Thursday, May 29, 2014

ውሸት ሲደጋገም ዕውነት እንዳይመስል፣ ስንናገርም ሆነ ስንጽፍ ልንጠነቀቅ ይገባል!

ተክሌ የሻው
ዛሬ ከአገራችን አውራ ችግሮች መካከል ዋናው፣ የተደጋገሙ ውሸቶች ዕውነት የመሰሏቸው ቡድኖች የሚያጎኑት በጥላቻ ላይ የተመሠረተ የዘር ፖለቲካ እና አንድን ነገድ፣ በኢትዮጵያ ተፈጠሩ ለሚባሉ ችግሮች ሁሉ ተጠያቂ የሚያደርገው ነው ብዬ አምናለሁ። አይደለም የሚለኝ ከመጣም የሚለውን ለመስማት ዝግጁ ነኝ። የተደጋገሙ ውሸቶች ሀውልት ሲያስቆሙ እያዬን ነው። የአኖሌን ሀውልት ለአብነት መመልከት ነው። የከተሞችን ስም ሲያስለውጥ እያዬን ነው። አዲስ አበባን ፊንፊኔ፣ ናዝሬትን አዳማ፣ ደብረዘይትን ቢሸፍቱ፣ አዋሣን ሀዋሣ፣ ዝዋይን —ሌላ ሌም አለ። ወደ ኋላ እንይ ከተባለ ወለጋ፣ ቢዛምን፣ ኢሉባቡር እናርያ፣ አርሲ ፈጠጋር፣ ወሎ ላኮመልዛ ወዘተ ማለት ይቻላል። ይህ ግን አይጠቅምም። የኋሊት ጉዞ ያስከትላል። ይህ ደግሞ ወደ አንጋዳ በራስ ኃይል መውደቅን ያመጣል። ይህ ሁሉ የሆነው ውሸት በመደጋገሙ ነው።

ለዚህ መነሻ ሀሳብ የዳረገኝ ተደጋጋሚ ውሸተቶችን በጋዜጠኞችና በፖለቲከኞች ሲራገብ በማዬቴና በመስማቴ ነው። የትኛው ዐማራ በተናጠልም ሆነ በቡድን« የዐፄዎቹ ሥርዓት እንዲመለስ» እንደሚታገል መረጃ ሳይቀርብ፣ ዐማራውን በድፍኑ ያለፈው ሥርዓት ናፋቂ ነው ብሎ መፈረጅ ተገቢ ካለመሆኑም በላይ ውሸት ስለሆነ የወሬውን አባቶች ለመሞገት ነው። ፍረጃው ኢትዮጵያውያን ለአንድነት ለሚያደርጉት ትግል ዐማራው ዋነኛ ችግር እንደሆነ ማሳዬት መሆኑ የአፈራረጁ ሁኔታ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። የዚህ የመጨረሻ ግብ ደግሞ፣ ከወዲሁ ዋስ ጠበቃ የሌለውን ዐማራ በአውላላ ሜዳ ላይ ማንም ስጥ(ስጦ) እንደበላ አህያ ከመወገር አልፎ፣በኢትዮጵያ ምድር የመኖርና የመሥራት መብቱን ተገፎ በስቃይ ላይ የሚኖረውን ገበሬ፣ «ከነፍጠኝነት፣ ትምክህተኛ፣ገዥ፣ ጨቋኝ መደብና ብሔረሰብነት » ከሚሉት የማዋረጃና አንገት የማስደፊያ ስሞች በተጨማሪ ፣ለኢትዮጵያ አንድነት ፀር ነው ወደሚል አዲስ ታርጋ እየተለጠፈለት መሆኑን አእምሮዬ ስለነገረኝ ነው።Tekle Yeshaw Ethiopian author and politician
የነገሩ ፈልሳሚ ዶ/ር መረራ ጉዲና ናቸው። እርሳቸውም «የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምስቅልቅል ጉዞና የሕይዎቴ ትዝታዎች» በሚል ርዕስ ባሳተሙት መጽሐፋቸው፣መደምደሚያ ላይ አንባቢያቸው አጽንዖት ሰጥተው እንዲመለከቱላቸው በሰጡት የማሳረጊያ ሀሳብ ላይ እንዲህ ብለዋል። “ በመጽሐፌ መደምደሚያ ላይ ለታሪክም፣ ለሕዝቡም አስቀምጨ ማብቃት የምፈልገው መሠረታዊ ነጥብ፣አብዛኛው የትግሬ ልሂቃን ሥላጣን ላይ የሙጥኝ እስካሉ ድረስ፣ አብዛኛው የአማራ ልሂቃን በአፄዎች ዘመን የነበረውን የበላይነት መልሸ አገኛለሁ ብሎ የሚጋፋውን የሕልም ፖለቲካ እስካልተዎ ድረስ፣ ብዙኃኑ የኦሮሞ ልሂቃን ኦሮሚያን ለብቻ የማውጣቱን ሕልም እስካልተዎ ድረስ ሀገራችን ከአደጋ ቀጠናና ቀውስ የምትወጣ አይመስለኝም።