(ተመስገን ደሳለኝ)
ከሩሲያውያኑ ቦልሼቪክና ሜንሼቪክ አንስቶ፣ የእኛዎቹ ኢህአፓና መኢሶን በፊት-አውራሪነት እስከ ተሳተፉበት ድረስ ያሉ በደም የጨቀዩ አብዮቶች በሙሉ በከተሞች የተካሄዱ ሲሆን፣ አብዛኛው አጋፋሪዎቻቸው ደግሞ ልሂቃኖች እንደነበሩ በጉዳዩ ዙሪያ የተፃፉ ድርሳናት ያወሳሉ፡፡ ይሁንና እነዚህ አብዮቶች (የተሳኩትም ሆነ የከሸፉት) ሰላማዊውንና ህጋዊውን መንገድ የተከተሉ ባለመሆናቸው ዛሬም ይዘገንናሉ፤ ለወደፊቱም ባልተደገሙ ያሰኛሉ፡፡ ስለምን ቢሉ? ግድግዳው ላይ የተቸከቸከው ፅሁፍ እንዲህ የሚል ምላሽ ያስነብባልና፡- በጭቁን ሕዝብ ስም የብዙሀኑን ቤት አፍርሰዋል፤ ሀገርና ታሪክ ለመቀየር የማይሳናቸው አፍላ ወጣቶችን እርስ በእርስ አጫርሰዋል፤ ‹አንቱ› ሊባሉ የሚችሉ ምሁራንን በአንድ ጀንበር ወደ ትንታግ ነፍሰ-ገዳይነት ቀይረዋል፤ ክስረቱም ከትውልድ ትውልድ የሚተላለፍ ጠባሳ ሆኖ ዛሬ ላይ ደርሷል…