ይገረም አለሙ
ከአንድ ሳምንት ወሬ የማይዘለው የሞላ አስግዶም ኩብለላ ብዙ ነገሮችን አያሳየን ነው፡፡ ወያኔ የሞላ ኩብለላ የሱ የሥራ ውጤት እንደሆነ አሳያለሁ ብሎ “ በቅሎ ሽንቷን አጠራ ብላ ሀፍረቷን አሳየች” የሚባለውን አይነት ድርጊት ፈጸመ፡፡ ለነገሩ ወያኔ መቼ ሀፍረት ያውቅና፡፡ አቶ ሞላም የተሰጠው ስልጠና የአጭር ግዜ ሆኖበት ሽክ ብሎ የቀረበበትን ጋዜጣዊ መግለጫ የወያኔና የራሱ መጋለጫ አደረገው፡፡ የወያኔ የመረጃ ስራ በጉልበት አንጂ በእውቀት እንዳልሆነ የምናውቀውንም ይበልጥ አረጋገጠልን፡፡
የቱንም ያህል ቢጩኹ፤የቻሉትን ያህልም ውሸት ቢደራርቱ እውነትን ማሸነፍ እንደማይቻል ወያኔዎች ብዙ ግዜ ሞከራው ከሽፎባቸው ያዩት ቢሆንም አንዴውኑ ከእውነት ጋር ተጣልተዋልና የህይወት መሰሶአቸውም ውሸት ሆኖአልና ከውሸት ሊላቀቁ አልቻሉም፡፡ ዛሬም እየዋሹ ብዙሀኑን ኢትዮጵያዊ በግድ ሊግትቱ ይዳዳቸዋል፡፡ ጥቂት አይናቸውን ለጆሮአቸው ያስገዙ ሰዎቻቸው ደግሞ እንዴት ብሎ መጠየቅ ለምን ብሎ ማመዛዘን የለም ብቻ ውሸቱን እየተቀበሉ ከበሮ ይደልቃሉ፡፡እውነቱ ሲጋለጥም ሌላ ውሸት ይፈበርካሉ እንጂ ለእውነት እጅ አይሰጡም፡፡
አቶ ሞላ በመግለጫው ትህዴን በርካታ የታጠቀ ሰራዊት ቢኖረውም ከመንግሥት ጋር ባለኝ ግንኙነት የሊቀመንበርነቴን ሥልጣን ተጠቅሜ ለአስር አመታት ምንም ጥቃት አንዳይፈጽምና ጉዳት እንዳያደርስ ለማድረግ የቻልኩበት ሁኔታ ነው የነበረው፡፡ ከዚህ በኋላ ግን ይህን ማድረግ የማልችልበት ሁኔታ ክፍተት እየታየኝ ስለመጣ የጥፋት ተባባሪ ላለመሆን ስል በርካታ ታጋዮችን በመያዝ እጅ ሰጥቻለሁ ቢል በመጠኑም ቢሆን የተሻለ ይሆን ነበር፡፡ ብዙ ከመቀባጠርም ያድነው ነበር፡፡ ሰልጣኙም አሰልጣኙም መሰረታቸው ውሸት ሆነና በጽሁፍ የሰጡትም ሆነ በቃል የተናገሩት መግለጫ ሀራምባና ቆቦ የረገጠ ሆነና የታሰበለትን ዓላማ ማሳካቱ ቀርቶ እነርሱኑ ያጋለጠ ሆነ፡፡ በዚህ ዙሪያ ከተለያየ አቅጣጫ የተጻፈ ስለሆነ እኔ አልደግመውም፡፡
የሞላ ኩብለላና መቀላመድ ድርጅቶች እድሜ ከመቁጠር ውጪ የተግባር እንቅስቃሴ የማይታይባቸው፣ ተባብሮ መስራትም የማይሆንላቸው ለምን እንደሆነ ቀድሞ የሚታወቀውንና በተለያየ ግዜና መንገድ የተገለጸውን አንዱን ምክንያት አረጋግጦልናል፡፡ ትህዴን በሰራዊት ብዛትና በመሳሪያ አይነት የተጠናከረ መሆኑ አነጋጋሪ አይደለም፡፡ እንዲህ አቅም እያለው ተግባራዊ እንቅስቃሴው አለመታየቱ የዘመቻ ወሎው አለመሰማቱ ግን አነጋጋሪ ብቻ ሳይሆን አጠያቂም ነበር፤ እነሆ ዛሬ ግን ምላሽ አገኘ፡፡
