በዚሁ ባለንበት ዘመን ያለፉት ስርአቶች ወደኃላ ተመልሰን ስናስታውስና አሁን ያለውን የህ.ወ.ሓ.ት መንግስት ስንመለከት ኢትዮጵያውያንን ለስድት የሚዳርጓቸዉ ችግሮች ነበሩ።
በዘመነ ዘውዳዊ አገዛዝ ስርአቱ ለዘውዳዊ ንጉሳዊ ቤተሰብ ለተቀማጠለ ኑሮ ቅድሚያ ስለሚሰጥ በወቅቱ ያጋጥሙ ለነበሩ እንደ ድርቅ ያርሶ አደሩ ሰብል በተባይ ሲጠቃ ህ/ሰቡ ስለሚራብና ስለሚቸገር ዘውዳዊ ስርአቱ ደግሞ መሰረታዊ የፖለቲካ ፣ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊ ችግሮች መፍትሄ የማይሰጥ ስለነበረ ብዙ ያልተማረ ህዝብ ወደ ስደት እየፈለሰ የመከራ ኑሮ ይገፋ ነበር።
በዘመነ ደርግም ወታደራዊ መንግስት መንግስቱ ሃ/ማርያም የሃገሪቱን ሃብት አሟጥጦ ለጦርነት ያውለዉ ስለነበረ እንዲሁም ወጣት ህ/ሰብ በሙሉ ያለ ፍላጎቱ ወደ ጦርነት ያስገባዉ ስለነበረ ባጠቃላይ መንግስቱ ሃ/ማርያም ፀረ-ዲሞክራሲና ገዳይ ስለነበረ ለሃገራችን ህዝቦች ሰብኣዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች የማያከብርና የምስራቅ ፖለቲካ በሃይል ለመተግበር ይፈልግ ስለነበረ ለዚሁ ስርአት የሚቃወሙ ሃይላት የጥያቄአቸዉ መልስ መርሸንት( ግድያ) ጦርነት የፈጠረዉ የህዝብ ፍልሰትም ስለነበረ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ህዝቦች ለስድትና ለፍልሰት ተዳርግዉ አብዛኛው ህዝብ በጎረቤት አገር በሱዳን፣ በስዐድ-ዓረቢያ፣ በደቡብ አፍሪካ፣ በየመንና ወደ ሌሎች የአፍሪካ አገሮች እንዲሁም ወደ አሜሪካና አውሮፓ አገሮች ተሰደዉ የከፋ ኑሮ ይኖሩ ነበር። ግን ደግሞ አሁን በዘመነ ህ.ወ.ሓ.ት ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ ስርአት ዜጎች በስደት ሄደዉ ያጋጠማቸዉ እንዳለዉ መከራና ግፍ የሚያጋጥማቸዉ አልነበረም።
ስደት በዘመነ ህ.ወ.ሓ.ት ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ መንግስት ገና ደርግን አስወግዶ ስልጣን ከያዘ ለታ ጀምሮ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የደርግ አባላት ፣ ደጋፊዎች፣ ወታደሮች ሲቪል የመንግስት ሰራተኞች፣ የዩኒቨርሲቲ አስተማሪዎች ወዘተ እንደ ጠላት ወይም እንደ ሁለተኛ ዜጋ ታይተዉ ከፖለቲካ ፣ ከኢኮኖሚ፣ ከማህበራዊ ተሳትፎ ስላስወገዳቸዉ አብዛኞቹ ያገኙትን አጋጣሚ ተጠቅመዉ በሁሉም አቅጣጫ የኢትዮጵያ ጠረፎች ከሚወዷት አገራቸዉ ተነጥለዉ ተሰደዉ ለመጥፎ ውርደትና ለከፋ ኑሮ ተዳረጉ።
