ዳንኤል ተፈራ
ትናንት አንድ ቀጠሮ ይዘን ነበር….. አዎ!... ይሄው በቀጠሯችን መሰረት ከች፤ የመብራቱ መኖርና ‹‹የኢንተርኔት ኮኔክሽን›› መከሰት ታክሎበት በትናንትናው ዕለት ከዶ/ር ነጋሶ ጋር ስለነበረኝ ቆይታና ትዝታ ጥቂት ለማለት በቃሁ፡፡
ዶ/ር ነጋሶ የሚኖሩት ብስራተ ገብርኤል አካባቢ በመንግስት ቤት ነው፡፡ ያውም ፖለቲካው ላይ ሲያከሩ ቂመኛው ህወሃት/ኢህአዴግ ‹‹ልቀቁ!›› እያለ እያንገራገራቸው ነዋ! ለአዛውንቱ ፕሬዘዳንት ግርማ በየወሩ 400 ሺ ብር ሆጭ እያደረገ የሚያቀማጥለው ገዥ ፓርቲ ለዶ/ር ነጋሶ ዞሮ መግቢያ ጎጆ ሊከለክላቸው ይፈልጋል፡፡ የመለስ/ኃይለማሪያም አገዛዝ በስልጣን ዘመናቸው የነበራቸውን መኪና ነጥቆ በእግራቸው ከህዝብ ጋር እየተጋፉ ሲሄዱ እየተመለከተ መሳቅ ያምረዋል - ጥርስ የለውም እንጅ፡፡ ነገርግን ዶ/ር ነጋሶ ከህዝብ ጋር በመሆናቸው ከበሩ እንጅ እንደጠበቁት አልተዋረዱም፡፡
ቁሳዊውን ዓለም ያሸነፉት ዶ/ር ነጋሶ አሁን ብዙ ግዜያቸውን የሚያሳልፉት ከግርጌ ካለው ፎቶ በስተጀርባ በምትመለከቷት ቢሮ ውስጥ ነው፡፡ እንደነገሩኝ ከሆነ እዚችው ቢሮ ሲያነቡና ሲፅፉ ይውላሉ፡፡ እዚች ቢሮ ገብቼ አውቃለሁ፡፡ ፓ! መረጃ አያያዝ፤ ኢህአፓ የበተነቻት የመጀመሪያዋ ወረቀት ሳትቀር አለች፡፡ ያ እሳት የላሰ ትውልድ ከመሳሪያ በተጨማሪ ሲራኮትባቸው የነበሩት ታገል፣ ታጠቅና ሌሎች መፅሔቶችም በክብር ተቀምጠዋል፡፡ በአጠቃላይ ቤታቸው የተደራጀ የታሪክ ላይበራሪ በሉት፡፡
የነጋሶ መንገድ የተቀዳው እዚህ ፀጥታ በረበበት ቤት ነው፡፡ ለቃለ መጠይቅ ብቻ ለሦስት ወር ከትሜ ነበር፡፡ የማስታወስ ችሎታቸው ድንቅ ነው፤ በልጅነታቸው ደምቢዶሎ ከቤታቸው ፊት ለፊት የነበረችውን ዛፍ ቁመትና ስፋት ሳይቀር ያስታውሳሉ፡፡ ከኦህዴድ/ኢህአዴግ ጋር ከተፋቱ በኋላ ቂም ተይዞባቸው ለረጅም ዓመት ጣሪያው በሚያፈስ ቤት ኖረዋል፡፡
በ2003 ዓ.ም በልግ ወቅት አንድ ቀን የቤታቸው ሳሎን ቁጭ ብለን ለማነሳላቸው ጥያቄ መልስ እየሰጡኝ እያለ ሰማዩ አጉረምርሞ እንባውን አረገፈው፡፡ ተንደርድረው በስተግራ በኩል ወዳለው ሰፊ ክፍል ሮጡ፤ አብሬያቸው ተንደረደርኩ፤ እንደወንፊት የተቦዳደሰው ጣሪያ ዝናቡን መመከት አቅቶት ያንዠቀዥቀው ይዟል፡፡ የሚበላሹ ዕቃዎችን ለማሸሽ ሞከርን፤ ወዲያው ፊታቸው ላይ አንጀት የሚያኮማትር ሀዘን ረበበ፤ ዓይኖቻቸው እንባ አቀረሩ፤ ፕሬዘዳንቱ ሲያለቅሱ ላለማየት ሰበብ ፈልጌ ወደ ውጭ ወጣሁ፡፡ ከደቂቃዎች በኋላ መሃረባቸውን ከኪሳቸው አውጥተው ዓይኖቻቸውን እያበሱ ወደ ሌላ በስተቀኝ በኩል ወደሚገኝ ክፍል ይዘውኝ ገቡ፡፡ ትላልቅ የብረት ቁምሳጥኖች ተገጥግጠዋል፡፡ ‹‹አየህ!...›› አሉ ሀዘን እንደ ሜትሪዮሎጅ አውሮፕላን በዙሪያቸው እየተሸከረከረ ‹‹አየህ…. እነዚህ ሁሉ የብረት ሳንዱቆች ታሪካዊ ሰነዶችንና ዶክመንቶችን የያዙ ናቸው፡፡ ዝናብ እንዳያበላሽብኝ ቆልፌባቸው ነው - ያሳዝኙኛል ግን ምንም ማድረግ አልችልም…..›› ያሉኝ ትዝ ይለኛል፡፡
