Sunday, December 22, 2013

የህወሓት/ኢህአዴግን ሌላ ዙር የብሔራዊ ሉዓላዊነት ክህደት እናውግዝ!

የድንበር ጉዳይ መፈታት ያለበት ግልፅነትና ተጠያቂነት ባለበት፣ የኢትዮጵያ ሕዝብና በተለይም በጉዳዩ ከዚህ በፊት ጥናት ያካሄዱ ምሁራን ሙሉ ተሳትፎ ባለበትና፣ የኢትዮጵያን ህጋዊ ታሪካዊና ብሔራዊ ጥቅም በሚያስጠብቅና አንድነቷንና ሉዓላዊነቷን በሚያስከብር መልክ መሆን እንዳለበት  ግልፅ ሀሳብ ነው።
ህውሃቶች ጥፋታቸውን በመቀጠል ከኢትዮጵያ ሕዝብ በስተጀርባ በምስጢር ከሱዳን መንግሥት ጋር ውል በመፈራረም፤ ርዝመቱ 1,600 ኪ.ሜ ስፋቱ ከ30 እስከ 50 ኪ.ሜ የሚደርሰውን በምዕራብ ኢትዮጵያ ድንበር የሚገኝ ለም መሬት ሱዳን በትግል ወቅት ለሰጣቸው ድጋፍ እንደ ገፀ-በረከት ለማቅረብ ተስማሙ።

እዚህ ላይ ይህንን ብሔራዊ ወንጀል ልዩ የሚያደርገው ይህ ምስጢራዊ ውል ከኢትዮጵያ ሕዝብ ዕውቅና ውጪ መፈፀሙና፤ ለመጀመሪያ ጊዜም ኢትዮጵያውያን ስለ ስምምነቱ ያወቁት ከሱዳን ጋዜጦችና ዜና ማሰራጫዎች መሆኑም ጭምር ነው። ምንም እንኳን ህውሃት ለብዙ ጊዜ ይህንን ስምምነት ማድረጉን ሲያስተባብል ቢቆይም ስምምነቱን ተከትሎ የሱዳን ሠራዊት ይገባኛል የሚለውን የተወሰኑ የኢትዮጵያን መንደሮች በመውረር፤ ቤቶችን በማቃጠል ኗሪዎችን በማጥቃትና አንዳንዶቹንም አግቶ ወደ ሱዳን በመውሰድ ያደረገው ጥቃት ጉዳዩን የበለጠ ይፋ እንዲወጣ አድርጎታል።
ህወሃት/ኢህአዴግ ከሕዝብ ጀርባ የሚያደርገው ሽፍጥና ደባ የተመላበት ስምምነት የህዝብ አወንታን ያላገኘ የአገሪቷን ሉዓላዊነት የሚያስደፍር ወንጀልና ክህደት በመሆኑ እያወገዝን፤ በድብቅ የሚደረገው ስምምነትና የድንበር ማካለል ስራ ላካባቢው ችግር ዘላቂ መፍትሄ የሚሰጥ ሳይሆን ማለቂያ የሌለው ውጥረትና ግጭት እንዲቀጥል አስተዋፅዖ የሚያደርግ አርቆ ማስተዋል የጎደለው ተግባር እንደሆነ ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንዲገነዘበው ያስፈልጋል።

አንዳንዶች ከህወሃት/ኢህአዴግ ታሪካዊ አመጣጥ በመነሳት ይህን ያሁኑን ድርጊቱን የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የማስደፈር አጀንዳው ቀጣይና አንዱ አካል አድርገው በመቁጠር ብዙም የሚያስገርም ሆኖ ባያገኙትም፤ ይህንን የመሰለውን ይቅር ሊባል የማይችል አፄ ዮሐንስ ሕይወታቸውን የሰዉበትና አፄ ቴዎድሮስ ደማቸውን ያፈሰሱለት የኢትዮጵያ አካል በፀረ-ኢትዮጵያ ኃይሎች እንደ ቀልድ አሳልፎ ሲሽጥ ትውልድ ይቅር ሊለው የማይገባ ብሔራዊ ወንጀልና ክህደት በመሆኑ በጥብቅ ሊወገዝ ይገባዋል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ  ይህንን የአገርና የግዛት አንድነትን የሚያህል ትልቅ ጉዳይ ከሕዝብ ዕውቅና ውጪ አሳልፎ ለመስጠት የሚደረገውን የመጨረሻ ሰዓት መሯሯጥና በጥብቅ ማውገዝ ያስፈልጋል። 
ከዚህ በፊት በነበሩት የኢትዮጵያ መንግሥታት ተቀባይነት ባላገኘ ውል የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም አሳልፎ የሚሰጥ የድንበር ማካለል ስምምነት በምንም መልኩ በሕዝባችንም ሆነ በቀጣይ መንግሥታት ተቀባይነት እንደማይኖረው  በጥብቅ ህውሃትን መንገር ያስፈልጋል።
ለአገሩ ቀናዒ የሆነ ማንኛውም ግለሰብም ሆነ ተደራጅቶ የሚገኝ ኢትዮጵያዊ ይሄንን ቀጣይ የሕወኃት/ኢህአዴግ ፀረ-ኢትዮጵያ ክሀደት በፅኑ እንዲያወግዝ፤ አጥብቆም እንዲቃወምና እንዲታገል  በጥሞና ማሳሰብ ያስፈልጋል።
የኢትዮጵያን ህጋዊ ታሪካዊና ብሄራዊ አንድነት እንዲሁም ጥቅም ማስጠባቅ የሁሉም ዜጋ ታሪካዊ ግዴታ ስለሆነ አባቶቻችንና እናቶቻችን እንዳደረጉት ዛሬም ሁሉም ኢትዮጵያውያን ልዩነቶቻችንን ወደ ጎን ትተን ይህ ታላቅ ሴራ እንዲከሽፍ በነጠላም ይሁን በቡድን በሚቻለው መንገድ ሁሉ የተጠናከረ ትግል እንድናደርግ  ።
የኢትዮጵያ አንድነትና ሉዓላዊነት በቋራጥ ልጆቿ ትግል ይከበራል!
ከሰብኣዊ

No comments:

Post a Comment