የቀረዉ ህዝብም የህ.ወ.ሓ.ት ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ ከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲ አማሮት ወደ ስደት ፈለሰ፡፡ በወቅቱ ወደ አሜሪካ አውሮፓ ካናዳ አውስትራሊያ የመሰደድ እድል ያጋጠማቸዉ ዜጎች የተሻለ የኑሮ እድል ሲያጋጥማቸዉ ወደ አፍሪካ አገሮች እና አረብ አገሮች የፈለሱ ግን ለከፋ ስቃይ ተዳረጉ፡፡ አቤት ብለዉ ቢጮሁም ህ.ወ.ሓ.ት ሰሚ ጆሮ አልነበረዉም ወደ የበለፀጉ አገሮች የመሰደድ እድል የነበራቸዉም በወቅቱ ከህ.ወ.ሓ.ት መሪዎች ጥሩ ግንኙነት የነበራቸዉና ዘመድ አዝማድ የነበሩ ናቸዉ። ሌላዉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወገኖች ግን በሱዳን፣ በኬኒያ፣ በጅቡቲ፣ በቀይባህር፣ በኤርትራ፣ በየመን ፣ በሊቢያ፣ ብዙ ሰዎች የመከራ ፅዋቸዉን እየጎነጩ ሲሻገሩ ሌሎች ደግሞ በመንገድ ሞተዉ ቀሩ። እነዚህ ዜጎች አብዛኞቹ የተማሩና በሞያ የተካኑ ነበሩ እንዲሁም በብልሹ አስተዳደርና ፍትህ በማጣት የገጠርና የከተማ ወጣቶች ፈለሱ።
ህ.ወ.ሓ.ት ግዛቱን እያጠናከረ በሄደና ስርአቱ መጀመሪያ ስልጣን ሲይዝ ለህዝብ ይሰጠዉ የነበረ የፖለቲካ የሰብአዊ መብቶችና ነፃነት እንዲሁም በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ በዲፕሎማሲያዊ ለውጥ አመጣለሁ ብሎ የገባዉ ቃል እየካደ ህ/ሰቡ ወዳጅ፣ ጠላት፣ መኸል ሰፋሪ ብሎ በመከፋፈል ስርአቱ በዘመድ አዝማድ በጋብቻ በጓደኝነት እየሆነ በመሄዱ የአገራችን ህዝብ ገንዘብ አሟጥጦ ለህ/ሰቡ ስራ ፈጣሪ በሆነ መንገድ እንደማሰማራት በሙስና በማባከኑ ባጠቃላይ በአገራችን ፍትህና መልካም አስተዳደር ጠፍቶ ብልሹ አስተዳደር በመንገሱ ህዝቡ እየደኸየና ኑሮዉ እየተበላሸ ስለሄደ የእለት ጉርሱን ለመፈለግ ቤተሰቡና መኖሪያ ቀየዉን እየጣለ ወደ ስደት ተመመ።
ከደርግና ከዘውዳዊ ስርአት የነበረ ስደት በባሰ መልኩ በሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ ተሰዶ የስቃይ፣ የሞት የመታሰር የግፍ ሰለባ ሆነ።
አሁን ያለዉ መንግስት በፈጠረዉ የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲ ምክንያት ባሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያዊ መሆን አሳፋሪ እና መዋረድ የሚሆንበት ሁኔታ ተፈጥሯል። በየመን እስር ቤት ታጉረዉ ቢጮሁ ሰሚ ጆሮ ለወገኑ የሚደርስ መንግስት አጡ። በሱዳን፣ በደቡብ አፍሪካ፣ በግብፅ ‹‹ህገ-ወጥ ስደተኖች ናችሁ›› ተብለዉ ሲታሰሩ፣ ሲገረፉ ፣ሲገደሉ ኩላሊታቸውና የሆድ ውስጥ አካላቸዉ አጥንታቸዉ እየታረደ ለአረብ ቱጃሮጅ ሲሸጥ ማንም የመንግስት ባለስልጣን እንደ አጀንዳም አይዘውም ነበር። በሻዕቢያ መንግስት ዜጎች እንጀራ ፍለጋ በተሰማሩበት በኤርትራ የባሪያን አገዛዝ የሚፈፀምባቸዉ እጅጉን ብዙ ናቸዉ። በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በቀይ ባህርና ህንድ ውቅያኖስ ሲሻገሩ በባህር ላይ ተጥለዉ አውሬ የበላቸዉ ኢትዮጵያውያን ስፍር ቁጥር የላቸዉም። ወደ አረብ ተሻግረዉ አሰሪዎቻቸዉ ግፍ ስለሚፈፅሙባቸዉ ከፎቅ የሚጣሉ፣ የሚገደሉ፣ በእሳት የሚቃጠሉ ፣ ያለአቅማቸዉ ሲሰሩ የሚሞቱ በእስር ቤት ማቀዉ የሚሞቱ አሳዛኝና ዘግናኝ አሳፋሪ ተግባር የሚፈፀምባቸዉ ብዙ ናቸዉ።
