Monday, May 11, 2015

“በሰማያዊ እና በፀጥታ ኃይሎች መካከል ለሚፈጠረው ችግር ተጠያቂው የከተማ አስተዳደሩ ነው” ሰማያዊ ፓርቲ

ሰማያዊ ፓርቲ ትናንት ሚያዝያ 29/2007 ዓ.ም ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በላከው ደብዳቤ ምርጫ ቦርድ በህግ የተሰጠውን ኃላፊነት እንዲወጣ ጠይቋል፡፡ የተሻሻለውን የምርጫ ህግ 532/1999 ዓ.ም አንቀፅ 58 ቁጥር 1 ላይ ‹‹አንድ ዕጩ ተወዳዳሪ መታወቂያ ካገኘበት ቀን አንስቶ ምርጫው ሁለት ቀን እስኪቀረው ድረስ ከአስተዳደሩ ሆነ ከማዘጋጃ ቤት ፈቃድ ሳይጠይቅ በፅሁፍ በማሳወቅ ብቻ የድጋፍ ስብሰባዎች አሊያም ሰላማዊ ሰልፎችን የመጥራት መብት አለው›› የሚለውን የጠቀሰው ሰማያዊ ፓርቲ ሆኖም ይህንን መብት መነፈጉን ገልጾአል፡፡
ሰማያዊ ፓርቲ በደብዳቤው ይህን ህግ ተከትሎ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተደጋጋሚ ጊዜ የህዝባዊ ስብሰባና የሰላማዊ ሰልፍ እውቅና ቢያቀርብም አስተዳደሩ ስለማይቀበል ፓርቲው በደተጋጋሚ ጊዜ ከፀጥታ ኃይሎች ጋር አለመግባባት እንዲፈጥርና ሌሎች ችግሮችም እንዲደርሱበት አድርጓል ብሏል፡፡ ፓርቲው ግንቦት 9/2007 ዓ.ም ከመራጩ ጋር ለመገናኘት መስቀል አደባባይ ላይ ህዝባዊ ስብሰባ እንደሚጠራ ለአስተዳደሩ ቢያሳውቅም ሁሉም ኢትዮጵያውያን ሊጠቀሙበት የሚገባው መስቀል አደባባይ ላይ ህዝባዊ ስብሰባ ማድረግ እንደማይችል በከተማ አስተዳደሩ መከልከሉን ገልጾአል፡፡

‹‹ይህ የከተማ አስተዳደሩ ተግባር እጅግ አድሎአዊ፣ ኢትዮጵያዊያን መሆናችን እንኳ ባላገናዘበ መልኩ ሌሎች የፖለቲካ ቡድኖች የሚሰበሰቡበት መስቀል አደባባይ ላይ ስብሰብ የማድረግ መብት እንደሌለን አሳውቋል፡፡›› ያለው ሰማያዊ ፓርቲ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተሰጠውን ኃላፊነት ተጠቅሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች በህግ የተሰጣቸውን መብት የሚሸረሽሩ አካላት ላይ እርምጃ እንዲወስድ ጠይቋል፡፡
በተመሳሳይ መስቀል አደባባይ ሚያዝያ 14/2007 ዓ.ም መንግስት ህዝባዊ ስብሰባ ጠርቶበት እንደነበር ገልጾ ይህን አደባባይ ሰማያዊ ፓርቲ ለተመሳሳይ አላማ ሊጠቀምበት ሲጠይቅ መከልከሉ ግልጽ አድሎአዊነት የታየበት መሆኑን በመግለጽ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በፃፈው ደብዳቤ የአስተዳደሩን ውሳኔ ተቃውሟል፡፡ ‹‹የከተማ አስተዳደሩ ሰማያዊ ፓርቲ የሚጠይቃቸውን ተመሳሳይ ጥያቄዎች በተደጋጋሚ ባለመቀበል በፓርቲውና በፀጥታ አስከባሪዎች መካከል በተደጋጋሚ አለመግባባቶች እንዲፈጠሩ ምክንያት ሲሆን ቆይቷል፡፡›› ያለው ፓርቲው የከተማ አስተዳደሩ እየፈፀመው ያለው ተግባር ከአድሎአዊነትም አልፎ በኢትዮጵያውይነታቸው ላይ ያነጣጠረ አደገኛ ተግባር ነው ብሎታል፡፡
በመሆኑም አስዳደሩ ሰማያዊ ፓርቲና በፀጥታ ኃይሎች መካከል አለመግባባት ከመፍጠር ተቆጥቦ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቋል፡፡ በተጨማሪም ሰማያዊ ፓርቲ መስቀል አደባባይ ላይ ህዝባዊ ስብሰባ ማድረግ አይችልም ማለቱ ህጋዊ መሰረት የሌለው በመሆኑ ፓርቲው አስቀድሞ ባስቀመጠው መሰረት፤ በተጠቀሰው ቦታና ጊዜ ህዝባዊ ስብሰባ እንዲሚያደርግ ታውቆ አስተዳደሩ አስፈላጊውን ትብብር ሁሉ እንዲያደርግ ጠይቋል፡፡
Semayawi Party- Ethiopia's photo.Semayawi Party- Ethiopia's photo.Semayawi Party- Ethiopia's photo.Semayawi Party- Ethiopia's photo.

No comments:

Post a Comment