ከቢላል አበጋዝ – ዋሽግቶን ዲሲ
ዛሬ ካለንበት ተነስተን ስናስብ ወያኔ ህወሃት ጋር ያለን ጠብ ሳይሆን ከወያኔ በኋላ በምን ሁኔታ የምትኖር አገርን እንሻለን የሚለው ጥያቄ ግዝፈት አለው።በኢትዮጵያም በኤርትራም ያለው ህዝብ ከወያኔም፤ከሻቢያም በላይ ነው።ያአንድ አገር እድል ከፖለቲካ ድርጅቶች ፤ከመሪዎችም በላይ ነው።የአካባቢውን ህዝቦች እጣ ፈንታ ስናስብ በወሰን ተገድበን እንዳይሆን ጥንታዊና በዙ መእዘን ያለው ትስስራችን አስበን ከስሜተኝነት ርቀን እንደ ችግር ፈችዎች እንድናስብ የግድ ይለናል። የኢትዮጵያና ኤርትራ ጉዳይ እንድንወያይበት በሚል ይህ ጽሁፍ ቀርቧል።
ችግርን ለመረዳትና ለመፍታት በተለያዩ አቅጣጫዎች ማውጣት ማውረድ አለ።ከውሳኔ በፊት ሁሉንም ማእዘናት ማየት ተገቢ ነው። ይህም በጣም የሚበጅ መንገድ ነው።ባለንበት ሁኔታ ደግሞ እጅግ ወሳኝ ነው።እንዲህ ያለው አቀራረብ ለግትርነት ቦታ አይሰጥም።ውሳኔ ጋ ሲደረስ ደግሞ የሚወሰነው ጉዳይ ምክንያትን የተመረኮዘ እንዲሆን ማረጋገጫ ይሰጣል።እዲህ መምከር ደግሞ ጥንቱንም ያገራችን ብልህ ሰዎች ዘዴ ነው።ከራሳቸው ለየት አድርጎ የሚያስበውን ይሰሙታል።
አያጥላሉትም።”እሱ የመከረውን ጨምረን ሳንሰማ” ይላሉ፤ ሁሉን ከየመዓዘኑ ለመስማት ማለት ነው።ለየት ባለመንገድ ማሰብ ክፉ አይደለም።በእግሊዝኛ “ከሳጥኑ ውጭ ማሰብ” ይሉታል።(Thinking outside the box) ከግርግሙ ወጣ ብሎ ማየት።ከተለመደው መንገድ በድፍረት ወጣ ብሎ ለመተንተን፤ለማሰብ መሞከር ለማለት ነው።ይህንን እንሞክረው ካልን ብዙ ጉዳዮችን ማንሳት እንችላለን።አንዱ የአገሮች ጉርብትና ይሁን:ሌላው ደግሞ ብሄር ብሄረሰብ መገንጠል።ክልል እያልን አርባ ዓመታት የተወዛገብንበት አቢይ ናቸው።የአገሮች ጉርብትና ላይ ብቻ አተኩረን እንቀጥል።
ማንም አገር ከጎረቤቱ በሰላም ቢኖር ለራሱም ለጎረቤቱም መልካም ነው።ጎረቤት አገራት በሰላም በጉርብትና የሚኖሩ ከሆነ የምጣኔ ሃብትን እድገት ጎዳና ይያያዛሉ።ጠብ ተነስቶ የጥይት ውርጅብኝ መለዋወጣቸው የማንኛውንም ወገን ህዝብ የኑሮ ሁኔታ አያሻሽልም።ሁሉም የወሰኑን ጉዳይ፤ ሌላም ብሄራዊ ጥቅሙን ይርሳ ሳይሆን ተከባብሮ፤በሰላም መኖር ላይ ማተኮር የሚበጅ ነው ለማለት ነው።ኢትዮጵያ ብዙ ጎረቤቶች አሏት።ሶማሊያ አንድዋ ናት።