Sunday, December 21, 2014

የፍረጃ ፖለቲካ አይጠቅመንም! መልስ ለሁኔ አቢሲኒያ ( ግሬስ አባተ)

በመጀመሪያ ይህን ፅሁፍ የምፅፍልህ ሌላውን ወገን ወግኜ ሳይሆን ይህ አካሄድ በመሰረታዊነት ትግሉን የሚጎዳ ስለሚመስለኝ ነው፡፡ በምንም ጉዳይ ትግሉን አንድ ኢንች በሚጎዳ ነገር ዝምታን አልመርጥም፡፡ ሲጀመር ሰራዊት ፍቅሬንና የተከበሩ አቶ ግርማ ሰይፉን በአንድ ሚዛን ላይ የሚቀመጡ ግለሰቦች አንዳይደሉ በደንብ የምታውቅ ይመስለኛል፡፡ የቆሙለት አላማ በራሱ ይህንን አስረግጦ ስለሚነግረን በዚህ ላይ ጊዜ ማባከኑ ትርጉም የለውም፡፡ የመረጥከው ርዕስ በራሱ ሶስቱን ለይተህ ማቅረብህ ግራ የሚያጋባ ነው፡፡ ያልመረጥናቸው ስትል ቀሪዎቹን ወይ መርጠሃቸዋል ወይ ይሁንታ ሰጥተሃቸዋል ማለት ነው፡፡
(ግርማ ሰይፉ)
(ግርማ ሰይፉ)
ያልመረጥናቸው ከምትል ይልቅ በምን መስፈርት ተመረጡ ብትል ጥሩ ይሆን ነበር፡፡ መብትህም ስለሆነ ! እንደምታውቀው የተከበሩ አቶ ግርማ ሰይፉ የተቋውሞው ፖለቲካ ብቸኛ የፓርላማ ተወካይ ናቸው፡፡ እንደምታውቀው የተቃውሞ ጎራው የግድቡን ጉዳይ ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ መዋሉ በተለይም የአረቡ አብዮት ወደ ኢትዮጵያ እንዳይመጣ ለማስቀየሻ የተመዘዘ እና በቂ ጥናት ሳይደረግበት ወደ ስራ በመገባቱ እንጂ የሚቃወሙት ግድቡ ለምን ተገነባ በሚል አይደለም፡፡ ስለዚህ አቶ ግርማ የፓርላማ አባል በመሆናቸው ብቻ የዚህ ልዑክ አካል መሆን ቢችሉ ብዙም የሚገርም አይደለም፡፡

