ከመልካም ብሥራት
ማርም ሲበዛ ይመራል ይላሉ አበው፡፡ ውሸታችሁ፤አስመሳይነታችሁ፤ ወሰን ያጣው በቀለኝነታችሁ፤ አቅመቢስነታችሁ፤ ዘረኝነታችሁ፤ ሙሰኝነታችሁ….ኧረ ስንቱ የናንተ ነገር ተዘርዝሮ ያልቃል? በዛ፤ መረረንም፡፡ መንግስት ህዝብን ወክሎ የአንድን ሀገር ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ የሚመራ ተቋም ሆኖ በእንቅስቃሴዎቹ ሁሉ ታሳቢና ተቀዳሚ የሚያደርገው የህዝብን ተጠቃሚነትና የሀገርን ልማት፤ እድገት፤ ብልፅግናና ሉዓላዊነት ነው፡፡
በዚህች መናኛ መለኪያ ስትለኩ የናንተ ቦታ የት ነው? ህዝብን የልማት ተጠቃሚ እያደረጋችሁት ነው? የትኛውን ህዝብ? ሀገሪቱን አለማችኋት? የግብርናው፤ የኢንዱስትሪው፤ የአገልግሎቱ ዘርፍ በናንተ የአገዛዝ ዘመን የት ደረሰ? ስራ አጥነቱ፤ መሰረተ ልማቱ የት ናቸው? የተፈጥሮ ሐብቶች ምን ላይ ናቸው? የዜጎች የፖለቲካ ተሳትፎ፤ መልካም አስተዳደሩ፤ ሰብኣዊና ፖለቲካዊ መብቶች እስከ ምን ድረስ ተከበሩ?
እናንተ መንበረ ስልጣኑን ከአምሳያችሁ ደርግ በጠመንጃ ነጥቃችሁ ከያዛችሁበት ጊዜ ጀምሮ በህዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን ግፍና መከራ በናንተ የመጣ ሳይሆን ህዝቡ ራሱ በራሱ ላይ ያመጣው እያደረጋችሁ በህዝብ ሰቆቃና ችግር እየቀለዳችሁና እያሾፋችሁ በሞቱና ውርደቱ እየተዝናናችሁ እስከአሁን አላችሁ፤፤ በጣም የሚገርመውና የሚያንገበግበው በቅርቡ በራሳችሁ ሸር የተነሳውን የሳውዲ አረቢያ ቀውስ ሲመቻችሁ ኮረጆ በመገልበጥ አልሆን ሲል በጠመንጃ ለምታጭበረብሩት ምርጫ ተብዬ ቁማራችሁ የምርጫ ፖለቲካ ስትጠቀሙበት እጅጉን ገረማችሁኝ::
ይህንን ዓይን ያወጣ አረመኔ አመለካከታችሁን አምርሬ ጠላሁት፤ መቼም በምንም ሁኔታ ለሀገርና ለህዝብ የማትጠቅሙ ከንቱዎች እነደሆናችሁና ከስህተቶቻችሁ ለመማር ያልተዘጋጃችሁ አድሮ ጥጆች፤ ጥፋትን በልማት ከመመለስ ይልቅ ለጥፋቶቻችሁ ሽፋን ሌሎች ጥፋቶችን ከመስራት የማትቆጠቡ ሞራለ ቢሶች ሆናችሁ አገኘኋችሁ፡፡ ከዚህ በኋላ ከእናንተ መልካም ነገር የሚጠብቅ የዋህ ማን ነው? ከእባብ የርግብ እቁላል መጠበቅ አይቀልምን?
