Monday, December 22, 2014

የእምዬ ሚኒሊክ ታሪክና የኛ ፖለቲካ፡- ዛሬ ከትላንት ሲደድብ

(Zeryihun Kassa)
የሰሞኑን በሚኒሊክ ጉዳይ የያዝነውን የማህበራዊ ሚድያ አተካራ ላየ ከታሪክ የሚማሩ ሳይሆን በታሪክ የሚባሉ ብንባል ሳይሻል አይቀርም። በትላንት ተባላን። ትላንትናን እንደነበረ መረዳት ተሳነን። ትላንትናን ከደማችን ተነስተን ሳይሆን በመረጃ ደርጅተን መቃኘት ቋቅ እያለን ነው። ትላንትና ግን አደለም ዋናው ችግር። ዋናው ችግር ትላንትናን መረዳት እና ለነገ ፋይዳ ባለው ሚዛናዊ አቋም ላይ መገኘት ያልቻለው ዛሬያችን ነው።
ሚኒሊክ በደቡቡ የሀገራችን ክፍል ኦሮምያንና ወላይታን ጨምሮ ጦርነት ማድረጋቸውን ታሪክ መዝግቦታል። እኛም በተጣመመም ይሁን በቀና መንገድ ያን ታሪክ ተምረነዋል። በቁምነገሩ ሚኒሊክ ጦርነት አድርገዋል። ጦርነት ደግሞ ክቡር ነፍስ ይነጥቃል። ሽንፈቱ አዋራጅ ሆኖ፤ ሞቱ ደግሞ ቁጭት ትቶ ሊያልፍ ይችላል። ጦርነቱ አሰቃቂ እንደነበር ይነገራል። እውነትነቱ መጠርጠር የለበትም። ይህን መካድ ነው ነውረኛ የሚሆነው።
Emperor Menelik
የምር እውነት ስንናገር ደግሞ ዛሬ እንኳ ተነጋግረን በማንስማማበት ሀገር ያኔ ምኒሊክ ይህን ጉዳይ በውይይት እንዲፈታው መጠበቅ ወይም ከወቅቱ ንጉሶች እና ፊውዳሎች ነባራዊ ባህሪ ወጥቶ ግዛት እንዳያስፋፋ እና ንግስናውን እንዳይፎክርበት ማሰብ የዋህነት ይመስላል። በአንድ በኩልም በወቅቱ ያልነበረን ዛሬም በአብዛኞቹ የሀገራችን ፖለቲካ ሀይሎች መሀከል የማይታይን ብስለት መሻት ይመስላል።
በበኩሌ መራራ ግድያዎች በተከሰቱበት ጦርነት መሀል ግን አሁን ያለንበት ኢትዮጵያዊ እርሾ መጣሉን አልዘነጋም። ሁለቱም ትውስታዎች ሊጠፉን አይገባም። ምሬቱም በጎ ውጤቱም።
አገራችን የምንለው ይሄ አገር ህዝባችን የምንለው ይህ ህዝብ የዛ ታሪክ ውጤት ነው። ሁሉም አገር ይህን በመሰለ ወይም ከዚ በከፋ ታሪካዊ ሂደት የተገነባ ነው። የሆነ ሆኖ ግን ይሄም ሀገራዊ ቅርጽም ቢሆን ይሄም አለማቀፋዊ ሀቅ ሟቾቹን ደግ ሚኒሊክ ገደላቸው ለማለት አያነሳሳንም። ያን ማለት ተገቢም አደለም።
ወደህ ካልገበርክ ገድዬ አስገብርሀለው የዛ ዘመን ፍልስፍና ነበር። ዛሬም እኮ ወይ ከኛ ጋር ቁም አለበለዚያ አይንህን ለአፈር የሚሉ ዜጎች አሉን። አሜሪካ የሚኖሩትን ያለ እኛ አዋቂ የለም ባዩች ጨምሮ። በሰለጠነ አገር የሚኖሩ ያልሰለጠነ እና ያለበሰሉ ህሊናዎች የመኖራቸው ማሳያም ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። ተደማምጦ መወያየት የማይችል ሰው ታዲያ ሌላ ምን ሊባል ይችላል።
