በምገኝበት አገር አብሮኝ የሚሰራ አፍሪካን-አሜሪካን ወዳጅ አፍርቻለሁ። ስለ ኢትዮጵያ አንዳንድ የታሪክ ግንዛቤዎች እንዲኖሩት ጉጉት ስላለው ደስ እያለኝ ከማውቃት አካፍለዋለሁ። አንዳንድ ጊዜ ግን የምደነግጠው እኔ ከማውቀው በላይ እየሄደ ስለ ኢትዮጵያ አዳዲስ ነገር፣ “ይቅርታ ምጥ ለእናቷ አስተማረች እንዳይሆንብኝ…” ይልና አዳዲስ ክስተቶችን ይነግረኛል። የትናንቱ ጥያቄው ደግሞ ልዩ ነበር። ይኸው ማይክል የምለው ጓደኛዬ “የኢትዮጵያ Gestapo ምን ስም አለው?” ብሎ አፋጠጠኝ። (በነገራችን ላይ ጌስታፖ ትልቁ የሂትለር የአፈናና የግድያ ተቋም ነበር። ይህ ከ 32,000 ሰራተኞች በላይ የነበሩት የስለላ ተቋምና ለአርያን ዝርያ ጠላት ናቸው የተባሉትን አይሁዶች፣ ኮሙኒስቶችና፣ የናዚ ፍልስፍና የሚቃወሙትን ሁሉ በስልት የሚያስወግድ ድርጅት በራሱ ጠንካራ ውስጣዊ መንግስት ነበር።)
በኢትዮጵያ የመለስን ራእይ ተከትሎ የተቋቋመ፣ ዳሩ ግን መቋቋሙ ብዙም ሳይወራ እንደ ጌስታፖ ያለ- ከቶም መብለጡን የማልጠራጠር- የስለላና የድምሰሳ ትልቅ ተቋም መፈጠሩን አልክድም። የአገራችንን የፖለቲካ ሁኔታ በቅርብና በጥልቅ የሚከታተለው አሜሪካዊ ግለሰብ ኢትዮጵያዊውን ጌስታፖ “አግአዚ ይባላል” አለኝ። ብዙ ንትርክ ለማንሳት አልፈለኩምና “አግአዚ” በአዲሱ ተቋም ውስጥ የሚገኝ ተወርዋሪ ሃይል- ጨካኝና ወደ አውሬነት የተጠጋ ስሜት ያላቸው ሰዎች ያሉት አካል መሆኑን ሳላወሳበት አልቀረሁም። የዚህ ታላቅ አካል ምርጥ የመሆኑ ምስጢር በጭካኔያቸውና በኢሰብአዊነታቸው ተመልምለው የገቡና ከጥቂት ስልጠና በኋላ ወደፍጹም “ባርባርነት” የተለወጡ ናቸው። ሂዱ ቀጥቅጡ። ከዛሬ ጀምሮ የምትጠቀሙበት ስልት በሞትና በህይወት መካከል የምታስቀሩበት፣ ጠላትን በሰውነቱ በሚያፍርበት ሁኔታ እንዲዋልል የምታደርጉበት ጥበብ ነው። …. ሌላም ሌላም ነው። ከወያኔ ገራፊዎች፣ መርማሪዎችና የህሊና ፖሊሶች እጅ ወጥተው ብዙ መናገር የሚያስጨንቃቸው ወገኖቻችን የሚነገር ብዙ ጉድ አለ።
በአንዳንድ የዚህ ሁሉ “ውርዴ” (መከራውን የጨለጡ) የሆኑ ግለሰቦች የሚዘከረው ሁሉ እስከወዲያኛው የሚቀፍፍና የሚዘገንን ነው።
በዚህ እድሜዬ ለእኔ ያንን በብዙ ወገኖቻችን ላይ የደረሰውን የወል ሩካቤ ( በሴቶችም፣ በወንዶችም)፣ በኤሌክትሪክ የመጠበስ፣ የጥፍሮች መነቀል፣ አባለዘር ማምከን፣ ህሊናን የመበረዝና፣ ልብን የመስለብ ምርመራ ወዘተ… ማውሳት አይመቸኝም። የናዚዎችን ኮንሰንትሬሽን ካምፖች ያየሁ፣ በሰብአዊነት በመረበሽ ለቀናት ስረበሽ የነበርሁትን ሁኔታ ሁሉ የማስተውል እድሜ ጠገብ ሰው ያ ወደ አገሬ ይመጣል ብዬ አስቤ አላውቅም።
