“ጅብ በማይታወቅበት አገር ሄዶ ቁርበት አንጥፉልኝ ይላል” የሚለው ጥሬ ንባብ፤ ስለ ጅብና ስለ ቁርበት መልእክት ለማስተላለፍ አይደለም። ጅቡ የሚወክለው አካል አለ። ቁርበቱ የሚወክለው ነገር አለ። በቁርበቱና በጅቡ መካከል ያለውን ግንኙነት ሳያውቁ ቁርበቱን ለጅቡ ያነጠፉለትም የሚወክሉት አለ። ይህ አገላለጽ በኢትዮጵያዊው ቅኔ ትምህርት፣ ቀመር፣ ስልት ሲመዘን፤ ጅቡ ሰም ነው። ቆርበቱም ሰም ነው። ሁሉም ሰም ነው። ወርቁ ከሰሙ ጋራ ጎን ለጎን ባለመቀመጡ፤ ወርቅ የጎደለው ‘ሰማ-ሰም’ ይባላል።
ወደ ጠቅላላ ይዘቱ ስንገባ፤ በጅብና በቁርበት መካከል ያለው ግንኙነት፤ በተበይና በበይ መካከል ባለው ግንኙነት ብቻ ሳይወሰን፤ የተደራረበ ሰይጣናዊ የአጠቃቀምን ዘዴ ይጠቁማል። ጅብ ቁርበቷን እንደሚበላት በማይታወቅበት አገር ሄዶ ቁርበቷን ‘አንጥፉልኝ ’ እንደሚል፤ አንዳንድ ሰዎችም በሚታወቁበት አገር ቢያደርጉትና ቢሰሩት ተቀባይነት የማያገኙበትን፤ ይልቁንም የሚዋረዱበትን ነገር፤ በማይታወቁበት አገር ሄደው እንዲደረግላቸው የሚፈልጉትን ለማስደረግ የሚጠቀሙበትን ዘዴ ይገልጻል።
ማታለልን ለመንቀፍና የመታለልንና የማታልያንንም ዘዴ ለመግለጽ “ጅብ በማይታወቅበት አገር ሄዶ ቆርበት አንጥፉልኝ ይላል” የሚለውን ሰማ-ሰም ምሳሌያዊ ከእኛ በፊት የነበሩ ኢትዮጵያውያን መጠቀማቸው የጅቡ ባህርይ የሚታይበት ሰው መንቀፍ ተገቢ መሆኑን ለማሳየት ነው። የጅቡን የማታለል ባህርይ ሳያውቁ ቆዳዋን ባነጠፉ ሰዎች ምሳሌነት የሚቀርቡትም፤ አታላይ ሰው ባገሩ ውስጥ የማያገኘውን፤ ይልቁንም የሚነቀፍበትንና የማይመጥነውን ክብር ሳያውቁ በማቅረባቸው ባይነቀፉም፤ መታለላቸውን እንዲያውቁ ሊገለጽላቸው እንደሚገባ ለማስተማርም ነው።
የፊደላችን፤ የስነ ጽሑፋችንና የበጎ ባህላችን ምንጭ የሆነችው ቤተ ክርስቲያናችን በሰጠችን መነጸር ይህን አባባል ስንመለከተው፤ የማታለል ባህርይ መነቀፍ እንዳለበት፤ የሚታለሉ ሰዎችም እንደተታለሉና ዳግም እንዳይታለሉ መነገራቸው አገባብነት እንዳለው እንረዳለን።
ነቀፌታ ተገቢ ባይሆን ኖሮ፤ መገኘት በማይገባው ቦታ አስመስሎ በመግባት ሲያታልል የተገኘውን ሰው፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፤ እጅ እግሩን አስራችሁ አውጡት “ (ማቴ 22፡11-13) ባላለ ነበር። ቅዱስ ጳውሎስም “በውጭ ባሉ ሰዎች መፍረድ ምን አግዶኝ። በውስጥ ባሉ ሰዎች ላይ አትፈርዱምን? በውጭ ባሉት እግዚአብሔር ይፈርድባቸዋል። ክፉውን ከመካከላችሁ አውጡ ” (1ኛ ቆሮ 5፡12 ) ባላለም ነበር። ከቤተ ክርስቲያን ውጭ በሆነ ቡድን ወደ መንፈሳዊ አመራር የሚመጣውንም መንቀፍ ክልክል ቢሆን ኖሮ፤ የቀኖና መጽሐፋችን በምድራዊ ኃይልና ድጋፍ የሰየመውንና የተሰየመውን ምቱራን ( ህይወት አልባ ሆነው የተወለዱ ናቸው) ባላላቸውም ነበር (ፍ.ነ. ፻፸፭) ። (ሙሉውን ጽሁፍ ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ)
No comments:
Post a Comment