የሀገራችን መሪዎች ግን ጠ/ሚኒስተር መለስ በነበሩበትና ባሁኑ ጊዜ ሃ/ማርያም ደሳለኝና የክልል መሪዎች ‹‹ለምንድነዉ ህዝቡ ወደ ህግ-ወጥ ስደት የሚዳረጉት›› ተብለዉ ሲጠየቁ የተበላሸ ስርአታቸውን እንደ መፈተሽ ፈንታ ‹‹እነዚህ እየተሰደዱ ያሉ ቸግሯቸዉ ሳይሆን ባቋራጭ ለመበልፀግ ስለፈለጉ ነዉ›› ብለዉ በመንግስት ብዙሃን መገናኛ ፣ በኮንፈረንስ፣በጉባኤ ልባቸዉን ነፍተዉ ይናገሩ ነበር።አሁንም ይናገራሉ ሃቁ ግን ለስደት ሰለባ ምንጩ የህ.ወ.ሓ.ት ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ የተበላሸ ስርአትና አመራር ነበር።
የህ.ወ.ሓ.ት ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ መንግስት ስራ አጥነት የሚፈታ ትላልቅ ፕሮጀክት እንደ መክፈት ህዝቡን ወደ ስደት እንዲሄድ ለከፋ አደጋ እንዲጋለጥ በማበረታታት ዜጎቻችን በህጋዊ ሽፋን ወደ አረብ አገሮች ተሰደዉ በላያቸዉ ላይ የባርያ አገዛዝ እንዲፈፀም አድርጓል።
ለዚህም ለማስረጃነት ባለፉት አመታት በርካሽ ዋጋ ወደ አረብ አገሮች በሳምንት 5500 ዜጎች በቦሌ አድርገዉ እንዲሰደዱ አድርጓል። ይህ ተግባር የሚፈፅመዉ መንግስት ባቋቋማቸዉ የአሰሪና ሰራተኛ አገናኝ ቡድኖች አድርጎ ነዉ የሚተገብረዉ። እነዚህን አገናኞች የነሱ ወኪሎች የሆኑት ሰዉ እየሸጡ የሚበዘብዙ በአረብ አገሮች ወኪሎች አሏቸዉ።
እንግዲህ ተመልከቱ አንድ ሰራተኛ ከኢትዮጵያ አረብ አገር ሲሄድ ኩንትራት ሲያስር በወር ከ800 ሪያል በታች ነዉ፡፡ እዛዉ የሚሰራዉ ግን በወር ከ2000 ሪያል በላይ ነዉ፡፡ እነዛ ህጋውያን የህ.ወ.ሓ.ት ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ መንግስት ያቋቋማቸዉ ደላሎች ለዜጎች በጥቂት ገንዘብ እየሸጡ የቀረውን ገንዘብ ለራሳቸዉ ይወስዳሉ፡፡ እነዚህ በጥቂት ገንዘብ የተሸጡ ዜጎች እዛዉ ሄደዉ የሰዎች ጉልበትና አእምሮ ስንት ይሸጥ እንዳለ ሲያውቁ የነበራቸውን ውል አቋርጠዉ ሌላ ቦታ ሄደዉ በውድ ገንዘብ ሲሰሩ እነዛ ሰዉ በላ ደላሎች ከአረብ ቱጃሮች በመተባበር አስረዉ ይገርፏቸዋል እስከ መግደልም ይሄዳሉ፡፡ ልክ እንደ ድሮ የባርያ ንግድ የሚባሉ እቤት ውስጥ ተዘግተዉ በጥበቃ እንዲሰሩ የሁሉም ዘር መንዘሩ የቤተሰብ ስራ ከአቅማቸዉ በላይ በመስራታቸዉ እስከ ሞት ይዳረጋሉ፡፡ የ ህ.ወ.ሓ.ት ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ ገዢዎች ግን እንደዚህ አይነት መከራ ለሚደርሳቸዉ እንደ ምቾት በመቁጠር ህጋዊ ስደት ያሟሉ ናቸዉ ይሉናል።
