ህወሓት/ኢህአዴግ አሁንም እንደገና በሀገሪቱ ምርጫ ሂደት ብቻውን ሮጦ ብቻውን ለማሸነፍ እንዲችል አስከፊ አፈናውንና እመቃውን አጠናክሮ ቀጥሏል። ተፎካካሪ የሆኑ የፖለቲካ ድርጅቶችን ከፖለቲካው በተለይም ከምርጫው ሂደት ተገፍትረው እንዲወጡ ለማድረግ ሳይታክት እየሰራ ነው። በሰሞኑም በአንድነት፣ በመኢአድና በሰማያዊ ፓርቲ ላይ የምርጫ ቦርድ ተብየውን በመጠቀም የሚደረገው ማዋከብ ህወሓት/ኢህአዴግ በምርጫው ሂደት ውስጥ ብቻውን ከራሱ ጋር እንዲቀር ለማድረግ የሚያደርገው ጥረት አንድ ክፍል መሆኑ የማይታበል ነው። በመሆኑም የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ ( ሸንጎ) ይህ የወያኔ/ ኢህአዴግ ቀኝ እጅ የምርጫ ቦርድ ተብየ እየወሰደ ያለውን አይን ያወጣ የአድሎ እርምጃ በጥብቅ ያወግዛል።
የኢትዮጵያ ህዝብ ልዖላዊነቱ ተከብሮ የራሱን መሪዎች በየነጻና ፍትሃዊ ምርጫ እንዲመርጥ የሚታገሉ ዜጎችን በስልጣን ላይ ያለው አምባገነን መንግስት በተለያየ የሀሰት ክስ በመወንጀል እስርቤት እያጎረ ነው። ሙሉ በሙሉ ወደ አንድ ፓርቲ አገዛዝ እያዘገመ ያለው ይህ ስርአት፣ የሀገሪቱን ተቋማትና ንብረት ወደ አንድ ፓርቲ ፍጹም አገልጋይነት እያዞረና የዜጎች መብት ከወረቀት የማያልፍ እንዲሆን እያደረገ ነው። ለህገ ማንግስቱ ብቻ ታማኝ መሆን የሚገባቸው የፍትህ አካላት የገዢው ፓርቲ የመጨቆኛና የማፈኛ መሳርያዎች ሆነዋል። ፍርድ ቤቶች የሚሰጡት የፖለቲካ ውሳኔ ሆኖል። በህገመንግስቱ የሰፈሩትን የዜጎች መብት ለህወሓት/ኢህአዴግ ብቻ የሚያገለግሉ ፣ ለዜጎች የማይገቡ ተደረገው እንዲታዩ በዚህም ተመስርተው ዜጎች ለአሰቃቂ በደል እንዲጋለጡ ሆነዋል። በወገንተኛነቱ ከሚታወቀው የምርጫ ኮሚሺን ተብየውም ፍትሃዊነት መጠበቅ የማይታሰብ ሆኗል። የሀገራችን ሁኔታ በዚህ ላይ እያለ ነው ለምርጫ 2007 ቀጠሮ የተያዘው።
ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ዋና መገለጫ ነው። ለነጻና ፍትሃዊ ምርጫ እውን መሆን የሚደረግ ትግልም ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት የሚደረግ ትግል ነው። ትግሉም የሁሉም ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ትግል እንጂ የአንድ ወይንም የሁለት ፓርቲዎች ትግል አይደለም። ትግሉ የጋራ ትግል ነው። ስለሆነም ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲም ይሁን ዜጋ ለዚህ ስርዓት ምስረታ በጋራ ለመታገል ቁርጠኝነት ሊኖረው ይገባል። የኢትዮጵያ ህዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ ለነጻና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ምስረታ በጋራ ለመታገል ሁሉም ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች በአንድ እንዲቆሙ ያላሰለሰ ጥረት ሲያደርግ እንደቆየው ሁሉ አሁንም ለዚሁ ትብብር የሚያቀርበው ጥሪ እንደገና ያስተጋባል ። ህዝቡም የትግሉን ገፈት በመቅመስ በግንባር ቀደምትነት እየሰሩ ያሉ ፓርቲዎች በነጠላ የጥቃት ሰለባ መሆኖቸውን ትተው ጊዜ ሳያጠፉ ኃይላቸውን አስተባብረው በአንድ ላይ እንዲቆሙ ግፊት እንዲያደርግና በመታተባበር ለሚታገሉትም የበለጠ ድጋፉን እንዲሰጥ ጥሪ እናደርጋለን።
ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ እውን የሚሆነው በጋራ ስንነሳ ነው!
የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ (ሸንጎ)
No comments:
Post a Comment