Monday, December 2, 2013

ሰልፍ ብቻ በቂ ነው ወይ? አንድ መላ እንበል….ተርበዋል፣ ተጠምተዋል..እንድረስላቸው በግሩም ተ/ሀይማኖት

saudi-2-225x300
በሳዑዲ ለተከሰተው ሁኔታ..ለወገን ድምጽ ለማሰማት ይህ ሁሉ ኢትዮጵያዊ በየሀገሩ የሚያደርገውን ሰላማዊ ሰልፍ ሳይ ልቤ ቅቤ ጥጥት ያደርግና ሳይበቃው አንድ ሀሳብ ውስጤ ስውጥ ብሎ ይጦልማል፡፡ እንደገና ብልጭ ይልና ምላሽ ፍለጋ ያንከራትተኛል፡፡ ‹‹..እያደረግን ያለነው በቂ ነው ወይ? ድብደባውም ይቁም የሞቱትም ይታወሱ…በህይወት ያሉትስ ምን ሁኔታ ላይ ነው ያሉት? በተለያየ ቦታ ታጉረው ምግብ እጦት፣ ውሀ ጥም..ሌላም ሌላም ችግር አለባቸው፡፡ ሀገር ሲገቡም ማረፊያ ቦታ የሌላቸው ሞልተዋል…ይህን ሳስብ ምን ብናደርግ ይሻለናል?›› የሚለው ጥያቄ በጉልህ ውስጤ ተጽፎ ምላሽ ይናፍቃል፡፡
አምጬ አምጬ..ውስጤ ሲላወስ ቆይቶ መፍትሄ ፍለጋ ከማውቃቸው ጋር ሁሉ ስወያይ ቆይቼ አንድ ስለሺ የተባለ ወዳጄ ከወደ ሀገረ እንግሊዝ ሀሎ ብሎ አማካረኝ፡፡ ውስጤ ያሰበውን ስለነገረኝ ወይም ምን ማድርግ እንዳለብኝ እያሰብኩ የነበረውን አወጋሁት፡፡
የምናደርገው እንቅስቃሴ ብቻ በቂ አይደለም፡፡ በእርግጥ በታሪካችን ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ ህብረት አሳይተናል፡፡ ለነገሩ ኢትዮጵያዊያን ስንነካ እንደ ንብ ግር ብለን ህብረታችንን እናሳያለን፡፡ ግን ይህ ብቻ በቂ ነው ወይ? የገቢ ማሰባሰቢያ ማድረግ እና በማጎሪያ ቦታ ያሉትን ምግብ የምናቃምስበት ሁኔታ ቢፈጠር ጥሩ ነው፡፡ ሀገር የገቡትስ ቢሆን ነገ ጎዳና አናያቸውም ብሎ ማሰብ ሞኝነት ይመስለኛል፡፡ ከሳዑዲ ከመጡት ውስጥ የተወሰኑትን ለማናገር ሞክሬ ነበር፡፡ 12 እና 13 አመት ሳዑዲ ሲኖር እናት አባቱ ሞተው ቤቱን ቀበሌ የተረከበበት ሁኔታ ያጋጠመው ልጅ እንዳለ..መግቢያ የሌለው በፊትም ቤተሰብ አጥቶ በባህር የወጣ አለ፡፡ ዛሬ የት ነው የሚገባው አግብቶ ወልዶ ያለም አለ ዛሬ የት ነው የሚመለሰው ቤተሰብ ላይ…ሁሉም ምላሽ የሌላቸው አሳሳቢ ነገሮች ናቸው፡፡
ገቢ አሰባስበን አንድ ነገር ማደድረግ እንዳለብን ይሰማኛል፡፡ እናንተ ምን ትላላችሁ? በውጭ ያሉ አርቲስቶችም ቢሆን የገቢ ማሰባሰብ ዝግጅት ቢያደርጉ በጣም በደስታ ብዙዎች እንደሚሳተፉ አምናለህ ወገን ለወገኑ የቻለውን ለማድረግ ወደ ኋላ አይልም የሚያሰባስበው ማጣት ይመስለኛል፡፡ እባካችሁ አንድ መላ እንበል….ተርበዋል፣ ተጠምተዋል..እንድረስላቸው

No comments:

Post a Comment