ህገ-ወጥ ሰራተኛ የሚሉት በባህር ወይም በሰሃራ በረሃ አቋርጦ እየሄደ ያለዉ የመንግስት ህጋዊ ደላላ የሚልካቸዉ በአነስተኛ ገንዘብ ስለሚሸጡ ራሳቸዉ ከሄዱ ደግሞ ተደራድረዉ በውድ ገንዘብ ጉልበታቸውንና አእምራቸውን ስለሚሸጡ ነዉ። ስለዚህ እነዛ መንግስት ህግ-ወጥ የሰዉ አዘዋዋሪ ደላሎች የሚላቸውና እራሱ መንግስት ፍቃድ ሰጥቶ ያቋቋማቸዉ ደላሎች ሁሉም ለጥቅማቸዉ ሲሉ ዜጎቻችንን እያጠፉ ያሉ ባንዳዎች ናቸዉ። ለዚህ ሁሉ ተጠያቂዎች ደግሞ የህ.ወ.ሓ.ት ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ ባለስልጣናት ናቸዉ። የኢትዮጵያ ህዝብም በአፍሪካና አረብ ሃገሮች የተሰደዱ ዜጎች የህ.ወ.ሓ.ት ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ መንግስት የፈጠረዉ ቀውስ በዜጎቻችን ላይ እየደረሰ ያለዉ ግፍ እየሰማ በግፍ የሞቱት ዜጎች እየቀበረ በውጭ ብዙሃን መገናኛ እየጮሁ እየሰማ ለመንግስት ተፅእኖ በማድረግ መፍትሄ እንዲያደርግ እርምጃ አይወስድም ዝምታ ይመርጣል።ለምን ይህ ተግባር ለመንግስት ተቃውሞ ማሰማት ይገባዉ ነበር። አሁንም እምባ እያበሱ ጥቁር ልብስ መልበሱ መፍትሄ አይሆንም ። ያለውን አጋጣሚ ተጠቅሞ በስደት የሚሰቃዩትን ወገኖች የሚድኑበትን መንገድ በማፈላለግ ለመንግስት ተፅእኖ በማድረግ መታገል አለበት። ለዚህ ችግር የማይቆረቆር መንግስት ግን ከስልጣን እስከ ማውረድ መታገል አለበት። በዚህ ላይ የውጭ ብዙሃን መገናኛዎች፣ ባገር ውስጥም የሚገኙ መፅሄት፣ ጋዜጦች ምስጋና ይገባቸዋል። እንዳንዳኞቹ አድር ባይ የግል ጋዜጦችን ግን አይጨምርም የህዝብ ወገንተኝነት የላቸውምና።
በሀገራችን ያሉት የመንግስት ብዙሃን መገናኛዎች ግን በህዝብ ሃብት ተገንብተዉ ህዝብ ግብር የሚከፍልባቸዉ ለህዝብ አገልግሎት እንደ መስራት ለገዢዎች ብቻ እያሞካሹ መኖሩ በታሪክ የሚያስጠይቃቸዉ ነዉ። ህ.ወ.ሓ.ት ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ ወደ ስልጣን ከመጣ ጀምሮ እስከ አሁን በአረብና በአፍሪካ አገሮች በኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን የሚደርሰዉ ግፍና ግድያ በሚመለከት በውጭና ባገር ውስጥ ብዙሃን መገናኛ ከተነገረላቸዉ በኋላ እንዲሁም በውጭ መንግስታትና ዲፕሎማቶች ተገፋፍተዉ ለፖለቲካዉ ፍጆታዉ ብሎ ካልሆነ በስተቀር ህ.ወ.ሓ.ት ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ በሚድያዎች ስለ ስደተኞች ችግር ትንፍሽ ብለዉ አያውቁም። አሁን በሳውዲ-ዓረቢያ እየደረሰ ያለዉ ግፍና ግድያ ሰቆቃ ዝምታን መርጠዉ ይገኛሉ።ታዲያ እነዚህ ሚድያዎች የማናቸዉ የአምናና ከዛ በፊት የነበሩዉ ጊዜ በዜጎቻችን ላይ የደረሰዉ ግፍና ሰቆቃ እንተወውና ባሁኑ ጊዜ በስዕድ-ዓረቢያ እየደረሰ ያለዉ ግድያና እንግልት ሰብዓዊ ክብር መደፈር መላዉ አለም እየተናገረበትና እየተጨነቀበት የኢትዮጵያ መንግስትና ሚዲያዎቹ አሁንም ተገደዉ ለፖለቲካ ፍጆታ ብለዉ ካልሆነ ትንሽ መተንፈስ የጀመሩት በወቅቱ ግን መተንፈስ አልቻሉም። ሌላዉ ቀርቶ በዚህ ባለፈዉ ሳምንት የሀገራችን የክልል መሪዎች የህ.ወ.ሓ.