ሶማሊያ ሰላም ያጣች አገር ናት።ጦሷ ለኢትዮጵያ የተረፈ ነው።ቀደም ብሎ በሁለቱ አገራት የሆነውን እናስታውሳለን።መጨረሻው የሶማሊያ መፍረስ ሆነ።ለኢትዮጵያ ደግሞ ችግር እንደሆነች መቅረትዋን ይሄው ዛሬ እናያለን።የሶማልያ ሰላም ማግኘት ለኢትዮጵያ ይጠቅማል።ከጦርነቱ የንግድ ልውውጡ ለሁለቱም አልሚ ነው። ስለዚህ የኢትዮጵያ ጥረት ሶማልያ ወደ ሰላምና መረጋጋት እንድታመራ መሆን አለበት።ወያኔ ህወሃት በዚህ ጉዳይ ከውድቀት ወደ ሌላ ውድቀት ሲሄድ እናየዋለን።ህወሃት ለሶማሊያ ሰላም አወንታዊ ሀይል አይደለም።ሶማልያ ካሉ ሀይሎች የአየለው ከዚው መውጣት አለበት።በውጭ ሀይላት የሚዘወር ከሆነ ለሰላም የተዘጋጀ አይሆንም።ባጭሩ የሶማሊያን ችግር ለሱማሌዎች መተው።ኢትዮጵያ ድንበር ጠረፏን ማስከበር።ወያኔ ህወሃት ይህን አድርጎ አያውቅም። በኢትዮጵያውያን ወታደሮች ላይ የደረሰው ከፍ ያለ በደል ሊሰማ ጊዜው እየጠበቀ ነው።
ሱዳንም የኢትዮጵያ አጎራባች ናት።ቀድሞ አንድ አገር ነበረች። ዛሬ ሁለት ያልተረጋጉ አገራት በመሆን ተከፋፍላለች።ይህ ደግሞ ኢትዮጵያ ሁለት ሰሜንና በደቡብ ያሉ የራስ ምታቶች አሏት ማለት ነው።ከመከፋፈሉ ይልቅ የሰላም መደፍረሱ ለኢትዮጵያ አስከፊ ነው።ቢያስ ስደተኛ ማስተናገድ አለ።የንግድ ልውውጥም ቀረ ማለት ነው።ዛሬ ኢትዮጵያ በጥቅሟ የሚደራደር መንግስት ሰንጎ ይዟት ከአረቧ ሱዳን ጋር ወያኔ ከተሸኘ በኋላ ጠብ የሚያስነሳ ስራ በወያኔ ተሰርቷል። ይህ አይበጅም።ጠብ ለኋላ ማሳደር ነው።ስለዚህ ሱዳንና የኢትዮጵያ መካከል ወያኔ ፈንጂ ቀበረ ማለት ነው።
ኬንያ ሌላዋ የኢትዮጵያ ወሰንተኛ ናት።የረጅም ጊዜ የሰላም ግነኙነት በመኖሩ በጦርነት ኢትዮጵያና ኬንያ አልተጠመዱም።የሶማልያ ሰላም ማጣት የጋራ ችግራቸው ነው።ኬንያ የንግድ መነሃረያ ናት።እየለማች ነው።ሶማልያ ውስጥ ግን ያለው አለመረጋጋት፤መንግስት አልባነት ኬንያን አልበደለም ማን ይላል?ምዕራባውያን በአፍሪካ ቀንድ የሚተኩሩት ሽብርተኛ ሀይሎችን መዋጋት ላይ ነው።ሽብርተኛነት የዓለማችን ችግር ነው።ለማንም አገር ቢሆን አውዳሚ ሀይል ነው።ሽብርተኛነት እንዲያውም አንዱ አፍሪካን ቀስፎ የያዘ ችግር ነው።ይህንም ችግር ተቋቁመው፤ተረጋግተውም ብቻ ነው አገራት ስለዕድገት ማሰብ የሚችሉት።