“የደወሉላቸው ደምበኛ ለግዜው ጥሪ አይቀበሉም።…” የምትለዋ አሰልቺ የቴሌ መልእክት ያላጋጠመው ቢኖር ወደ ኢትዮጵያ ስልክ ደውሎ የማያውቅ ሰው ብቻ መሆን አለበት። ኮ/ል መንግስቱ ሃይለማርያም ወደ ቀድሞ ወዳጆቻቸው መደዋወል ጀመሩና በመሃል ተስፋ ቆረጡ አሉ። አስር ለሚያህሉ አርሶአደሮች እና የሰራዊቱ አባላት ዘንድ ደውለው አልተሳካለቸውም። ለሁሉም ጥሪ ያገኙት ምላሽ “የደወሉላቸው ደምበኛ ለግዜው ጥሪ አይቀበሉም።” የሚል ሲሆንባቸው ራሳቸውን ነቀነቁ። ሰው ሁሉ የጨከነባቸው መሰላቸው። እንዲህም አሉ። “የሃገሬ ሰው እንኳን የስልክ ጥሪ፤ የእናት ሃገር ጥሪስ መች ተቀበለ።”
ለአመታት በተከታታይ በሁለት ድጅት እያደገች ያለች ሃገር የስልክ መስመር ችግር ይገጥማታል ብሎ ማሰብ ይከብዳል። ችግሩን በደንብ ላልተረዳው፣ ሰው የሞባይል ስልክ የሚገዛው እንዲሁ ይዞ ለመታየት ነው ያስብል ይሆናል። ይህ አባባል በከፊል ትክክል ነው። ዘመናዊ ስልክ በመያዝ ለላንቲካነት ብቻ የሚጠቀሙበት ሰዎች አይጠፉም። የቻይናው ቀፎ ከሞዴል አርሶ አደሮች አልፎ ተራው አርሶ-አደር እጅ ላይም ገብቷል። አብዛኞቹ ግን ተንቀሳቃሽ ስልካቸውን አይጠቀሙበትም። ለዚህም ይመስላል በርካታ ተንቀሳቃሽ ስልክ የሚይዙ ሰዎች እንዲሁ ለእይታ እና ለላንቲካ ብቻ የሚመስላቸው። አገልግሎቱን በተመለከተ ግን 99 በመቶ የሚሆነው ችግር የመዋቅር ችግር ነው።
ለዓውዳመቱ ወደ ኢትዮጵያ ስልክ የደወላችሁ ካላችሁ፤ ይህ ነገር እንደገጠማችሁ እርግጥ ነው። ዘንድሮ ደግሞ ቴሌ ከፍቷል። የሞባይሉ መስመርማ እንደ አይን እልም ብሎ ነው የጠፋው። ከበርካታ ሙከራ በኋላ መስመር ያገኘ ሰው ካለ በደስታ ይዘልላል። የተቀባዩም ስልክ ካቃጨለ ተዓምር ነው የሚባለው። ከርማ ብቅ እንደምትለው የአዲስ አበባ መብራት … ልክ እንደ ቧንቧ ውሃ፤ ስልኳም “መጣች – መጣች!” ብሎ መጨፈሩ አይቀርም።
(በመከራ መስመር ሲገኝ እንዲህ ያስደስታል)
“እንኳን አደረሳችሁ!” ለማለት እኔም ወደ ሃገር ቤት ስልክ መታሁ።
“የደወሉላቸው ደምበኛ ለግዜው ጥሪ አይቀበሉም።” የሚል መልስ ነበር ያገኘሁት። ለሁለተኛ ግዜ ስሞክር ደግሞ “የደወሉት ስልክ ለግዜው ከአገልግሎት መስጫ ክልል ውጪ ነው።” የሚል ምላሽ አገኘሁ። ደቂቃ ባልሞላ ግዜ ውስጥ ጥሪ ያማይቀበለው ስልክ ከአገልግሎት መስጫ ክልል መውጣቱ አስገረመኝ። ተስፋ ሳልቆርጥ ደገግሜ ሞከርኩ። ቢያንስ ከአስር ግዜ ሙከራ በኋላ፤ መስመር አገኘሁና ሎተሪ የወጣልኝ ያህል ተሰማኝ።
ደስታዬ ግን ብዙም አልዘለቀም። በመሃል እንግዳ ነገር ተፈጠረ። ስልኩን የተቀበለኝ የደወልኩለት ሰው አልነበረም። የተፈጠረው ክስተት – ባለንበት የመረጃ ዘመን እንደ 17ኛው ክፍለዘመን “ቴሌ በኦፐሬተር መስራት ጀመረ እንዴ?” ያሰኛል። ነገሩ ግን ሌላ ነው። ስልኩን ያነሳው የተለመደው የስልክ ጠላፊ ስለመሆኑ አንዳች ጥርጥር አልነበረኝም። ሶማሌያውያን መርከብ ሲጠልፉ ጸሃዩ መንግስታችን ደግሞ የስልክ ፓይረት መሆኑን ሂዩማን ራይትስ ዎች በዚያን ሰሞን ነግሮን ነበርና።
