Sunday, June 7, 2015

‹‹አማራ በመሆኔ ዘሬን እንዳልተካ ተደርጌያለሁ›› 1ኛ ተከሳሽ ጌታቸው መኮንን (መቶ አለቃ)

Tesfaye tariku
[በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር]
ከወራት በፊት በሽብር ተጠርጥረው ከአማራ ክልል ተይዘው በእስር ላይ የሚገኙ የተቃዋሚ ፓርቲ የዞን አመራሮች የሽብር ክስ ተመሰረተባቸው፡፡ በ13/07/07 በተጻፈና ዛሬ ግንቦት 28/007 ዓ.ም በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት በንባብ በተሰማው የአቃቤ ህግ ክስ ላይ እንደተመለከተው በአንደኛ ተከሳሽ ጌታቸው መኮንን መዝገብ 16 ሰዎች የሽብር ክስ ተመስርቶባቸዋል፡፡ከተከሳሾቹ መካከል የመኢአድ፣ የሰማያዊና የአንድነት ፓርቲዎች አመራሮችና አባላት የተካተቱበት ሲሆን፣ ተከሳሾቹ በ2001

ዓ.ም የወጣውን የጸረ-ሽብርተኝነት አዋጅ አንቀጽ 7(1) እና በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀጽ 32(1)(ሀ) በመተላለፍ ክስ እንደተመሰረተባቸው ተመልክቷል፡፡ ተከሳሾቹ ‹‹ራሱን ግንቦት ሰባት እያለ በሚጠራውና ከዚሁ የሽብርተኛ ድርጅት ጋር ከተቀላቀለው ራሱን አርበኞች ግንባር እያለ በሚጠራው የሽብር ድርጅት ውስጥ አባል በመሆን በማናቸውም መልኩ ለመሳተፍ በማሰብ›› ተከስሰዋል፡፡በዚህ መዝገብ ስር የተካተቱት ተከሳሾች የሚከተሉት ናቸው፡-
1ኛ. ተከሳሽ ጌታቸው መኮንን (መቶ አለቃ)
2ኛ. ›› ›› በላይነህ ሲሳይ
3ኛ. ›› ›› አለባቸው ማሞ
4ኛ. ›› ›› አወቀ ሞኝሆዴ
5ኛ. ›› ›› ዘሪሁን በሬ
6ኛ. ›› ›› ወርቅየ ምስጋና
7ኛ. ›› ›› አማረ መስፍን
8ኛ. ›› ›› ተስፋዬ ታሪኩ
9ኛ. ›› ›› ቢሆነኝ አለነ
10ኛ. ›› ›› ታፈረ ፋንታሁን
11ኛ. ›› ›› ፈረጀ ሙሉ
12ኛ. ›› ›› አትርሳው አስቻለው
13ኛ. ›› ›› እንግዳው ዋኘው
14ኛ. ›› ›› አንጋው ተገኘ
15ኛ. ›› ›› አግባው ሰጠኝ
16ኛ. ›› ›› አባይ ዘውዴ፣ …..ናቸው፡፡

     ተከሳሾቹ በማዕከላዊ የወንጀል ምርመራ በነበሩበት ወቅት የደረሰባቸውን የመብት ረገጣ ለፍርድ ቤቱ ለማስረዳት የሞከሩ ቢሆንም ፍርድ ቤቱ በማረሚያ ቤት ስላለው ጉዳይ እንጂ በማዕከላዊ በነበራችሁበት ወቅት ስለደረሰው ጉዳይ ከጠበቃችሁ ጋር ተነጋገሩ የሚል መልስ በመስጠት ሊያልፈው ሞክሯል፡፡ ሆኖም ግን ተከሳሾች ‹‹እናንተ ካልሰማችሁን ለማን ሄደን እንናገራለን›› በማለት ችግሮቻቸውን ለማስረዳት ሞክረዋል፡፡አንደኛ ተከሳሽ የሆነው ጌታቸው መኮንን ‹‹አማራ በመሆኔ ዘሬን እንዳልተካ ተደርጌያለሁ….በጣም ብዙ በደል በማንነቴ ብቻ ደርሶብኛል…›› ሲል ፍርድ ቤቱ ሳያስጨርሰው አቋርጦታል፡፡ተከሳሹ ግን በዚህ ሳያበቃ፣ ‹‹የደረሰብኝን በደል ይሄው ማሳየት እችላለሁ….›› በማለት የደረሰበትን ለዳኛው አሳይቷል፡፡ 7ኛ ተከሳሽ አቶ ተስፋዬ ታሪኩ በበኩሉ ‹‹አንዴ ብቻ ስሙኝ…ከዚህ በኋላ አልናገርም…እንደፈለጉ ይወስኑ…›› በማለት የደረሰበትን
ለማስረዳት እድል እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ግን አቤቱታችሁን በጽሑፍ አቅርቡ በማለቱ ከዚህ በላይ መናገር አልተፈቀደለትም፡፡ሌሎችም በዚህ መዝገብ የተካተቱት ተከሳሾች በማንነታቸው ላይ የተመሰረተ ጥቃት እንደተፈጸመባቸው ከመግለጻቸው በተጨማሪ የህክምና አገልግሎትም እያገኙ እንዳልሆነ ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡ ተከሳሾቹ የክስ መቃወሚያ ካላቸው እንዲያቀርቡ ለሐምሌ 1/2007 ዓ.ም ቀጠሮ ተሰጥቷቸዋል፡፡በሌላ የፍርድ ቤት ውሎ በእነ ብርሃኑ ተክለያሬድ የክስ መዝገብ የሽብር ክስ የተመሰረተባቸው ብርሃኑ ተ/ያሬድ፣ እየሩሳሌም ተስፋው፣ ፍቅረማርያም አስማማው እና ደሴ ካህሳይ ዛሬ ፍርድ ቤት ቀርበው የነበር ሲሆን፣ ለዛሬ እንዲያቀርቡ ይጠበቅ
የነበረውን የክስ መቃወሚያ ማረሚያ ቤቶች እንድንገናኝ ስላላደረጉን መቃወሚያ ማቅረብ አልቻልን በማለታቸው ለሰኔ 9/2007 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷቸዋል፡፡
በዚህ መዝገብ የተካተቱት ተከሳሾች በማረሚያ ቤቶች እየደረሰብን ነው ያሉትን የመብት ጥሰት በቃል ያሰሙ ሲሆን፣ፍርድ ቤቱ ግን አቤቱታቸውን በጽሑፍ እንዲያቀርቡ አዝዟል፡፡ስለሆነም ተከሳሾች አለን የሚሉትን አቤቱታ መቃወሚያ በሚያቀርቡበት ዕለት አብረው ማቅረብ እንደሚችሉ 
ተመልክቷል፡

No comments:

Post a Comment