ት ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ ስራ አስፈፃሚዎች ስብሰባ አድርገዉ ነበር፡፡ በነዚህ ስብሰባዎች በሳወዲ-ዓረቢያ መንግስት በሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች ግፍ ሲያደርስ ለዚህ አስመልክቶ መግለጫ ይሰጣሉ የሚል ግምት ቢኖርም ነገር ግን እነዚህ መሪዎች ስለ ህዝብ ሳይሆን የሚያስቡት ስልጣናችንን እንዴት እናራዝም ስልጣናችን በማራዘም የአፈና መዋቅር እንዴት እናጠናክር ብለዉ ነዉ ሲደሰኩሩ የሰነበቱት።
ታዲያ ህዝብ ካልተያዘ ስልጣን ይራዘማል? ብሶት የመረረዉ ህዝብ መሪዎችን ለመብላትና ለመዋጥ የሚያግደዉ ሃይል የለምና ከዘውዳዊ አገዛዝና ከደርግ አገዛዝ አወዳደቅና የኢትዮጵያ ህዝብ እንዴት እንደበላቸዉ ሁላችን አይተናል፡፡ ህ.ወ.ሓ.ት ኢ.ህ.አ.ዴ.ግም ልትማሩበት ትችሉ ነበር። ነገር ግን በጥቅምና በብልሹ አስተሳሰብ አይናችሁ ስለተሸፈነ መጭዉ አደጋ አይታያችሁም።
ከላይ የጠቀስኩት የህዝባችን ግፍ ለመፍታት የሀገራችን አምባሳደሮች ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስተር እየሰሩ የነበሩ አሁንስ ምን እየሰሩ ነዉ? በኔ ትእዝብት እነዚህ ዜጎች በሃገራችን አንጥራ ሃብት ለዘር መንዘራቸዉ የሚበቃ ደሞዝ በዶላር እየተከፈላቸዉ በስደት ለሚኖረዉ ለሚሰቃየዉ ህዝብ እንደመጣበቅና እንደ መቆርቆር ለሁሉም ዜጋ እኩል እንደማገልገል ፈንታ ያቺ ትንሽ የሚሰጧት አገልግሎትም እገሌ የማን ተቀዋሚ ፓርቲ አባል ነዉ ለህ.ወ.ሓ.ት ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ ፓርቲዎች ይደግፋል ወይ በማለት እንደ ስርአታቸዉ መመሪያ ወዳጅ ጠላት መሃል ሰፋሪ ብለዉ በመከፋፈል በህዝብ ገንዘብ የተሰራዉ ህንፃቸዉ ተዘግተዉ ነዉ የሚኖሩት ስለዜጎች አያስቡም። ስደተኞቹ ችግር አጋጠመን ብለዉ ሲያመለክቱ እንደ ዜጋ ተቆርቁረዉ መፍትሄ እንደ ማፈላለግ ህግ-ወጥ ስደተኞች ስለሆናችሁ አይመለከተንም ነዉ የሚሉት። አሳፋሪ ለዜጎች የማይቆረቆርና ለዜጎች የማይጣበቅ አምባሳደር ዜጋ ነዉ ይባላልን?መልሱን ለኢትዮጵያ ህዝቦችና በስደት ለሚሰቃየዉ ህዝባችን።
ሌሎች ሃገሮች እኮ ዜጎቻቸውን ያከብራሉ አንድ ዜጋቸዉ ከተበደለ ህጋዊ ይሁን አይሁን እስከ ዲፕሎማሲ ግኑኝነታቸውን ማቋረጥ እና እስከ ጦርነትም ይሄዳሉ ።ለዚህም እንደ ምሳሌ እስራኤል አንድ ወታደሯ ኢ-ህጋዊ በሆነ መንገድ የፊልስጤምን ጠረፍ ጥሶ በመግባቱ በፍልስጤሞች ታፍኖ ከተወሰደ በኋላ ጦርነት ተከፍቶ ላንድ ሰዉ ሲባል ብዙ ሰዉ ሞቶ ከብዙ ጦርነት በኋላ ወታደሩ በሃይል ተመልሷል። ሌላም የስዊድን ጋዜጠኞች በህግ-ወጥ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ ዘልቀዉ ገብተዉ የስዊድን መንግስት ግን ዜጎቹ ህገ-ወጥ ቢሆኑም ለዜጎቹ ተቆርቋሪ ስለሆነ ስለተቆጣ የኢትዮጵያ መንግስት ከስዊድን መንግስት ዲፕሎማሲ ግንኙነቱን እንዳይቋረጥበት ፣ የሚያገኘውን እርዳታ እንዳይከለክሉት ፈርቶ ተንበርክኮ ሊለቃቸዉ ችሏል። የዜጎች ጠበቃ ማለት ይህ ነዉ።ህ.ወ.ሓ.ት ኢ.ህ.አ.ዴ.ጎች ከዚህ ሊማሩ አልቻሉም በየቀኑ በሂወት ወደ ስደት ሄደዉ በግፍ ተገድለዉ ሬሳ ቦሌ ሲገባ እየተቀበሉ ይኖራሉ አሳፋሪ ነገር ነዉ።
