Thursday, December 11, 2014

ህገ መንግስቱ እና ያለፉት 20 ዓመታት… (በጋዜጠኛ መድሃኒት)

‹‹ አራት ሰዓት ላይ ኃላፊ ቢሮ ስብሰባ እንድትገቡ›› የመሥሪያ ቤታችን ተላላኪ ጎርናና ድምጽ በየቢሯችን ተወንጭፎ ገባ፡፡ ‹ኤጭ› አልን፣ የተላላኪዋ ድምጽ ተኖ ሳያልቅ፣ የምሥራች ይዞ እደመጣ ሰው በፈገግታ ስትወዘወዝብን የበተነችው የቁርጭጫ ጸጉሯ ርጋፊ ነፋስ ጠርጎ ሳይወስደው፣ ዓረፍተነገሯን ለማንበልበል የሳበችውን ኦክስጅን አቃጥላ ሳታስወጣ፣ ጆሮዋ ከአፋችን ሳይርቅ በአንድ ድምጽ ‹ኤጭ› አልናት፡፡ መስማት አለመስማቷ ግድ አልሰጠንም፡፡ መቼም ይገባታል ጠባችን ከእሷ እንዳልሆነ፣ የመንግሥት ሠራተኛ ከቀበሌ ስኳርና ዘይት ቀጥሎ የስብሰባ ነገር እንዳንገሸገሸው፡፡
Medhanit
Medhanit

የተባለው አራት ሰዓት ደርሶ ፊቱን ያንከረፈፈው ሠራተኛ ያረጀች ማስታወሻ ደብተሩን እያንጠለጠለ ኃላፊው ቢሮ ተገኘ፡፡ ኃላፊው ለአጭር ቁመቱ ማካካሻ ይሆንለት ይመስል አለቅጥ የረዘመ ተሸከርካሪ ወንበሩ ላይ ለጠጥ ብሎ ወደ ቢሮው የሚገባውን ሠራተኛ በዓይኑ ይገመግማል፡፡ ከፊት ለፊቱ በጥቁር የብረት መደብ ላይ በትልልቅ ነጭ ፊደላት የተቀረፀ ስምና የሥራ ድርሻው ከጠረጴዛው ጫፍ እስከ ጫፍ ተዘርግቷል፣ አቶ — የ—- ዞን ፍትህ መምሪያ ኃላፊ፡፡