ከእናንተ አዕምሮና ከሬዲዮና ቴሌቪዥናችሁ ከንቱ ልፈፋ ያላለፈው የኢኮኖሚ ፖሊሲያችሁ እድገትን እያቀጨጨ፤ ስራ አጥነትን እየፈለፈለ፤ የኑሮ ውድነትን ጣራ እያስነካ፤ ሰላምን አያናጋ፤ አንድነትንና አብሮ መኖርን እያፈረሰና መሰረቱን እየናደ፤ በምትኩ ጥላቻን፤በቀልን፤አለመተማመንን እያነገሰ ለመጭው ትውልድ ስቃይና መከራን ልታወርሱት ቀን ከሌት እየዳከራችሁ መሆናችሁን ከቶ መቼ ይሆን ልብ ልትሉት የምትችሉት? የስኬቶቻችሁ መገለጫዎችና ውርሶቻችሁስ ዘረኝነት፤ አለመተማመን፤ ጥላቻ፤ በቀል፤ድህነት፤ሞራለቢስነት መሆናቸውን ለመረዳት ማን እስኪነግራችሁ ነው የምትጠብቁት?
እግርና እጅ የሌለውና የተጨማለቀው፤ ለኢትዮጵያ የማይመጥነው፤ ከእንቅልፋችሁ በባነናችሁ ቁጥር የምትለዋውጡት የተደበላለቀ የነፃ ገበያ የኢኮኖሚ ፖሊሲያችሁ፤በየትኛውም የዓለም ክፍል የሌለ የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ማደናገሪያችሁ፤ የህዝብን ተጠቃሚነት ሊያረጋግጥ ባልቻለና ይልቅስ ውስንና ሰንካላ፤ የጥቂት ቡድን አባላትን፤ ሌቦች ባለስልጣናትን፤ የስርዓቱ ታማኝ ጀሌዎችን ተጠቃሚነት የሚያሳይ ልማት ተብዬ የሀብት ቅርምታችሁ ከእናንተ አልፎ ለህዝብ ጠብ የሚል ነገር ስላላመጣ ውጤት አልባው ከንቱ ጥረታችሁ ጠብ ሲል ስደፍን እንዲሉ ውሃ በወንፊት መቋጠር እንደሆነባችሁና ውል የሌለው ክር መሆናችሁን ለመረዳት የሚያስፈልጋችሁ የጊዜ ርዝመት ምን ያህል ነው?
የአስተዳደራችሁ ድምር ውጤት በሆኑት ስራ አጥነት፤ ስደት፤ ርሀብ፤ እስር፤ እንግልት፤ ውርደት፤ አለመተማመን ወዘተ ምክንያት በሁሉም የዓለም ማዕዘናት በሚኖሩ ስደተኞች ላይ ለሚደርሰው የኢትዮጵያውያን መከራ ተጠያቂው ከእናንተ ውጭ ማን ሊሆን ይችላል ብላችሁ ታስባላችሁ? አስተዳደራችሁስ የበጀውና እሰየው ያስባለው የትኛውን የህብረተሰብ ክፍል ነው? ሙስሊሙን? ክርሰቲያኑን? አማራውን? ትግሬውን? ኦሮሞውን? ሲዳማውን? ጉራጌውን? ሃድያዉን? አኙዋኩን? ሶማሌውን? አፋሩን? ወጣቱን? አዛውንቱን? ሴቶችን? ወታደሩን? ገበሬውን? ሙሁሩን? የትኛውን የህብረተሰብ ክፍል ነው የበጃችሁት? ጥቃት ያላደረሳችሁበት ማን ይሆን? የበግ ለምዳችሁ ባለፉት ሃያ ሁለት ዓመታት ተቀዳዶ እርቃናችሁን ስለቀራችሁ ለምዳችሁ ኣያታልለንም፡፡ተጨማሪ በደል እንድትፈፅሙ እድልም አንሰጣችሁምና ለለውጡ ከመተባበር ያለፈ ተስፋ እንደሌላችሁ እወቁት ልላችሁ እፈልጋለሁ፡፡ በሴራዎቻችሁ እና በወጥመዶቻችሁ ያተረፍነው መከራና ስቃይን ብቻ መሆኑን ከተረዳን ውለን አደርን፡፡ ተስፋ ቁረጡ፡፡ መዝሙራችን ሠላም፤ ፍቅር፤ አንድነት፤ ህብረት፤ ብልፅግና ሁኗል፡፡
ቸር ይግጠመን
ቸር ይግጠመን
zehabesha
No comments:
Post a Comment