Wednesday, May 7, 2014

ወደ ህሊናችን እንመለስ

አንተነህ መርዕድ
የመሬት ጥያቄ ብዙ መስዋዕት የተከፈለበት ቢሆንም አሁን በባሰ ሁኔታ ወያኔ ከሁሉም ዜጋ ነጥቆ በግሉ አድርጎታል። ማንም ኢትዮጵያዊ የሃገሩ፣ የመሬቱ ባለቤት አይደለም። ከዚህ የባሰ ዜጎችን የማዋረድ ተግባር የለም። አባቶቻችን መሬታቸውን ለባዕድ አንሰጥም በማለት ህይወታቸውን ከፍለው አቆይተውናል። ዛሬ እኛ የራሳችን መሬት ባለቤት እንዳንሆን ሁላችንንም መሬት አልባ ያደረገን ስርዓት ዜጎችን አፈናቅሎ ካድሬዎቹን በመሬት ችብቸባ አሰማርቷል። ለባዕዳን ከመሸጥ አልፎ “እኛም የመሬት ባለቤት ልንሆን ይገባናል” ያሉትንና ይህንኑ የዜጎችን ህጋዊ መብት የጠየቁትን ሁሉ በጠራራ ፀሃይ ባደባባይ ይገድላል።

Ethiopia land grab
ተመንጥሮ ለ ‹‹እርሻ›› የተዘጋጀ መሬት
ጋምቤላዎች፣ አፋሮች፣ ሲዳማዎች፣ ጉጂዎች፣ ሶማሌዎች ዛሬ ደግሞ አምቦዎችና ጎንደሮች የተገደሉት መሰረታዊ የሆነውን የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ በማንሳታቸው ነው። በየቦታው እያናጠለ ዜጎችን የሚገድለው የወያኔ ስርዓት በቀነበበልን ጠባብ መንደር ተከልለን ጥቃቱ ወደየቤታችን እስኪመጣ የምንጠብቅ ገልቱዎች መሆናችንን ከብዙ የህይወት መስዋዕት በኋላ እንኳ የተማርን አይመስልም። ትናንት አገራዊ አጀንዳ ይዘው የመታገልና መስዋዕት የመክፈል ታሪክ ያላቸውን የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች “የትግራይ፣ የአማራ፣ የኦሮሞ፣ የሶማሌ…” እያለ ከፋፍሎ በወንድሞቻቸው ላይ የሚደረገውን ጥቃት በጋራ እንዳይከላከሉ እስከ ማድረግ ደርሷል። አያቶቻችን ከሰሜን ከደቡብ፣ ከምስራቅ ከምዕራብ ተጠራርተው ጠላታቸውን በመከላከል ተደራርበው የወደቁባት ይህች አገር የማን ናት? ኦጋዴን፣ ኤርትራ፣ መተማ ወዘተ. የወደቁ አባቶቻችንን አጥንት የየትኛ ጎሳ አባል እንደሆኑ መለየት እንችላለን?
ከመቶ ዓመት በፊት ተገደሉ የተባሉ ዜጎቻችንን ካረፉበት መቃብር እየተቆፈረ ለፖለቲካ ፍጆታ፣ ለከፋፋይ ዓላማ የሚያናፍሰው ስርዓት በሁሉም የአገሪቱ ክልሎች ዜጎች መሰረታዊ መብታቸውን በሰላማዊ መንግድ ስለገለጹ ብቻ እየገደለ ነው። ሰሞኑን ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና እንዲሁም የኦሮሞ ፌዴራሊስት አመራር አባላት እንደገለጹት ያለፈ ታሪክ ስህተትን ስንቆፍር አዲስ ኢትዮጵያን በጋራ ለማለም አልቻልንም። ተባብረን አሁን በተከሰተ ችግር ዙርያ እንታገል ሲሉ ያቀረቡት ጥያቄ ተገቢ ነው።