“ በማለት የዐማራውን ልሂቃን በሞጭ የዐፄዎች ሥርዓት ናፋቂ አድርገው ስለውታል። ስለኦሮሞዎቹ ከእርሳቸው በላይ ኦሮሞ ልሆን ስለማልችል፣ በኦሮሞ ልሂቃን ላይ ያቀረቡትን ትችት ውሸት ነው አልልም። እርሳቸውም የዚሁ አካል ናቸውና። ለዚህም ነው «የኦሮሞ ብሔራዊ ኮንግረስ» የሚል ፓርቲ መሥርተው የብሔር ፖለቲካውን ከሚያጦዙት በኦሮሞ ስም ከተደራጁት 12 የፖለቲካ ድርጅቶች አንዱ የሆኑት።
ስለትግሬዎች የተነሳው ሥልጣንን የሙጢኝ ብሎ የመያዙ ጉዳይ፣ ጥያቄ የሚያስነሳ አይመስለኝም። ምክንያቱም 17 ዓመት በትጥቅ ትግል፣ ዐማራውን በጠላትነት ፈርጀው፣ ለትግራይ የበላይነት ሞተው፣ ቆስለው፣ ሌሎች ብሔርተኞችን አሰልፈው ለሥልጣን የበቁት ሥልጣን ስለሚወዱና በሥልጣን የሚገኘውን ጥቅም ስለሚያውቁ ነው። ሥልጣን መውደዳቸው በራሱ ወንጀልም ኃጢያትም አይደለም። ወንጀልና ኃጢያት የሚሆነው ሥልጣንን መከታ በማድረግ የሚሠሩት አገርና ትውልድ አጥፊ የሆነው ፖሊሲያቸው ነው። ከፋፋይነታቸው፤ ዘረኝነታቸው፣ ሁሉን ለትግሬ ብቻ ማለታቸውና የኢትዮጵያን ታሪክ መካዳቸው ነው። ዐማራን በዘር ጠላትነት ፈርጀው የዘር ማጥፋትና የዘር ማጽዳት ወንጀል መፈጸማቸው ነው። የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለባዕዳን አሳልፈው በመስጠታቸው ነው። ወዘተ ወዘተ–
አያሌ ዘመን ተጉዘው፣ ስንት መከራ አሳልፈው፣ሕይዎት ገብረውና ሺበሺ ገድለው፣ሕይዎት ነሰሺ፣ ሀብት አደላዳይና ነጣቂ የመሆንን፣ ኃይልን በፈለጉት ቦታና ጊዜ የመጠቀም መብትን ከሚያጎናጽፍ የሥልጣን ማማ ላይ የወጡ ሰዎች፣ ተገደው ካልሆነ ወደው ሊለቁ እንደማይችሉ ግልጽ ነው። ይህ ደግሞ የፖለቲካል ሣይንስ ተማሪ ፣ያውም ፕሮፌሰር ነኝ ለሚል ሰው የሚገድና ብዙ የሚያመራምር ጥያቄ አይደለም። በሠራችሁት ወንጀል አትጠየቁም፣ ብቻ ሥልጣኑን ልቀቁ እንኳ ቢባሉ፣ ወደው አይለቁም። ሥልጣን በመልቀቅ የሚያጡት የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና የማኅበራዊ የበላይነትን እንዳለ በቅጡ ያውቃሉ ። ይህም በመሆኑ ወደው ሥልጣን አይለቁም። ሥልጣን ደግሞ እንኳን በኋላቀር አገሮች ቀርቶ ፣ የሰለጠኑ ናቸው በሚባሉትም የሚነጠቅ እንጂ ወዶ ሥልጣኑን የሚሰጥ ግለሰብም ሆነ ድርጅት የለም። ስለሆነም የትግሬ ልሂቃንን ከሥልጣን ለማውረድ በሚያመቸው መንገድ ለመንጠቅ መዘጋጀት እንጂ፣ ይሰጡናል፣ ሥልጣን ሙጢኝ ብለዋል ብሎ ማልቀስ ከዓለም ነባራዊ ሁኔታ ውጭ ነው።
ወያኔዎችን (በዶ/ር መረራ አባባል የትግሬ ልሂቃኑ) ለምኒልክ ቤተመንግሥት ካበቋቸው ዋና ዋና ምክንያቶች አንዱ ኦነግ ለወያኔ እጁን ሰጥቶ የሽግግር መንግሥት እንዲመሠረት ያደረገውና ኢትዮጵያን በመናድ የተጫወተው ጉልህ ሚና የሚዘነጋ አይደለም። ኦነግ ከወያኔ ጋር የፈጠረው ሽርክና፣ ኢትዮጵያን አፍራሽ የሆነው ሕገ-መንግሥት ተጠቃሚ እሆናለሁ ከሚል እሳቤ በመነሳት እንደሆነ ማንም የሚስተው አይደለም። ሌሎቹም መሰል በኦሮሞ ስም የተደራጁት ድርጅቶች ከኦብኮ ጭምር ይህን አዲሱን በዘር ላይ የተመሠረተ ፌደራላዊ አደረጃጀትን ከልብ የተቀበሉ ናቸው። ምክንያቱም ክላምፍ የጫናቸውን በኢትዮጵያ ታሪክ የማይታወቅ « ኦሮሚያ» የሚል ግዛት ሰጥቷቸዋልና ነው። አብዛኝዎቹ የኦሮሞ ልሂቃን ከወያኔ ጋር ያላቸው ጠብ የሕዝብ ቁጥራችን ከፍተኛ ነው፤ ክልላችን በተፈጥሮ ሀብት የበለጸገ ነው፣ ስለሆነም ወሣኝ የሥልጣን ቦታዎች በኦሮሞ ልጆች መያዝ አለባቸው ወይም ይገባናል የሚለው የሥልጣን ጥያቄ ነው። ይህ ጥያቄ ደግሞ የወታደራዊ የበላይነት ባለው ወያኔ የሚዋጥ አልሆነም ። እኛ ታግለን፣ እኛ ሞተን፣ ጥንት የማታውቁትንና በሕልማችሁ የነበረ ክልል ኦሮሚያ ብለን ሰጥተን፣ በቋንቋችሁ እንድትስተዳደሩ ፈቅደን፣ ጠላታችን ነው የምትሉትን፣ የእኛም ጠላት የሆነውን ዐማራ እያሳደድን እየፈጀንላችሁ እያለ ከወሣኝ የፖለቲካ ቦታዎች ለቃችሁ አስረክቡን ማለት የማይታሰብ ነው አሏቸው። ስለዚህ ለወያኔዎቹ ሥልጣን መጨበጥ ጉልህ ሚና የተጫዎቱት የኦሮሞ ልሂቃን፣ ይህን የትግሬዎቹ ልሂቃን ከጨበጡት ሥልጣን በውድ ሊለቁ አለመቻላቸውን መገንዘብ አለመቻላቸው፣ ስለሥልጣንና መንግሥት ባህሪያት ባይተዋር መሆናቸውን ከማሳየቱ በላይ፣ የበለጠ ደግሞ “ሥልጣን ሙጢኝ ብለው ይዘዋል“ ይህም የኢትዮጵያ ችግር ነው፣ የሚለው ከቀድሞው የከፋ ጅልነት ነው። ይህ የትግራይ ልሂቃን ሥልጣን ሙጢኝ ብለው መያዛቸው የሚያስገርም ወይም የሚያስደንቅ አይደለም። ሥልጣንን ሙጢኝ ብለው መያዛቸውንም ለኢትዮጵያ ሕዝብ ነጋሪ አያሻውም። የወያኔ ባለሥልጣኖች የደም ዋጋ የከፈልንበትን በሕዝብ ድምፅ ለመልቀቅ ፈቃደኞች እንዳልሆኑ ደጋግመው ከመናገራቸውም በላይ፣ ምርጫ 97 ታሪካዊ ትምህርት አስተምሮን አልፏል። መቼምና ምንጊዜም ቢሆን ወያኔ ወዶ ሥልጣኑን አይሰጥም። ሥልጣን የፈለገ በሕዝብ የተባበረ አመጽ፣ ወይም ወያኔ በመጣበት መንገድ ተጉዞ መንጠቅ አለበት። ይህ ነባራዊ ዕውነት ነው።
ወደተነሳሁበት ፍሬ ነገር ሳልገባ ብዙ አስጓዝኳችሁ። ጉዞዬ ዓላማዬን መሠረት ለማስያዝ በመሆኑ አንባቢዎቼ ትረዱልኛለችሁ ብዬ አስባለሁ። በመረራ ጉዲና ከተነሱት “ ሀገራችንን ከአደጋ ቀጠናና ቀውስ ውስጥ የምትወጣ አይመስለኝም“ብለው ላቀረቡት በከፍተኛ ጥርጣሬ የተሞላ ሀሳብ የችግሩ ምንጮች ናቸው በተባሉት፣ በትግሬ ልሂቃንና በኦሮሞ ልሂቃን ላይ የቀረበውን ትችት ፣በአብዛኛው በመሬት ላይ ያለና አንድ ሁለት ተብሎ ማስረጃ የሚቀርብበት ነው። ይህም የአገራችን ችግር እንደሆነ ይረዳኛል። ሆኖም ስለዐማራው ልሂቃን የቀረበው ትችት ግን ማስረጃ ያልቀረበበት፣ በመሬት ላይም የሚታይ ምንም ነገር የሌለው ስለሆነ ይህን ልሞግት ተነስቻለሁ። ሙግቴን በነቃሽ ልጀምር፣ የለውጥ አቀንቃኝ በነበረው የ60ዎቹ የተማሪዎች እንቅስቃሴም ሆነ፣ በዛሬው የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ የዐፄዎች ሥርዓት ይመለስ ወይም የዐማራ የበላይነት ይንገሥ ያሉ በግለሰብም ሆነ በድርጅት ደረጃ፣ በዶ/ር መረራ እና ባድናቂው አቶ ተመስገን ደሣለኝ ኅሊና ውስጥ ካልሆነ በቀር፣ በምድር ላይ የለም። ስላለፈው የዐፄዎች ሥርዓት መመለስና ለዐማራ የበላይነት የሚታገል የዐማራ ልሂቃን በድርጅት ቀርቶ በግለሰብ ደረጃ አንድ ሰው መጥራት የሚችል ይኖራል ብየ አላምንም። መረጃ የለም። ካለ በተጨባጭ ይቅረብ። አለ ከተባለ በቅድሚያ ዶ/ር መረራ ጉዲና ቀጥሎም ይህን በመረራ ኅሊና ውስጥ ያለ ጉዳይ፣ በገሐዱ ዓለም እንዳለ አስመስለው ለሕዝብ የሌለና በመረጃ ያልተደገፈ «የአባቶቻችን ስንብት» በሚል ርዕስ በዘሐበሻ ደረገጽ ላይ የጻፈው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሣለኝ አለን የሚሉት ያለፈ,ው ሥርዓት ናፋቂ፣ የዐፄዎችን ሥርዓት ለመመለስ የሚጥር፣ የዐማራን የበላይነት ለማምጣት የሚታገል ድርጅትና ግለሰብ የዐማራ ልሂቃን የት እንዳለ/እንዳሉና ማን/ እነማን እንደሆኑ ሊነግሩን ይገባል። “ አብዛኛው የዐማራው ልሂቃን በዐፄዎች ዘመን የነበረውን የበላይነት መልሸ አገኛለሁ ብሎ የሚጋፋውን የሕልም ፖለቲካ እስካልተው፣—ሀገራችን ከአደጋ ቀጠናና ከቀውስ የምትወጣ አይመስለኝም፤“ ሲል የደመደመውን ሀሳብ ዕውነት ነው በማለት፣ ተመስገን ሀሳቡን አራግቧል፤ አሰራጭቷል።ይህ ደግሞ ዕውነት የመፈለግ ኃላፊነት ካለው ሙያተኛ የሚጠበቅ አይመስለኝም። ሁልጊዜ ዐማራውን ለምን ዓላማ ተጠቂ እንዲሆን እንደሚፈለግ ምክንያቱ ይገባኛል። ራሱ ዐማራው ለራሱ ኅልውና መቆምና መከራከርን አልደፈረም። በመሆኑም ሁሉም አጥፊነው እያለ ዘመቻ ይከፍትበታል። የዘመቻው ግብም ኢትዮጵያን ማጥፋት መሆኑ ግጽል ነው።
ማንም የኢትዮጵያን ተማሪዎች ንቅናቄ የተከታተለ ሰው በግልጽ እንደሚረዳው፣ ከሁሉም በላይ በውስጡ ያለፉ ሰዎች በቅጡ እንደያሚያውቁት የንቅናቄው ፈር ቀዳጅ የሆነው የ1953 በነመንግሥቱ ንዋይ የተመራው መፈንቅለ መንግሥት መሆኑ ዕውነት ነው። የመፈንቅለ መንግሥቱ መሠረታዊ ዓላማም የዘውዳዊ ሥርዓቱን በዘመናዊ መንገድ ለማሻሻል የሚል እንደነበር ይታወሳል። የዚህ ንቅናቄ መሪዎች ደግሞ የደጃዝማች ገርማሜ የልጅ ልጆች የሆኑት፣ የንዋይ ልጆች ዐማራዎች ናቸው። ኮሎኔል ወርቅነህ ገበዬሁ ዐማራ ነው። ሁሉም ይህ ቀረብን የማይሉ፣ የንጉሡ ባለሟሎችና ባለሥልጣኖች የነበሩና የሥርዓቱ ተጠቃሚዎች ነበሩ። እነርሱ ግን ለዘመናዊነትና ለሕዝብ ሁለተናዊ ጥቅም ለውጥ ያስፈልጋል ብለው በማሰባቸው ለለውጥ ተነሱ። የኋላ ውጤቱ ምን ሊሆን እንደሚችል ማወቅ ባልችልም፣ጥያቄአቸው ዘውዳዊ ሥርዓት ለለውጥና ለመሻሻል በር ይክፈት ሲሉ ባነሱት የለውጥ ሀሳብ፣ ራሳቸውን ቤዛ ያደረጉ ኢትዮጵያውያን ዐማሮች መሆናቸው ግልጽ ነው። እነዚህ ሰዎች በዚያ ጊዜ የዐማራው የበላይነት ይጠበቅ ብለው ቢያምኑና ቢያስቡ ኖሮ፣ ሥርዓቱም የዐማራ መሆኑን ቢያምኑ ኖሮ፣ መኮንን ሀብተወልድን፣ብላታ አየለ ገብሬን፣ሊቀመኳስ ታደሰ ነጋንሺ፣አቶ ገብረወልድ እንግዳ ወርቅን፣ደጃዝማች ለጥ ይበሉ ገብሬን፣አቶ ክብረት አጥናፉን ወዘተ የመሰሉ ሰዎችን ባልገደሉም ነበር። ከመጀመሪያውም ለለውጥ ባልተነሱ፤ ሥርዓቱንም አሳልፈው ባላጋለጡ ነበር።
በኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ ጉልህ ቦታ አለው የሚባለው ዋለልኝ መኮንን ዐማራ ነው። ያን ሥርዓት ኮንኖ ለኮናኞች አቀብሎ አገሪቱ ዛሬ ለምትገኝበት ምስቅልቅል ሁኔ ብቻ ሳይሆን፣ የጥፋቷን መንገድ ያመቻቸውን የዐማራ ልሂቃንን ያን ሥርዓት ሊመልሱ፣ የዐማራውን የበላይነት ሊያነግሡ ይታገላሉ የሚሉን። መረራና ተመስገን እንደሚሉት ልሂቃኑ ለዐማራ የበላይነትና ለዐፄዎች ሥርዓት ጸንቶ መኖር ቢሹና ለዚህም መጠበቅ ቢያስቡ ኖሮ፣ ዋለልኝ መኮንን፣« ኢትዮጵያ የብሔረሰቦች እስር ቤት ናት» የሚለውን፣ አገሪቱ ዛሬ ለምትገኝበት ምስቅልቅል ሁኔታና ለኢትዮጵያ ባሕር አልባ መሆን የዳረጋትን መነሻ ሀሳብ ሊጽፈውና ሊያሰራጨው ቀርቶ፣ በኅሊናው ቦታ አይሰጠው እንደነበር መገንዘብ አይገድም። ከዚሁ ጋር ተያይዞ የዐማራው ልሂቃን ለዐፄዎች ሥርዓት መቀጠል ፍላጎቱና ምኞቱ ቢኖራቸው ኖሮ፣ ወያኔ ከበቀለበት ቀዬ የበቀሉት፣ ጥላሁን ይግዛው፣ ብርሃነ መስቀል ረዳ፣ ዘሩ ክሸን፣ ተስፋዬ ደበሳይ፣ አታክልቲ ቀጸላ፣ ወዘተ በመሩት ኢሕአፓ እና ኢሕአሠ ፣በተሰኙት ወታደራዊና ፖለቲካ ድርጅቶች የዐማራው ልሂቃን ገብተው ውድ ሕይዎታቸውን ባልከፈሉም ነበር። ኃይሌ ፊዳ በመራው መኢሶን፣ ሰናይ ልቄ በመራው ወዛደር ሊግ ዕንቁ የነበሩት የዐማራ ልሂቃን ባልገቡና የሕይዎት ዋጋ ባልከፈሉ ነበር።
እነኮሎኔል እምሩ ወንዴ፣ ኮሎኔል አስናቀ እንግዳ፣ መቶ አለቃ አያልሰው ደሴ፣ ዶ/ር ዓለም አንተገብረሥላሴ፣ ዶ/ር ማሞ ሙጨ፣ ጌታቸው ማሩ፤ ወዘተ ወዘተ ቆጥሬ የማልጨርሳቸው ዐማሮች፣ የብሩኅ አዕምሮ ባለቤቶች የትግሉ አጋር ይሆናሉ ተብሎ አይታሰብም ነበር። መረራ ጉዲና ካልዘነጉ « ለመሬት ላራሹ ጥያቄ መልስ ማግኘት የዐማራው ምሁራን ከሌሎች ብሔረሰብ አባሎች በፊት ግንባር ቀደም ሚና ተጫውተዋል፤ ዛሬ ግን እኛ በየራሳችን ብሔር ጎጆ ገብተን የዐማራውን ልሂቃን ካድነው» ማለታቸውን አስታውሳለሁ። ሀቁ ይህ ነው። ዐማራው በሌሎች ተክዶም መካዱን አያውቅም ወይም ለማመን ይቸግረዋል። በዚህም የተነሳ የኢትዮጵያ ችግሮች ሁሉ ፈጣሪ ተደርጎ ይሳደዳል፣ ይወቀሳል።
በመጀመሪያስ ዛሬ የትግራይ ልሂቃን እንደሚያደርጉት የሁለንተናዊ ሀብትና ሥልጣን ባለቤት የሆነ ፣በሁለንተናው የዐማራው ነገድ የበላይነት የነገሠባት ኢትዮጵያ ነበረች ወይ? ብለን ብንጠይቅ አማርኛ ቋንቋ በአገሪቱ ከመነገሩ ውጭ፣ ዐማራው ከሌሎች የተለየ መብትና ሥልጣን ጠቅሎ የያዘባት ፣ኢትዮጵያ በብሔርተኞቹ ኅሊና የተሳለች ካልሆነች በዕውኑ ዓለም የለችም። ነገሥታቱ ካንድ ብሔር የተወለዱ አልነበሩም። ከበርካታ ነገዶች የተወለዱ ኢትዮጵያውያን ነበሩ። ዝርዝር መረጃውን ለማወቅ የሚፈልግ« ሥልጣን ተሻሚዎች ትግሬዎች እና የኢትዮጵያ አንድነት» የሚለውን በዚህ ጸሐፊ የተጻፈውን መጽሐፍ ይመልከቱ። ለአብነት ያህል፣ ዐፄ ቴዎድሮስ ቅማንትና ዐማራ ናቸው። አፄ ተክለጊዮርጊስ አገው ናቸው። ዐፄዮሐንስ 4ኛ ትግሬ ናቸው። ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ ጉራጌና ዐማራ ናቸው። ከፍ ስንልም የበርካታ ነገዶች ደም ቅልቅል አለባቸው። ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ጉራጌ፣ ኦሮሞና ዐማራ ደም ያለባቸው ናቸው። ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ኦሮሞና ዐማራ ናቸው። ቀዳማዊ ኃይለስላሴ የዘርም ልዩነት ስለሌለባቸውም ልጆቻቸውን ያጋቡትት፣ ለጉራጌ፣ ለኦሮሞ፣ ለትግሬ ነው።
በዐማራነት የሚከሰሱትን የምኒልክን መኳንንቶች ብንወስድ አብዛኞቹ ዐማራዎች አይደሉም። ወሣኝ የሚባሉት የምኒልክ መኳንንቶችና አካባቢያዊ ገዥዎች የሚከተሉት ነበሩ።የማን ነገድ አባል እንደሆኑ አንባቢ በስማቸው ማወቅ ይችላል። እነዚህም የሚከተሉት ናቸው፦
1. ንጉሥ ተክለሃይማኖት ጎጃም፣
2. ራስ ( በኋላ ንጉሥ) ሚካኤል አሊ ወሎ፣
3. ራስ ወልደጊዮርጊስ አቦዬ ከፋ፣
4. ካዖ ጦና ወላይታ፣
5. ራስ ዳርጌ ሣህለሥላሴ አርሲ፣
6. ራስ መኮንን ወልደሚካኤል ጉዲሳ ሐረርጌ፣
7. ራስ ጎበና ዳጬ የጦር አበጋዝ፣
8. ራስ መሸሻ ቴዎድሮስ ደንቢያ፣
9. ራስ መንገሻ ዮሐንስ ትግራይ( ምዕራብ)፣
10. ራስ ተሰማ ናደው ኢሉባቡር፣
11. ራስ አባተ ቧያለው ሀዲያናገምባታ፣
12. ራስ ቢትወደድ መንገሻ አቲከም አገው ምድር፣
13. ራስ ጉግሳ አራኣያ ትግራይ ( ምስራቅ )
14. ራስ አሉላ አባነጋ(አሉላ ቁምቢ) የጦር አበጋዝ፣
15. ራስ ናደው አባወሎ፣
16. ራስ ወሌ ብጡል የጁ፣
17. አፈንጉሥ ነሲቡ መስቀሎ ሚኒስቴር፣
18. ፊታውራሪ ገበየሁ ጎራ( ተክሌ) የጦር መሪ፣
19. ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዲ የጦር ሚኒስቴር፣
20. ሱልጣን አባ ጅፋር ጅማ፣
21. ሱልጣን ሞሐመድ አንፍሬ አፋር፣
22. ደጃዝማች ገብረእግዚአብሔር ሞረዳ ወለጋ ነቀምት ዙሪያ፤
23. ደጃዝማች ባልቻ ሣፎ ( አባነፍሶ) ሲዳሞ፣
24. ደጃዝማች ጆቴ ቱሉ ወለጋ ጊንቢ አካባቢ፣
25. ደጃዝማች ሞረዳ በከሬ ወለጋ፣
26. ደጃዝማች ደምሰው ነሲቡ፣
27. ደጃዝማች መሸሻ ወርቄ ዲፕሎማት፣
28. ደጃዝማች ገብረሥላሴ ባርያ ጋብር ፣
29. ሸህ ሆጄሌ አሊ ሐሰን አሶሳ፣
30. ቢትወደድ አልፈርድ ኢልግ አማካሪ የውጭ ዜጋ
