Monday, February 16, 2015

ዘንድሮ ምርጫ ያለ አይመስልም፣ አዲስ አበባም እንቅልፍ ላይ ናት -በላይ ማናዬ

አዲስ አበባ ከዛሬ ነገ ትነቃለች ተብላ ብትጠበቅም እንቅልፍ ውስጥ ናት፡፡ ጭልጥ ብላ ተኝታለች፡፡ 10 ዓመት ሙሉ እንቅልፍ ያልሰለቻት ከተማ ብትኖር አዲስ አበባ ናት፡፡ የዛሬ 10 ዓመት በዚህ ወቅት ከተማዋ የምር ንቁ ሆና ነበር፡፡ እድሜ ለቅንጅትና ለህብረት እንጂ ያኔ በዚህ ወቅት ላይ አዲስ አበባ በየዕለቱ አዲስ ክስተትን ታስተናግድ ነበር፡፡ ያኔ ሸገር እንቅልፍ አልነበራትም፤ የፖለቲካ ግለት ውስጥ ነበረች፡፡ አሁን ላይ ያቺ ግለታም ከተማ እንቅልፍ ላይ ነች፡፡ ምርጫ እንደሁ የአንድ ቀን ክንውን ነው፡፡ ዳሩ ግን የምርጫ ጣዕሙ ሂደቱ ነው፡፡ ሂደት ያለው ምርጫ ከተማን ቀርቶ ገጠርን አያስተኛም፤ ግለታም ነው፡፡ ሂደት ያለው ምርጫ ልክ እንደ 1997 ዓ.ም ምርጫ ወቅት ሀገርን ያነቃቃል፤ ድብርትን ይገፍፋል፡፡ በተለይማ እንደ አዲስ አበባ ያሉ ከተሞች ሂደት ባለው ምርጫ እንቅልፍ አይኖራቸውም፡፡ ዘንድሮ ግን ምርጫ ያለ አይመስልም፡፡ ምርጫ አለ ከተባለም ሂደት የሌለው ምርጫ ነው ማለት ነው፡፡
ለዚህም ነው አዲስ አበባ ያልነቃችው፡፡ ለዚህም ነው አዲስ አበባ ሙቀት አልባ የሆነችው፡፡ ለስሙ ዘንድሮ ምርጫ አለ ተብለናል፡፡ ምርጫ አለ ከተባላችሁ ሌላ ምን ፈለጋችሁ ይመስላል ነገሩ፤ ምክንያቱም ሂደቱን እያየነው አይደለምና ነው፡፡ የምርጫ ጣዕሙ ሂደቱ ሳይሆን ውጤቱ ነው ሊሉን የተዘጋጁ ይመስላል፡፡ ለቅጥፈታቸው ሀፍረት የላቸውም፡፡ እነሱ ደፋሮች ናቸው! “It is enough that the people know there was an election. The people who cast the vote decide nothing. The people who count the votes decide everything” እንዳለው Joseph Stalin ነገሩን ሁሉ ለእኛ ተውት፣ እናንተ ምርጫ አለ ካልናችሁ ይበቃችኋል ማለታቸው ነው፡፡ እናም አዲስ አበባ ብትነቃም ባትነቃም ለውጥ ያለው አይመስልም፡፡ ሲጀመር አዲስ አበባን አባብሎም ሆነ አስፈራርቶ የማስተኛቱ ስራ ከ97 ምርጫ ማግስት በደንብ የተጠናከረ ጉዳይ ነው፡፡ አዲስ አበባ የሚያስተኛት እንጂ ቀስቃሽ አጥታለች፡፡ በግላቸው የሚውተረተሩ ቀስቃሾቿም አሁን በየእስር ቤቱ ታጉረዋል፡፡ በፓርቲ ደረጃ አለን የሚሉትም መሬት ላይ ወርደው ከህዝብ ጋር መገናኘት አልቻሉም፡፡ መሬት ላይ ላለመውረዳቸው ደግሞ ሁለት ምክንያቶች አሉ፤ አንደኛው አዲስ አበባ ቀስቃሽ እንዳታገኝ ነቅቶ የሚሰራው ገዥው አካል ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ አዲስ አበባን ለመቀስቀስ ሚና ይኖራቸዋል የሚባሉት ፓርቲዎች የራሳቸው የውስጥ ድክመት ነው፡፡ አዲስ አበባ ፍዝዝ ቅዝዝ ስትል ሀገሪቱ በሙሉ ፍዝ ትሆናለች፡፡ አዲስ አበባ ስትነቃ ደግሞ ሀገሪቱ ትንቀሳቀሳለች፡፡ ምክንያቱም አዲስ አበባ የኢትዮጵያ የግለት መለኪያ ማዕከል ናት፡፡ ስለሆነም ሀገሪቱን ለማንቀሳቀስ አዲስ አበባን ከእንቅልፏ መቀስቀስ ግድ የሚል ይሆናል፡፡ በግሌ ዘንድሮ አዲስ አበባ ትነቃቃለች የሚል ተስፋ ነበረኝ፤ (አጉል የምርጫ ተስፈኛ ነበርኩ ማለት ነው)፡፡ በእስካሁኑ ሁኔታዋ ግን አዲስ አበባ እንቅልፏ ጭልጥ ያለ ሆኗል፡፡ እንዲያውም ከተማዋ ምርጫ መኖሩን ሁሉ ያወቀች አይመስለኝም፤ አልያም ደግሞ ምርጫው ምርጫ እንደማይሆን ቀድሞ ገብቷታል ማለት ነው፡፡ በእርግጥም ሂደት አልባ ምርጫ ከማላገጫነት አይዘልም፡፡ የዘንድሮው ምርጫ አካል ሆኖ ታህሳስ 12 ቀን 2007 ዓ.