Tuesday, September 29, 2015

በኢትዮጵያ ታሪክ ጉዳይ ላይ ኢሕአዴግን እንዴት ማመን ይቻላል?! በዲ/ን ኒቆዲሞስ

ወንድማችን ዲ/ን ዳንኤል የኢትዮጵያችን ልዩ ቅርስ በኾነው የዘመን አቆጣጠራችንን በተመለከተ አንድ ጥያቄ አንስቶአል፡፡ ይኸውም የኢትዮጵያን የዘመን አቆጣጠር በተመለከተ ‹‹ጠቅላይ ሚ/ሩን እንመን ወይስ አርቲስቶቻችንን?!›› የሚል ጥያቄ አንስቶ አንድ ትዝብትና ማሳሰቢያ አከል ጽሑፍ አስነብቦናል፡፡ እኔ ግን እንዲህ እላለሁ በኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠርም ሆነ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ታሪክ ጉዳይ ላይ ኢሕዴግን/ክቡር ጠቅላይ ሚ/ሩን እንዳናምናቸው የሚያደርጉን አንዳንድ የታሪክ ሐቆች እንዳሉ ላንሣ፡፡
እስቲ እነዚህን ሐቆች በጥቂቱ ብቻ ለማየት እንሞከር፡፡ በመሠረቱ የአገሪቱን ታሪክ ወደ መቶ ዓመት አውርዶ ለሚተነትነው፣ ጥንታዊው የሆነው ፊደላችን፣ ሦስት ሺሕ ዘመንን ያስቆጠረውን የሥነ-መንግሥት ታሪክ ‹‹የአቢሲኒያውያን/የነፍጠኞች ቅኝ ገዢዎች ታሪክ›› አድርጎ የኢትዮጵያን ሕዝቦች ታሪክ በብሔር ብሔረሰቦች ማዕቀፍ ቀንብቦ ዳግም ለመፍጠር ለሚውተረተረው፤ አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የሚመሩት የኢሕአዴግ መንግሥት በምን ሞራልና ተጠየቅ፡- ‹‹ከአፍሪካ አገራት ሺሕ ዘመናትን ያስቆጠረ የራሳችን ፊደልና የዘመን አቆጣጠር ያለን ኩሩ ሕዝቦች …፡፡›› ተብሎ በአደባባይ ሊነግሩን እንደደፈሩ አይገባኝም፡፡ የታሪክ እውነት/ሐቅ ሲያሻን የምንደርበው እንዲያ ሲል ደግሞ አውልቀንና አሽቀንጥረን የምንጥለው የበረሃ ሽርጥ ኾነ እንዴ ጎበዝ …?! ይሄ በእውነት ያስተዛዝባል፡፡ ወይስ ደግሞ እንደው ሳንሰማ ኢሕአዴግ በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ያለውን አቋም አስተካክሎ ይሆን እንዴ … እ…እ…እ… አይመስለኝም፡፡

