍል ውስጥ ገባን። ማረፊያችንን ካስተካከልን በኋላ ወደ መመገቢያ ቦታ አመራን። ከነበረው የሰው ብዛት አንፃር ረዘም ያለ ሰልፍ ቢኖርም እንደ እውነቱ ከሆነ ተገቢውን አገልግሎት ማግኘት ችለናል። የማታ ዝግጅት እስከሚደርስ ድረስ ወደ ማረፊያችን ተመልሰን ለተወሰነ ሰዓት አሸለብን። ጣፋጭ የማይረሳ እንቅልፍ አንቀላፋን።
እነሆ የማታው ፕሮግራም ከመጀመሩ በፊት ትኩረት የተነፈጉት ጋዜጠኞች ቀድመው ይድረሱ ስለተባለ ሁላችንም ተነስተን ወደ ዝግጅት ሥፍራው አመራን። እያንዳንዱን ነገር በራሳችን መስመር ለግብአት የሚሆኑ መረጃዎችን ሰበሰብን። ሰዓቱም ገፋ፣ መሸ። ሁሉም በተዘጋጀላቸው ሥፍራ ላይ ተሰየሙ። ዝግጅቱም ተጀመረ። ከክብር እንግዶች የተለያዩ ንግግሮች ቀረቡ። በመጨረሻም የሙዚቃ ዝግጅት ይቀርብ ጀመር። ጋዜጠኛው ቀድሞ የመጣ በመሆኑ እራት አልበላም። ስለዚህም ሥራውን ቀድሞ የጨረሰ ቀስ እያለ ምግብ ወደ ተዘጋጀበት ቦታ መሄድ ጀመረ።
ምሳ የተዘጋጀበት ቦታ ሁሉም ነገር ተነስቷል። መብራትም ጠፋፍቷል። የሚበላም የለም …. ግራ ተጋባን። በአቅራቢያ የነበሩ ሰዎችን ስንጠይቅ እራት ተበልቶ ሁሉም ወደ ሙዚቃ ዝግጅቱ ሄደዋል አሉን። “ያላቹሁ ምርጫ ከፍላችሁ የሠራተኞች ክበብ መመገብ ነው” አሉን። ሠራተኞች ክበብ ገባን። ያለው ጥብስ ብቻ ነበር። ተገኝቶ ነው፤ ጥብስ አዘዝን። በዚህ መካከል የፌዴሬሽን ም/ቤት ከፍተኛ ኃላፊ የሆኑት አቶ ዳንኤል መጥቶ አጠገባችን ተቀመጠ። ከመካከላችን አንዱ ያውቀው ነበር። የተፈጠረውን ሁሉ አንስቶ ነገረው። በፌዴሬሽን ጽ/ቤት ሁሉም ጋዜጠኛ ቅሬታ እንዳለውም ገለጸለት። የምንበላው አጥተን ወደዚህ ክበብ መምጣታችንንም አስረዳው። “በተፈጠረው ሁሉ አዝናለሁ። በፌዴሬሽኑ ስም ይቅርታ እጠይቃለሁ” ሲል አቶ ዳንኤል የተሰማውን ስሜት ገለጸልን። ከምንም ይሻላል በሚል ተቀበልነው። ተሰናብቶን ሲወጣም እኛ የተመገብነው ምግብ መከፈሉን ገልጾልን ሄደ። እኛም በአፀፋው እናመሰግናለን የሚል ምላሽ ሰጠን። የእኛ ምሽት በዚህ መልኩ አለፈ። የኢቲቪ ጋዜጠኞች ሰቆቃ ግን ልባችንን ረበሸው።
ለኢትዮጵያ ሕዝብ ከሕዳሴው ግድብ በቀጥታ ዘጠነኛውን የብሔር ብሔረሰቦች በዓል ሲያሰራጩ አምሽተው በእኩለ ለሊት ወደ ምግብ አዳራሹና ማረፊያቸው ቢደርሱም የሚበሉት አንዳች ነገር አልነበረም። ከዕድምተኛ በፊት ኢቲቪዎች ሙሉ ክሩዋቸውን ይዘው ወደ ዝግጅት ቦታው መንቀሳቀሳቸው እና ዝግጅቱ ከተጠናቀቀ በኋላ ምን ሊያስፈልጋቸው እንደሚችልም እየታወቀ ትኩረት የሰጣቸው ግን አልነበረም። ግማሹ የኢቲቪ ጋዜጠኛ ጠኔውን ይዞ ወደ ማረፊያው ሲያቀና ግማሹ በዛ ድቅድቅ ለሊት መኪናቸውን አስነስተው ወደ አሶሶ ከተማ በረሩ። በዚያ ለሊት አደጋ ቢደርስባቸው አንድ መጥፎ ነገር ከዋሻው ቢገጥማቸው የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤና ጽ/ቤታቸው ምን ሊሰማቸው እንደሚችል መገመት ከባድ ነው። ለዚህም ነው፣ “በአርቲስቶች” ፍቅር የተንሸዋረረው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ጽ/ቤት የሚል ርዕስ የሰጠነው።