ወደ ነገሬ ስመለስ የታሪኩን አሳዛኝ ገጽታ እምናነሳው ሚኒሊክ እንዲጠላ በማሰብ ከሆነ ፋይዳ ቢስ አብዮት ነው። ሚኒሊክ ተወደዱ ተጠሉ ለሳቸው ትርጉም የለውም። የዚያን ዘመን ታሪክ የምናነሳው የአባጅፋርንም አሰቃቂ የዳውሮና ከፋ አያያዝም ለመርገም ከሆነ ፋይዳ ቢስ ነው። ቁምነገሩ ከዚያ ታሪክ የምንማረው ነው። ስለ ጦርነት አስከፊነት ስለ መበደል መራራነት። ሌላው ትርፍ ነው።
እውነቱን ለመናገር ሚኒሊክን በመሰሉ ታሪካዊ ሀቆቻችን ዙርያ በወዲህም በወዲያም የሚነሱት አጉራ ዘለል ትችቶች አይመቹም። ይሄ ከታሪክ መማር የማይችል ስብራቱን የቀጠለበት ማህበረሰብ ማሳያ ነው። አንደኛ ሚኒሊክ በጨለንቆ ያደረጉት ጦርነት በአማራና በኦሮሞ መሀል የተደረገ ያስመስለዋል። ሁለተኛ ደገሞ ጦርነቱ በአካባቢው ፊውዳልና በሸዋው ፊውዳል መሀል የተደረገ ሳይሆን በጨቋኝና በነጻ አውጪ መሀል የተካሄደም ያስመስለዋል። ማን ይሙት ስለፊውዳል ሲወራ ደም ምን ቦታ ይኖረዋል።
ህዝብን ጪሰኛ አድርጎ ለሚኖር ስርአት እና ነገስታት መወገን ምን ፋይዳ አለው። ሁለተኛ ነገር የሚኒሊክ ጦር በኦሮሞ ፊትአውራሪዎች እና ወታደሮች የማይመራ ለማስመሰልም ይሞክራል። ይሄ ግራ የገባው ንባብ ኦነግና የቀኝ አክራሪው ተቃዋሚ የፈጠሩት ስሜት ፈለቅ ትርክት ውጤት ነው። ሁለቱም ከታሪኩ የሚፈልጉትን ገጽ የሚያነቡና የነሱን ማደማደሚያ የማይደግፈውን እውነታ ሽምጥጥ አድርገው የሚክዱ ናቸው። አንደኛው የአውሬ ምስል ቀርጾ ህዝብ ለማነሳሳት የሚተም ሁለተኛው ደግም ብሄራዊ ጀግና ስሎ የፈጸማቸውን ወይም ያስፈጸማቸውን አረመኔያዊ ግድያዎች እና ቅጣቶች ለማረሳሳት የሚሞክር።
ደም ከህሊና ጋር ስሜት ከእውቀት ጋር ሲደባለቅ ሁሌም የጠራ ነገር ማግኘት የሚሳነንም ለዚህ ነው። ወላ ቴድሮስ በለው፣ ዮሀንስ በለው፣ አሉላ በለው፣ ሚኒሊክ በለው፣ አባጅፋር በለው፣ ጾና በለው ከህዝብ ጥቅም አንጻር ሲመዘን ፊውዳል ፊውዳል ነው – በህዝብ ጫንቃ ላይ የሚኖር መሪር ሸክም። የሚኒሊክም ይሁን ሌላው ታሪካችን የሚፈልገው ተቆርቋሪ ወይም አጣጣይ አደለም። ቀና ተማሪ መሆን በቂ ነው። ድክመቶችን ድክመት ጥንካሬዎችን ጥንካሬ ብሎ መውሰድ የሚችል ቀናነት።