ካላይ ካለው የስም ዝርዝር መገንዘብ እንደሚቻለው፤ራስ ጎበና፣ ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ፣ ፊታውራሪ ገበዩሁ ተክሌ(ጎራ) ፣ወዘተ ከሚጠቀሱት የኦሮሞ ተወላጆች ዋነኞቹ ናቸው። የአካባቢ ገዥዎች የየአካባቢው ተወላጆች ነበሩ። ወለጋ ደጃዝማች ጆቴ፣ እና ደጃዝማች ኩምሳ( ገብረእግዚአብሔር) ፣ወላይታ ካዎ ጦና፣ ወሎ ራስ ሚካኤል(ዓሊ) ጎጃም ንጉሥ ተክለሃይማኖት(አዳል ተሰማ)፣ ትግሬ ራስ መንገሻ ወዘተ ነበሩ። ወደ ቀኃሥ ስንመጣም ዋና ዋና ባለሥላጣኖቹ ከተለያዩ ነገዶ የሚወለዱ ናቸው። ለአብነት ራስ ካሣ የአገው የደጃዝማች ኃይሉ ልጅ ናቸው። ራስ ደስታ ዳምጠው በእናታቸው ጉራጌ ናቸው። ራስ አበበ አረጋይ የራስ ጎበና ዳጨ የልጅ ልጅ ናቸው። ይልማ ደሬሣ ፣ጄኔራል ሙሉጌታ ቡሊ፣ጀኔራል ታደሰ ብሩ፣ ጄኔራል ጃጋማ ኬሎ፣ደጃዝማች ደረሱ ዱኬ፣ ወዘተ ኦሮሞዎች ናቸው። እንዲህ እያልን ዘር መቁጠር ከጀመርን ዐማራው በብቸኝነት ኢትዮጵያ የገዛበት ወቅት አለመኖሩን እንረዳለን። ውሸት ተደጋግሞ ሲነገር ዕውነት መስሎ ዐማራው ቋንቋው የመንግሥት የሥራ ቋንቋ በመሆኑ ብቻ፣ እንደገዥ ተቆጥሮ ነገዱ ባላየውና ባልበላው ዕዳ ከፋይ እየሆነ ይገኛል። መረራ እንዳለውና ተመስገን ደሣለኝም እንዳጸደቀው፣ የዐማራ ልሂቃን ለዐፄዎቹ ሥርዓት መጠበቅና ለዐማራው የበላይነት የሚታገሉና የታገሉ ቢሆን፣ያን ሥርዓት ለመጣል መራር መስዋዕትነት ለመክፈል ሳንጃ ወድረው፣ ቃታ ስበው ፣በርሃውን ሜዳዬ፣ ዱሩን ቤቴ ባላሉ ነበር። ይህ መረጃ ያልቀረበበት የመረረና የከረ፣ በዐማራ ልሂቃን ላይ የተሰነዘረ በቋሚ ሰነድ ላይ የሰፈረ ትችት ፣ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊነት ሲሉ ውድ ሕይዎታቸውን የከፈሉትን የዐማራ ነገድ ልጆች አጽም ያስቆጣል። በሕይዎት ያሉትምን ያስቆጫል። ለካ ለዚህ ኖሯል የደከምነው ብለው የወጣትነት ሕይዎታቸውን ያሳለፉበትን የትግል ዘመን እንዲረግሙ ያደርጋል። ይህ ደግሞ ደግ አይደለም።
ዶ/ርመረራ ያመነጨው፣ አቶ ተመስገን ደሣለኝ ያስፋፋው ይህ በዐማራው ላይ የተሰነዘረው ያለፈ ሥርዓት ናፋቂነት፣ «የዐማራን የበላይነት መልሸ አገኛለሁ ብሎ የሚገፋው የሕልም ፖለቲካ» ሲል የደመደመው ቃል የዐማራው ልሂቃን የሌሎች ነገዶች ልሂቃን እንዴት እንደሚያዩዋቸውና እንደሚንቋቸው የሚጠቁም ነው። ዐማራው እንደ መረራና መሰሎቹ በሄዱበት መንገድ መጓዝ ኢትዮጵያዊነትን ይጎዳል፣ አብሮነትን ይሸረሽራል፣ አንድነትን ይጎዳል ከሚል ሠፊ የአመለካከት ባሕር ውስጥ ገብቶ፣ በአድሮ እንዬው ፣ነገሮች ይብላሉ ብሎ በትብዝት ብሔርተኞቹን እዬተመለከተ እንጂ፣ የበላይነቱን ከፈለገውና ሥልጣን ለመረከበ በነገዱ ዙሪያ ከተደራጀ ብሔርተኞቹ ከተጓዙበት የጊዜ ርዝመት ባጠረ የፈለገውን ማድረግ የሚያስችል ሁለንተናዊ የአቅም ባለቤት እንደሆነ ያጡታል አይባልም። ይህ ግን ሰው በሰውነቱ ዕኩል ነው፤ ሰዎች በተግባራቸው እንጂ፣ በነገዳቸው መመዘን የለበትም፣ የሕግ የበላይነት እንጂ፣ የነገድ የበላይነት መኖር የለበትም ብሎ ለሚያምነው አብዛኝው ኢትዮጵያዊ የሚፈልገው አይደለም። በመሆኑም እባካችሁ ዐማራውን ባልዋለበት ስም እየሰጣችሁ ወደ ማይፈልገውና ወደማያምንበት አቅጣጫ አትግፉት።
