Friday, February 6, 2015

በአማራና ትግራይ ድንበር የተነሳውን ውዝግብ ለመፍታት የተጠራው ስብሰባ ተበተነ

ጥር ፳፰(ሃያ ስምንት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በአማራና በትግራይ ክልል ድንበሮች አካባቢ የተነሳውን ችግር ለመፍታት ከፌደራል መንግስት ፣ ከትግራይና ከአማራ ክልል የተውጣጡ ከፍተኛ ባለስልጣኖች ጥር 26 ቀን 2007 ዓም ከሁለቱም ክልሎች የተውጣጡ 300 ነዋሪዎችን ሰብስበው ያነጋገሩ ቢሆንም፣ መግባባት ሳይቻል በመቅረቱ ለየካቲት 4 በድጋሜ መቀጠሩን የአካባቢው ምንጮች ገልጸዋል።የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስትር ሽፈራው ተክለማርያም፣ የአማራ ክልል ፕ/ት ገዱ አንዳርጋቸው፣ የትግራይ ክልል ፕ/ት አባይ ወልዱ፣ ቴዎድሮስ ሃጎስ፣ የሰሜን ምእራብ እዝ አዛዥ ሌ/ጄ ብርሃኑ ጁላ፣ የመከላከያ ዘመቻ ሃላፊ ሜ/ጄኔራል ገብረእግዚአብሄር መብራቱ እና ሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣኖች በስብሰባው ላይ ተገኝተዋል።
በመጀመሪያው ቀን ስምምነት ባለመደረሱ በማግስቱ ከሁለቱም ክልሎች የተውጣጡ 30 ነዋሪዎች ከባለስልጣናቱ ጋር ተሰብስበው የነበረ ቢሆንም፣ አሁንም ሳይሳሙ በመቅረታቸው ለየካቲት አራት ቀጠሮ ይዘው ተለያይተዋል። በአማራ ክልል በኩል የሚኖሩ ነዋሪዎች የትግራይና የአማራ ክልሎች ድንበር ተከዜ ሆኖ እያለ ፣ ክልሉ ከዚህ ቀደም በጉልበት ከተከዜ በመሻገር ሁመራ እና ዳንሻ የመሳሰሉ ቦታዎችን መቆጣጠሩንና አሁን ደግሞ እስከመተማ ያለውን ቦታ በመያዝ ሰሜን ጎንደርን በግማሽ ለማጠቃለል ያስባል በማለት የክልሉን የመስፋፋት ፖሊሲ ተቃውመዋል። በትግራይ ባለስልጣናት በኩል ደግሞ የክልሉ ድንበር እስከመተማ ይደርሳል የሚል አቋም የተንጸባረቀ ሲሆን፣ የአካባቢው ነዋሪዎች የያዙት አቋም የትግራይ ክልል ባለስልጣናትን አበሳጭቷል። በአካባቢው ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሰራዊት አባላትና የፌደራል ፖሊሶች የተሰማሩ ሲሆን፣ ህዝቡን ያስተባብራሉ የተባሉ የአካባቢው መሪዎች እየተለቀሙ በመታሰር ላይ ናቸው።በአካባቢው ያለው ውጥረት በቀላሉ አይበርድም የሚሉት ነዋሪዎች፣ ችግሩ ቶሎ ካልተፈታ ወደ ግጭት ሊያመራ ይችላል በማለት ያስጠነቅቃሉ። በቋንቋና ዘር ላይ የተመሰረተ የፌደራል ስርዓት ከተመሰረተ ጊዜ አንስቶ በክልሎች መካከል የሚታየው የድንበር ውዝግብ እየጨመረ በመሄድ ላይ ነው።በኦሮምያና በሶማሊ፣ በኦሮምያና በደቡብ፣ በአፋርና በአማራ፣ በአማራና በትግራይ፣ በደቡብና በጋንቤላ፣ በትግራይና አፋር እንዲሁም በሶማሊና በአፋር ባልተፈቱ የድንበር ግጭቶች በርካታ ዜጎች አልቀዋል። Source:: Ethsat - See more at: http://www.zehabesha.com/amharic/archives/38768#sthash.PlQQnoI9.qba0YYdh.dpuf

No comments:

Post a Comment