ይህ ደግሞ ምዕራባውያን የሚፈቱት ችግር ወይም እነሱ አዝማች የሚሆኑበት ሳይሆን አፍሪካውያን እራሳቸው ጥረው ግረው መፍታት ያለባቸው መሆን አለበት።ኬንያ እንደምን አድርጋ ራስዋን ለሽብርተኞች መመልመያ እንዳደረገች ማስተዋል አያቅትም።እስላም የሆኑትን ዜጎችዋን በጅምላ በመኮነን፤በማሰቃየት፤በመግደል ለአልሸባብ ሰራዊት መመልመያ ሆነች።ሁኔታው ከበረታ የልማትዋ ደንቃራ ይሆናል ማለት ነው።ወያኔ ህወሃት ኬንያ ደፍሯል።የችግር ጅማሮንም ታዝበናል።
ኤርትራ የኢትዮጵያ አካል የነበረች ዛሬ ደሞ ጎረቤት ናት። ከተበጠበጠች ኤርትራ ሰላም ያሰፈነባቱ ትመረጣለች። ጎን ለጎን ያሉ ቤቶች ለሳት አደጋ የሚጋለጡት በጋራ ነው። ለኤርትራም ሰላም ያላት የተረጋጋች ኢትዮጵያ ትሻላታለች። ሰላም ካለ ሁለቱም ጦር ከመስበቅ ይልቅ ወደልማት ያተኩራሉ። ይበለጽጋሉ።በመጨረሻ ኤርትራም ኢትዮጵያም ከጦርነት የሚያተርፉት የለም።መሳሪያው የገዙበትን ብድር ይዘው ይቀራሉ እንጂ።የኤርትራ መንግስት ኢትዮጵያን መበታተን አላማው መሆኑን በምክንያት ሳይደግፉ የሚያቀርቡ አሉ።ዛሬ ያለችው ኢትዮጵያ በሙስና ተቦርቡራ፤ተርባ፤ደካማ ሆና ትገኛለች።እነዚህ የህወሃት አፈቀላጤ ከትግራይ ብሄር ያልሆኑ ወያኔዎች ከወያኔ የበለጠ የጦርነት ከበሮ ደላቂዎች ናቸው።ለሁለቱም ለኤርትራም ለኢትዮጵያም ሰላም ላይ የተመረኮዘ ጉርብትና እንጂ ሌላ ምን ይበጃቸዋል? የህወሃት አፈቀላጤዎች የሚሉት “የባህር በር” ጥያቄ ላይ የመለሱ ህወሃት ምን ድርሻ ነበረው ?እዚህ ውዝግብ ውስጥ መግባት ሳይሆን ለመቶ ሚሊዮን ህዝብ ሰላም ማግኘት፤መብት መከበር፤በልቶ ማደር፤የዜግነት ክብር አሁን ምን ይደረግ ?ሀያ አራት ዓመታት የበደለው፤የቀማው፤የከፋፈለው ህዝብን ያዋረደው ህወሃት ይቀጥል አይቀጥል ነው ጥያቄው።ቅድሚያው ጥያቄ ይህ ነው።ድሮ ኢትዮጵያ ጠብ ቢኖራት ያው ከሶማሊያ ጋር ነበር በብዛት።ዛሬ ወያኔ አሁን ከተሰራችው ደቡብ ሱዳን ጉዳይ ጣልቃ ይገባል።ኬንያን ይደፍራል።ሶማሊያ ተቀርቅሯል።ኤርትራን ሳንቆጥር ዙሪያው በችግር አጥሯል ማለት ነው።