ከሁለቱም ወገን ያሉ ጽንፈኞች የሚያካሂዱትን የጥላቻ ዘመቻ ችላ ብለን አሁን ባለ የጋራ ችግር ዙርያ ትግልን በማቀናበር የምንመኛትን ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ኢትዮጵያ ለመገንባት መተባበር የወቅቱ አብይ ቁም ነገር ነው።
የሁሉም ኢትዮጵያውያን ህይወት ክቡር ነው። ለንጹህ ዜጎች መሞትና መታሰር ሃላፊ የሆኑትን ሁሉ ኢትዮጵያዊ ሰብአዊ መብት ተቋማት፣አክቲቢስቶች፣ የፖለቲካ ድርጅቶችና ግለሰቦች እየመዘገቡ መያዝ ያስፈልጋቸዋል። ሁሉም በሰራው ነገ ተጠያቂ መሆኑ አይቀርምና።
የኢህአዴግ አባላትና ደጋፊዎች ከደርግ አወዳደቅ ለመማር ጊዜው ሩቅ አይደለም። መንግስቱ ኃይለማርያምና ከጥቂት ባልደረቦቹ በቀር አብዛኞቹ ላለፈ ተባባሪነታቸው ዋጋ ከፍለውበታል። ከሁሉም በላይ ግን የህሊና ጠባሳቸው ቀላል አይደለም። አቅፋችሁና ደግፋችሁ የያዛችሁት ስርዓት ተጠቃሚዎችና ወንጀለኞች ጥቂትና በጣት የሚቆጠሩ ናቸው። ለማምለጫቸው ቦታ፣ ለኑሮአቸው ከፍተኛ ንብረት አሽሽተው የመጨረሻውን ቀን እየተጠባበቁ ነው። እነሱ ሲሄዱ በጠራራ ፀሃይ ልጆቻቸው የተገደሉባቸውን፣ መሬታቸውንና ንብረታቸውን ተነጥቀው የተፈናቀሉን፣ በየእስር ቤቱ በግፍ ሲማቅቁ የነበሩትን፣ ባጠቃላዩም ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ግፍ ሲፈጽምባቸው የነበሩ ኢትዮጵያንን ቀና ብላችሁ ማየት የማትችሉበትና ለድርጊታችሁ ተጠያቂ የምትሆኑበት ጊዜ ይመጣል። ወደ ህዝባችሁ መመለስ ካለባችሁ ጊዜው አሁን ነው።
ሁላችንም ወደ ህሊናችን እንመለስ። እየጠፋ ያለው ነገ አገሪቱን የሚረከቡ ወጣቶች ህይወት ነው። በደርግ ወቅት በእርስ በርስ መጨራረስ ከተሞች ወስጥ ያለቀው፣ በኦጋዴን በረሃ፣ በኤርትራና በትግራይ ጋራዎች የረገፉ ወጣቶቻችን፤ ወያኔ ስልጣን ላይ ከወጣ ጊዜ ጀምሮ በኢትዮ-ኤርትራ ትርጉም አልባ ጦርነት እንዲሁም በየቦታው የተገደሉ ዜጎች ቁጥር የባከነውም ንብረት አገራችንን አሁን ላለችበት የዓለም ጭራነት ዳርጓታል። ከዚህ በኋላ ሌላ ውድ ህይወትና የአገር ሃብት ማጥፋት የማንኛውም ቅን ኢትዮጵያዊ አላማ አይሆንም። ችግራችን የጋራ ነው። አገሪቱም የጋራችን ናት። የገራ የሆነ አገርና ህዝብ ደህንነት የሚጠበቀው በጋራ ተሳትፎ ነው። ድብቅ አጥፊ ዓላማ ካላቸው በቀር ሁላችንም ለጋራ ቤታችንና ህዝባችን ባንድ እንቁም።
ኢትዮጵያን እግዚአብሄር ይባርክ
አንተነህ መርዕድ amerid2000@gmail.com

No comments:

Post a Comment