Wednesday, May 14, 2014

ኢትዮጵያዊነት ክፍል ሁለት ትግሬ ሆነህ አታንብበው (ሄኖክ የሺጥላ)



ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም በሰማያዊ ፓርቲ አዘጋጅነት ፣ ” መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ” የሚለው መጽሐፋቸው ላይ በሚደር ውይይት ካንድ ተሳታፊ ለቀረበላቸው ትያቄ ሲመልሱ፣
“አንዳን የሚያሳዝኑ ነገሮች ተነስተዋል እዚህ አካባቢ ነው መሰል ትግሬ ነኝ ያለ ልጅ አለ፣ ትግሬ ነኝ ብለሃል፣ እኔም ትግሬ ነኝ፣ ነገር ግን ልዩነታችን ትግሬ ሆነህ በማንበብህና ኢትዮጵያዊ ሆነህ በማንበብህ ላይ ነው። እውነት ነው፣ ትግሬነትን እያሰቡ እንደ ኢትዮጵያዊ መኖር አይቻልም፣ ኦሮሞነት ኢትዮጵያዊ ለመሆን ባሰበ ቁጥር የተበዳይነት እና የተገፊነት ስሜት የሚጭር ከሆነ በምንም መልኩ ኢትዮጵያዊ መሆን አይቻልም። ፋሲለደስን ስንመለከት አማራ አደረሰብን የምንለው በደል ከሆነ ትዝ የሚለን ኢትዮጵያዊ መሆን አይቻልም ፣ አክሱምን ስንመለከት የትግሬዎች ክፋት ከሆነ ትዝ የሚለን ኢትዮጵያዊ መሆን አይቻልም፣ ሰንደቅ አላማችንን ስንመለከት አሁንም ሰንደቁ ከተሸከመው ምልክታዊ ትርጉም ውጪ የአማራነት መለኪያአንድን ጎሳ የጥፋት ብብሃር ታሪክ ካደረግነው አሁንም ኢትዮጵያዊ መሆን አይቻልም። ስለ ብራና እና መሰንቆ ስናወራ ወደ አእምሮዋችን ቀድሞ የሚመጣው ቁሶቹ የኢትዮጵያውያኖች እሴት ስለ-መሆናቸው ካልሆነ ኢትዮጵያዊ መሆን ይከብዳል።
Henok Yeshitla
ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ ማርያም በዚሁ ከላይ በጠቀስኩት መጽሐፋቸው ላይ “ድሃነት የጥቃት መከታ መሆኑ የልማቱ መንገድ ፍጽሞ መክሸፉን የሚያረጋግጥ መንገድ ነው ” ይላሉ።
አዋ! የተጠቂነት ስሜትን አዝሎ የተጠያቂነት ባለቤት ነው ከምንለው አካል ጋ የፖለቲካ ውህደት ሲደረግ ጥምረቱ ሳይመሰረት ይፈርሳል ። ሁለት በፍጹም የተለያየ አላማ ያላቸው አካላት ፣ በጋራ ጠላትነት የሚፈርጁት አንድ የጋራ ጠላት ስላላቸው ብቻ ውህደታቸው መፍትሄ ያመጣል ብሎ ማሰብ ዘበት ነው። አንበሳም ጅብም ሚዳቆን አድነው ይበሉ ይሆናል፣ የሚዳቁ’ዐ ምግብነት ግን አንበሳ እና ጅብን ዘመድ አያደርጋቸውም ፣ ምክንያቱም በአመጋገብ ስርዓታቸውም ይሁን ፣ በተፈጥሮ ባህሪያቸው የተለያዩ ፍጥረቶች ናቸውና።
የተበዳይነትን ስሜት የትግል አላማው አድርጎ የተነሳ ድርጅት የተሸነፈው ሲመሰረት ነው። የተፈጠረበትን ምድር፣ መልካም ምድራዊ አቀማመጥ፣ የህዝቡን ባህል፣ ስነልቦናና ታሪክ ወደ ጎን ጥሎ ፣ መሆን አለበት ብሎ ስለሚያስበው ነገር ብቻ እያሰበ በርሃ የወረደ ታጋይ ቢያሸንፍም እንኩዋ ተሸንፎዋል ፣ ለዚህ ከወያኔ የተሻል ጥሩ ምሳሌ ማግኘት አንችልም። ግን ማሸነፍ ብለን የምንለው፣ መንበሩን መቆናጠጥ፣ ወዲህ ሂድ፣ ወዲህ ተመለስ የሚል ት’ዛዝን መስጠት ከሆነ እሱ ሌላ ነገር ነው። እንደምሳሌ ብዙ ግዜ የምሰማው እና የሚገርመኝ ነገር አለ። አብዛኛዎቹ የትግል አቀንቃኞች ” ወያኔን አሸንፈን መስቀል አደባባይ ተሰብስበን እንዲህ እናደርጋለን፣ እንዘፍናለን፣ አንተም ሄኖክ ግጥም ታነብልናለህ ወዘተ ወዘተ ሲሉ መስማት አሁን አሁን የተለመደ ነገር ሆኖዋል። ቁም ነገሩ እኮ መስቀል አደባባይ ላይ መደነስ አይመስለኝም ፣ዳንሱ የድሉ ማድመቂያ እንጂ የድሉ የመጨረሻ ግብ መሆን አለበትም ብዬ አላስብም። ሕልማችን ከድል አጥቢያ ጭፈራ ልቆ መሄድ ያለበት ይመስለኛል። ፍጹም ተገዢዎች ሆነን ሳለ ከድል ማግስት ስለምንረግጠው ጮቤ ከሆነ የምናስበው፣ ገና ስንነሳ ነው የወደቅነው። የትግል አላማ ከዚህ ሁሉ ፍሬ ከርስኪ ሃሳቦች ይልቃል የሚባለው ለዚያ ነው። ታግለው አሸንፈው ለውጥ ማምጣት በቻሉትና ምንም ባልተሳካላቸው ( እንደውም ወደ ባሰ መቀመቅ በመሩን) መሪዎቻችን መሃከልም ያለው ልዩነት ይሄው ነው ። የትግላቸው መነሻ እራሳቸውን ደርሶብናል ብለው ያሳመኑት በደል ሲሆን፣ መድረሻው ደሞ በቀል ነው።
ጆን ዶኔ (ትርጉም በቀብጽ እና በግርድፉ ) ብቻህን ተነጥለህ የምትኖር አንተ ማነ ነህ? ደንመና ውቂያኖሱን ቢጠርገው አውሮጳ ታንሳለች፣ የማንም ሰው ሞት እኔን ያጎለኛል ምክንያቱም ሰው ነኝና ምናምን ይላል ) በሱ ቁዋንቁዋ
No man is an island,
Entire of itself,
Every man is a piece of the continent,
A part of the main.
If a clod be washed away by the sea,
Europe is the less.
As well as if a promontory were.
As well as if a manor of thy friend’s
Or of thine own were:
Any man’s death diminishes me,
Because I am involved in mankind,
And therefore never send to know for whom the bell tolls;
It tolls for thee.
እኔም ከሱ የተለየ ስሜትም እምነትም የለኝም፣ ግን ሞትህ የሚያሳዝነኝ ቢያንስ ቢያንስ አንተ በኔ ሞት ባታዝን እንኩዋ ደስተኛ እስካልሆንክ ነው። አንተ ለኔ መቆም ባፀራ እንኩዋ ለጥፋቴ እስካልታተርክ ድረስ ነው። አዎ ሞትህ ያሳዝነኛል፣ በደልህ ያመኛል፣ ስቃይህ ይቆጨኛል፣ ግን ቢያንስ ቢያንስ የሃዘኔን ያህል ባይሆንም እንኩዋ የሰው ልጆች የመሆናችንን ያህል አንተም ለኔ ፍቅር ይኑርህ። እኛ ግን እንደዚያ አይነት አይደለንም እኛ
“ No man can Judge his agony against an objective scale, his toothache is more than a 1000 death in another part of continent “
እንዳለው አይነቶች ሆንን። ላይቤርያ ውስጥ አንድ ሺ ሰው አለቀ ሲሉን ” የራሳቸው ጉዳይ እኔ ጥርሴን አሞኛል ” የምንል ሆነን። የበደል ትንሽ የለውም፣ የሞት ግማሽ የለውም።
አንተ አንቦ ላይ ስትገደል ለምን አላዘንክም አትበለኘን ይልቅ እኔ ሌሎች ሲበደሉ ተሙዋግቼላቸዋለሁ ወይ ብለህ ራስህን ጠይቅ፣ እምነት ቢኖርም ባይኖርም በሰፈሩት ቁና መሰፈር አይቀርም፣ ተሰፋፋሪ ሆኖ ከመኖር ግን የሚሻለው ተፋቅሮ መኖር ነው። ፍቅርን መሰረት ያላደረገ ትግል ፣ እሱም ላይ ሌላ ትግል እንዲነሳ ያደርጋል እንጂ የለውጥ ምሰሶ አይሆንም። በእርግጥ እወድሃለሁ፣ በእርግጥ ግማሽ ማንነቴ አንተ ነህ፣ ግን ፍቅሬን መሰረት አልባ አታድርገው፣ ካንተም፣ ከራሴም ፣ ከማውው ጥሩ ነገር ሁሉ ሃገሬን አስቀድማለሁ፣ ምክንያቱ ደሞ አማራ ወይ ኦሮሞ ስለሆንኩ አይደልም፣ ምክንያቱ እኔና አንተ አላፊና ጠፍ መሆናችንን ስለማውቅ ነው። ስለዚህ አስብ ይሄ የምለውን ነገር ትግሬ ሆነህ አታንብበው ይልቁንስ ኢትዮጵያዊ ሆነህ አንብበው።

No comments:

Post a Comment