እንዲህ አይነት ሰው በሰው ላይ በሚያደርሰው ጭንቀትና ስቃይ ነፍሴን እያሰቃየሁ በንባብም ጭምር መከታተሌን ሳስብ እኔም እንደ አንዳርጋቸው ጽጌ “ሞትን የመሰለ ጸጋ የት ይገኛል?” እላለሁ፥ እሱ አራዊት በማይደርሱበት “ክርስቶሳዊ ስሜት” እኔ ደግሞ እንዲህ ያለውን ፍጹም በሆነ የአራዊት አለም የሚፈጽመውን ህሊናዬ ላይ በተፈጠረው ቁስል! በነገራችን ላይ የ21ኛው ክ/ዘመን አውራ ጀግናችን የሆነው አንዳርጋቸው ጽጌ ለእንግሊዙ አምባሳደር ሞትን ማግኘት አለመቻሉን የገለጠበት ቋንቋ ብዙ መጽሃፍ ይወጣዋል። የሚናገረው ብዙ ታሪክ አለው። የብዙ ፊልም ትረካ የሚገባው ነው። ሁላችንም እንደተከታተልነው ደግሞ “የፕሮፓጋንዳ ጊኒፒግ” ሊያደርጉት በመፈለግ በቴሌቪዥን ባቀረቡት ቁጥር ስቃይን የሚመሰክሩ በሲቃ ከአፉ የሚወጡ ቃላት እስከወዲያኛው የሚዘነጉ አይሆኑም። በዚያ ባለግርማ ሰውነቱ ላይ የደረሰው መከራ፣ በህሊናው ላይ የተካሄደው አስጨናቂ አገላለጥ፣ በሁላችንም መንፈስ ላይ የጣለው ጠባሳ በቀላሉ የሚይታይ አይደለም። በተኩሱና በሌላ ሌላው ምክንያት አራዊት ከአገራችን እንደናው ተሰደው የሰው አራዊት መተካታቸው የሚገርም አይደለም። እነሆ የአራዊት ስራ!
በሌላ በኩል ደግሞ የአንዳርጋቸው የአንድ ጊዜ ኢንተርቪው የተባለው አስራ አንድ ቅጥልጥል ፊልም ግጥምጥም ነው። በሁሉም ቅጥልጥል ፊልም የስቃይ ድምፅ ተከስቷል። አንዳርጋቸው በአማርኛም ሆነ በእንግሊዝኛ ሲናገር ማንንም የሚማርክና የሚያፈዝዝ ሲሆን ራሱን እንዲያወግዝ፣ ጓደኞቹንና ሌሎችን ፀረ-ወያኔ የሆኑ ኢትዮጵያውያንን “ያለቦታውና ያለነገሩ” እንዲራገም ያስገደዱትን እንኳ በምን አይነት የመቃተት ስሜት እንደተናገረ አይተናል።
አይ ሰው የመሆን ጣጣ! እነዚህ ሁሉ ለፕሮፓጋንዳ የቀረቡ የአረመኔዎች ስራዎችና የኢትዮጵያ ህዝብ የወደቀበትን መከራ የሚመሰክሩ ናቸው። ለባረቀው ፕሮፓጋንዳ ደግሞ ለበረከት ስምዖን ልናጨበጭብ እንችላለን። (ሔኖክ የሺጥላ እንቅፋት አይምታውና “ሰሞኑን በፌስቡክ “በረከት ስምዖን ሞቶ አንዳርጋቸውን ሆኖ ተነሳ” የሚል ወደር የሌለው መጣጥፍ አቅርቦልናል። እንደእውነቱ ይበል የሚባልለት ቅኔ ነው። “ቅኔ” ሁሉ ቤት መምታት የለበትም!)