የኢትዮጵያ መንግስት በስዑድ-ዓረቢያ መንግስት በኢትዮጵያ ስደተኞች እያደረሰ ያለዉ ግድያ መደፈር ሰቆቃ እንዲቆም በአሜሪካ ፣ በስዊድን፣ በኩቤት በሌሎች አውሮፓ አገሮች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ቁጣን ስለፈጠረ ተቃውሞአቸውን ገልፀዋል ብለዉ ውጭ ጉዳይ ሚኒስተር ቴድሮስ አድሃኖም በነዛ የኢትዮጵያውያን ቁጣ እንደተደሰቱ ገልፀዋል፡፡ በሌላ በኩል ግን በ 6/03/2006 ዓ/ም ሰማያዊ ፓርቲና ሌሎች ኢትዮጵያውያን በስዑድ-ዓረቢያ ኤምባሲ በስዑድ-ዓረቢያ ለሚኖሩ ዜጎቻቸን ይደርስባቸዉ ያለዉ ግፍ በመኮነን ግፉ መቆም አለበት ብለዉ ሰላማዊ ሰልፍ አድርገዉ የመንግስት ፌዴራል ፖሊስ በመደብደብ በመቶ የሚቆጠሩ ህዝቦች እስር ቤት አጉሮአቸዋል፡፡ 14የሚሆኑ ዜጎች በፅኑ በመያዝ በጨርቆስ ክ/ከተማ እስር ቤት ታስረዉ ይገኛሉ።በተለያዩ ክልሎችም ያለዉ ህዝብ ሰላማዊ ሰልፍ በማድረግ የስዑድ-ዓረቢያ መንግስት በህዝባችን ላይ እያደረሰ ያለዉ ግፍ ያቁም በማለት ሰላማዊ ሰልፍ ሊያደርጉ ይፈልጋሉ፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ግን ኢትዮጵያውያን ሰላማዊ ሰልፍ እንዳያደርጉ እየከለከለ ይገኛል።
ያዲያ ቴድሮስ አድሃኖም ባአገር ውስጥ ለሚደረገዉ የተቀውሞ ሰልፍ ላደረጉ ዜጎች እያሰሩ ና እያፈኑ የኩቤትና አሜሪካ ዜጎች ያደረጉትን የሰላማዊ ሰልፍ ቁጣ አስደስቶኛል ብለዋል ይህ ግን ማጭበርበር ነዉ ። በአሜሪካና በኩቤት የተደረገዉ ሰልፍ ከቁጥጥራቸዉ ውጭ ስለሆነ ሳይወዱ በግድ ነዉ ለውጭ ፖለቲካ ፍጆታ ሲሉ ነዉ የተናገሩት ።
በስዑድ ዓረቢያ መንግስት በውጭ አገሮች ዜጎች አሰቃቂ እርምጃዉ በግንባር ቀደምት የኢትዮጵያና የፊሊፕንስ ህዝቦች ይጠቀሳሉ፡፡ የፊሊፕንስ ውጭ ጉዳይ ሚኒስተር ግን አገራቸዉ በከባድ የንፋስ ማእበል ምክንያት በትልቅ አደጋ ላይ እያሉ ብዙ ዜጎችዋ እየሞቱ እያሉ ነገር ግን በስዑድ-ዓረቢያ መንግስት ህገ-ወጥ ናቸዉ ተብለዉ ስቃይ ለሚደርስባቸዉ ዜጎቹ በመቆርቆር እና መቆርቆር ስዑድ-ዓረቢያ ገብቶ ከመንግስት ባለስልጣኖች ጋር ተደራድሮ በዜጎቹ ይደርስ የነበረውን አደጋ ቀንሶታል። ለዜጎቻቸዉ ተቆርቋሪዎች ስለሆኑ።
ቴድሮስ አድሃኖምና ጓዶቻቸዉ ግን አሁን በውጭ ፖለቲካ ተገፋፍተዉ በሃገራቸዉ ውስጥ ሆነዉ የሚያሰሙት ዲስኩር ብለዉ ነበር ለማለት ነዉ እንጂ በህዝባቸዉ ከመቆርቆር የመነጨ አነጋገር አይደለም፡፡ የመቆርቆርና የመጣበቅ ፍላጎት ቢኖራቸዉ እሳቸዉ የሚመሩት የኢትዮጵያ በስዑዲ አምባሳደር ህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ህዝባችን እጅግ ብዙ ዜጎች ተገድለዉና አካላቸዉ ጎድሎ በረሃብ በውሃ ጥም በጠባብ ቤት ታፍነዉ እየሞቱ እያሉ በህዝባችን ላይ ብዙ ጉዳት አልደረሰም ሁለት ሰዎች ብቻ ነዉ የሞቱት ብለዉ በውጭና ባገር ውስጥ ብዙሃን መገናኛ የሚነገር ሁሉ ውሸት ነዉ ብለውናል። የቴድሮስ አድሃኖም አነጋገርም ልክ እንደ መዋቅራቸ አምባሳደሩ ሃቀኝነት የለዉም።