በመጨረሻም ወደ አሶሳ ከተመለስን በኋላ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ አቶ ካሳ ተክለብርሃን ጋዜጣዊ መግለጫ ይሰጣሉ የሚል መልዕክት ስለደረሰን በጉዳዩ ላይ ለአጭር ደቂቃ ውይይት አደረግን። በቦታው ላይ ላለመገኘት የወሰንን ቢሆንም የኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት የሥራ ባልደረቦች የመግባቢያ ኀሳብ አቀረቡልን። ከጋዜጣዊ መግለጫው በኋላ አፈጉባኤውን ማናገር እንደምንችል ገለፁልን። ተነስተን ሄድን። ጋዜጣዊ መግለጫውን ተከታተልን።
ጋዜጣዊ መግለጫው እንዳለቀ፣ አቶ ካሳ ተክለብርሃንን “ችግር ገጥሞናል እርስዎን ማነጋገር እንፈልጋለን” ብለን ጠየቅናቸው። ሊያናግሩን ፈቃደኛ አይደሉም። በጥሩ የአፍ ሽንግላ “አዲስ አበባ መነጋገር እንችላለን። እዚህ ያሉ የጽ/ቤቱ ሠራተኞች እና ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት በጋራ በመሆን ከእናንተ ጋር በእኔ ጽ/ቤት እንወያያለን” አሉን። አዲስ አበባ ገባን። አቶ ካሳም ሆኑ ጽ/ቤታቸው የውሃ ሽታ ሆኑ። የአርቲስቶች ነገር የማይሆንላቸው አፈጉባኤ እኛን በአፍ ሽንገላ ሸኝተው እንዲሁም ሰኞ ዕለት ከለሊቱ አስር ሰዓት ከአሶሳ ከተማ ለቀን እንድወጣ አደረጉ።
ማክሰኞ ዕለት ጠዋት የምስጋና ፕሮግራም አፈጉባኤው ለአርቲስቶቹ አዘጋጁ። በስሱ አስረሽ ምቺው ከተባለ በኋላ በተዘጋጀላቸው አውሮፕላን ከአፈጉባኤው ጋር አዲስ አበባ ገቡ። ጋዜጠኛው ወለጋ ከተማ ደርሷል። ነቀምቴ ከተማን 3ሺ የሚጠጉ የጤና ባለሙያዎች ለስልጠና ገብተው አጨናንቀዋታል። ከአንዱ ሆቴል ወደ ሌላኛው ሆቴል አልጋ ፍለጋ ሩጫው ቀጥሏል። ሁሉም አልጋዎች ለስልጠና ተይዘዋል። አማራጩ ወደ መንደር ውስጥ ገብቶ የተገኘውን አልጋ መፈለግ ነበር።
ሰላሳ እና አርባ ብር የሚከፈልባቸውን አልጋዎች ፍለጋ ተጀመረ። በኮምፐልሳቶ የተከፋፈሉ ክፍሎች በብዛት ወደ አልጋ ክፍልነት ተቀይረው ተዘጋጅተዋል። አልጋዎቹን ገለጥ ስናደርጋቸው ጥሩ ነገር መመልከት አልቻልንም። አማራጭ የለም። ሁሉም ተዳክሟል። ማራገፍ ተጀመረ። የደፈረ ተኛ፣ ያልደፈረው ሲዞር አመሸ። በምሽት ጨዋታ መሀል አንዱ ከመካከላችን መፈክር አሰማ፤ “የአርቲስቶችን ሌጋሲ እናስቀጥላለን!”… “የአርቲስቶችን ሌጋሲ እናስቀጥላለን!”… “የአርቲስቶችን ሌጋሲ እናስቀጥላለን!”……
የፌዴሬሽን ም/ቤት ጽ/ቤት የመንግስት እና የግል ጋዜጠኞችን በተለየ መልኩ ቦታ የነፈገው መሠረታዊ የአመለካከት ችግር ስላለው ነው። የልማታዊ መንግስት ጉዞን፣ ወደ ጭብጨባ እና ርካሽ ተወዳጅነት የማውረድ አዲስ መስመር የዘረጋም ይመስላል። ገዢው ፓርቲ እስከምናውቀው ድረስ የጭብጨባ መንግስት አይደለም። ወይም የሙድ መንግስት አይደለም። ይህን አይነት አዲስ ባሕሪ በፌዴሬሽን ጽ/ቤቱ ማቆጥቆጡ ሊፈተሽ ይገባዋል።
ሥራችንን በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ተወጥተን ወደ አዲስ አበባ የመልስ ጉዞ ስናደርግ ሁሉም ጋዜጠኞች በደረሰባቸው ኢ-ፍትሐዊ አድልኦና እንግልት እንዳዘኑ ነበር። የጊዜ ጉዳይ ነው፣ አንድ ቀን ጋዜጠኞችም በዚህ ኅብረተሰብ ውስጥ ተገቢውን ሥፍራ ያገኙ ይሆናል። ዘላለማዊ ክብር ለእኛ የብዕር ነፃነት ለጋ ዕድሜያችሁን ለከፈላችሁ ሰማዕታት!!!
No comments:
Post a Comment