ለፕሮፓጋንዳ ብለው ባቀረቡት አንደኛው የአንዳርጋቸው መግለጫ በስተጀርባው የሚገረፍ ሰው ሃይለኛ ድምፅ ይሰማል። በቀድሞዋ ሶቪየት ህብረት ከፓርቲው መስመር ውጭ የሆነ አመለካከት ያለው ሁሉ “የሕዝብ ጠላት” የመባል ጣጣ ነበረበት። ይልቁንም በግልጽ በስነጽሁፍ ረገድ የምእራቡ አለም ያወቃቸው እንደ ሶልቬትሲን፣ ቦሪስ ፓስተርናክ፣ ሶርኮብ ወደ “ጉላጎች” እየተላኩ ምድራዊ አበሳ እንዲቀበሉ ይደረጋሉ። በኋላ ጊዜ አመለካከቱ ከፓርቲው መስመር ውጭ የሆን ሁሉ የህዝብ ጠላትነት ካባ ይደርቡለትና አዳዲስ በተቋቋሙ የሩሲያ የፖለቲካ ሆስፒታሎች እየተባሉ በሚጠሩ “ሳይካትሪካል ሆስፒታሎች” ውስጥ ይገባሉ። ገሃነም፣ ሲዖል የሚባሉ ስፍራዎች መግለጫና ማስረጃ ያገኙት በእነዚህና እንደ ሻህ ኦፍ ኢራን፣ ራሳቸው አያቱላህ ኮሚኒ፣ ኢዲ አሚን የፍርሃት ሪፑብሊክ ሳዳም ሁሴን፣ የደቡብ አፍሪካ ቮርስተር ባቋቋሙአቸው የአፈና፣ የጭንቀትና የምድራዊ ስቃይ መቀበያ ስፍራዎች ደህና መገለጫ አግኝተዋል። የወያኔ አገዛዝ ደግሞ ከኮሎኔል ጎሹ ቀደም ብለው በትንቢት መልክ እንደገለጡት ከፖልፖት ያንሰያሪ አገዛዝ የከፋ ነው።
ማጋነን አይደለም። ማጋነን አልወድምም። በእኔ በኩል እንዲያውም እውነቱን በጠንካራ ቋንቋና በውል ማስረጃ (እያለኝ) ለማብራራት አቅም ማጣት የሚሰማኝ ነኝ። ወይም በወያኔ እስር ቤቶች የደረሰባቸውን ሁሉ ለመግለጥ በባህላዊ ሽብር ውስጥ መግባት ነው። የኢትዮጵያውያን ይሉኝታና ጠበቅ ያለው ባህል የወያኔ ምርመራና እስራት ምን ማለት እንደሆነ ባለ”ውርዴዎቹ” በአደባባይ ወጥተው እንዳይናገሩ የህሊናቸው ተቆጣጣሪ አድርጓቸዋል። የአሜሪካው ዲፓትርመንት አንድ መግለጫ በተወሰኑ እህቶቻችን ላይ ወያኔዎች ያደረሱትን ወራዳ ተግባር ሲገልጥ በሚችል መልኩ “ማስረጃ አለን” ይላል። የዚያን አይነት ስቃይ የደረሰባቸው እህቶቻችን አደባባይ ወጥተው ያንን ባይገልጡ የሚፈረድባቸው አይመስለኝም። ይህ ደግሞ ወያኔዎች በባህላችን ላይ የሚጫወቱት አንድ ታሪክ ነውር መደበቂያ ሆኖላቸዋል።
ካለኝና ካላችሁ መረጃ በመነሳት ይህን “የፖሊስ ስቴት” የሆነ መንግስት ጨምላቃ ገመና መዘክዘክ ይቻላል። ይኽ ደግሞ በስሜትና በአጫጭር ሃተታ የሚጻፍ ሳይሆን ለትውልድ በሚቀሩ መጻህፍትና ፊልሞች ቢሆን ይመረጣል። በአጭሩ ለመግለጥ ግን በዛሬው ቀን በዚህ ሰዓትና ዘመን እነደብረጽዮንና ጌታቸው አሰፋ ከሚመሩት “ፖሊስ ስቴት” የባሰ ገሃነም በአለም ላይ ያለ አይመስለኝም። ( ወያኔዎች ገና የመንግስትነትን ስም ከመቀዳጀታቸው በፊት በትግራይ ህዝብ ላይ ሲያደሩ የኖሩትን ስቃይ ከሚገልጸው “አሞራ” ከተሰኘው መጽሃፍ አንስቶ እስከ ካፕተን ተሾመ ተንኮሉና፣ የዱባይ ወንድማችን መግለጫ ቪዲዮ ድረስ ያለውን ሁሉ ተከታትያለሁ። ኢትዮጵያ ከፖልፖቱ ካምቦዲያ፣ ከሳዳም ሁሴን ኢራቅ፣ ከ… የባሰች የጭንቀት አገር ናት። ጓደኛ የላትም። እንደተከታተላችሁት ደግሞ ውዱ ጠቅላይ ሚኒስትራችን በፕሬዚዳንት ኦባማ ጉብኝት “ገለጣ”ው ላይ እስካሁን የተፈጸመው ሁሉ በ “ዲሞክራሲ ልምምድ” መልክ ነበር። በሩብ አመት አላለቅንም። ሁለተኛው ሩብ ምዕተ-አመት እየቀጠለ ነው።