ውጭ ሃገር ያለ ኢትዮጵያዊ ዘመድ ለመጠየቅ መደወሉ አይቀርም። ተስፋ የማይቆርጥ፤ ደጋግሞ ይሞክራል። እንደ እድል የስልኩን መስመር ካገኘ ደግሞ ሌላ ችግር ይገጥመዋል። ዘው ብለው የሚገቡ የስልክ ጠላፊዎች መስመሩን ያውኩታል። ሌላው አማራጭ ደግሞ አጭር የጽሁፍ መልእክት ነው። በኢትዮጵያ ቴሌኮም አጭር መልእክት ከመላክ ይልቅ ደብዳቤ ጽፎ በፖስታ መላኩ እየፈጠነ መጥቷል። አጭር መልእክት የሚደርሰው ከቀናት ብኋላ ነው። ከላኪው ዘንድ መልዕክቱ መድረሱ ቢረጋገጥም ተቀባዩ ጋ ጨርሶ ላይደርስም ይችላል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ በቅርቡ በሰጡት ጋዤጣዊ መግለጫ “የኢትዮጵያ ቴሌኮም ቴክኖሎጂ ከዴንማርክ፣ ከኖርዌይ እና በከፊል ከእንግሊዝ ቴክኖሎጂ ጋር አንድ ነው” ብለው ነበር። በዚህ መግለጫቸው አቶ ሃይለማርያም የኢትዮጵያን የኢንተርኔት አገልግሎት፣ እንዲሁም የስልክ መስመሩ ጥራት እና አስተማማኝነት በደንብ አድርገው ነበር “ለጋዜጠኞቹ” የገለጹላቸው። ይህን ተናግረው እንዳበቁ ግን የራሳቸውም ስልክ መጠለፉን ሰማን። ጆሮ ለባለቤቱ ባዳ ነው እንዲሉ አልሰሙት ይሆናል እንጂ፤ “እኛ ሲም ካርድ፤ አንተ ደግሞ ቀፎ ነህ!” ይሏቸዋል – ከላይና ከታች ያሉ አለቆቻቸው።
የኢትዮጵያን ስልክ አገልግሎት ከዴንማርክ፣ ኖርዌይ እና እንግሊዝ ጋር አወዳድረው ማወደሳቸው ግን ራሳቸው ካዴሬዎቹንም ሳይቀር ሳያሰፍራቸው አልቀረም። ሰውየው የኢትዮጵያን ቴሌኮም እያወዳደሩ ያሉት 99.9 በመቶ ሳያቋርጥ አገልግሎት ከሚሰጠው አራተኛው ጀንሬሽን የምእራቡ ቴክኖሎጂ ጋር ነው። መቼም ሁሉም ይዋሻሉ። ነብሳቸውን ይመርና አቶ መለስ ዜናዊም ይዋሹ ነበር። ለዛ ያለው ውሸት አለ። እጅ፣ እግርና አይን የሌለው ውሸትም አለ። እንዲህ አይነት ያፈጠጠ ውሸት ግን እመራዋለሁ የሚሉትንም ሕዝብ እንደመናቅ ይቆጠራል። እኚህ ሰው የሞራል እሴታቸውን ሁሉ አሽቀንጥረው ሊጥሉት ይችሉ ይሆናል። ምሁራዊ ግብአታቸውንም ለተራ ፖለቲካ ጥቅም ሊያስወግዱት ይችላሉ። እምነታቸውስ እንዲህ አይነቱን ቅጥፈት ይፈቅድላቸው ይሆን?
የቴሌ የኢንተርኔት አገልግሎት የመንግስት አልባዋ ሶማልያን አንድ መቶኛም። ኮሜዲያን ክበበው ገዳ እንደቀልድ የነገረኝ ቁም-ነገር የኢትዮጵያን ኢንተርኔት ፍጥነት በደንብ ይገልጸዋል። ክበበው ሰሜን አሜሪካ የስራ ጉብኝቱ ወቅት ፎቶ ተነስቶ ለቤተሰቡ በኢሜይል ይልካል። የላከው ፎቶ መድረሱን ለማረጋገጥ በነጋታው ወደ አዲስ አበባ ደወለ።
“ፎቶ ደረሰ?”
“አልደረሰም!”
ሌላ ቀን እንደገና ደውሎ የላከው ፎቶ እንዳልደረሰ ተነገረው። ለሶስተኛ ግዜ ደውሎ ኢሜይሉ እንደደረሰ ጠየቀ። አሁንም አልደረሰም ተባለ። እንዲህ እያለ ሳምንት ሞላው።
“በሳምንቱ እኔ ቀድሜ ደረስኩ።” ነበር ያለው ክበበው።
የኢሜይል መልእክቱ መድረሱ ከተረጋገጠ በኋላ – ሌላ ችግር ገጠመው። ኢሜይሉ ሲከፈት ግማሽ አካሉን ነበር የሚያሳየው። ፎቶው እስኪያወርድ (ዳውንሎድ እስኪያደርግ) ደግሞ ግማሽ ቀን መፍጀቱ ግድ ነበር።