እኔ ግን እላለሁ: የትግራይ ህዝብ የህዝብ ጠላት የለውም። ከድሮ ጀምሮ የትግራይ ህዝብ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወገኖቹ ጋር በሰላምና በአንድነት የኖረ ህዝብ ነው። አሁንም አብሮ ይኖራል።
የትግራይ ህዝብ ጠላት ካለ እሱ ጨቋኝ ስርዓት ብቻ ነው። የህዝብ ጠላት ህዝብ አይደለም። የህዝብ ጠላት ስርዓት ነው። ማንኛውም ህዝብ ለጨቋኝ ስርዓት መምበርከክ የለበትም። ለዚህም ነው ፀረ ጨቋኝ ስርዓት የምንታገለው፤ ፀረ ህዝብ የሆነ ስርዓት ለማስወገድ። ዓላማችን ፀረ ህዝብ (የህዝብ ጠላት) የሆነ ጨቋኝ ስርዓት ለማስመለስ ሳይሆን ለማስወገድ ነው።
የኛ ዓላማ የኢትዮጵያውያን ህዝቦች አንድነትና ሕብረት ለመጠበቅ ጥረት ማድረግ ነው። የኢትዮጵያውያን አንድነት ለመጠበቅ የመከፋፈልና የጥላቻ ፖለቲካ ማስወገድ አለብን። የጥላቻ ፖለቲካ ለማስወገድ ህዝቦች በጠላትነት አንፈርጅም። ሁሉም ሰው ወዳጅ ነው፤ እኩል ነው።
የህዝቦች ነፃነትና ልአላዊነት የሚረጋገጠው በህዝቦች አንድነት ነው። በህዝቦች አንድነት የህዝብ ጠላቶች (ጨቋኝ ስርዓቶች) ማስወገድ ይቻላል። ፍላጎታችን ህዝቦች በአንድነት፣ በመከባበርና በመተሳሰብ የሚኖሩባት ኢትዮጵያ እውን ማድረግ ነው።
ስለዚህ የትግራይ ህዝብ (እንደ ማንኛውም ሌላ ህዝብ) ከኢትዮጵያ አንድነት ተጠቃሚ እንጂ ተጎጂ አይሆንም። አንድ ህዝብ ወይ ብሄር ከሀገራዊ አንድነት ተጎጂ ከሆነ ገዢው ስርዓት ፍትሐዊ አይደለም ማለት ነው። ስርዓቱ በህዝቦች እኩልነት የማያምን ከሆነ ብቻ ነው ተጎጂ የሕብረተሰብ ክፍል ሊኖር የሚችለው። አድሎኣዊ ስርዓት ካለ ደግሞ ማስወገድ ይኖርብናል። ስለዚህ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባት ከቻልን ከኢትዮጵያዊ አንድነታችን ተጠቃሚ እንጂ ተጎጂ አንሆንም።
ስለዚህ ህወሓት “ጠላቶችና ወዳጆች” እያለ ህዝቦች ከመከፋፈል እንዲቆጠብ እመክራለሁ። የትግራይ ተወላጆችም የህወሓት የጥላቻ ፖለቲካ ወደጎን በመተው ኢትዮጵያዊ አብሮኖታችንን እንደምናስቀጥል አልጠራጠርም።
የትግራይ ህዝብ ከህወሓት በኋላም እንደሚኖር ማሰብ አለብን። ከህወሓት በኋላ ሌላ የተሻለ ስርዓት እንደምንገነባ ማሰብ አለብን።
It is so!!!
No comments:
Post a Comment