የስፖርተኞች ስም የተለጠፈበት ልብስ ለብሼ አላውቅም፡፡ ግን በስማቸው የታተመ ልብስ ብለብስላቸው ከማያሳፍሩኝ መካከል ኃይሌ አንዱ ነበር፡፡ ገና በልጅነቴ በሬድዮ የሀይሌን ማሸነፍ ሰምቼ ዘልያለሁ፣ ተሸነፈ ሲባል በጣም አዝኜ አውቃለሁ፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ለኃይሌ የተለየ ስሜት ነበረኝ፡፡ በቅርብ ግን ኃይሌ እየወረደብኝ መጣ፡፡ በቅርብ አመታት ኃይሌ ለምን ድሆችን (አካል ጉዳተኞችም፣ ህጻናትና አዛውንቶችን ጨምሮ) እንደማይረዳ ሲጠየቅ በተደጋጋሚ ‹‹ሰርተው ይብሉ!›› ሲል አዳምጬ ገርሞኛል፡፡ የሜቄዶንያው ቢኒያም ይህ የኃይሌ አባባል እንዴት ያናድደው?!
ከ3 አመት በፊት ግን የኃይሌ ስም ያረፈበትን ቲሸርት ብለብስ ኖሮ ይቆጨኝ እንደነበር የሚያስታውስ ነገር ሲናገር ሰማሁት፡፡ ‹‹ለምን ሰርተው አይበሉም!›› የሚለው ኃይሌ ሰርተውም የዋጋቸውን የማይከፈላቸው መምህራን ‹‹የስራ ዋጋችን ይከፈለን፣ ደመወዝ ይጨመርልን!›› የሚል ጥያቄ ሲያነሱ፣ እሱን የለመኑት ይመስል ይህን ጥያቄ ቅብጠት አድርጎ ሲወርፋቸው በሬዲዮ ሰማሁ፡፡
በሰይፉ ፕሮፍራም፡፡ ወቅቱ ኃይሌ ፕሬዝደንትነት ትልቅ ስልጣን መስሎት ‹‹ፕሬዝደንት›› ለመሆን የቋመጠበት ወቅት ነበር፡፡ መምህራን ደመወዝ ይጨመርልን ሲሉ መንግስት እንኳ እንዲህ የከፋ ዘለፋ አላወረደባቸውም፡፡
ያ ለመለስ ዜናዊ የተንሰቀሰቀው ኃይሌ፣ ለድሃ የሚራራ አንጀት የለውም፡፡ በዚህ ወቅት 15 ሚሊዮን ህዝብ ተራበ ቢባልም ‹‹ለምን ሰርተው አይበሉም!›› የሚል ይመስለኛል፡፡ እውነት ነው ኃይሌ የኢትዮጵያን ስም አስጠርቷል፡፡ በክፉ ቀን ስሟ ሲጠራ ግን መድረስ አይፈልግም፡፡ የእሱ ሜዳሊያ ሲያሸንፍ ለጨፈሩት፣ ሲሸነፍ ላለቀሱት አሁን ደግሞ ስቃይ ላይ ለሚገኙት ያመጣው ፋይዳው ያን ያህል ነው፡፡ በክፉ ቀን አለመድረሱ አንድ ነገር ሆኖ ቁስላቸው ላይ ጨው ለሚጨምርባቸው ደገሞ ሜዳሊያው ምንም ነው፡፡
እንደ ኢትዮጵያ ባለ በጭቆና ባለ ሀገር በተለይ ታዋቂ ሰዎች ልዩ ሚና ሊወጡ የግድ ነው፡፡ ለሚደግፋቸው ህዝብ የመኩላቸውን ሊወጡ ግዴታ አለባቸው፡፡ ያን ባያደርጉ እንኳ ዝምታ ከምንም ይሻላል፡፡ ከስርዓቱ ጋር ከቆሙ፣ ስርዓቱ በስንት ጊዜ አንዴ ‹‹ችግር›› ሲደርስበት እየተነፋረቁ እድሜ ልኩን እንዳይሰራ፣ ቢሰራም ለውጥ እንዳያመጣ በስርዓቶች የታሰረ ህዝብ ላይ ‹‹ለምን ሰርቶ አይበላም›› እያሉ ካላገጡ ክብርና ዝናቸውን መቀበል ይከብደኛል፡፡ ለእነ መለስ በአደባባይ እያለቀሰ፣ አደባባይ ላይ የወደቁትን አዛውንቶችና ህፃናት ‹‹ለምን አይሰሩም›› የሚለው ኃይሌም ለእኔ ክብሩን ንዷል፡፡ አሁን ድሮ በምናውቀው ሩጫው ሳይሆን የሥርዓቱ አሯሯጭም ሆኗል፡፡ ከስርዓቱ ጋር እየተሞዳሞዱ ባለሃብት በመሆን ከሆነ ህንዶችም፣ ቱርኮችም፣ ግብፆችም፣ ህወሓቶችም፣ ብአዴኖችም…..አሉ፡፡ በዚህ ኃይሌ የተለየ አይሆንም፡፡
በአጠቃላይ ኃይሌ ለህዝብ፣ ለክብሩ የሮጠ አይመስለኝም፡፡ እናም ጫማውን ቢሰቅል ባይሰቅል ጉዳዬ አይደለም፡፡ በሚቀጥለው አመት ተመልሻለሁ ብሎ ሪኮርድ ቢሰብር፣ ቢያሸንፍ፣ በታዕምር በ90፣ በ103…..አመቱ ቢሮጥ….ከማጨብጨቤ በፊት የሚታየኝ እሱ ለኢትዮጵያውያን ሳይሆን ለጨቋኝ ስርዓት አጨብጫቢ መሆኑ ነው፡፡ የሚታወሰኝ በህዝብ ላይ የሚቀልድ፣ ለስርዓቱ እንባ፣ ለህዝብ የአዞ እንባ እንዳለው ነው፡፡ እናም ኃይሌን፣ ለማስታወስ፣ ለማድነቅም……ኃይሉም ሞራሉም የለኝም፡፡
No comments:
Post a Comment