ለማንም አገር ቢሆን ሰላም ለዕድገት መራመድ ፋታ ይሰጣል። ቻይና ላለፉት አምሳ ዓመታት ሰላም ብታገኝ ይሄው ዛሬ ከዓለም ሁለተኛው የምጣኔ ሃብት አንቀሳቃሽ ሆናለች። ሰላም ፋታ ቢሰጣት ዕድገት ላይ አተኩራ ቆየች። በኢትዮጵያ ከኢጣልያ ወረራ በኌላ ቢያንስ ሰላሳ አምስት ዓመታት ትንሽ መተናፈሻ ተገኝቶ ትምርት፤እድገት፤የብልጽግናም መንገዱ ተይዞ ነበር።ከወያኔ በአንጻር ሲታይ የወታደራዊ ደርግ ብልጽግናን ያልተጻረረ ነበር ቢባል ስተት አይሆንም።ጭብጡን በአሃዞች ደግፈው የምጣኔ ሃብት ጠበብቶች አንድ ቀን ያወጡታል ብየ ተስፋ አደርጋለሁ።ወያኔ እዚህ ትንታኔ ውስት አይገባም።ምክንያቱም ትንታኔው የተመሰረተው ልማት እድገት ብሄራዊ ብልጽግና መመሪያ የደረጉ መንግስታትን ስለሚመለከት ነው።በሃያ ዓመታት ለወያኔ ኩራቱ በሙስና መክበር ነው።ብሄራዊ ልማትን አልነካውም።ስልክ፤ኤሌትሪክ ሀይል፤ውሃ፤የራብ መወገድ፤ስደት፤የረባ ትምህርት ነው።የሃያ ዓመታቱ ውጤት አሳፋሪና አስከፊ ነው።
እስቲ ዛሬ እንድፈርና ኤርትራና በኢትዮጵያ መካከል ሊሆን ስለሚችለው ሰላም እንነጋገር።ዛሬ ወያኔ ኢትዮጵያን ትልቅ እስር ቤት አድርጎ የሚገኝ መንግስት ነው።እንዲህም ለመቀጠል የጦርነት ከበሮ መምታትን ይመርጣል ወደ ሰላም ከማሰብ ይልቅ።ወያኔ በኢትዮጵያም በኤርትራም የበላይነትን ይመኛል።የሰላም ሀይል መግባባት ፈጣሪ ለሰላም ጥረት አድራጊ ቢሆን ኖሮ በሶማልያ፤በደቡብ ሱዳን ውጤት ባሳየ ነበር።ወያኔ ለኢትዮጵያም ለአፍሪካ ቀንድም ባዕድ ሀይል ነው።የዚህን አካባቢ ሰለም መረጋጋት መምጣት ጋር አይያያዝም።የራሱን ህልውና ከባዕዳን ፍላጎት ጋር ዘንቆ ህዝቡን ጠርጥሮ ለህልውናው ሁሌ ሰግቶ የሚኖር፤ በቋፍ ያለ፤ ገደል አፋፍ ላይ የቆመ መንግስት ነው።ላንዴም ቢሆን ላፍታው ከወያኔ የጦር ከበሮ ርቀን የኤርትራና የኢትዮጵያን በሰላም ተጎራብቶ መኖር፤ችግርን በጠረጴዛ ዙሪ መፍታትን እናስበው።ይህ ነው ከኤንቬሎፑ ውጭ ማሰብ።ደፈር ብሎ ወጣ ብሎ ማሰብ።እንቅፋት ሆኖ የሚገኝው ወያኔ ነው።ለህዝብ ተጠሪነት ሞቱ ነው።ከኤርትራ ጋር ግንኙነት ሲባል የሚታየው ተቃዋሚው ሀይል ነው።ተቃዋሚው ሀይል ደግሞ እራሱ ወያኔ ምርጫዎችን ሁሉ ወስዶ፤ ገፍቶ ያስወጣው ነው።ወያኔ ተቃዋሚውን ላጥፋ እንጂ ልደራደር የሚል ብልህ ሀይል አይደለም።ሁሉ በተንኮል ሁሉን በጉልበት እወጣዋለሁ የሚል ህልውናውን እንጂ ብሄራዊ ጥቅም የሚያስብ አይደለም።ባጭሩ ወያኔ ለጉርብትና ፈጽሞ የሚመች አይደለም።መልካም ግንኙነት አለኝ ቢል ዛሬ ከሰሜን ሱዳን ጋር ነው።አሳልፎ የሰጠው ሰጥቶ በዚያ ወሰን ተቃዋሚ እንዳይንቀሳቀስበት ድርድሩን አድርጎ ነው።
