Friday, November 29, 2013

የወያኔ በዲሞክራሲ ቁማር እስከመቼ?

በአሸናፊ ንጋቱ
በስልጣን ላይ ያለው የወያኔ መንግስት የዛሬ 22 ዓመት አንግቦት የነበረውን የዲሞክራሲ መፈክር በማየት ዲሞክራሲ የጠማው የኢትዮጵያ ህዝብ የደስታ ጮቤ በመርገጥ ነበር የተቀበለው፡፡ ነገር ግን ይህ መፈክር ድራማ መሆኑ እየዋል እያደረ ነበር እየተጋለጠ የመጣው። ጮቤ እየረገጠ፤ ትግሉን ተቀላቅሎ መስዋት የከፈለውን ህዝብ የቁልቁል ወደ ባሰ የመከራ ማጥ ከቶታል።
ወያኔ እራሱ ህግ አውጥቶ እራሱ የማፍረስና በህጉ ያለመገዛት አባዜ የተጠናዎተው አንባገነን ስርአት መሆኑ በሃያ ሁለት አመታት የስልጣን ጉዞው አስመስክሯል፡፡ በትክክል እንደ ህገ-መንግስቱ ቢሆን ኖሮ ህገ-መንግስት የህጎች ሁለ የበላይ ህግ ነው፡፡ነግር ግን ወያኔ ያለምንም ከልካይ እንዳሻው ያለ ህዝብ ተሳትፎ ለስልጣናቸው እርዝማኔ ይመች ዘንድ ሲዘርዙትና ሲደልዙት ይስተዋላል፡፡
ሲፈልግ ስልጣን መብት ሲሰጥህ/ሽ ሳይፈልግ ደግሞ ሲከለክልህ/ሽ በስመ ዲሞክራሲ እየነገደ የሚኖር የማፍያ ስርአት ነው፡፡ የአምባገነን መንግስታት መለዬ በሆነው ሃይልን እየተጠቀመ በመግደል፤ በእስር፣ በመሳርያ እና በዱላ እያስጨነቀ የህዝቡን ስነ ልቦና በማድከም የስልጣን ቆይታውን ማርዘምም የስርአቱ ዋና አላማ፡፡ እንዲህ አይነቱ አምባገነንና በዲሞክራሲ ስም ህዝባችን ላይ ቁማር የሚጫዎት ስርአት ለኢትዮጵያውያችን አያስፈልግም፡፡ ስለዚህ ይህንን በጨካኝኔ የተሞላ ስርአት ከሃገራችንና ከህዝባችን ጫንቃ የምናስወግድበት ሰአት አሁንና አሁን ብቻ ነው።
በዲሞክራሲ ቸነፈር መመታታችን ሳያንሰን አገር አልባ ለመሆን በተቃረብንበት እና ማንነታችን ጥያቄ ውስጥ በገባበት በዚህ ጊዜ ዲሞክራሲን መናፈቃችን ብቻ ተፈጥሮአዊ አያደርገንም፡፡ በተፈጥሮ ያገኘነውን ነፃነት በተግባር ስናስጠብቅ ብቻ ነው፡፡ ይህ ሁሌ ፍዳና መከራ የሆነው በሃገራችን ላይ በጣም ገኖ ከእኔ በላይ ላሳር በማለት በሃይል በጉልበት በስልጣን ላይ በተቀመጠው የወያኔ ስርአት ነው፡፡ የወያኔ ስርአት ስልጣን ከያዘ ቀን ቀንን እየተካ፤ ሳምንት ሳምንታትን እየተካ፤ ወር ወራትን እየተካ፤ አመት አመታትን እየተካ ይኸው እነሆ 22 አመታችንን አስቆጠርን፡፡ በዚህ 22 ዓመት በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ለዲሞክራሲ፤ ፍትና ነፃነት የዘመሩ ዜጎች አልቀዋል፤ ለስደትም ተዳርገው የድራማው ሰለባ ሆነዋል፡፡ አሁንም ዝም ካልነው ሌላ ብዙ አስርት የመከራ አመታትን መጋፈጥ ሊኖርብን ነው፡፡ እስከመቼ ዝም እንደ ምንለው ግን ወገን አይገባኝም፡፡ አሁንም ህፃን፤ ወጣት፤  ጐለምሳና አዛውንት ወገኖቻችን ሲረግፍ፤ ሲሰደዱ ማየት ከሆነ ህልማችን መልካም! ግን ይህንን የሚያልምም ሆነ የሚመኝ ንፁህ ኢትዮጵያዊ ያለ አይመስለኝም፤ ከራሳቸው ከወያኔ ሆዳደር ካድሬዎች በስተቀር፡፡ ስለዚህ ወገኔ ሆይ ይህንን መንግስት ዝም ብለን ልናየው አይገባም፡፡ ወይም እንደ ፈለገ ሊፈነጭብን ቦታ መስጠት የለብንም፡፡ እስካሁን በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ያደረሰው ጭቆናና በደል ይበቃል ልንለው የግድ ነው፡፡