ጦርነቱ ቅዱስም ርኩስም አልነበረም። በሁለት ፊውዳሎች መካከል የተካሄደ አሰቃቂ ጦርነት ነበር። በዚህም በዚያም በኩል ክቡር ነፍሶች የተቀጠፉበት ነበር። በዚህም በዚያም በኩል ኦሮሞ የተሰለፈበት፣ የተዋጋበት፣ ያዋጋበትም ነበር። ያ አሰቃቂ ጦርነት እና ሰቆቃ ታለፈ። የሆነ ሆኖ በዚያ አሳዛኝ ሂደትም ቢሆን እምንወዳት ሀገር አግኝተናልና እንጽናናለን።
ምርጥ ታጋዮቻችን በህወሃት እና በኢህዴን መስምርም ደርግን ሲፋለሙ እኮ ክቡር ነፍስ ቀጥፈው የወንድማማቾች ህሊና በጥይት ፈርጦ እኮ ነው። የጦርነትን አስከፊነት የአላማው ጥራት አይቀይረውም። የአላማ ጥራት ጥይት እስከመጠጣት ይወስዳል እንጂ ጥይት መጠጣት እና ጦርነት በማንኛውም የአላማ ጥራት ምክንያት አስከፊነቱ ሊፋቅ አይችልም። በባህሪው መራራ ነው።
የግድ እቺ አገር ይሄ ቅርጽ ሊኖራት ይገባል የግድ ይህን ቅርጽ ለማግኘት ያ ጦርነት ሰዎችን መቅጠፍ ነበረበት ብዬ ባላምንም ከሆነና ካለፍንበት ግን የከፍልነው ዋጋ በአንድነታችን ደምቆ በልማታችን ፍሞና በፍትሀዊነታችን ታትሞ ሊቀጥል ይገባል እንጂ በመነቋቆር እንዲደበዝዝ ልንፈቅድ አይገባም።
በመጨረሻ አማራ ስለሆንኩ ብቻ ሚኒሊክ አማራ በመሆኑ ውዳሴ እንዲከተብለት ከሻትኩና ጭካኔ የተሞላባቸው ተግባሮቹ አይነሱ ካልኩ – ትግሬ ስለሆንኩ እና ለትግራይ መዳከም ሚኒሊክ ሚና ነበረው በሚል እሳቤ በረባም ባረባም እማብጠለጥለው ከሆነ – ኦሮሞ ስለሆንኩ ሁሌም የሚኒሊክን ሌጌሲ በፈጸመው የጭካኔ ድርጊቱ ብቻ እምገልጸው ከሆነ – እውን ድርጊትን በድርጊትነቱ ግለሰብን በግለሰብነቱ ከመረጃዎች ተነስቼ የማድነቅና የመተቸት ሚዛኔ ከወዴት ሊሆን ነው።
በኔ አተያይ አብዛኛው በሚኒሊክ ዙርያ የሚነዛው አስተያየት ሚዛኑን የሳተው ከመነሻው ዘረኛ አስተያየት የነበረ ስለሆነ ነው። ሚኒሊክ በታሪክ ተደናቂም ተወቃሽም መሆኑን ማንም ቃል በማስዋብም ቃል በማምረርም ሊቀይረው አይቻለውም። ታሪክ እንደገና ስለማይደረግ ማለቴ ነው።
በዚህ መሀል ግን ግፎቹንም ጥንካሬዎቹንም በማንሳት ጉዳዩን ከበቀሉበት ዘር አንጻር ሳይሆን ከመረጃዎችና ሀቆች አኳያ ባዩ ወንድምና እህቶቻችን ሚዛናዊነት ኮርተናል። ጎበዝ ይሄን የስነምግባር ስብራታችንን አርመን እንቀጥል። አስቻጋሪው ፖለቲካው ሳይሆን የኛ ያደፈ ስነምግባር ሆኗል። በመሆኑም ለቀና ፖለቲካ ቀና ፖለቲካዊ ባህሪዎች መገንባት እንዳለብን አስባለሁ።
ሚዛናዊነት አንዱ ትልቁ ለፖለቲካችን መስከን የሚያስፈልገን ቀና ባህሪ ነው። እንሁነው እንኑረው። የቀረው ይቆየን።
************

No comments:

Post a Comment