እያንዳንዱ እንቅስቃሴ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊም ሆነ ወታደራዊ በተፈጥሮ የተሰጡ፣ በእውቀትና ልምድ የካበቱ፣ ለሚሰሩት ስራ እምነትና ጽናት ያላቸውንና ከራስ በላይ የሚያስቡ መሪዎችን ይሻል፡፡ ያ ሳይሆን ሲቀር ውጤቱ ኪሳራ ነው፡፡ ብዙዎቹ ድርጅቶች ዕድሜ አንጂ ውጤት የማይታይባቸው እንዲህ ትግሉና መሪው ታጋዩና አታጋዩ አልገጥም ብለው ነው፡፡ ከሰሞኑ “ማጋላጫ” እንደተረዳነው ሞላ አስር አመት ኤርትሪያ የኖረው በድርጅት ስም እያውደለደለ እንጂ እየታገለ እንዳልሆነ ነው፡፡
ሞላ ለወያኔ ፕሮፓጋንዳ እሰራ ብሎ (ታዞ) በማውደልደል እንደኖረ ሀፍረቱን ኩራት አድርጎ ነገረን፡፡ የነገረን ሁሉ የተሟላላት ከሆነ ይህ ሰው ምን ፍለጋ ይታገላል፡ እንደውም ድርጅቱ በተቋቋመበት አላማ መሰረት ይንቀሳቀስ በቂ ሰራዊት አስተማማኝ መሳሪያ ይዘን ጠመንጃ ታቅፎ መቀመጡ በዛ ታጋዩም እየተሰላቸ ነው የሚል ጥያቄ የሚያነሱ ቢገኙ በተለያየ ዘዴና መንገድ ጸጥ ያሰኛል አንጂ የሰራዊቱን ተነሳሽነት አይቶ ጥያቄአቸውንም ተቀብሎ ዘመቻ ሊያስብ አይችልም፡፡ ጥምረቱን በመቃወምም ለግል ድሎት እንጂ ለሀገር ነጻነት የተሰለፈ አለመሆኑን አረጋግጧል፡፡
አሁን ሁኔታው ተለወጠ በአንድ በኩል የተግባር እንቅስቃሴ ተጀመረ፡፡ ከዚሁ ተያይዞ ከሌሎች ጋር በጥምረት መሰራት መጣ፤ ሞላ ይህን ሁሉ አስቀርቶ እየታገለ ሳይሆን እያውደለደለ መኖሩን ለማስቀጠል የተቻለውን ሁሉ ጣረ ተጣጣረ አልተሳካለትም፡፡ አልሆንልህ አለኝ ብሎ የተሰጠውን ተቀብሎ አንዳይቀጥል ሰግሞ ምክትሉ እንደነገሩን በአመራር ድክመት ተገምግሞ፣ አብሮ መስራት ባለመፈለግ ተኮንኖ፣ ድርጅቱን አስር ኣመታት ያለውጤት በማኖሩ ተወንጅሎ ከመሪነቱ ሊነሳ እንደሆነ ተረዳ፡፡ ልብ በሉ ከመሪነት መነሳቱ ተራ ሥልጣን ብቻ አይደለም የሚያሳጣው፡፡ ቤቱ መኪናው መንደላቀቁ ወዘተ ሁሉ ነው አብሮ የሚቀረው፡፡ ከከተማ ከተማ እየዞረ ምግብና መጠጥ ሌላ ሌላውንም ያማርጥ የነበረ ሞላ ጠመንጃ አንግቦ ከታጋዮች ጋር ሊውል ሊያድር ! አረ ምን ሲደረግ፤መኮብለል እያለ፡፡
አመታት ያስቆጠሩ በሀገር ቤትም በውጪም የሚኖሩ፤ ሰላማዊም ይሁን የጠብ መንጃ ትግል ነው የምናካሂደው የሚሉና አንዳችም ውጤት ያላሳዩ ድርጅቶች ቢፈተሹ ችግራቸው ተመሳሳይ ነው፡፡ መሪዎቹ ያጡትም የጎደለባቸውም ነገር የለም፤ ምኒልክ ቤተ መንግሥትን እያለሙ የተቀዋሚ መሪ ተብሎ መኖር በቂያቸው ነው፡፡ እናም ትግሉ የሚጠይቀውን አመራር በመስጠት ወደ ድል ለማቅናት ትግል ይጠይቃል መስዋእትነት ያስከፍላል፡፡ ይህን በማድረግ ሰላማዊዎቹ አባሎቻቸው ባለጠመንጃዎቹ ታጋዮቻቸው የሚከፍሉትን መስዋዕትነት ወደ ራሳቸው ለምን ያመጣሉ በፕሮፓጋንዳ ተኮፍሰው በተግባር ኮስሰው በድሎት መኖር እያለ፡፡ ከሌሎች ጋር ተባብረው መስዋዕትነቱን ተጋርተው ትግሉን አጠንክረው ለማስኬድ ደግሞ የፓርቲ መሪ መባሉን የሳጣናል ብለው ይሰጋሉ፡፡ የቤተ መንግስቱ ቢቀር የፓርቲ መሪነቱን እንዴት ይጡ!