በዚህ ረገድ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትራችን የነበሩት አቶ መለስ ዜናዊም፣ ‹‹… የኢትዮጵያ ታሪክ የመቶ ዓመት ታሪክ ነው፣ የአክሱም ሐውልት ለወላይታው ምኑ ነው …?! እንዳላሉን ኹሉ የኢትዮጵያ ሚሊኒየም ሲከበር ባደረጉት ንግግራቸው፣ ‹‹… እኛ ኢትዮጵያውያን የሦስት ሺሕ ዘመን ታሪክና መንግሥት ያለን ነጻና ኩሩ ሕዝቦች …›› ሲሉ ሰምተናቸው መገረማችንን አስታውሳለኹ፡፡ እዚህ ጋራ የኢትዮጵያን ታሪክ ‹‹በአቢሲኒያውያን/በነፍጠኞች ቅኝ ግዛት ወረራ›› የታሪክ መነጽር የሚመለከተው ኢሕአዴግ ሙሉ ድጋፉንና ፈቃዱን በቸረበትና የኤርትራውያን ጥያቄ ‹‹የቅኝ ግዛት ጥያቄ ነው›› በሚል የኤርትራውያን ነጻ እንዲወጡ ባደረገበት ወቅት የኾነውን የታሪክ ቀውስም በጥቂቱ ማየት እንችላለን፡፡
ትናንትና የኢትዮጵያ አካል የነበሩት ኤርትራውያን ወገኖቻችን ነጻነታቸውን ባወጁ ማግሥት የዘመን አቆጣጠራቸውን ወደ ጎርጎርሳውያን የቀየሩት የኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር ቅኝ ገዢዎቹ አቢሲኒያውያን/ነፍጠኞች እንደ ብርድ ልብስ የደረቡብን የእኛ ያልሆነ- ታሪካችንን፣ ቅርሳችንንና ማንነታችንን የሚያራክስ፣ የሚያጣጥል ነው በሚል አመክንዮ እንደሆነ የምንስተው አይመስለኝም፡፡ የኋላ ኋላ የኾነውን ነገር ኹሉ እናስታውሳለን፤ ባልነበረ የፈጠራ ታሪክ ሺሕዎች ጭዳ የኾኑበትን የጦርነት፣ እልቂት መዘዝ በኀዘን እናስታውሳለን፡፡ አሁንም ድረስ የኹለቱ አገራት ጉዳይ የተዳፈነ እሳት ሆኖ አለ፡፡
በዚሁ የፈጠራ ታሪክ ጦስ የሆነውን ሌላኛው ትዝብቴን ላክል፡፡ ኤርትራዊ ብሔርተኝነትን በአዲስ የታሪክ ሂደትና ትንታኔ ለመፍጠር ሲውተረተር የነበረው የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂና ደጋፊዎቹ/ብሔርተኛ ኤርትራውያን ባለፈው ዓመት ደግሞ፣ ‹‹… ለመሆኑ እንደው የሆነስ ሆነና ኢትዮጵያ ከማን ተሸላ ነው እኛን ሥልጡን፣ የራሳችን የዘመናት ታሪክ፣ ቅርስ፣ ባህልና ሥልጣኔና ያለንን ሕዝቦች ቅኝ ለመግዛት የቻለችው?!›› በሚል ለዓመታት ሲያቀነቅኑ የነበረውን ‹‹ኢትዮጵያ ቅኝ ገዘታናለች›› የሚለውን የታሪክ ምጸት በውስጣቸው የፈጠረውን የበታችነት ስሜትና የማንነት ቀውስ በሌላ ተረት ተረት ላማከምና ኤርትራዊ ብሔርተኝነትን በሁለት እግሩ ለማቆም ደፋ ቀና ሲሉ ታዝበናቸዋል፡፡
በተጨማሪም ሰፊው የኦሮሞ ሕዝብንም ለዘመናት ሲጠቀምበት የነበረውን ፊደሉን ከግእዝ ፊደል ወደ ላቲን ፊደል እንዲቀይር ያስገደደው ይኸው ኢሕአዴግ በሚያቀነቅነው ‹‹የአቢሲኒያውያን/የነፍጠኞች የቅኝ ገዢዎች ታሪክ›› ትንታኔ መነሻነት እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ታዲያ ባለ ሥልጣኖቻችን እንዲህ የሚያጣጥሉትንና የሌሎችና ታሪክና ቅርስ፣ ማንንት ያመከነና የዘረፈ ነው ብለው የሚከራከሩበትን የኢትዮጵያን ታሪክና ቅርስ እንዴት በአደባባይ ሺሕ ዘመናትን ያስቆጠር የፊደል፣ የዘመን አቆጣጠር ያለን የሦስት ሺሕ ዘመናት ታሪክ ባለቤት ሕዝቦች ሊሉን የቻሉበትን ድፍረት የት እንዳገኙት ለመጠየቅ፣ ለመሞገት እንገደዳለን፡፡ እንዲህ እንደ እስስት በመለዋወጥስ የታሪክ ሐቅን መለወጥ ይቻላል እንዴ?!