ሌላዉ ቴድሮሰ አድሃኖም በስዑድ-ዓረቢያ የሚገኘዉ ህዝባችን እንዴት እናደነዉ ብለዉ ሂወት ለማዳን እንደመሯሯጥ ፈንታ ህዝብን ለማደናገር ከስደት ተመላሽ ህዝባችን ለማቋቋም አምሳ ሚሊዮን ብር ብዙ ተገኝቶ ለማቋቋሚያ መድበናል ካነሰም እንጨምራለን ብሏል። ይህ ጉዳይ አምሳ ሚሊዮን ብር በህ.ወ.ሓ.ት ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ መንደር ምንም ትርጉም የለዉም የህ.ወ.ሓ.ት ኢ.ህ.አ.ዴ.ጎ ሙሰኞች አንድ ወይም ሁለት ሰዎች የሚመዘብሩት ነዉ ። ስለዚህ ባገር ውስጥና በውጭ አገር የሚገኙ ከሰማኒያ ሚሊዮን ህዝቦች በላይ ጥያቄ
1ኛ በስደት በሚገኙት ዜጎቻችን እየደረሰ ያለዉ ዘግናኝ ድርጊት እንዴት ይቁም፣ 2ኛ ወደ አገራቸዉ እንዴት ይግቡ 3ኛ የሞቱት፡ንብረታቸዉ የተወረሱት እንዴት ካሳ ያግኙ ማንስ ነዉ ተጠያቂዉ 4ኛ በስዑድ -ዓረቢያ እየተሰቃዩ ያሉት ዜጎች ሳይሆን በተመሳሳይ ግፍ ይፈፀምባቸዉ ያለዉ በሱዳን፣ ሊቢያ፣ ግብፅ፣እስራኤል አረብ አገሮች ደቡብ አፍሪካ፣ ኤርትራ ፣ጀቡቲ፣የመን ታስረዉ እየተሰቃዩ ያሉና ሰውብኣዊ ክብራቸዉ የሚዋረዱና እየተገደሉ ያሉት እንዴት እናድናቸዉ? የሚለዉ ህ.ወ.ሓ.ት ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ መንግስት ለህዝቡ ተቆርቋሪ ከሆነ ቴድሮስ አድሃኖም ለዚህም መልስ ሰጥተውበት ይሂዱ፡.፡. ቴድሮስ አድሃኖም ስለ የስዑድ-ዓረቢያ መንግስት እየፈጃቸዉ ያለዉ ዜጎች ተቆርቋሪ ከሆኑ የኢትዮጵያ መንግስት ብዙሃን መገናኛ ለምን ዝምታ መረጡ ? አልጀዚራ፣ ቢቢሲ፣ ሲኤን ኤን፣ ዶች ቬሌ፣ ቪኦኤ ወዘተ የብዙሃን መገናኛ ለኢትዮጵያ ህዝብ አይቀርቡትም ።ግን ወዳኞቻችን ናቸዉ የህዝባችንን ችግር እያስተጋቡ ያሉት ግብር ከፍለን ሃብታችን ከፍለን ያቋቋምናቸዉ ሚዲያዎች ግን የህዝብ ወገንተኝነት አለመያዛቸዉ የሰዑድ-ዓረቢያ ዝምታ መምረጣቸዉ ትልቅ ወንጀል ነዉ።
አንድ ነገር ግን ልበል እኔ ወደ የኢትዮጵያ የሚገቡ የአከባቢ አገሮ ስደተኞች ተቀብሎ መንከባከቡ ሰብኣዊ መብታቸውን መጠበቁ አልቃወምም፡፡ ግን ህ.ወ.ሓ.ት ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ(ራስ ሳይጠና ጉተና ) እንደሚባለዉ ለነዚህ የውጭ ዜጎች ለውጭ ፖለቲካ ፍጆታ ብለዉ ሲንከባከብ በውጭ ለሚሰቃዩ ዜጎቹ ለሚደርስባቸዉ ግፍ መማጎት ወይም መከራከር በአለም ፍ/ቤት መድረክ ወጥቶ መሟጎቱ ዜጎቹን አጓጉዞ አገራቸዉ እንዲገቡ ለምን አያደርግም ? ህግ-ወጥም ቢሆኑ ዜጎች ናቸዉ ነውና።