ከገሃነም ያመለጡ እህቶቻችን፣ ወንድሞቻችንና ጓደኞቻችን የደረሰባቸውን ለመግለጥ ያፍራሉ፥ ይፈራሉ። በባህላዊው ይሉኝታና ሌሎች ሌሎች ምክንያቶች ተሸብበዋል። በዚህ መካከል ድፍረቱ በድፍረት ሳይቆጠር፣ የማስተዋል ችሎታችንን በሚደፍር አገላለጥ አደባባይ ወጥቶ የሚሰድብን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ተዎድሮስ አድሃኖም ሆኗል።
ዶ/ር ቴዎድሮስ እንደሚነግረን አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን እያንሸራሸረ በኢትዮጵያ የተሰራውን የልማት ስራ ሁሉ እያስጎበኘ ነው። በናዝሬት መንገድ ላይ ያለውን ግዙፍ የልማት ስራ አስጎብኝተውታል (የትግራይ አይሻልም ነበር?)። አንዳርጋቸው ደግሞ በዚህ ሁሉ ተመስጦ ኮምፒውተር እንዲሰጠው ጠይቆ መጽሃፍ ኣየጻፈ ነው። (ስላሴ ቅኔ አይሻልም ነበር?)
ቴዲ በአሜሪካ ድምፅ ራዲዮ ላይ እንዲህ ያለ አዛባ ጥሎ ደህና እንድንነጋገርበት አስችሎናል።
በብላቴን ጌታ ህሩይ፣ በሎሬንዞ ታእታዝ፣ በ አክሊሉ ሃብተወልድ፣ በዘውዴ ገብረ-ህይወትና ዘውዴ ገብረስላሴ፣ በይልማ ደሬሳ፣ በሃዲስ አለማየሁ ወንበር ላይ የተቀመጠው ቴዎድሮስ! የእኛንም ዘመን ጎሹ ወልዴን በኩራት እንጠቅሳለን!
ወያኔዎች መንግስት በያዙ ሰሞን፣ “ማዕከላዊ” ይባል በነበረው የምርመራ ማዕከል የታወቀ ገራፊ በቴሌቪዥን አቅርበው ለፕሮፓጋንዳቸው ተጠቅመዋል። “ውቃው” እየተባለ ይጠቀስ የነበረው “ገራፊ” ሲል የነበረውን ታስታወሳላችሁ? “ለምርመራ የሚቀርቡ ሰዎችን እንዲያውም ሻይና ቡና ኣየጋበዝሁ… በወንድማዊ ስሜት …” ይል ነበር። ቴዲ የረሳው “አንዳርጋቸውን ማታ ማታ ሸራተን ሆቴል ኣየጋበዝን … ራትና ሻምፓኝ እየ…” ስንቱን … ሲናገር ኣንዲህ ያለውን … ነገር ለምን ረሳ? በነገራችን ላይ እኔና ልጄ የምናውቀው አንድ ደራሲ በመጽሃፉ ውቃውን በማሰብ፣ “ደርግ በውሃ አጥምቆአል። ኣውነተኛው በእሳት የሚያጠምቀው በጊዜ ማህፀን ውስጥ ነበር። እነሆ ወያኔ ኢህአዴግ!” የሚል ቋንቋ ተጠቅሟል። (ከትዝታ በትዝታ የጠቀስኩት ነው።)
በዚህ ዘመን ከተገኙ ጀግኖች እናንተን በማስፈቀድ “አውራ ጀግናችን” የምለው አንዳርጋቸው እዉን መጽሃፍ ጻፈ? ይጽፋል? ወይስ አያ በረከት በሩን ዘግቶ ሁለተኛውን “ የሁለት ምርጫዎች ወግ” እየጻፈ ነው? የመጀመሪያ አልባረቀም ወይ? አለዚያ ሁላችንም እንደበረከት አድናቂና ብር ሰፋሪ አረብ ሳናነብና ሳይነበብልን እንድናደንቀው ልንገደድ ነው? (የበረከትን “ታላቅና ድንቅ” መጽሃፍ ባያነብበውም ኣንዳነበበው እንዲቆጠርለት የፈለገው ማን ነበር? የታላቁን ነቢይ ስም በመጠቀሙ ሆዴን ያመኛል።)
አንዳርጋቸው ጽጌ ያለበትን ሁኔታ የምናውቅ ይመስለኛል።