ከኢትዮጵያን ታሪክ አንስቶ እስከ ፊደላችን ድረስ በርካታ ጥያቄዎች አሉብን፡፡ ለአንዳንዶች የኢትዮጵያ የሺሕ ዘመናት ታሪክ የአቢሲኒያውያን/የነፍጠኞች ቅኝ ግዛት ታሪክ እንደሆነ ነው የሚሰማቸው፡፡ ለአንዳንዶች ደግሞ ፊደላቱ ያለ ቅጥ በዝተዋልና ይቀነሡ በሚል ሽንጣቸውን ገትረው ይከራከራሉ፡፡ ይህን ጥያቄ መዳኘትና መልስ መስጠት የሚገባቸው ከእውነት ጋር የወገኑ የእውቀት ሰዎች-ጠቢባኑ ደግሞ ከመድረክ ተገፍተው ታሪክን እንዳሻቸው የሚተነትኑ አድር ባዮች፣ በአገሪቱ ታሪክ ማኅፀን ሌላ ለከፋፋይ ፖለቲካቸው የሚመቻቸውን ጽንስ እያበጁ እያየንና እየሰማን ይኸው በፍርሃት ተሸብበን አለን፡፡ እነርሱም ያለ ምንም እፍረት ታሪካችንን ለጊዜያዊ ፖለቲካቸው ጥቅም ሲሉ እንዳሻቸው ሲለዋውጡት በአግርሞት እያየናቸውና እየሰማናቸው ነው፡፡
በመጨረሻም ወደ ዘመን አቆጣጠራችን ጉዳይ ስመለስ ዛሬ ዓለም ኹሉ እየተደመመበት ያለውንና ይህ የዘመን አቆጣጠርም ከሥነ ፍጥረት ሕግና ሂደት ጋራ የተስማማ እንደሆነ የሚያሳዩ መረጃዎች እየወጡ ነው፡፡ ባለፈው ዓመት የካቶሊኩ ፖፕ የነበሩት ጀርመናዊው ፖፕ ቤኔዲክት የአውሮፓውያኑ የዘመን አቆጣጠር ስህትት እንደሆነና ከአውሮፓውያኑ የዘመን አቆጣጠር ይልቅ ይኸው የእኛው የኢትዮጵያ ዘመን አቆጠጠር ትክክል እንደሆነ Jesus of Nazareth: The Infancy Narratives በሚል መጽሐፋቸው ለመላው ዓለም አሳውቀዋል፡፡
የኢትዮጵያን ዘመን አቆጣጠርና ደማቅ ክብረ በዓሉን በተመለከተ ደግሞ ዘንድሮ በተለየ ሁኔታ እንደ ለንደኑ ቢ.ቢ.ሲ፣ የአሜሪካው ሲ.ኤን.ኤን፣ የዶሃው አልጀዚራና የኢራኑ ፕሬስ ቴሌቪዥኖች ሽፋን በመስጠት ዘግበውት ነበር፡፡ በተለይ ደግሞ የኩባ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ በስፓኒሽ ቋንቋ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ኩባውያን ስለ ኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር ሰፊ ሽፋን ሰጥተው ልዩ ዘገባ እንዳቀረቡ ተከታትለናል፡፡ ተወደድም ተጠላ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ቅርስ የኾነው ይህ የዘመን አቆጣጠራችን ከአፍሪካ አልፎ የዓለም ኹሉ ቅርስ ወደመሆን እየተሸጋገረ እንዳለ እየታዘብን ነው፡፡ ይህን ዓለም ሁሉ አምኖ የተቀበለውንና የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ደማቅ አሻራ ያለበትን የአገሪቱን የታሪክ ሐቅ መካድ፣ ማፋለስ፣ መበረዝ፣ … ከራስ ጋራ፣ በፍቅርና በአንድነት የጥበብ ልዩ ሸማ ከተዋበው፣ ዘመናት ካልሻሩት ኢትዮጵያዊ ማንነት፣ ታሪክና ቅርስ ጋራ መጣላት መሆኑን በመግለጽ ልሰናበት፡፡
ሰላም!

No comments:

Post a Comment