በየፓርቲዎቹ ያሉ አባላትና ታጋዮች መሪዎቻቸውን የመጠየቅ ነጻነት አለፍ ሲልም የማስገደድ መብት ኖሮአቸው እንደ ሞላ እጃቸውን እየተጠመዘዙ ድርጅቶቻቸው ከሌሎች ጋር ትብብር ቢፈራረሙ ወይንም ወደ ተግባር አንቅስቃሴ ቢገቡ ወደ ወያኔ ባይኮበልሉም ሲታገሉና ሲያታግሉ ሳይሆን ሲያውደለድሉ የኖሩበትን ድርጅት ጥለው የሚሄዱ አለያም ተገንጥለው ሌላ መታገያ ሳይሆን መኖሪያ ድርጅት እንደሚፈጥሩ በተደጋጋሚ አይተናል፡፡በውጪም በውስጥም ያሉ ፓርቲዎች ቁትራቸው እንዲህ የበዛበት አንዱና ዋናው ምክንያት ይህ ነው፡፡ ድርጅት ህይወታቸው፤ ስመ ትግል መኖሪያቸው ከሆነ ለምን ብለው ወደ ተጨባጭ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ይገባሉ፤ ለምንስ ብለው የድርጅታቸውን ህልውና የሚያከትምና የእነርሱንም መሪነት ሊያሳጣ የሚችል ትብብርና ውህደት ይቀበላሉ፡፡
ወያኔዎችም ሥልጣን ወይንም ሞት ያሉት እንዲሁ ሆኖባቸው ነው፡፡ ሁሉንም ነገር ያገኙት ሥልጣንን መሳሪያ በማድረግ ነውና ሥልጣናቸውን ባጡ ማግሥት ሁሉንም ነገር የሚያጡ መስሎ ይሰማቸዋል፡፡ የትም በማንምና በምንም ሁኔታ የሚደረግ አንቅስቃሴም ሆነ የሚጻፍና የሚነገር ከሥልጣናቸው የሚያስነሳቸው እየመሰለቸው ነው በጥፋት ላይ ጥፋት በክፋት ላይ ክፋት እየፈጸሙ ከሰዋዊ አስተሳሰብ የወጡት፡፡ ነገርን ነገር ያነሳዋል እንዲሉ ወያኔዎች ከግንባርነት ወደ አንድ ፓርቲነት ለመሸጋገር ዝግጅታቸውን አጠናቀው አንደነበር አቶ መለስ ሳይቀሩ በ1990ዎቹ አጋማሽ ላይ ነግረውን ነበር፡፡ የውሀ ሽታ ሆኖ የቀረበት ምክንያት ምን ይሆን? እነርሱም የየፓርቲ ሊቀመንበር መባሉ እንዳይቀርባቸው ብለው ይሆን! ወይንስ ጠቅላዩ ህወኃት አናሳ መሆኑን ተገንዝቦ ውህደት ቢፈጠር እዋጣላሁ ብሎ ፈራ?
