አርሶ አደሮች መሬታቸውን ያለካሳ እየተነጠቁ ነው
መራዊ፡- በምዕራብ ጎጃም ዞን ሜጫ ወረዳ ያለ ፈቃዳችን መሬታቸውን አሳልፈን አንሰጥም ያሉ አርሶ አደሮች እስርና ድብደባ እየደረሰባቸው መሆኑን ከአካባቢው የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡ በመራዊ አካባቢ ሜጫ ወረዳ እናሸንፋለን ቀበሌ መንግስት የከርሰ ምድር ውሃ ቁፋሮ እናካሂዳለን በሚል ከ400 በላይ የሚሆኑ አርሶ አደሮች ከመሬታቸው እንዲለቁ የተደረገውን እርምጃ አርሶ አደሮቹ በመቃወማቸው እስርና ድብደባ እየደረሰባቸው መሆኑን የነገረ ኢትዮጵያ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
በአካባቢው ከአሁን ቀደም ተመሳሳይ እርምጃዎች የተወሰዱ ሲሆን የአርሶ አደሮቹ መሬት በአበባ ኢንቨስትመንት ላይ ለተሰማሩ ባለሀብቶች ተሰጥቶባቸዋል፡፡ ይህም በአሁኑ ወቅት መንግስት ውሃ ለመቆፈር በሚል አርሶ አደሮቹ ከመሬታቸው እንዲለቁ የሚወስደው እርምጃ በተመሳሳይ ለአበባ እርሻ ሊሰጥባቸው እንደሆነ በማመናቸው ከመሬታቸው አንለቅም ብለዋል፡፡ እስካሁን ለአበባም ሆነ ለሌሎች ተግባራት መንግስት ከአርሶ አደሮቹ መሬት ሲወስድ ያለ ምንም ካሳ በመሆኑ አርሶ አደሮቹ አሁንም ቢሆን ያለ ካሳና ያለምንም ፈቃድ እየተነጠቁ በመሆኑ ተቃውሟቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ አድርጓዋል፡፡
ከአርሶ አደሮች ባሻገር በከተሞች የሚኖሩ የአርሶ አደሮቹ ቤተሰቦች ጭምርም ችግር እየደረሰባቸው መሆኑን ምንጮች ጨምረው ተናግረዋል፡፡ በተለይም ታሳሪዎቹን የሚጠይቁት የአርሶ አደሮቹ ቤተሰቦችና ሌሎች የአካባቢውና በየከተማው የሚኖሩ ግለሰቦችም ለእስር መዳረጋቸውን ለመረዳት ተችሏል፡፡ አርሶ አደሮቹ መሬታቸውን ያለ ፈቃዳቸው አሳልፈው እንደማይሰጡ በመግለጽ ጠንካራ ተቃውሞ ማንሳታቸውን ተከትሎ በአካባቢው ፖሊስና መከላከያ በብዛት መሰራጨቱን ምንጮች አክለው ገልጸዋል፡፡
በምስራቅ ወለጋ ዜጎች እየተፈናቀሉ ነው
በምስራቅ ወለጋ ስቡ ስሪ ወረዳ ‹‹ይህ አገር የእናንተ አይደለም፡፡ አገራችሁን ግቡ፡፡›› በሚል 200 ያህል አርሶ አደሮች እንደተፈናቀሉ አስታወቁ፡፡
በ1990ዓ.ም ጀምረው በአካባቢው የኖሩት እነዚህ ዜጎች ‹‹የመኖሪያ መታወቂያ ተሰጥቶን፣ውጡ ተብለን እየታሰርንና እየተባረርን እንኳ ግብር እያስከፈሉን፣ ንብረት አፍርተን አገራችሁ አይደለም ተብለን እየተፈናቀልን ነው›› ሲሉ ምሬታቸውን ለዝግጅት ክፍላችን ገልጸዋል፡፡ አርሶ አደሮቹ ከዚህ ቀደም በ1992 በተመሳሳይ ቤትና ንብረታቸው ወድሞ ተፈናቅለው የነበረ ቢሆንም መንግስት እንደገና እንዳቋቋማቸው ይገልጻሉ፡፡
‹‹በአንድ በኩል አገራችሁ አይደለም ውጡ!›› የሚሉት የአካባቢው ባለስልጣናት በሌላ በኩል ደግሞ ‹አካባቢውን ልንሰራበትና ልናሰራበት ነው ይሉናል፡፡ በ1992ም መንግስት እንደገና አቋቁሞናል፡፡ አሁንም ቦታው ከተፈለገ መንግስት ተገቢውን ካሳ ሊሰጠን ይገባል፡፡› ብለን ስንጠይቅ ደግሞ ‹እናንተን መንግስት አያውቃችሁም፡፡ ይሉናል› በሚል እየደረሰባቸው ያለውን ህገ ወጥ ተግባር ይናገራሉ፡፡
ተፈናቃዮቹ ከጥር 22 2006 ዓ.ም ‹‹ለቃችሁ ውጡ፡፡ ለቃችሁ ካልወጣችሁ ለቤትና ንብረታችሁ ብቻ ሳይሆን ለህይወታችሁም ኃላፊነት የላችሁም›› መባላቸውን ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ተደጋጋሚ እስራትና ድብደባ እንደደረሰባቸው ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡
‹‹ለቃችሁ ውጡ!›› በተባሉበት ወቅት አቤቱታ ሲያቅረቡ የነበሩ 42 ሰዎች ያለ ምንም ምግብ ለ30 ቀናት ታስረው መቆየታቸውንና በየጊዜው ፖሊስ ከፍተኛ ድብደባ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡ ከቀያችን ተፈናቅለን፣ ልጆቻችን ትምህርታቸውን አቋርጠው፣ በችግር ላይ እንገኛለን የሚሉት ተፈናቃዮቹ ‹‹ሀገርና ተቆርቋሪ የሌለን ዜጎች ሆነናል፡፡ ከ16 አመት በላይ የኖርንበትን ቀያችን ለቀን ወደ የት እንሂድ? የሚመለከታችሁ አካላት ሁሉ በተግባር እርዱን›› ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ (ምንጭ፡ ነገረ ኢትዮጵያ)
No comments:
Post a Comment