አንዳንዴ ምን ይገርመኛል መሰላችሁ እኛ ኢትዮጲያዊያን ነገሮችን ሞቅ በማድረግና ወዲያው እርግፍ አድርጎ በመተው (በመርሳት) በሽታ የተለከፍን ይመስለኛል ….ለዛም ነው ታሪካችን በእንጥልጥል ፣ እውቀታችን በእንጥልጥል ፣ ስልጣኒያችን በእንጥልጥል ፣ፍቅራችን በእንጥልጥል ሁሉም ነገራችን በእንጥልጥል የሚቀረው !! …እንደኔ እንደኔ የፕሮፌሰር መስፍን የ‹‹መክሸፍ›› ቲዎሪ ከመክሸፍ ይልቅ ‹‹ተንጠልጥሎ መቅረት›› የሚለው ቃል በትክክል የሚገልፀው ይመስለኛል …መክሸፍ የተጀመረ ነገር ዳግም ላይመለስ ላያንሰራራ እንደገናም ከቆመበት ላይቀጥል መበላሸት መጨናገፍ መቆም ነው ትርጓሜው …እንደውም መክሸፍ እረፍት ነው !! በቃ አንድ ነገር ላይመለስ መኮላሸቱን አውቆ ከ ሀ ለመጀመር ሳያበረታታ አይቀርም ! ለመክሸፍማ አልታደልንም!
የእኛ ችግር ሳይከሽፍም ሳይቀጥልም የሆነ ቦታ ላይ ተንጠልጥሎ መቅረት ነው … ለምሳሌ በጣም ከቀላሎቹ ብንነሳ …. ዘመናዊ ትምህርት አልከሸፈም አልቀጠለም አንዴ በጥራት ሌላ ጊዜ በብዛት እያሳበበ ተንጠልጥሎ በእንጥልጥል የቀረ እውቀት የሞላቸው ‹ሙሁራንን› እያመረተ አለ ! ኪነጥበብ …. የተጀመረበት ዘመንና ዛሬ ያለበትን ስንመለከት አልከሸፈም አልቀጠለም …እንደተሰቀለ ፊኛ ራሱን በሚያምር ቀለምና በባዶ አየር ወጥሮና አሳምሮ በእንጥልጥል ወደነፈሰበት እየተገፋ ይወዛወዛል ….ዲሞክራሲ አልከሸፈም አልቀጠለም ምርጫ ሲቀርብ ጠጠር ሲያልፍ ላላ እያለ በእንጥልጥል እንደገዥው ባህሪና ጡንቻ እየተወዛወዘ በእንጥልጥል አለ …ባቡሩ ….የንፋስ ሃይል ማመንጫው ….ሌላው ይቅርና የድንበራችን ጉዳይ እንኳን ከኤርትራ ጋር ‹በእንጥልጥል› ነው ያለው በማንኛውም ጊዜ ግጭት ሊነሳ ይችላል…ሰላማችንም እንጥልጥል ….ሱዳንም ጋር ቢሆን ጥርት ያለ የድንበር ክልል የሌለባቸው አካባቢዎች አሉ …. ((ህዝብ አስፈቅደን ኤርትራን መውጋቱ(ሂሂ)))… በቀን ሶስት ጊዜ የመብላት ተስፋችን …..ፍትሁ ቀጠሮ ቀጠሮ እንጥልጥል….ሰው ሲፈታ እንኳን ነፃነቱ በእንጥልጥል ነው ለምን ተፈታ ለምን ታሰረም ይሄ ነው የሚባል አጥጋቢ ምክንያት አይሰጥም !!ይሄ ሁሉ ተንጠልጥሎ የቀረ ነው ጎበዝ ….