“ሰይጣን ለተንኮሉ ከመጽኃፍ ቅዱስ ይጠቅሳል” እንደሚባለው የሚመሩት ድርጅት ስም ይዞ ከመቀመጥ ወጥቶ ተግባራዊ እንቅስቃሴ አንዳያደርግም ከሌሎች ጋር ተባብሮ እንዳይሰራም የሚፈልጉ የድርጅት መሪዎች ወያኔን ስለማስወገድ፤ ትግሉን ስለማጠናከር፣ ስለመተባበር አስፈላጊነት አልፎም ስለ ውህደት ለማውራት የሚያህላቸው የለም፡፡ እወነተኛ ማንነታቸው የሚጋለጥበት አጋጣሚ እስኪፈጠር ያለነሱ ታጋይ እየተባሉ ውደሳውም ልገሳውም ይጎርፍላቸዋል፡፡
በተለይ በተቃውሞው ጎራ የምንገኝ የሞላን ኩብለላ አስመልክቶ ወያኔ በትግረኛ ሲጨፍር ቅኝቱንም ሆነ ግጥሙን ሳይረዱ ቡጊ ቡጊ ለሚደንሱ ወገኖች በሁኔታቸው እያዘንን በድርጊታቸው እያፈርን መተው እንጂ እሰጥ አገባ መግጠሙ አንካ ሰላንትያ መያያዙ አስፈላጊ አይሆንም፡፡ የሚበጀው ኩብለላው የጥምረቱ ውጤት መሆኑን በማየትና ከዚህ በመማር ሌሎች ተባብረው ለመስራት ፈቃደኛ ያልሆኑበትንና የሚፈለገው የተቃውሞ ጎራ ጥንካሬ እንዳይመጣ ምክንያት የሆኑትን ጉዳዮች መመርመርና መፍትሄ መሻት ላይ ማተኮር ነው፡፡የምንደግፋቸውን ድርጅቶች ዝም ብለን በስሜት ከማድነቅ ወጣ ብለን ምን ሰሩ ምን እየሰሩ ነው ምን ለመስራ እየተዘጋጁ ነው ብለን እንይ፤የሚታይ ነገር ከሌለ ደግሞ ልን ብለን እንጠይቅ፤ በግል ጠንክሮ ላለመታሉም ሆነ ከሌሎች ጋር ህብረትና ውህደት ላለመፍጠሩ ዋናው ችግር ድርጅቶች የአንድ ወይንም የሁለትና ሶስት ሰዎች የግል ንብረት መሆናቸው ነውና ከዚህ ለማላቀቅ እንጣር፡፡ትህዴን የሊቀመንበሩን ጥምረቱን አለመፈለግ በድምጽ ብልጫ ውድቅ ሲያደርግ በግለሰብ ተጠርንፎ ከመኖር ራሱን ነጻ ማድረጉን አሳይቷል፡፡ ሌሎችም እንደዚሁ ለቆሙለት ዓላማ እንጂ ለመሪ ግለሰቦች ፍላጎት የማይገዙ መሆናቸውን የሚያሳዩበት፣ ድርጅቱ ማለት መሪው መሪው ማለት ድርጅቱ ከነበረበት ሁኔታ የሚላቀቁበትን ዘዴ ብንዘይድ ነው የሚጠቅመው፡፡
ከላይ ለማሳየት እንደሞከርኩት የሚታገሉ ሳይሆኑ እንደ ሞላ እያውደለሰሉ አመታት የቆጠሩ መሪዎች እዛም እዚህም ነበሩ፡፡ ዛሬም የድርጅት መሪ መባል እንጂ ትግሉንም ድርጅቱንም የማያወቁ ግን በስሙ ኑሮአቸውን አደላድለው የሚኖሩ የድርጅት መሪዎች ይኖራሉ፡፡ እነዚህ በምንም ተአምር ትግሉን ሊያንቀሳቅሱም ሆነ ከሌሎች ጋር ተባብረው ሊሰሩ አይችሉም፡፡ ሌሎች የተግባር እንቅስቃሴ ሲጀምሩም እንቅፋት ከመሆን አይመለሱም፡፡ ስለሆነም በርግጥ ድርጅቶቹ የተቋቋሙትና የሚፈለጉት ለትግል ከሆነ ከግለሰብ ንብረትነት እንዲላቀቁና በተናጠል የተግባር ድርጅት እንዲሆኑ ከሌሎችም ጋር ተባብረው እንዲሰሩ አባሉም ደጋፊውም ጥረት ማድረግ አለበት፡፡ ውግዘትና ጩኸት ወያኔን እያለመለመው ለመቶ በመቶ አሸናፊነት አደረሰው አንጂ ለውጥ አንደማይመጣ ከበቂ በላይ የተረጋገጠ ይመስለኛል፡፡ ስለሆነም ድጋፋችን ድርጅትን እንጂ ግለሰብን አይሁን፣ ርዳታችን በተግባር እየመዘንን አንጂ በምላስ እየተታለልን አይሁን፡፡
