ረፖርተር
የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትሩ አቶ ሱፍያን አህመድ፣ ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፍ የቦንድ ገበያው አንድ ቢሊዮን ዶላር ብድር ማግኘቷን፣ ፓርላማው ደግሞ እስከ ሁለት ቢሊዮን ዶላር የቦንድ ገበያ ብድር እንደፈቀደ አስታወቁ፡፡
ሚኒስትሩ ማክሰኞ ዕለት በጽሕፈት ቤታቸው በሰጡት መግለጫ በቦንድ ሽያጩ በ6.625 በመቶ ወለድ ክፍያ አንድ ቢሊዮን ዶላር መገኘት መቻሉን አብራርተዋል፡፡
ይህ ማለት ግን መንግሥት በቦንድ ሽያጩ አማካይነት በየጊዜው ይበደራል ማለት አለመሆኑንና አስፈላጊ ሲሆን ብቻ ሽያጩን በድጋሚ በማከናወን ብድር ማግኘት እንደሚቻል አብራርተዋል፡፡
የተገኘው አንድ ቢሊዮን ዶላር ለኢንዱስትሪ ዞኖች ግንባታ፣ ለኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ዝርጋታና ለተወሰኑ የስኳር ፋብሪካዎች ግንባታ እንደሚውል ገልጸዋል፡፡ ‹‹የተገኘው ብድር በጭራሽ ለህዳሴው ግድብ አይውልም፡፡ የህዳሴ ግድብ በኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ ብቻ ያለማንም ጣልቃ ገብነት የሚገነባ ነው ብሎ መንግሥት አቅጣጫ አስቀምጧል፤›› ብለዋል፡፡
የተገኘው ብድር የሚኖረውን አንድምታ በተመለከተ በሰጡት አስተያየት የውጭ ኢንቨስተሮች ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ ከማበረታታቱም በላይ፣ የኢትዮጵያን ገጽታ በመቀየር ረገድ ጉልህ ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡
‹‹ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ዕድገት ሊተቹ ይችላሉ፡፡ ቦንዱን የገዙት ኢንቨስተሮች ግን የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ዕድገት በገንዘባቸው ነው የመሰከሩት፤›› ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት ብድሩን ላይከፍል ይችላል በሚል ከተቀመጡት ሥጋቶች መካከል ከኤርትራ ጋር ጦርነት እንደሚከሰት፣ ድርቅ ኢኮኖሚውን ሊያስተጓጉል እንደሚችል፣ በ2007 ዓ.ም የሚደረገው አገር አቀፍ ምርጫ ገዢው ፓርቲ ተሸንፎ የፖሊሲ ለውጥ ሊኖር ይችላል የሚሉና የመሳሰሉት ናቸው ያሉት ሚኒስትሩ፣ የሁሉም የሥጋት ዓይነቶች ደረጃ ግን ዜሮ ስለሆነ በእዚህም ምክንያት ብድሩ ሊገኝ እንደቻለ አብራርተዋል፡፡
No comments:
Post a Comment