ግድቡን አስመልክቶ የስርዐቱ አንዱ ችግር እንደውም ሌላውን ወገን አግልሎ የራሱን ፕሮፓጋንዳ መጫወቻ ማድረጉ ነው ትልቁ ችግር፡፡ ስለዚህም ይህን ግብዣ ማድረጋቸው እንደ ጥሩ ጅማሬ አድርጌ እቆጥረዋለሁ፡፡ ሁኔታው ይህ ሆኖ እያለ በተለይም ከውጭ ጉዳይ ሚ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ጋር ተጨባብጠው ፎቶ መነሳታቸውን አስመልክቶ ‹‹የልኡካን ቡድኑ ውስጥ አቶ ግርማ ሰይፉ የሚል ስም ተሰማ…፤ በዚህ በርካቶች ተገረሙ ወይ እቺ አገር ሲሉም አዘኑ›› ይህ የተጋነነ ነው፡፡ ከዚህ ግድብ ጋር ተያይዞ ስርዐቱ በሚፈጥረው ፕሮፓጋንዳ ስንቶች በተቃውሞ ፖለቲከኞች እንዳዘኑ ብነግርህ እንዳይገርምህ፡፡ አንተ እንዳልከው ማዘን መገረም ሳሆን ህዝቡ ጋር ያለው ከዚህ በተቃራኒ እንደሚሆን እምነቴ የፀና ነው፡፡
547 የስርዐቱ አባላት ባሉበት ፓርላማ የሚቻለውን ማድረግ የቻለ ግለሰብ ነው፡፡ ሰው የሚችለውን ሁሉ ያደርጋል፡፡ አንድ ድምፅ ይዞ የጎላ ለውጥ የሚያመጣበትን ምክንያት ከቻልክ ንገረኝ? እንዲሁ ሌላው ለሰራ ክሬዲት መንፈግ ካልሆነ በቀር ይህ አንድ ድምፅ ይዞ እንደሌሎች ለወከላቸው ህዝብ ሳይሆን ለፓርቲቸው ተጠሪ የሆኑ 545 ሰዎች ባሉበት ፓርላማ ያንን ያህል ጠንካራ ስራ አልሰሩም ተብሎ ሊወቀሱ አይገባም ባይ ነኝ፡፡ ከቻልክ ፖለቲካውን ከስሜትና ከጥላቻ በዘለለ ለማየት ሞክር፡፡ ፍረጃ ላለፉት ምናምን አመታት የሄድንበት ስለሆነ ያንን መድገም ካልሆነ በቀር የሚያመጣው ለውጥ የለም፡፡
ወደ ፍረጃ መሮጥህ ተገቢ ያልሆነ ነው፡፡ ቆይ አንተ የተከበሩ አቶ ግርማ ሰይፉን እንዴት አድርገህ ነው ምታያቸው? እስከሚገባኝ ግለሰቡ በሰላማዊ ትግል ለውጥ አመጣለሁ ብለው እየታገሉ ያሉ ግለሰብ ናቸው፡፡ አንተ ሰላማዊ ትግል ለውጥ ኤመጣም ልትል ትችላለህ፡፡ መብትህም ነው፡፡ ይህ ከሆነ እውነታው አቶ ግርማን ጨምሮ ሰማያዊ ሆነ አንድነት ውስጥ ያሉ የፓርቲ አባላትን ሕወሃት/ኢህአዴግ ጠላታችሁ ነው ወይ ብትላቸው? የምን ጠላት ነው፡፡ በሰላማዊ ትግል ጠላት የሚባል ነገር የለም ይሉሃል፡፡ባለው የህግ ማእቀፍ ውስጥ ሆኖ በሰላማዊ ትግል እየታገለ እንዴት እንደጠላት እንዲተያይ ወይም ግብዣ ሲቀርብለት ከጠላቶቼ ጋር እንዲል ትጠብቃለህ? የሚታገለው እኮ በሰላማዊ መንገድ ያለውን ስርዐት ለመቀየር ነው፡፡
ግለሰቦች የሚሉትን አስመልክቶ ፖለቲካው ላይ አቧራ ባናስነሳ ይሻለናል፡፡ አሁን መሬት ላይ ያለውን እውነት ይዤ ለመሞገት እንጂ ስለ አቶ ግርማ ጥብቅና ለመቆም አይደለም፡፡ ስለግለሰቦች መቶ ሺ ጊዜ ብንከራከር ለውጥ አናመጣም፡፡ አሉት የተባለው በራሱ ያን ያህል ለውንጀላ የሚቀርብ አይደለም፡፡ አንተ ራስህ ያቀረብከውን ልጥቀሰው ‹‹ይህ የአሁኑ ሰንደ ቃላማ ለእኔ ከበፊቶቹ ይሻለኛል፤ ሁሉም የታሰሩት ፖለቲከኞች እና ጋዜጠኞች ንፁህ ናቸው ብዬ አላምንም›› ያለውን ጠቅሰሃል በናትህ ፖለቲካውን ከስሜት በዘለለ ተመልከተው፡፡ በዚህ ሁኔታ ከቀጠልን አንድም ኢንች ወደፊት መራመድ አንችልም፡፡ ቀደም ብዬ አንዳልኩት ይህን አለ እከሌ እከሊት ይህን አለች የሚባል ፖለቲካም የለም፡፡
አሁን አሉት የተባለውን ከዚህ ቀደም አቧራ ተነስቶ ብዙ ሲባል አስተውያለሁ ነገሩን በቅንነት ማየት ነው የሚሻለው፡፡ የግለሰብ መብት በቅድሚያ እንዲከበር የሚታገል ድርጅት እንዴት ይህን ተናገርክ ብሎ ሊከሰው ይችላል፡፡ እንዳንተ ቢሆን ይህ ሰው ሂስ ማውረድ አለበት፡፡ በአንድነት ቤት ግን ይህ አይሆንም፡፡ ቃሉ በራሱ የሚለው እኮ ‹‹ይህ የአሁኑ ሰንደ ቃላማ ለእኔ ከበፊቶቹ ይሻለኛል›› እናስተውል! ለአንድነት አይደለም ያለው ‹‹ለእኔ›› ነው፡፡ ይህ መብቱን ታድያ ማን ሊከለክለው ይችላል? ለምሳሌ እኔን ብትጠይቀኝ ምንም ሌለበትን አረንጓዴ፣ቢጫ ፣ቀዩን ነው ምልህ! ግርማ እንዲህ ስላለ ግን ምንም ልል አልችልም መብቱ ነው፡፡ ለምን እኔ የመረጥኩትን ካልመረጥክ እንዴት ልለው እችላለሁ? ይህን ከቻልክ ብታስረዳኝ?
የታሰሩትን አስመልክቶ የሠጠው ለኔ ምንም የሚያስከፋ ነገር የለውም፡፡ ምንድነው ያለው ‹‹ሁሉም የታሰሩት ፖለቲከኞች እና ጋዜጠኞች ንፁህ ናቸው ብዬ አላምንም›› አሁንም እዚህ ጋር ሲገልፅ አንድነት ምናም ሳይሆን እራሱን ወክሎ ነው ሚናገረው፡፡ ይህ ማለት ግን የታሰሩት ሁሉ ወንጀለኞች ናቸው ማለት አይደለም፡፡ አልያም የታሰሩት በሙሉ ንፁሃን ናቸው ማለት አይደልም፡፡ ለምሳሌ ሁሉም ነፃ ናቸው ለማለት ቃሊቲን ጨምሮ በአገሪቷ ውስጥ ያሉ ሁሉም እስር ቤቶች ውስጥ ያሉ ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞችን በሙሉ ማወቅ ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ አንተኑ ልጠይቅህ በዝዋይ ምን ያህል ፖለተከኛና ጋዜጠኛ ታስሮ ይገኛል? ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ… እያልክ የምታውቃቸውን ብቻ ትጠራለህ እንጂ የማታውቃቸውን ከየት አምጥተህ ትጠራልኛለህ? ስለማታውቃቸውስ ጥብቅና ልትቆም ትችላለህ? ስለዚህ ‹‹ሁሉም›› ያሉበት ሁኔታ ስህተት ሊሆን አይችልም፡፡ ለምሳሌ እኔን ብትጠይቀኝ ብዙ የፖለቲካ እስረኞች እንዳሉ ልገምት እችላለሁ ተናገር ብባል ግን አሁንም እንዳንተው እስክንድር፣ ርዕዮት ነው ልል የምችለው እንጂ የታሰሩት ሁሉ ንፁሃን ናቸው ለማለት በአገሪቷ ውስጥ ያሉ እስረኞችን ሁሉ ማወቅ ይጠበቅብኛል፡፡ ይህ ደግሞ የማይቻል ነው፡፡ ይህ ከሆነ እውነታው የሰጡት አስተያየት እንዴት ስህተት ሊሆን ይችላል?
እንዳልከው የልዑካን ቡድኑ ውስጥ ስለተካተቱ ግለሰቦች ይመጥናሉ አይመጥኑም በሚለው መነጋገር እንችላልን፡፡ ብንነጋገር እንኳ የመምረጥ እድሉ አልሰጡንም፡፡ ወይንም ህዝቡ እንዲመርጥ እድል አልተሰጠውም፡፡ ይህ ማለት ግን በጭፍኑ እዛ ውስጥ ያሉ ሁላ ከአንድ ምንጭ የተቀዱ ናቸው ማለት ጅምላ ፍረጃ ከመሆን ውጪ አያልፍም፡፡ እንዳልከው በዚህ ልኡካን የተካተቱ ግለሰቦች በስልጣን ዘመናቸው አንተ የጠቀስካቸውን ጨምሮ በርካታ ወንጀሎችን ሰርተዋል፡፡ እየሰሩም ይገኛሉ፡፡ የተከበሩ አቶ ግርማ ከዚህ ልዑክ ጋር አብረው መሄዳቸው እንዴት ሆኖ ነው ከነዚህ አምባገነኖች ጋር መተባበር ተደርጎ የሚወሰደው? የልዑኩ አላማስ ምንድን ነው? የሚለውን ጨምረህ ብትመልስልኝ አወዳለሁ፡፡
ቀደም ብዬ ያልኩትን መድገም ነው የሚሆነው፡፡ ግርማ ወደ እዚህ ልዑክ ሲሄድ እንዳልኩት በፓርላማ አባልነቱ እንጂ አንድነት ፓርቲን ወክሎም አይደልም፡፡ ይቅርታ የሚጠይቀውስ ምን አድርጌያለሁ ብሎ ነው? አንድነት ፓርቲስ ግለሰቡን የሚቀጣው በምን መስፈርት ነው? ፓርቲውስ መግለጫ የሚሰጠው በምን ምክንያት እንደሆነ አብራራልኝ፡፡ አሁን የመጣች ፋሽን አለች ግለሰቡ ይህን ተናገረ ይህን አሉ ያም በአመራር ደረጃ ያለ ስለሆነ የፓርቲው አቋም አድርገን እንወስዳለን የምትል ቀልድ፡፡ ለጊዜው አትመጥንምና ተዋት፡፡ ስለጉዞው ለምን አልነገረንም ለሚለው ከፈለገ የሚለን ይኖራል ሊገደድ የሚችልበት አመክንዮ የለም፡፡ ማንም እንደሚረዳው ብቸኛ መቀመጫ እንዳለው አባል መካተቱ ብዙም የሚገርም አይደለምና፡፡ አትሳሳት ፓርቲው ግን መልስ እንዲሰጥ አትጠብቅ፡፡ እዚህም እዚያም ለሚነሳ አቧራ ፓርቲው መግለጫ በመስጠት ጊዜ ሚያባክንበት ሁኔታ ተገቢነቱ አይታየኝም፡፡
ጥሩ ጊዜ ተመኘሁ!♡
https://www.facebook.com/gracet.sewoch/posts/9048768128693

No comments:

Post a Comment