ወሬ ….ወሬ ራሱ ኢትዮጲያ ውስጥ አይከሽፍም አይቀጥልም ….አንድ ሰሞን ሞቅ ይልና …ባለበት ተንጠልጥሎ ይቀራል …ለምሳሌ አንዱን ወዳጃችሁን ‹‹ባለፈው እንደዛ መፅሄቱ ጋዜጣው ሲያወራለት የነበረው ጉዳይ እምን ደረሰ ›› ብትሉት በእርግጠኝነት ‹‹በዚህ በዚህ ምክንያት እንደዚህ ተብሎ አልቋል›› አይላችሁም …ወይም ‹‹እሱማ እንደዚህ ተስተካክሎ እንደዛ ቀጠለ›› አይልም ….‹‹እንጃ ምን እንደደረሰ›› ብሏችሁ በእንጥልጥል አእምሮው ውስጥ የቀረውን ወሬ በእንጥልጥል ምላሹ ይገፋላችኋል ! አሁንም ካሉበት ማስቀጠል የምንችላቸው …..ሳይከሽፉም ሳይቀጥሉም በእንጥልጥል የቀሩ ሃሳቦች ድርጊቶች ወሬዎች በጣም ብዙ ናቸው !! እኔ የምላችሁ እስቲ ሁለት አእምሮየ ውስጥ ተንጠልጥለው የቀሩ በዛ ሰሞን የሰማኋቸውን ወሬወች ምን እንደደረሱ ልጠይቃችሁ …በቂ ምላሽ ካላችሁ ስጡኝ …ከሌለ ለምን ነገሮችን እስከመጨረሻው ተከታትለን ሙሉ መረጃ የማግነት መብታችንን አሳልፈን እንደሰጠን ራሳችንን እንጠይቅ !!
የመጀመሪያው ….በዛ ሰሞን አንድ ቤተክርስቲያን ውስጥ መስቀል ከሰማይ እንደወረደ ሰምተን ነበር …በመሃል ነገሩ ተድበስብሶ ቀረ …ለመሆኑ በትክክል የመስቀሉ ጉዳይ ከምን ደረሰ …መቸም መስቀሉ የመላው ህዝበ ክርስቲያን ነው! እንደተባለው ከሰማይ መስቀሉ ወርዶ ከሆነ ለበረከትና ፈውስ ነውና ይህን መብት አማኙ መከልከል የለበትም …እህ ምን ደረሰ ?እርግጠኛ መልስ ያለው ብቻ ይመልስልኝ ይሄ ጉዳይ በእንጥልጥል ያለ ነውና ….
ሁለተኛው የሃና ኦላንጎ ጉዳይ የዛች አንድ ፍሬ መቀጨት …አንገብግቦን ከዳር እስከዳር ተነስተን አቧረውን ስናጨሰው ከረምን … ወር አልሞላውም ጭጭ ! ውሳኔው ከምን ደረሰ … በእርግጥ ፍርዱ በቂ ነው ወይ…ሌሎች እህቶቻችን ላይ ይህና የባሰም ጉዳይ እንዳይፈፀም ምን ማስተካከያ እርምጃ ተወሰደ …የሴቶችእና ህፃናት ምንትስ ቅብርጥስ ሚኒስትር ምን ሰራ እንደው ሌላው ቢቀር ጥናት ቢጤ …
ሶስተኛው ውጭ ጉዳይ ሚንስትራችን ወደአምስት ሚሊየን ደላር ይዛ ስለተከሰተች አንድ ፍሬ ልጅ ነግረውን (ከነስሟ ብሪቱ …ስምን በልዓክ ያወጣዋል ሂሂ ) በትውልድ መንደሯ ትምህርት ቤት እንዲገነባ ያንን ሁሉ ብር ለመንግስት ‹‹ጀባ›› እንዳለች ገልፀው አስደምመውን ነበር …ብሩን አወስትራሊያ ይሁን የት ብቻ በሽልማት አግኝታ ነው ብለውን ሸለመ የተባለው ድርጅት ‹‹አይ ዶክተር ይሄን ያህል ብር እኛንም የሚሸልመን ባገኘን›› ብሎ ፈገግ አስብሎናል …እሽ የብሩ ምንጭ ጉዳይ ‹‹በእንጥልጥል›› ይቆየንና ..ዶክተርየ ትምህርት ቤቱ ግንባታ ከምን ደረሰ??
ልቀጥል ? ተውት! አሁን ወደስራ እየገባሁ ነው …..ከትላንት ‹‹በእንጥልጥል ያደረ›› ብዙ ስራ አለብኝ፡)እስቲ መልካም ቀን ወርቆቸ …ዛሬ እንኳን ለመጭው አዲስ ዓመት የተንጠለጠለ ጉዳይ ይዘን እንዳንሻገር እጃችን ላይ ያለችውን እንፈጣጥማት !
No comments:
Post a Comment