ም የተደረገው የምርጫ ታዛቢዎች ምርጫ ምን ይመስል እንደነበር ማስታወስ ይቻላል፡፡ በዕለቱ የህዝብ የምርጫ ታዛቢ ተብለው የተመረጡ ሰዎች የገዥው ፓርቲ አባላትና በተለያዩ አደረጃጀቶች ውስጥ ለስርዓቱ አገልጋይ የሆኑ ግለሰቦች መሆናቸውን የተቃዋሚ ፓርቲዎች ተወካዮች በአካል ተገኝተው በሰበሰቡት መረጃ አመልክተዋል፤ በታዛቢዎች ምርጫ የነበረውን ችግር ፓርቲዎቹ በመግለጫም አውግዘዋል፡፡ ይህም ሂደት አልባው ምርጫ እየመጣ እንደነበር አንዱ አመላካች ደወል ነበር ማለት ይቻላል፡፡ አዲስ አበባም ይህን ከማየት መተኛትን መረጠች፡፡ አዲስ አበባ እውነት አላት፡፡ ታዛቢ የሌለው ምርጫ ውጤቱ ቀድሞ የሚታወቅ ነው፡፡ በዚህ በታዛቢዎች ምርጫ ቅሬታ ያደረባት አዲስ አበባ ሌላም ተጨማሪ ቅሬታን ማስተናገድ ግድ ሆነባት፡፡ አዎ የ97ቱን ግለቷን የታዘበላት፣ ታዝቦም እውነቱን የመሰከረላት የአውሮፓ ህብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን የዘንድሮውን ምርጫ እንደማይታዘብ ሰማች፡፡ ለመሆኑ የአውሮፓ ህብረት ምርጫውን አልታዘብም ሲል ምን ማለቱ ይሆን? የመድረክ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ ዶ/ር መረራ ጉዲና የአውሮፓ ህብረት ከታዛቢነት ራሱን ማግለሉ በመድረክ ወደ ምርጫ መግባት እና አለመግባት ላይ ተጽዕኖ እንደሚኖረው በመግለጽ ህብረቱ አልታዘብም ሲል መልዕክት አለው ይላሉ፡፡ ‹‹እነሱ አንታዘብም ሲሉ ዝም ብለው አይደለም፡፡ በጨዋታው ተስፋ ቆርጠው ይሆናል፡፡ ህብረቱ እኛንም ሲጠይቅ እየዞረም ሲያጠና ነበር፡፡ እናም ዝም ብሎ መጣላት እንጂ ሌላ ምንም አይነት ትርጉም የሌለው ስለሆነ ይሆናል›› ይላሉ የፖለቲካል ሳይንስ ምሁሩ ዶ/ር መረራ፡፡ አዲስ አበባም የእንቅልፏ መብዛት በምርጫው ተስፋ ከማጣት ይሆናል፡፡ ምርጫ አለ መባሉ በራሱ በቂ ነው የሚል የሚመስለው መንግስት (ኢህአዴግ) ደግሞ እናንተ ከአውሮፓ ህብረት ምን አላችሁ ምርጫውን እኮ የአፍሪካ ህብረት ይታዘበዋል ይላል፡፡ መረራ ግን ይህ አይዋጥላቸውም፡፡ የምን የአፍሪካ ህብረት ታዛቢ ነው ባይ ናቸው፡፡ ‹‹የአፍሪካ ህብረት ታዛቢዎች እከክልኝ ልከክልህ የሚባለው ነገር ነው፡፡ በአብዛኞቹ የአፍሪካ ሀገራት ነጻ ምርጫ እየተካሄ እንዳለ እሙን ነው፡፡ ስለዚህ የአፍሪካ ህብረት ታዛቢ ቡድን ምርጫ ለመታዘብ መሄድ ማለት መዝናኛ እንደመሄድ ማለት ነው-ለእነሱ›› በማለት የአፍሪካ ህብረት ምርጫን ለመታዘብ ሞራሉ እንደሌለው ይናገራሉ፡፡ ይህንንም አዲስ አበባ የተስማማችበት ጉዳይ ለመሆኑ በድብርቷ አሳይታለች፡፡ የአፍሪካ ህብረት ስለምርጫ መታዘብ ማውራት ማለት ፌዝ ነው ያለች ትመስላለች፡፡ የሰማያዊ ፓርቲ የውጭ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሰለሞን ተሰማ ይህንን የሚያጠናክር አስተያየት አላቸው፣ ‹‹የአፍሪካ ህብረት ምርጫውን ይታዘበዋል ማለት ፌዝ ነው፡፡ የአፍሪካ ህብረት የትም ቦታ ታዝቦ ትክክለኛ ውሳኔ ሲሰጥ አይተንም አናውቅም፡፡ እኛም አንጠብቅም፡፡›› እንግዲህ በዚህ ሁኔታ ውስጥ አዲስ አበባ ባትተኛ ነው የሚገርመው፡፡ ኢትዮጵያ ለምርጫ ጆሮ ዳባ ልበስ ባትል ነው የሚያስደንቀው፡፡ ሂደት የሌለው ምርጫ ድብታም ነው፡፡ አዲስ አበባ ከእንቅልፌ ይቀሰቅሱኛል ብላ ተስፋ የምታደርጋቸው ፓርቲዎች በሴራ ተጠልፈው አይሆኑ ሆነዋል፡፡ አሉ የሚባሉትም ቢሆን በእስካሁኑ እርምጃቸው የ10 ዓመት ድብትን ማስለቀቅና ከተማዋን ማነቃቃት አልቻሉም፡፡ አዲስ አበባን ከማንም ቀድመው ይቀሰቅሷታል ተብለው ይጠበቁ የነበሩት ሚዲያዎች እንኳን የተኛን ለመቀስቀስ እድል ሊያገኙ ይቅርና ራሳቸውም እንዲያሸልቡ ከመደረግ አልተረፉም፡፡ ታዲያ እነአጅሬው ያለ ነጻ ሚዲያ ምርጫ አለ ይሉናል፤ ያለ ሲቪክ ማህበራት ምርጫ አለ ይሉናል፡፡ ያለ ገለልተኛ ታዛቢ ምርጫውን እናደርጋለን ይሉናል፡፡ አዲስ አበባን እንኳ ከእንቅልፏ ባልቀሰቀሰ ሂደት አልባ ምርጫ ‹ህዝቡ በነቂስ ወጥቶ…በዚህ ወጥቶ በዚህ ገብቶ…› እያሉ ይደሰኩሩብናል፡፡ ዲስኩራቸው ግን ከንቱ ነው፡፡ የዲስኩራቸው ከንቱነት ማሳያ ደግሞ ማዕከላችን አዲስ አበባ ናት፡፡ አዲስ አበባ ዘንድሮ ምርጫ የለም ብላ አርምማለች፡፡ አሁን ላይ አዲስ አበባ የምትነቃቃው በሂደት አልባው ምርጫ አይመስለኝም፡፡ አዲስ አበባ ከእንቅልፏ የምትነቃው ወደ ምርጫ ሊወስድ ከሚችል ቅድመ-ምርጫ የህዝብ ንቅናቄና ቁልፍ የፖለቲካ ውሳኔዎች ነው፡፡ አለበለዚያ ግን በዚህ ሁኔታ ምርጫን ማድረግ ትርፉ ከድሆች የተሰበሰበን ገንዘብ ማባከን ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ምርጫ ማድረግ በእያንዳንዱ ዜጋ ስም በእርዳታ የተገኘን ሀብት ማባከን ነው፡፡ ከምርጫው በፊት የማነቃቂያ እርምጃዎች ያስፈልጋሉ፡፡ የምር አዲስ አበባን ከእንቅልፏ ለማንቃት አብይ የፖለቲካ ውሳኔዎችን ማሳለፍ የሚጠይቅ ይመስለኛል፡፡ በግፍ የታሰሩ የህሊና እስረኞችን መፍታት፣ የነጻው ፕሬስ እንዲያንሰራራ ማድረግ፣ ለተቃዋሚ ፓርቲዎች በነጻነት የመንቀሳቀስ ነጻነትን ማክበር፣ የተቋማትን ገለልተኝነት ማረጋገጥ እና ሌሎችንም ውሳኔዎች ከምርጫ በፊት መወሰን በሀገር ደረጃ የተጣባንን የፖለቲካ ድብት ለማራገፍ ወሳኝነት ያለው ይሆናል፡፡ (በቀረው ሶሰት ወር ስንቱ ተደርጎ ይደርስ ይሆን? ) የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ቢሆን ለዚህ አይነቱ እርምጃ መንግስት ላይ በጋራ ጫና ማሳደር የሚኖርባቸው ጊዜ ላይ ናቸው፡፡ አልያ ግን ምርጫ ነበር ከመባል ውጭ በምርጫው የተለየ ውጤትን መጠበቅ ቂልነት ከመሆን አይዘልቅም፡፡ አዲስ አበባም ከድብቷ አትላቀቅም፡፡ - See more at: http://www.zehabesha.com/amharic/archives/39007#sthash.pWR1SaoH.dpuf

No comments:

Post a Comment