ሁሉም ሠራተኛ ተጠቃሎ መግባቱን ሲያረጋግጥ ጉረሮውን ሞርዶ ንግግሩን ጀመረ…
‹‹እ….. ዛሬ የተሰባሰብንበት ምክንያት ያው ከፊታችን የሚከበረውን የብሔረሰቦች ቀን አስመልክቶ ያው እንደመምሪያ እንድንወያይ ያው ከበላይ አካል በመጣው ትዕዛዝ መሠረት ያው…›› ሥራ እንዳልፈታ ብዬ ‹‹ያው›› እና ‹እንደ መምሪያ››ን መቁጠር ጀመርኩ..አንድ..ሁለት…ሦስት…. አሥራ ሁለተኛው ‹ያው› ላይ ፍሬ ነገሩ ተገኘ..
‹‹ያው እንግዲህ ህገ-መንግሥታችን ከተደነገገ ጀምሮ ባለፉት 20 ዓመታት መንግሥት ምን ምን ቁልፍ ተግባራት አከናወነ የሚለውን ሰነድ እንደ መምሪያ አዘጋጅተን እንድንወያይ ነው››
ስብሰባው ከመጀመሩ አንዱ ቀዥቃዣ እጁን ሽቅብ ቀሰረ
‹‹እሺ አቶ ዳንኤል ጥያቄ አለህ?››
‹‹እኔ መጠየቅ የፈለኩት እንግዲህ ሃያ ዓመት ስንል ስንት ነው? የሚለውን ነው አመሰግናለሁ›› ከሰፊ ፊቱ መሀል ለምልክት የተቀመጡ ዓይኖቹን ይበልጥ አጥብቦ ግራ በገባው ድምጽ ጠየቀ፡፡ አገጩ ጠረጴዛው ላይ ደርሶ የማስታወሻ ደብተሩን ከመከለል ለጥቂት ያመለጠ አጭሬ ነው፡፡ አፍንጫው ከ20 ሜትር ርቀት ጨፍነው የወረወሩት ጭቃ ይመስላል፡፡ አንድ ቃል ባወጣ ቁጥር ግራና ቀኝ የሚያወናጭፋቸው ዱካክ እጆቹ እንደ ስፕሪንግ ሽቦ በተጥመለመሉ ከርዳዳ ፀጉሮች ተወረዋል፡፡
‹‹ አቶ ዳንኤል ጥያቄህ ላንተም ግልጽ የሆነልህ አልመሰለኝም እስኪ አብራራው›› ኃላፊው በግርታ ጠየቀ
‹‹ማለት የፈለኩት መንግሥታችን እንደሚታወቀው የ23 ዓመታት እንደውም 24ተኛውን ሊደፍን ወራት የቀሩት ወጣት ሆኖ ሳለ ወደ ኋላ የ20 ዓመት ጎረምሳ ማድረጋችሁ ግራ ቢገባኝ ነው፡፡ ውይይታችን መሆን ያለበት ኢህአዴግ አባት ድርጅታችን ባለፉት 23 ዓመታት ምን አከናወነ ነው፡፡ በድጋሚ አመሰግናለሁ››
‹‹ይሄ ለሌሎቻችሁም የሚሆን መልዕክት ነው፡፡ በግማሽ ልባችሁ እዚህ ባትቀመጡ ይመረጣል፡፡ የተባልነው ህገ መንግሥቱ ከፀደቀ ወዲህ እንጂ ኢህአዴግ ሥልጣን ላይ ከወጣ ጀምሮ አይደለም››
‹‹አሃ…. ነው እንዴ? ይቅርታ ጓዶች ይቅርታ›› አጭሬ በፈገግታ የተጥለቀለቀ ይቅርታ አቀረበ፡፡
አራት ሰዓት ላይ ስብሰባ የተቀመጠ ሠራተኛ አባት ድርጅቱ ኢህአዴግ ህገ-መንግሥታችሁ ነው ያለውን ካፀደቀ ወዲህ ለ20 ዓመት ያከናወናቸውን አበይት ተግባራት ቆፍሮ ለማውጣት የምሣ ሰዓቱን ሰውቶ አእምሮውን ጨመቀ…ትውስታውን አንጠፈጠፈ…የዕድሜ ልምዱን በረበረ፡፡ ለቀጣይ ዓመት ሹመት ተስፋ የጣለ እጁን እየሰቀለ የዚህን መንግሥት ቅዱስ ሥራዎች ተነተነ፡፡ በግምገማ ሰበብ የያዟት ቁራሽ እንጀራ ከአፋቸው እንዳትነጠቅ ስጋት የገባቸው አዛውንት አንደበቶች ከጎን እና ጎናቸው ያለውን ሰው ቃኘት አድርገው ሽርፍራፊ ግልምጫዎችን ለቃቅመው የቀረ ያሉትን የኢሀአዴግ በጎ ሥራ ተነፈሱ፡፡
እኔም የበኩሌን ማዋጣት ነበረብኝና ማስታወሻ ደብተሬ ላይ ይህቺን ጫርኩ፡፡
