Saturday, December 14, 2013

ኢህአዴግ እና የማንዴላ ፓርቲ (ANC) በምን ተገናኙ?

ኢህአዴግ ይቅር የተባባለው ከአና ጐሜዝ ጋር ብቻ ነው!
የብሄር ብሄረሰቦች ቀን “የፍቅር ቀን” መስሎኝ?

እኔ የምላችሁ … በጅግጅጋ የተከበረው ስምንተኛው የብሄር ብሄረሰቦች ቀን እንደጉድ ደምቆ ተከበረም አይደል (ያውም የግመል ወተት በቧንቧ እየተቀዳ!) ለካስ እውነተኛው “እንግዳ ተቀባይነት” ያለው የሶማሊያ ህዝብ ጋ ነው፡፡ ምንም እንኳን በአካል ቦታው ላይ ተገኝቼ በዓሉን ለመታደም ባልታደልም ሁሉንም መረጃ ከኢቴቪና ጅግጅጋ ከሄዱ ባልደረቦቼ አግኝቼአለሁ፡፡ “አጃኢብ ነው መስተንግዶ!” ተብሏል፡፡

 
በርካታ ከመሃል አገር የሄዱ የበዓሉ ታዳሚዎችም የሶማሊያውያንን ጢም ብሎ የተትረፈረፈ ፍቅርና እንግዳ አክባሪነት እንደጉድ መስክረዋል፡፡ አንዷ ከአዋሳ የሄደች የበዓሉ ታዳሚ ስትናገር፤ “ከርቀቱ አንፃር መንገዱ ሊያደክመን ይገባ ነበር፤ ግን ፍቅራቸው አላደከመንም” ብላለች፡፡ እናላችሁ … ከዚህ ቀደም ከተከበሩት “የብሔር ብሔረሶች ቀን” ሁሉ የዘንድሮው “ሳይታሰብ” ደምቋል፤ ፈክቷል… እያልኳችሁ ነው፡፡ ትንሽ ያልተመቸኝ ግን ምን መሰላችሁ? ለፍቅርና እርስ በርስ ለመተዋወቅ፣ ለመከባበርና ለመቻቻል የታሰበው በዓል፤ ለመወቃቀሻና ለመወነጃጀያ መዋሉ ነው። እኔ የምለው … እንዲህ የሚመስለውን ውይይት በጂግጂጋ ያዘጋጀችው የኢቴቪ ጋዜጠኛ ሙያውን ተወችው እንዴ? (ካድሬ ነዋ የምትመስለው!)
ከምሬ ነው … የድሮ ቁርሾ ማንሳት ፋይዳው ምንድነው? (የብሄር ብሄረሰቦች ቀን የፍቅር ቀን መስሎኝ?!) እስቲ አስቡት … የደጋ ሰው ሶማሌዎችን “ሽርጣም ሶማሊያ ይል ነበር፤ ሶማሌዎች ደግሞ “ህፃን ልጅ ሲያለቅስ አበሻ እንዳልጠራብህ እያሉ ያስፈራሩ ነበር፡፡” ወዘተ…የሚሉ አሉታዊ አስተያየቶች ምን ይሰራሉ? ደሞ እኮ ሁሉም በደልና ጭቆና የተፈፀመው ዛሬ ሳይሆን በንጉሱና በደርጉ ዘመን ወይም ከዚያ በፊት ነው፡፡ እናላችሁ … ይሄን ቁርሾ መቆስቆስ ትውልዱን ለማፋቀር ነው ወይስ ለማቃቃር? በኢቴቪ አስተያየት የሰጠች አንዲት የበዓሉ ታዳሚ ምን አለች መሰላችሁ? “ትላንት ጥሩ ያልሆነ ነገር ነበር፤ እሱ ትላንት ተሰርቶም ተወርቶም አልፏል!” (ማን ነበር “የምንለውን ብለናል፤ አሁን ወደ ተግባር” ያለው?) ሰው እንዴት የዛሬ ነፃነቱን በትላንት ጭቆና ላይ ያከብራል? (ያውም በቁጭት ተሞልቶ!) እውነታውን ለመሸሽ ብዬ እንዳይመስላችሁ! በቀደሙት መንግስታት ተፈፀሙ የተባሉትን የበደል ታሪኮች ለመካድም አይደለም፡፡ እንዲህ ያሉ የአገራችን የቆዩ በደሎች ግን ትክክለኛ ቦታቸው የታሪክ መፃሕፍት ውስጥ ይመስለኛል፡፡ (የፈለገ እዚያ ያያቸዋል!) እንዴ … አሁን እኮ Live እየቀረበ ነው፡፡ “አውጫጭኝ” ሁሉ ይመስላል!! ችግሩ ግን በዳይና ተበዳይ በሌሉበት ሆነ! እንዴ … ሌላ የተሻለ በጐ ታሪክ የለንም እንዴ? (በ“አዲሲቱ ኢትዮጵያ” አሮጌ ልብ ይዘን አንዘልቅም?)