ግን ደግሞ የህ.ወ.ሓ.ት ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ መሪዎች ለዜጎቻቸዉ ክብር የማይሰጡ መሆናቸዉ ባህሪያቸዉ ነውና ኢትዮጵያዊ በህ.ወ.ሓ.ት ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ ብልሹ አስተዳደር ተበሳብሶ በስድት ሄዶ እየጮሀ መኖር እስክ መቼ ህዝቡ አማራጭ ይፈልግ።
ወደ ስደት ፍልሰትና በስደት ሄደዉ አጋር አጥተዉ ተሚሞቱት የባሪያ ግዛት የሚፈፀምባቸዉ ባገር ውስጥ ሰከን ብለዉ ሰርተዉ እንዳይኖሩ ያደረገ ጠንቁ ማነዉ? በኔ እምነት ለዚህ ሁሉ ግፍ በኢትዮጵያውያን እየደርሰ ያለዉ ዋናዉ ተጠያቂ ደፍሮ የሚጠይቅና ተነስ የሚለዉ የለም እንጂ ፡፡ የህ.ወ.ሓ.ት ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ መሪዎችና መዋቅራቸዉ ናቸዉ። ምክንያቱም በፖለቲካ አቅጣጫ ስንመለከተዉ የዜጎች ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብት ያላረጋገጠ የህግ የበላይነትና የዜጎች ነፃነት በሁሉም መልኩ የነጠቀ አፋኝ ስርአት በመሆኑ፣ የተሳሳተ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ለዜጎች ስራ ፈጥሮ ማህበራዊ ችግርን አስወግዶ የተረጋጋ ኑሮ ያልፈጠረ ስርአት በመሆኑ ዜጎች ባገራቸዉ ነፃ ሃሳብ ሊያንሸራሽሩ ባለመቻላቸዉ የሃገራችንን በብለሹ አስተዳደና በሙስና ያባከነ በመሆኑ ዜጎች በፖለቲካ አመለካከታቸዉ በጠላት በመፈረጅ ለእስራት ፣ ለስቃይ ፣ ለስደት የዳረገ በመሆኑ በዚች አገራችን ዜጎች የመሬታቸውን ባለቤትነት ተነጥቀዉ የሚኖሩባት አገር በማድረጉ፣ ህ.ወ.ሓ.ት ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ በሚሰራቸዉ ስራዎች የምሁራንና የዝህብ ተሳትፎ ስለሚነፍግ ሁሉም ስራ እኔ ካልኩት ውጭ አይሰራም በማለት አባታዊና ኣምባገነናዊ አካሄድ ስለሚከተል በነዚህ የተዘረዘሩ ጠንቅ መሪዎች ናቸዉ ።
መጨረሻ የኢትዮጵያ ህዝብ ከስደት፣ ከውርደት ባህር ውስጥ ገብቶ በመሞት ከፎቅ ተወርውሮ ሂወቱን ከማጥፋት ባገር ውስጥም በአምባ ገነኑ ህ.ወ.ሓ.ት ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ መንግስት አንገት ደፍቶ ከመኖር ኣገር ውስጥም በስደት ያለዉን ህዝብ አንድነትና ህብረት በማጠናከር በሰላማዊ መንገድ ታግሎ መብትን ማስከበር ያስፈልጋል። ካለበለዚያ ህ.ወ.ሓ.ት ኢ.ህ.አ.ዴ.ጎች 22 አመት ገዝተዉ ለውጥ ሊያመጡ አልቻሉም። ይህ ካልተደረገ መከራዉ እየከፋ ነዉ ያለዉ አሁንም ለነዚህ በስዑዒ መንግስት ግፍ እየተፈፀመባቸዉ ያለዉ ዜጎችና በሱዳን፣ በግብፅ፣ በየመን በሌሎችም መከራ እየደረሰባቸዉ ያሉት ዜጎች መንግስት እንዲያድናቸዉ መላዉ የኢትዮጵያ ህዝብ ሰልፍ ወጥቶ ለመንግስት ተፅእኖ እንዲያደርግ በተጨማሪም ለአለም ህ/ሰብ ጩሀቱን ማሰማት አለበት። የኢትዮጵያ ህዝብ ወገኑ ሲጎዳ ወገኑን ለማዳን ደራሽ ነበረና ።አሁንም ለዚህ ወገን ህዝብ እንድረስለት ።
source. abrahadesta
No comments:
Post a Comment