አንዳንድ የኦሮሞ የፌስ ቡክ "አክቲቪስቶች" ግንቦት7 ኦነግን አፈረሰው እያሉ አዲስ ታሪክ መጻፍ ጀምረዋል። እነዚህ ሰዎች ግንቦት7ትን ሲወነጅሉ ኦነግን እያሳነሱት መሆኑ አልገባቸውም። እስኪ እግዜር ያሳያችሁ፣ የ40 ዓመቱን ጎልማሳ ድርጅት የ7 አመቱ ግንቦት 7 አፈረሰው ሲባል፣ ድክመቱ የማን ነው? አንድ የ40 ዓመት ጎልማሳን የ7 ዓመት ልጅ ደብድቦ ቢጥለው ፣ ሰውዬው 40 ዓመት ሙሉ ምን ይሰራ ነበር? ግንቦት7 ኦነግን አፍርሶት ከሆነ፣ ኦነግ ከመጀመሪያውም ድርጅት አልነበረም ማለት ነው፤ እንዲህ በቀላሉ የሚበታተን ድርጅት ከሆነም ኦነግ በስም እንጅ በገሃዱ ዓለም ያልነበረ ድርጅት ነበር ማለት ነው።
በእኔ እምነት ኦነግ የተዳከመው ገና ከጥንስሱ ነው። የዛሬ 40 ዓመት በተንሸዋረረ ታሪክና በአደገኛ አላማ ላይ የተቋቋመው ኦነግ፣ የሚታገልለት አላማ ጠልፎ የጣለው ይመስለኛል። የኦነግን የተንሸዋረረ አላማው ለማስተካከል ጀግናው ጄ/ል ከማል ገልቹ ሃላፊነቱን ወስዶ ታገለ። ብዙ ድጋፍ ባያገኝም አላማው ለኢትዮጵያ ህዝብ የሚበጅ መሆኑን መካድ አይቻልም። ጄ/ል ከማል ለስልጣን ብሎ አላማውን አልቀየረም፣ ጄኔራሉ እሱን ከሚተቹት ሰዎች በላይ አዋቂና የገባው ነው። ስልጣን ቢፍልግ ኖሮ ዛሬ የት በደረሰ? ጄ/ል ከማል ለወሰደው እርምጃ ሃላፊነቱ የጄ/ል ከማል እንጅ የሌላ ድርጅት ሊሆን አይችልም። ጄኔራሉ ከሌሎች ጋር በመሆን አንድ ቀን እንደሚሳካለት አምናለሁ። አልተሳሳተም እንጅ ጄ/ል ከማል በሰራው ስራ ግንቦት7 የሚጠዬቅበት ምክንያት አሳማኝ አይሆንም።
የኦሮሞ አክቲቪስቶች ሁሉንም ነገር ከመተቼት ተላቀው፣ አላማቸውን አስተካክለው ፣ የዲሞክራሲ ሃይሎችን ቢቀላቀሉ እንወክለዋለን የሚሉትን ህዝብ ጥቅም ማስከበር ይችላሉ። እነሱ ተቀላቀሉ አልተቀላቀሉ ግን፣ ዲሞክራሲን ግብ ያደረጉ ሃይሎች፣ የትኛውንም ብሄር ጥያቄ ፣ የትኛውንም የግለሰብ ጥያቄ መመለሳቸው አይቀርም ምክንያቱም ዲሞክራሲ በችግሮቻችን ላይ ቁጭ ብለን እንድንነጋገር የሚደርገን ቅዱስ ነገር ነውና። ቁጭ ብለን ከተነጋገርን የማንፈታው ችግር አይኖርም። ዲሞክራሲን ከማስፈን የበለጠ የትግል አላማ ይኖራል? አይመስለኝም፤ ዲሞክራሲ የተወሰኑ አገሮችን ወደ መልካም አገርነት ሲለውጥ ተመልክተናል። በቲዮሪ ሳይሆን በተግባር ተፈትኖ አልፎአል።
በፈረንጅ አገር በስደት የምንኖር ሰዎች በአገራችን ያላገኘነውን ዲሞክራሲ እዚህ እንደ ልብ እያገኘነው ነው። ታዲያ እዚህ ያገኘነውን ዲሞክራሲ ለአገራችን የስርኣቱ መሰረት እንዲሆን መታገል ምንድነው ክፋቱ? በእኔ በኩል ካልመጣ ካላልን በስተቀር ፣ ማንም ያምጣው ማንም፣ ዲሞክራሲ የችግራችን የመፍቻ ቁልፍ መሆኑን ካመንን የሚታገለውን ሃይል " ይቅናህ" ብለን መመረቅ እንጅ፣ መርገም ፣ ትግሉን ላያስቆመው ፣ ዋና የገለውም። ህወሃት ዲሞክራሲን ቢያሰፍን ኖሮ እኮ ህወሃትን ስናመሰግን መኖራችን አይቀርም ነበር። አሁንም እነአርበኞች ግንቦት7፣ ደሚት፣ የአፋር ድርጅትና የአማራ ድርጅት ዲሞክራሲን እናስፍናለን ብለው እስከታገሉ ድረስ እንደግፋቸው፣ ቃላቸውን ሲያጥፉ እንታገላቸው። እነሱ የሚያመጡት ዲሞክራሲ "ጥንቅር ይበል" ማለት ግን አንድም ግብዝነት ሌላም... አራት ነጥብ።
No comments:
Post a Comment