እኔማ ምን አሰብኩ መሰላችሁ? የብሄር ብሄረሰቦች ቀን “ይቅር የምንባባልበት ቀን” እንዲሆን! በእርግጥ የአሁኑ ትውልድ የፈፀመው በደል የለም። ላለፉት ትውልዶች ነው ይቅር የምንባባለው፡፡ (“የአባት ኃጢያት ለልጅ ይተርፋል” አሉ!) እናም ይቅር ብለንና ተባብለን ስናበቃ … በፍቅር የተሟሸች አዲሲቱን ኢትዮጵያ ወደ መገንባቱ ብንገባ ሸጋ ይመስለኛል፡፡ (የሚሰማኝ ሲኖር አይደል!) 
በብሄር ብሄረሰቦች ቀን ያለፈውን በደልና ጭቆና ማራገብ ለመረጠው አውራው ፓርቲ የማሳስበው ጉዳይ አለኝ፡፡ ምን መሰላችሁ? የብሄር ብሄረሰቦች መብት ተከብሯል በሚባልበት በአሁኑ ወቅት በየክልሉ “ማንነታችን ተጨፈለቀ”፤ “በቋንቋችን የመጠቀም መብታችንን ተነጠቅን” የሚሉ የተለያዩ ብሄሮች አሉና ብልሃትና ጥበብ የተመላበት መፍትሔ መስጠት ይገባል፡፡ (የትላንቱን ስንተርክ፣ ዛሬያችን ትላንት እንዳይሆን እኮ ነው!)
እውነቴን ነው የምላችሁ…ቢያንስ ለልጆቻችን የቁርሾ ታሪክ እንዳናስረክብ መጠንቀቅ ይገባናል። ያለዚያ ግን አዲሱ ትውልድ ይታዘበናል (እኛ የ60ዎቹን ትውልድ እንደታዘብነው!) እኔ የምለው ግን … መቼ ነው የጦቢያ የ60ዎቹ ፖለቲከኞች ይቅር ተባብለው የሚተቃቀፉት? (እርስ በእርሳቸው የተፋጁት ለጦቢያ መስሎኝ!) እንዴ … የተኮራረፈ ትውልድ በዛ እኮ!  ከምሬ ነው … እዚህ ጉዳይ ላይ “ቸክለን” ካልሰራን ለመጪው ትውልድ የሚያኮራ ታሪክ አናስረክብም፡፡ ኢህአዴግም ቢሆን እንደ መንገዱ ልማት፣ እንደ ህዳሴው ግድብ ግንባታ፣ እንደ ባቡሩ ዝርጋታ … ለእርቅና ለአገራዊ መግባባት መትጋት አለበት፡፡ (ያማረ ታሪክ ትቶ ማለፍ ከፈለገ!) እሱ ራሱ እኮ በ20 ምናምን ዓመት የስልጣን ታሪኩ ይቅር የተባባለው ከአና ጐሜዝ ጋር ብቻ ነው (የምር ከሆነ ማለቴ ነው!)
የነፃነት ታጋዩ ኔልሰን ማንዴላ ህልፈት ዓለምን “የቀወጠው” እኮ … ያሰሯቸውን ሰዎች ይቅር ብለው መቻቻልና አገራዊ መግባባት ስለፈጠሩ ነው -በፍቅር!! እርግጥ ነው ቀንደኛ ኮሙኒስት ለነበረው አውራው ፓርቲያችን (ያውም የአልባኒያ) ፍቅር … እርቅ… አገራዊ መግባባት … ወዘተ… ላይጥሙት ይችላሉ፡፡ (ትግል ነዋ የለመድነው!) ድህነትን ለማጥፋት ትግል! አገሪቱን ለማበልፀግ ትግል! የሃይማኖት መቻቻል ለማምጣት ትግል! ምሩቃን ወደ ኮብል ስቶን ስራ እንዲገቡ ትግል! … (ከ“ትግል” ወደ “ፍቅር” መግባት እኮ ፈታኝ ነው!) 