ርዕሴን ለማጠቃለል፣ እባካችሁ ይህን የመረራ ጉዲናን ሀሳብ የምትጋሩ ሰዎች የት? መቼ? ማን? የዐፄዎች ሥርዓትን ለመመለስና ያልነበረ የዐማራ ሥርዓት ሊመልስ የቆመ ግለሰብ ወይም ድርጅት እንዳለ ጠቁሙኝ። በልዑል ኤርሚያስ ሣህለሥላሴ የሚመራውን የዘውድ ምክር ቤት ካላችሁኝ አልስማማም። ምክንያቱም ልዑሉ እናቱ ልዕልት ማኅፀንተ ድብልቅ ያልሆነ የወለጋ ኦሮሞ ናቸው። አባታቸው ልዑል ሣህለሥላሴም ባባታቸው የኦሮሞ፣ የጉራጌ ተወላጅ ሲሁኖ፣ በእናታቸው በእቴጌ መነን አስፋውም የንጉሥ ሚካኤል የልጅ ልጅ በመሆናቸው ኦሮሞነት አለባቸው። እርሳቸው ዘውዳዊ ሥርዓትን እንደ እንግሊዝ፣ ጃፓን፣ ስዊድን በባህላዊና ታሪካዊ ፋይዳው ይኑር የሚሉ እንጂ፣ እንደአባታቸው በሁለንተናው መልኩ ፈላጭ ቆራችነት ልቀጥል የሚሉ አይመስለኝም። የእርሳቸው ፍላጎት ደግሞ የአብዛኛው የዐማራ ልሂቃን ፍላጎት ነው ማለት የሚቻል አይመስለኝም። በዚህም የዐማራው ልሂቃን የኢትዮጵያ ችግሮች ናቸው ለማለትና የችግሩ አካሎች አድርጎ መቁጠር ተገቢም፣ ትክክልም ካለመሆኑም በላይ ታላቅ ስህተትና ድፍረት ነው።
በሌላ በኩል ዕድገት ወደፊት እንጂ ፣ወደኋላ አይጓዝም። የተፈጥሮም ሕግ እንዲሁ ወደፊት እንጂ ፣ወደኋላ አይሄድም። ዛሬ ዓለም ከደረሰበት የካፒታሊስት ሥልተምርት ወደ ባሪያ አሳዳሪው ወይም ወደ ፊውዳሉ ሥልተምርት እንመልስህ ቢሉት የሚቻል ብቻ ሳይሆን ፣ለማሰብም የማይቻል ነው። ከዚህ አንጻር « አብዛኛው የዐማራ ልሂቃን በዐፄዎች ዘመን የነበረውን የበላይነት መልሸ አገኛለሁ ብሎ የሚጋፋውን የሕልም ፖለቲካ እስካልተወ ድረስ፣—-ሀገራችን ከአደጋ ቀጠናና ቀውስ የምትወጣ አይመስለኝም» ሲል መረራ ጉዲና የደረሰበት ድምዳሜ የታሪክንና የኅብረተሰብን የጉዞ አቅጣጫ ያጤነው አይመስልም። የተቃጠለን ወረቀት መልሶ ወረቀት ማድረግ የሚቻል አይሆንም። የዐፄዎች ሥርዓትም ላይመለስ ሁሉም የኢትዮጵያ ልጆች እገሌ ከገሌ ሳይባል፣ አውቀውም ሆነ ሳያውቁ በዘመቻ ንደውታል። ያ ይመለሳል ብሎ ማሰብ ራስን አለማመን ነው። በሌልም በኩል ከፍ ሲል ለመጥቀስ እንደሞከርኩት የዐማራ የበላይነት ከቋንቋው መነገር ውጭ አልነበረም ፣ ኖሮም አያውቅ። እንዲኖርም የሚታገል የለም። ካለ ይነገረን ፤እንወቀው። የሀሳቡ አፍላቂና አድናቂዎች ይኸ ይጠፋቸዋል አይባልም። ሀሳቡ እንዲሰራጭ የተፈለገው ለዐማራው ተጨማሪ መክሰሻ ወንጀል መፈለጉ ነው። ይህ ደግሞ መረራ እንዳሉት አንድነት የሚያመጣ ሳይሆን፣ ዐማራው ለካ በዚህም ዘመን እንደዚህ የሚከሱን አሉ? በሌለንበት መከሰሳችንና የኣንድነት ፀሮች መባላችን ካልቀረ በነገዳችን ዙሪያ እንሰባሰብ የሚለውን የሞረሽ ወገኔን ዐማራ ድርጅት ጥሪ የሚያስተጋባ ነው። በዚህ መልኩ ለተኛው ዐማራ መቀስቀሻ እሳት ለጫሩልን ወገኖች ጉዳዩ ከዕውነት ያልተነሳ ቢሆንም ልሂቃኑ ማንነቱን እንዲያውቅና ከነማን ጋር እንደቆመ ራሱን እንዲመረምር የሚገፋፋ ስለሆነ በሉ ከግፉ ጨምሩበት እላለሁ። መገፋት አመጽን፣ አመጽ መሰባሰብንና የሀሳብ አንድነትን ይፈጥራልና!

No comments:

Post a Comment