ከላይ ለማሳየት እንደሞከርኩት የሚታገሉ ሳይሆኑ እንደ ሞላ እያውደለሰሉ አመታት የቆጠሩ መሪዎች እዛም እዚህም ነበሩ፡፡ ዛሬም የድርጅት መሪ መባል እንጂ ትግሉንም ድርጅቱንም የማያወቁ ግን በስሙ ኑሮአቸውን አደላድለው የሚኖሩ የድርጅት መሪዎች ይኖራሉ፡፡ እነዚህ በምንም ተአምር ትግሉን ሊያንቀሳቅሱም ሆነ ከሌሎች ጋር ተባብረው ሊሰሩ አይችሉም፡፡ ሌሎች የተግባር እንቅስቃሴ ሲጀምሩም እንቅፋት ከመሆን አይመለሱም፡፡ ስለሆነም በርግጥ ድርጅቶቹ የተቋቋሙትና የሚፈለጉት ለትግል ከሆነ ከግለሰብ ንብረትነት እንዲላቀቁና በተናጠል የተግባር ድርጅት እንዲሆኑ ከሌሎችም ጋር ተባብረው እንዲሰሩ አባሉም ደጋፊውም ጥረት ማድረግ አለበት፡፡ ውግዘትና ጩኸት ወያኔን እያለመለመው ለመቶ በመቶ አሸናፊነት አደረሰው አንጂ ለውጥ አንደማይመጣ ከበቂ በላይ የተረጋገጠ ይመስለኛል፡፡ ስለሆነም ድጋፋችን ድርጅትን እንጂ ግለሰብን አይሁን፣ ርዳታችን በተግባር እየመዘንን አንጂ በምላስ እየተታለልን አይሁን፡፡
ከሞላ ኩብለላ ያታየው ሌላው ነገር ወያኔ በቀደደው የዘር ቦይ የሚፈሱ ወገኖች ጉዳዮን የጎሳ ካባ አልብሰው ድሮም ሞላዎች ሲሉና ከትህዴን ጋር መጣመርን ሲኮንኑ መሰማታቸው ነው፡፡ የሚገርመው ይህን የሚሉት ብዙዎቹ እነርሱ እንደግፋቸዋልን የሚሉት ፖለቲከኞች ርስ በርስ መተማመንና መስማማት ተስኖአቸው በአንድ ስም አምስትና ስድስት ድርጅት የሚመሩ መሆናቸው ነው፡፡ ከስሜት ይልቅ እውነት ሚዛን ቢደፋ፤ እንዲህ ባላተባለ ነበር፡፡ ሌላውን ከመኮነን በፊት ራስን ማየት ጥሩ ነው፡፡ ራሳቸው መተማመን አጥተው በአንድ ስም አምስትና ስድስት ሆነው ተለያይተው እየተናቆሩ ሌላውን የማይታመን ማለት አንዴት ይቻላል? አረ ጎበዝ ስራችንም ሆነ ንግግራችን ብሎም ጽሁፋችን እየተስተዋለ ይሁን፡፡ እነዚህ ወገኖች ነገሮችን ሁሉ በጎሳ መነጽር መመልከት እንደማይበጅ ተገንዝበው ሰከን ብለው ቢያስቡ መልካም ነው፡፡ ወያኔ ነገሮች ሁሉ የጎሳ መልክ እንዲይዙለት መፈለጉና መስራቱ በኢትዮጵያዊነት አስተሳሰብ ስር ዓላማውን ማሳካት እንደማይችል ስለሚያውቅ፣ አንድነት ከጠነከረ በሥልጣኑ እንደማይሰነብት ስለገባው ነው፡፡ ወያኔን የሚያወግዙ የሚኮንኑ በዚሁ በወያኔ መንገድ መሄዳቸው ግን ለምን ይሆን፡፡ ሞላን መሰል ሰዎች ከየድርጅቶቹ ቢነቀሉ አይደለም ትብብር ውህደት በወራት ውይይት ተግባራዊ ይሆናል፡፡ እናም አባልም ደጋፊም የሆንባቸው ድርጅቶች እንዲጠሩ እንስራ፡፡ ብሽሽቁና አንካ ሰላንቲያው የአንድ ሳምት ጉንጭ ከማልፋት በቀር ጥቅም የለውም፣አጋጣሚዎችን ሁሉ ለበጎ ስራ አንጠቀምባቸው ፣ በቸር ያሰንብተን ፤ፍቅር ይስጠን ልቦና ያድለን፣ለስሜት ሳይሆን ለእውነት ለመቆም ያብቃን፣አሜን!
No comments:
Post a Comment