‹መንግሥታችን ባለፉት 20 ዓመታት (ህገ መንግሥቱ ከፀደቀበት ዓመት ጀምሮ እንዳልል ህገ-መንግሥቱ እንደ ተረት ዓለም ጭራቅ በስም ብቻ ስለ ቀረ ብዕሬ ተሸማቆ ዘሎት ነው) ያከናወናቸው አበይት ነገሮች ቢዘረዘሩ እንኳን የ1 ቀን ጉባኤ የ 1ዓመት ሱባኤም አያጠራውም፡፡ የ97ቱ የድምጽ ዝርፊያና የእናቶች ለቅሶ ብቻውን አርባ ቀን አርባ ለሊት ጉባኤ ያስቀምጣል፡፡
ባለፉት 20 ዓመታት የህትመት ብርሃናችን ብልጭ ብላ ላትነቃ አሸለበች፡፡ ‹ጋዜጠኛ› የሚል ማዕረግ ከስሙ በፊት ላስቀደመ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ቃሊት መውረድ አልያም ስደት መውጣት ከአንዱ የሥራ ክፍል ወደ ሌላው የመዛወር ያህል ዋዛ ሆነ፡፡ ይኸው በ20 ዓመታት ውስጥ ከጎፈሬ አበጣጠርና የአሳማ ሾርባ አዘገጃጀት ምክር ለጋሽ ‹ጋዜጦች› ውጭ እጃችን ላይ የወረቀት ዘር እንዳይገኝ ሆነን ተከረከምን፡፡
አዲስ ኃይማት በመቀበል የሚቀድማት የሌለ ሀገራችን ‹አብዮታዊ ዴሞክራሲ› የተባለውን የብዙ አማልክት ኃይማት ተቀበለች፡፡ ‹የህዝብ› የሚል ታርጋ የለጠፉ መገናኛ ብዙሃኖቻችንም ‹ቅዱስ…ቅዱስ…ቅዱስ..› ሲሉት ይውላሉ፡፡ ምዕመኖቹም በፍርሃት ተሸብበበው ይሰግዱለታል፡፡ ካህናቱም የወሬ መባቸውን ይዘው በቤተ መቅደሱ ይመላለሳሉ፡፡ አማልክቱም በኩራት ‹‹እነሆ በሚሊየን የሚቆጠር ተከታይ አፍርተናልና በኩራት ከፍከፍ አልን›› ይላሉ፡፡
ይኼ እኔ ወፌ ቆመች ስል ወፍ ጠባቂ መስሎ የገባ መንግሥት ለ20 ዓመታት ማሽላችንን በግሪሳ ሲያስበላና ሲበላ፣ ሲያስጠረጥርና ሲጠረጥር ፣ሲያስፈለፍልና ሲፈለፍል፣ ሲያሳጭድና ሲያጭድ ከርሞ ወጣትነታችን አገዳው የቀረ ማሳ ውስጥ ይንቀዋለላል፡፡ ‹አርባ በመቶ ገቢዬ ከጫት ነው› ሲል ከአፉ ቀልበን ‹እንኳን እኛ መንግሥትም በጫት ይከብራል›ን እየዘመርን መጽሐፍት ቤቶቻችንን አፍርሰን መቃሚያ ቤቶች ገነባን፡፡ ባለፉት 20 ዓመታት….›
ከማስታወሻ ደብተሬ ቀና ስል ተሰብሳቢዎቹ የእለቱን ስብሰባ አገባደው በረሃብ የሚጮህ ሆዳቸውን ጥያቄ ለመመለስ እየተቻኮሉ ጠረጴዛው ላይ ከተዘረጋው ሰፊ አጀንዳ ላይ ውልግድግድ ፊርማቸውን እያኖሩ ነው፡፡ ውልግድግድ፣እንደ አንደበታቸው ቃልና እደልባቸው እውነት መስመሩ ያልተገናኘ፣ መስመሩ የተራራቀ ውልግድግድ ፊርማ፡፡ የፃፍኩትን ዓየት አደረኩ፡፡ ሁለት ገጽ የሚሞላ የ20 ዓመት ነውር ማሰናዳት ቀላል ነው፡፡ ይኼን ነውር ማቅረቡ ነው ዳገት፡፡ ለማን ይቀርባል? ማንን ያስነብቧል? ይኼ መንግሥት እደሆነ አመሉ የአራስ ልጅ ነው፡፡ አራስ ልጅ ባማረ አልጋ ብታስተኛው በገዛ ቅዘኑ ፊቱን አክፍቶ እርር ምርር ብሎ ያለቅሳል፡፡ ቅዘኑን ለማጠብ ብትቀርበው ለቅሶውን ሳያቋርጥ ባልጠና እግሩ ሊራገጥ ባልሰላ ጥፍሩ ሊቧጥጥ ይታገላል፡፡ ይህን ሁሉ ችለህ አጥበህ አጽድተህ መልሰህ ስታስተኛው የሹፈት ሳቁን በድዱ እየሳቀ ለሌላ ቅዘን ራሱን ያዘጋጃል፡፡ አይጠዳሽ! አይጠዳሽ መንግሥት መነካካት እርግጫው፣ ቡጨራው ቅዘኑ እኔንም ይድረሰኝ እንደማለት ነውና ይኼን ማስታወሻ ደብተሬን እኔው ራሴ ደግሜ ከማላነብበት ቦታ አኖርኩት፡፡

No comments:

Post a Comment