- ዕርቀ ሰላሙንና የፓትርያሪክ ምርጫውን በተጓዳኝ እንዲካሄድ ለማስወሰን ታስቧል
- ‹‹ዕርቀ ሰላሙ ይቅደም›› የሚሉት አባቶች አቋምና ብዛት እየተጠናከረና እየጨመረ ነው
- የሰላምና አንድነት ጉባኤው ለቅዱስ ሲኖዶሱ ደብዳቤ ጽፏል
- ከ4ኛው ፓትርያሪክ ጋራ ፊት ለፊት መወያየት ቀጣይ የመነጋገሪያ ነጥብ ነው ተብሏል
ቅ/ሲኖዶስ በነገው ዕለት አስቸኳይ የምልአተ ጉባኤ ስብሰባ ለመቀመጥ በሚዘጋጅበት ዋዜማ ዐቃቤ መንበረ ፓትርያሪክ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ በይፋ መጠየቃቸው ተሰማ፡፡ ዐቃቤ መንበሩ ጥያቄውን ያቀረቡት ለመንግሥት አካል በጻፉት ደብዳቤ ነው ተብሏል፡፡ ደብዳቤው የተጻፈው ሁለት ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት (አቶ ኣባይ ፀሃዬ እና ዶ/ር ሽፈራው ተክለ ማርያም) በሳምንቱ መጨረሻ በዐቃቤ መንበረ ፓትርያሪኩ ቢሮ ተገኝተው ከተወያዩ በኋላ መኾኑ ተገልጧል፡፡
ጥያቄው ስለቀረበበት ምክንያት የዜናው ምንጮች ሲያስረዱ÷ ‹‹ቅድሚያ ለዕርቀ ሰላሙ›› በሚል ለስድስተኛው ፓትርያሪክ ምርጫ የሚደረገውን ዝግጅት በሚቃወሙ ብዙኀን ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት እና ‹‹ዕርቀ ሰላሙ ከፓትርያሪክ ምርጫው ጋራ ግንኙነት የለውም፤ ሁለቱም በተጓዳኝ/በትይዩ ሊከናወኑ ይችላሉ›› በሚሉ ጥቂት ነገር ግን ተጽዕኖ ፈጣሪ ናቸው በሚባሉ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት መካከል በተያዘውና ከዕለት ወደ ዕለት እየተካረረ በመጣው ፍጥጫ ሳቢያ ነው ብለዋል፡፡