እኔ የምላችሁ … በማንዴላ ህልፈት (ያውም በ95 ዓመታቸው አርፈው!) ማን ያላዘነ፣ ማን ባንዲራውን ዝቅ አድርጐ ያላውለበለበ፣ ማን ለቀብር ደቡብ አፍሪካ ያልገባ አለ? ቀብር ሳይሆን የዓለም መሪዎች ስብሰባ እኮ ነው የመሰለው! (የሊቢያው ጋዳፊም እኩል ሞቱ ይባላል?) “አሟሟቴን አሳምረው” የሚባለው ለካ ያለ ነገር አይደለም፡፡ (“የስልጣን አወራረዴን እንዳወጣጤ አሳምረው” ቢባልም ያስኬዳል!) የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ፤ በማንዴላ የቀብር ሥነስርዓት ላይ ንግግር ሲያደርጉ፤ “ከአሁን በኋላ የማንዴላ ዓይነት ሰው አይፈጠርም” በማለት ዓለምን ሁላ ተስፋ አስቆርጠዋል፡፡ (ግን እኮ እውነት ነው!) የማንዴላ ህልፈት በተሰማ በነጋታው፣ የጦቢያም መንግስት የሀዘን መግለጫ  በኢቴቪ አስተላልፎ ነበር፡፡ ከሁሉም የማረከኝና ያስደመመኝ ግን የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ያወጣው የሃዘን መግለጫ ነበር፡፡ በተዋበ ቋንቋ አምሮና ተከሽኖ የተጠናቀረው የጽ/ቤቱ የሃዘን መልዕክት፤ የደቡብ አፍሪካን ህዝብ “አይዞአችሁ! የታላቅ መሪ ሞት እንዴት መሪር እንደሆነም እኛም ቀምሰነዋል” በማለት እንዲፅናኑ ምኞቱን የሚገልፅ ሲሆን ኢህአዴግና የማንዴላ ፓርቲ ANC ያላቸውን የዓላማ አንድነትም በቀጥታ ሳይሆን በዘወርዋራ ለመጠቆም ይሞክራል፡፡ ኢህአዴግን ከ“አፍሪካን ናሽናል ኮንግረስ”፣ የቀድሞውን ጠ/ሚኒስትር ከማንዴላ፣ የኢትዮጵያን ህዝብ ደግሞ ከደቡብ አፍሪካው አቻ ጋር ለማስቀመጥ ፅ/ቤቱ እንዴት እንደለፋ መግለጫው በደንብ ይጠቁማል፡፡ ግን ንፅፅሩ ወይም ምስስሉ ለምን አስፈለገ? (ኩሩ ህዝብ እኮ ነን!)  በነገራችሁ ላይ … የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤትና የኢህአዴግ ጽ/ቤት ሳይቀላቀሉ አልቀረም። (የሀዘን  መግለጫው ኢህአዴግ ኢህአዴግ ሲሸተኝስ!) ግን እኮ … ኢህአዴግና መንግስት አብረው ቢያዝኑና ለቅሶ ቢደርሱ ኃጢያት የለውም (ኧረ ፅድቅ ነው!) ኢህአዴግና የማንዴላው ፓርቲ ANC በነፃነት ታጋይነታቸው ሊመሳሰሉ ይችላሉ። ከቂም በቀል ይልቅ እርቅ፣ ይቅር መባባልና መቻቻልን መፍጠር … በሚለው ረገድ ግን ሆድና ጀርባ ናቸው፡፡ “የለም… አንድ ናቸው” ብሎ የሚሟገት ካለ፣ ኢህአዴግ ላይ ፈተና ሊያበዛበት የፈለገ ሰው ነው ማለት ነው፡፡ (ኢህአዴግ ከፍቅር ይልቅ ትግል ብሏላ!) ከሁሉም የሚገርመው ምን መሰላችሁ? ኢህአዴግም ተቃዋሚዎችም ማንዴላን አድናቂና አወዳሽ መሆናቸው ነው፡፡ ከማንዴላ የመቻቻል፣ የመግባባትና እርቅ የመፍጠር ተምሳሌታዊ መርሆዎች ግን አንዱንም አይተገብሩም፡፡ (መሆን ሌላ፤ መመኘት ሌላ!)  

ከኤልያስ
አዲስ አድማስ

No comments:

Post a Comment