ኢትዮጵያና ኤርትራ ሁለቱም ኋላ ቀር ደሃ አገሮች ናቸው።ይህ አያከራክርም።ከዚህ ካሉበት ሁኔታ መውጫው ደግሞ ጦርነት ነው ማለት ከእብደት ብቻ የሚመነጭ አባባል ነው።ድህነትን ለማስወገድ ሰላም አግኝቶ ማምረትን ይጠይቃል ከላይ አንስተነዋል።በትላልቆቹ አገሮች እንየው።አማሪካና ኢራን ስምምነት ባይደርሱና ጦርነት ቢጀምሩ የሁለቱ አገራት የልማት እቅዶች ታጥፈው ጥረት ሁሉ ወደ ጦርነት ይሆናል።ሁለቱም ያጣሉ። አካባቢውም ዛሬ ካለው ሁኔታ ይብስበታል።የዓለምም ሰላም ከፍ ካለ ስጋት ይወድቃል።ሞት ስደት ይከተላል።ጦርነት መዘዙ አያሌ ነው።
ያለፉት ጥቂት ዓመታ የጦርነት አጥፊ ጎን ለማሳየት፤የአገር በሰላም መቆየት መበጀት አሳይተውናል።የአንድ ሊቢያ ሰላም ማጣት ራስዋን ሊቢያንና በታችዋ ያሉት አገራት እንዳናጋ አይተናል።የኢራቅን መፈራረስ ለዓመታት አይተናል።ሶርያ አሁን ከፊታችን እየነደደች፤እየፈረሰች ነው።እሷ ስትወድም ዜጎችዋ ወደ ስደት።የመን ደግሞ ባህር ይለየን እንጂ ታሪክ፤ባህልም፤ንግድም ያስተሳሰረን ነን።ሰላም ማጣት፤ጣልቃ የገባ ጠላት የመንን ምን እያደረጋት እንደሆን እያየን ነው።እንዲህ ወዳለች በጦርነት የደቀቀችን አገር ምርጫ አድርገው ወገኖቻችን ወደ የመን ይሄዳሉ።የኢትዮጵያ ሁኔታ ለመክፋቱ ማመሳከሪያ እንደተፈለገ ሁሉ።
ስለዚህ ወያኔና አፈቀላጤዎችን ትተን ለአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋትን የምንመኝ ሁሉ ደፈር ብለን ኢትዮጵያና ኤርትራ በሰላም ተጎራብተው ቢኖሩስ ብለን እፋስብ።ልብ እንበል ሁለት የነበሩ አገራት ያውም ሰው የሰራው ግንብ በመሃላቸው የነበረ ሁለት ጀርመኖች ዛሬ አንድ አገር ናቸው።አምሳ ዓመታት የተገለለችው ኩባ በምዕራቡ መታቀፍዋ ከኤንቬሎፑ ውጭ ለማሰብ የደፈሩ ሰዎች የስራ ውጤት ነው።ኩባና ምዕራቡም አቸናፊ የሚሆኑበት የድርድር ውጤት ማለት ነው። እኛም ደፈር ብለን እናስብ የወያኔ አሽቃባጮችን ንቀን።
ለክርስቲያን ወገኖቸ መልካም በዓል !
አነድነት ሀይል ነው!
ድል ለመብቱ ለነጻነቱ እየታገለ ላለው የኢትዮጵያ ህዝብ!
ኢትዮጵያ በህዝቦችዋ አንድነትና ፍቅር ለዘለዓለም በነጻነት ትኑር!
No comments:
Post a Comment