ትናንት ስሄድ ግን ለቤቱ መጠነኛ እድሳት ስለተደረገለት ቢያንስ አያፈስም፡፡ ዶክተሩ ከማንኛውም የፓርቲ ፖለቲካ ራሳቸውን ስላገለሉ መረጋጋት ይታይባቸዋል፡፡ የጥናትና ምርምር ስራዎችን ሲሰሩ እንደሚውሉ ቢሯዋቸው ጠረፔዛ ላይ የተዝረከረኩ ሰነድና መፅሐፍቶች ያሳብቃሉ፡፡ ነብይ በሀገሩ ባይከበርም ምናልባት እንድ ቀን እንጠቀምበት ይሆናል፡፡
ከዶ/ር ነጋሶ ጋር በደንብ የተግባባነው አንድነት ፓርቲን ከተቀላቀሉ በኋላ ነው፡፡ በ2002 ምርጫ ወቅት ወደ አርባ ምንጭና ደቡብ ኦሞ ለቅስቀሳ ሲሄዱ አብሬያቸው ሄጄ ነበር፡፡ መንገዱ ረጅምና አሰልቺ ቢሆንም ዶ/ር ነጋሶ የሚነግሩን የህወሃትና ኦነግ ታሪክ ድካማችንን አሽቀንጥሮት ነበር፡፡ አስታውሳለሁ የዶ/ር ነጋሶን ታሪክ የመፃፍ ውጥን ያሳደርኩት በዚህች ቀን ነበር፡፡ ከኃይለማሪያም ሀገር ወላይታ ሶዶ እስከ አርባ ምንጭ ባለው የምሽት ጉዟችን ሁለት ጥያቄ አነሳሁላቸው፡፡
አንደኛው ስለ አወዛጋቢው ጋዜጠኛ ወ ፖለቲከኛ ተስፋየ ገብረአብ ነበር፡፡ ‹‹ተስፋየ ገብረአብ በኦሮሞ ጉዳይ ላይ የሚያነሳቸውን ሀሳቦች እንዴት ይመለከቷቸዋል…..›› የሚል ያልተደራጀ ጥያቄ ሰነዘርኩላቸው፡፡ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ሶለን እንደዚህ ብለው ጀመሩ፡- ‹‹ተስፋየ ከኦሮሞ በላይ ኦሮሞ ልሁን ይላል፡፡ ተስፋየ ብቻ ሳይሆን አንድ ጀርመናዊም ነበረ (እኔ ነኝ ስሙን የረሳሁት እንጅ ነግረውን ነበር) ከኦሮሞ በላይ ኦሮሞ ልሁን የሚል፡፡ የእኔ አውቅልሃለሁ ስሜት የተጠናወታቸው……..፤ አየህ ተስፋየ ገብረአብ……›› እያሉ ቀጠሉ፡፡ በጥቅሉ አሁን ተስፋየ ገብረአብ ያለበትን አቋም ያኔ ተረኩልን፡፡ ባለ ውብ ብዕሩና ‹ተንኮለኛው ደራሲ› ተስፋየ ገብረአብም የነጋሶን ‹‹በማይመለከትህ ጥልቅ አትበል!›› አስተያየት ሰምቶ በስደተኛው ማስታወሻው ይመስለኛል መልስ ለመስጠት ሞክሯል፡፡ '
ሁለተኛው ጥያቄየ፡- ‹‹መለስ ዜናዊን ሲያውቁት ምን አይነት ሰው ነው…›› የሚል ነበር፡፡ ‹‹መለስ ጎበዝም ሴረኛም ነው፡፡ ጠላት ብሎ ያሰበውን ሳያስወግድ እንቅልፍ የማይተኛ፡፡…… በስብሰባ እረፍት ጊዜ በተከታታይ እያጨሰ ስብሰባው ውስጥ ምን ማድረግ እንዳለበት አሰላስሎ የሚገባ፤ ግን ደግሞ ጎበዝ አንባቢ…….›› እያሉ ቀጠሉ፡፡ በአጠቃላይ ሁለቱን ጥያቄዎች እያብራሩ አርባ ምንጭ ገባን፡፡ በዚህ ሁናቴም ዳንዲ- የነጋሶ መንገድ ተጸንሶ ተወለደ፡፡
ዶ/ር ነጋሶ አንድነት በጋሜ በመቅረቱ አዝነዋል፡፡ ብዙ የደከሙበት ድርጅት ነበር፡፡ በተለይ በወጣቶች የተቀነቀነው የለውጥ ፈላጊነት እንቅስቃሴ ጥርስ ውስጥ እንደከተተው ነግረውኛል፡፡ በሳምንት ሁለት ቀን ጋዜጣ ማተም፤ የማተሚያ ማሽን መግዛት፤ ህዝባዊ ንቅናቄ ይፋ ማድረግ…. ለኢህአዴግ ምን ማለት እንደሆነ ግልፅ ነው፡፡ ቢሆንም አንድ ድርጅት የታለመለትን ዓላማ የማያሳካ ከሆነ መኖሩ ካለመኖር እኩል ነው፡፡ የነጋሶ ስንብት የአንድነት የመውደቂያው መጀመሪያ ይላል ሀገር የተቀማው ትውልድ…….. ‹‹እንግዲህ ወገኖቼ›› የምትለውን ቃል ልዋስና ልሰናበት፡፡ ቀጣዩን ቴሌና መብራት ሃይል ፈቅደው ለፌስቡክ አይነስጋ ከበቃን እንቀጥለዋለን፡፡
ረጅም ዕድሜ ከጤና ጋር ለተከበሩት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ሶለን በመመኘት
No comments:
Post a Comment