– ከአመት በላይ አካላዊና ሳይኮሎጂካል ግርፋትና እንደጥፍር መነቀል፣ መድፈቅና ሌላ ሌላው ስቃይ እንደደረሰበት ገጹና አነጋገሩ በግልጽ ይመሰክራሉ።
– የጄኔቫ ኮንቬንሽንና ሌሎች አለም አቀፍና ወያኔዎች ያወጡአቸው ህግጋትና ድንጋጌዎች ከሚያዝዙትና ከሚያራምዱት ውጭ ግለሰቡን ከጠበቃ፣ ከህጋዊ አማካሪዎች፣ ከቤተሰብ … አርቀው አስረዋል። አያያዙም ኢንተርናሽናል ውንብድና ነው።
– የፖለቲካ አክቲቢስቶች ከሆኑ ዳኞች ዘንድ እንኳን ያልቀረበ በመሰረቱ የጦር ምርኮና ነው፥ እነሱ እንዳቀረቡት።
– የእንግሊዝ አምባሳደር እንደምንም ብለውና ምን አልባትም የእንግሊዝ መንግስት አጠንክሮ በማስፈራራት አንዳርጋቸውን አነጋግረውታል። ለሰውየው በሰጠው ምላሽ ሞት ለእሱ በጣም እንደራቀና የሚፈልገውና የሚመኘው “ ሞትን” መሆኑን ገልጦላቸዋል። ይህንን ነው መጻሕፍት የሚወጡት የስቃይ ድምፅ ያልሁት። ወያኔዎች ከገባቸው ዛሬውኑ በወያኔዎችና በህዝባችን መካከል ወደመጨረሻው መተላለቅ የሚያመራ በሆነ ነበር። እግዚአብሄር ይመስገን ህዝባችን አልተጣደፈም።
– ከአምባሳደሩ ጉብኝት በኋላ የወጣው መግለጫ ይህ የእነ ቴዲ መንግስት በአስቸኳይ አንዳርጋቸውን አንዲፈታና ለደረሰበት የህሊናና የአካል ስቃይ ካሳ እንዲከፈል ነው።
እኔ ብሆን እነዚህንና የመሳሰሉትን ጥያቄዎች በአደባባይ የምናውቃቸውን ጉዳዮች አነሳበት ነበር። ቴዎድሮስ አድሃኖምን በመሰረቱ ኣንዲያደግ የሚሻ የዋህ ማይም ይመስላል። ይሁንና አደባባይ ይዞ የሚወጣው ነገር ሁሉ እድገቱን የሚቀጭ ነው። ከቶዉንም ይኽ የሚጠቀስበትን ለሃኪሞች የሚገባ ስያሜ ከየት እንዳመጣ እጠይቃለሁ። አበበ ገላውን።
አንዲት ተናጋሪ ወፍ እንዲህ ያለ ወግ አላት። የእንግሊዙ ኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ የፍልስፍና ፕሮፌሰር ለተማሪያቸው አንድ ጥያቄ አቅርበውለት መልሱን ይጠብቃሉ። ፕሮፌሰሩ ለፒኤችዲ ዲግሪው የመጨረሻ ፈተና ከተቀመጠው ወጣት ብዙ የምርምር ውጤቶችንና ረቂቅ የፍልስፍና ትንተና ይጠብቃሉ። እርግጥ መልስ ተሰጥቶአልና በየገጹ ቀያይ መስመሮች አጋድመዋል። እዚህም እዚያም። ተማሪው ይሞግታቸዋል። “ውሸት ነው፣ ትክክል መልስ አልሰጠህም ነው የሚሉኝ ሲል” ወዳጄ የጻፍኸውንም ሁሉ አንብቤአለሁ። ይሁን ኣንጂ “ውሸት ነው የጻፍከው። ዋሾ ነህ” የሚል ክብር ልሰጥህ አልችልም። አሉ የሚል አሳብ ከአንድ የኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ መጽሄት አንብቤአለሁ። ታዲያ ይፈቀድልኝና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትራችንን “ውሸት ተናግረዋል። ቀጣፊ ነዎ! አወናባጅና ዋጋ የማያወጣ ነገር ይዘው ገበያም ሆነወደ አደባባይ አይወጡ” ማለት ይቻላል። ደስ የሚለው የኦክስፎርዱ ፕሮፌሰር መግለጫ ነው “ዋሾ የሚል ክብር አልሰጥህም” ከዚያ በታች ምን አለ? ቢንጎ!
No comments:
Post a Comment