ይገረም አለሙ
ከአንድ ሳምንት ወሬ የማይዘለው የሞላ አስግዶም ኩብለላ ብዙ ነገሮችን አያሳየን ነው፡፡ ወያኔ የሞላ ኩብለላ የሱ የሥራ ውጤት እንደሆነ አሳያለሁ ብሎ “ በቅሎ ሽንቷን አጠራ ብላ ሀፍረቷን አሳየች” የሚባለውን አይነት ድርጊት ፈጸመ፡፡ ለነገሩ ወያኔ መቼ ሀፍረት ያውቅና፡፡ አቶ ሞላም የተሰጠው ስልጠና የአጭር ግዜ ሆኖበት ሽክ ብሎ የቀረበበትን ጋዜጣዊ መግለጫ የወያኔና የራሱ መጋለጫ አደረገው፡፡ የወያኔ የመረጃ ስራ በጉልበት አንጂ በእውቀት እንዳልሆነ የምናውቀውንም ይበልጥ አረጋገጠልን፡፡
የቱንም ያህል ቢጩኹ፤የቻሉትን ያህልም ውሸት ቢደራርቱ እውነትን ማሸነፍ እንደማይቻል ወያኔዎች ብዙ ግዜ ሞከራው ከሽፎባቸው ያዩት ቢሆንም አንዴውኑ ከእውነት ጋር ተጣልተዋልና የህይወት መሰሶአቸውም ውሸት ሆኖአልና ከውሸት ሊላቀቁ አልቻሉም፡፡ ዛሬም እየዋሹ ብዙሀኑን ኢትዮጵያዊ በግድ ሊግትቱ ይዳዳቸዋል፡፡ ጥቂት አይናቸውን ለጆሮአቸው ያስገዙ ሰዎቻቸው ደግሞ እንዴት ብሎ መጠየቅ ለምን ብሎ ማመዛዘን የለም ብቻ ውሸቱን እየተቀበሉ ከበሮ ይደልቃሉ፡፡እውነቱ ሲጋለጥም ሌላ ውሸት ይፈበርካሉ እንጂ ለእውነት እጅ አይሰጡም፡፡