በዲሞክራሲ እጦት ሃገራችንን ማስጨነቁ አልበቃው ያለው ይህ ክፉ ስርአት በአሁኑ ጊዜ የህዝባችንን ኑሮ ከድጡ ወደ ማጡ አድርጎት ይገኛል፡፡ ህዝባችን በኑሮ ውጣ ውረድ ህይወቱ ሰላም አጥቷል። ወያኔ ስርአቱን የሚቃወሙትን ብሎም የዲሞክራሲ ጥያቄን ያነሱ ንፁሃን ዜጐችን መግደል፤ ማሰርና ማሰቃየት መለዬው ነው። ወያኔ ይህን ስትራቴጂ የሚጠቀመው ለሃገራቸው መልካም የሚመኙትን እና ለሃገር ይሰራሉ ተብለው የሚገመቱትን ሃገር ወዳድ ዜጐች ማጥፋት ከመፈለጉ የተነሳ ነው፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ሰዎች ሁሌም ለሃገራቸው ደህንነት ለህዝባቸው ኑሮ የሚጨነቁ ስለሆኑ ስርአቱን የመደገፍ ፍላጎት ስለማይኖራቸውና እየፈፀመ ያለውን አረመኔ ተግባር ለህዝብ ሊያጋልጡብኝ ይችላሉ ብሎ ስለሚፈራም ነው፡፡ ታዲያ በዚህ ሁኔታ የሚቀጠለው እንዴት ነው? ውድ ኢትጵያውያን በአሁኑ ጊዜ ህዝባችን ስቃይ ላይ ነው፡፡ ልንደርስለትና ከህዝባችን ጐን ተሰልፈን  ነፃነታችን ማፋጠን ይገባናል፡፡
በስተመጨረሻም መጠየቅ የምፈልገው በዲሞክራሲ እየነገደ ያለው ይህ የወያኔ ስርአት በሃገራችን ገነባሁት፤ እያበበም ነው የሚለው የዲሞክራሲ ስርአት የቱ ይሆን?
በየትኛው ዲሞክራሲ፡ ነፃነትና ፍትህ ያለበት ሃገር ላይ ነው አንድ መንግስት ለ22 አመታት ሲገዛ ያየነው? ዲሞክራሲ፡ ነፃነት እና ፍትህ አሰፍናለሁ ብሎ ቃል የገባላትን እናት ሃገር ዛሬ ግን ድንበሯን በመሸራረፍ እየሸጧት፣ እየለወጧት ብሎም ህዝባችንን በኑሮ እሳት ረመጥ እያቃጠሉት፤ ነፃነቱ ቀርቶ የሃገራችንን ህዝቧን እየከፋፈሉ የብሄር ብሄረሰብ መብትን አስከብራለሁ እያሉ እርስ በእርስ ህዝቡን ማጋጨትና ማጨፋጨፉ ይሆን የሃገራችን ዲሞክራሲ መገለጫው?
ነው ወይስ ዲሞክራሲ ለወያኔ ህዝቡን መከፋፈል፣ እንደልብ እንዳይናገር ማፈን፣ መሬትን ያለባለቤቱ ፈቃድ እየነጠቁ መሸጥ፣ ሙስናን ተዋጋሁ እያሉ በሙስና ተጨማልቆ መገኘት፡፡ ይሄ ነው የወያኔ ዲሞክራሲና እና ፍትህ? የቆሰለችውን ኢትዮጵያ አድንሻለሁ ብሎ ለባሰ ህመም መዳረግስ ለምን!? እውነት ግን በተቃራኒው በቁስሉ ላይ እየሸነቆሩ ማድማት ነበር እንዴ አላማቸው? የተራባችሁትን ሰላም እና ዲሞክራሲ እሰጣችኋለሁ ብሎ ቃል የገቡለትን ህዝብ እልል ብሎ ሲቀበል፣ በታሪኩ አይቶት የማያውቀው የመከራ ጦስ መክተት ነበር እንዴ የወያኔ አላማ!? ስራቸውና ተንኮላቸው የገባው/ት ለምን ብሎ ሲጠይቅ/ ስትጠይቅ ወደ ወህኒ እና ወደ ሞት መጣል መሆን አለበት እንዴ የዚያ የምስኪን ህዝብ ለሰራው ውለታ መልሱ? ታዲያ የወያኔ ዲሞክራሲያዊ ግዛት ይኼ ነው?
ዛሬ ህዝባችን የተወለደበትን ምድርና ቀየ በሃይል በማስለቀቅ መሬቱን በኢንቨስትመንት ስም እየተሸነሸነ እየተሸጠ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ታዲያ ይሄ ጭቁን ህዝብ ምድሩን ለቆ ወዴት ይሂድ የትስ ይድረስ? ነው ወይስ ስርአቱ ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ነው ቆርጦ የተነሳው? ወገኔ ሆይ ሃገር አለን ብለን የምንኮራው መቼ ይሆን? እስኪ መልሱልኝ፤ የቀን ከሌት ጥያቄየና በራሴ መልስም ለማግኘት ባለመቻሌ አንድ ብትሉኝና ለአምሮየና ለመንፈሰይ ሰላምን ባገኝ ነው ለዘመናት የሚመላለስብኝን ጥያቄዎች መሰንዘሬ፡፡ በእኔ በኩል ይህንን አፋኝና አምባገነን ስርአት ያለምንም ልዩነት በአንድ ልብ በቃ ልንለውና፤ በቁርጠኝነት ልንታገለው ይገባል ባይ ነኝ።
ድል ለጭቁኑ ኢትዮጵያ ህዝብ!!!


ለአስተያየትዎ: andethiopia16@gmail.com የኢሜል አድራሻየ ነው።

No comments:

Post a Comment