ኢትዮጵያን ልትሸጥ ?
ይቺ ኢትዮጵያ የምትባል ሃገራችን ፈርዶባት በየቀኑ፤ በየሰአቱ፤ በየደቂቃው፤ በየሴኮንዱ አዳዲስ ችግርና መከራ እያፈጠጠባት ለስቃይ የተሰራች ሃገር እየሆነች ነው፡፡ ሀገራችን ብለን በፍቅር የምንጠራትና፤ ከክፉ ነገር እንድትጠበቅ፤ የምንጸልይላትና አቅማችን በፈቀደልን መጠን የምንጠብቃት በርካታ ልጆች ብንኖርም፤ በየደቂቃውና በየሴኮንዱ ክፉ የሚያስቡላት፤ መከራዋን የሚመኙላት፤ ዜማ ጭፈራቸው ጥፋቷን የሚመኝላት፤ ጥቂት፤ ከራሳቸውም፤ ከዜግነታቸውም፤ ከሰብአዊነታቸውም፤ ከተፈጥሯቸውም ተጣልተው፤ ከሆዳቸው ጋር ብቻ ተፋቅረውና ተግባብተው የሚኖሩ ኢምንት አርጉም የእንግዴ ልጆችም አሏት፡፡
ፈርዶባት ሁለቱንም ተሸክማ ታኖራለች፡፡ የእናት ሆድ ዥንጉርጉር እንዲሉ ከአንድ ሃገር የበቀሉ ቢሆኑም፤ ሕሊናቸው የሳተ፤ አስተሳሰባቸው
የተዛባ፤ አመለካከታቸው አቅጣጫውን የሳተ፤ ፍላጎታቸው እራሳቸውንም የሚያስከዳ፤ ሕልም ቅዠታቸውም ጥፋትን ብቻ የሚያስታውሳቸው፤ ራዕያቸው ነገን የማያስብ፤ ለዛሬ ሆድ ሙላት ብቻ የተዘረጋ፤ አያት፤ ቅድመ አያቶቻቸው ለሃገራቸውና ለሰንደቅ ዓላማቸው የነበራቸውን ፍቅርና ከበሬታ በአባቶቻቸው የተጀመረውን ክህደት በማጠናከር ለፍጻሜ ለማድረስ በእንፉቅቅ የሚሽመደመዱ ሆነው አንድ ላይ እንኖራለን፡፡
የነዚህ ሽምድምድ ጸረ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን መዘውርና ፈጣሪቸው የሆነው፤ ተንኮሉን በጭራ ነስንሶባቸው ሥራየ ጥላቻ ወእኩይን ካጠመቃቸውና ከገበሩለት በኋላ፤ በድንቁርና ተብትቦ፤ የመሃይምነት ካባ ደርቦላቸው፤ አለሁ እያለ መኖርን ሲያስመስል ሰንብቶ፤ ደህና ዋል ብለውት ለእንደምን አመሸህ ሳይበቃ፤ ለማንም ሳይነግር፤ የመሰሪነት ነፍስ አባቱን አስቀድሞ ልኮ ከእስርም ሳይፈታ፤ ሹልክ ብሎ እንደወጣ ቀረ፡፡ አለ ሲሉለት፤ ድኗል ሲሉለት፤ ለአዲስ ዓመት እንኳን አደረሳችሁ ይላል ሲሉለት፤ እረፍት ውሰድ ተብሎ ነው ሲሉለት ከረሙ፡፡ አቦይ ስብሃትና አባይ ጸሀዬም ከበረከት ጋር ዶልተው ከሚስቱ ተማክረው ‹‹አበበ ገላው እርግማኑን እንዲያነሳ እንማጸነው›› ብለው ሃሳብ ተቀባብለው ከውሳኔ ሳይደርሱ ጦርነት ሲመጣ ሹልክ ማለትን ተክኖታልና በዚያው መልክ ሹልክ ሽው ብሎ አመለጣቸው፡፡
ኢትዮጵያዊያንን ከሃገር እያስወጡ ለውጭ ግርድናና መከራ በመሸጥ ከፓስፖርትና ከሌሎችም ክፍያዎች በሃገር ውስጥ ገንዘባቸውን አጋብሶ ፤ ወደ ተሸጡበትም ሃገር ከሄዱ በኋላ የሚያገኙትን ገንዘባቸውን ቤተሰቦቻቸውን ለመርዳት የሚልኩትን ሂሳብ በውጭ ምንዛሬ እየተቀበለ ያለበትን የውጭ ገንዘብ እጥረት ሲወጣበት ከኖረ በኋላ፤ ሰሞኑን እንዳየነው ኢትዮጵያዊያንን ለሳውዲ የሸጠው ወያኔ፤ ዘረኛው ጠላታችን፤ ለሕዝብና ለሃገር ቅንጣት ግድ የሌለው መንግስታችን፤ በወገን ሞትና ስቃይ ፖለቲካ ሊነግድ፤ በሕዝብ ሰቆቃ ጮቤ ለመርገጥ የፈለገው ወያኔ ጉድ አሰማን፡፡ ጉድ አሳየን፡፡
በዓለም ዙርያ ያሉት ኢትዮጵያዊያን በነዚህ ወገኖቻችን ላይ የደረሰው ግፍና ሰቆቃ፤ ግድያ፤ አስቆጭቷቸው በሰው ሃገር ላይ ለወገን በመቆርቆር ሰልፍ ወጥተው አቤት እሪ ሲሉና ያሉበት ሃገር ሕዝቦችና የመንግስት ባለስልጣናትም ጥያቄው የሰብአዊ መብት መከበር ነውና፤ በሰልፉም ላይ ተሳትፎ እስከማድረግ በቅተዋል፡፡ ኢትዮጵያዊያን በያሉበት በዚህ ጉዳይ ላይ ሰልፍ ሲወጡ ጥበቃ በ ማድረግ ሲተባበር ተመልክተናል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ሕዝቦች ለሰልፍ ሲወጡ የከለከለና፤ ሰልፉን ከመበተን አልፎ ተሰላፊዎቹን ለእስር የዳረገ፤ የፈነከተና መሬት ላይ አጋድሞ ልክ በሳውዲ በወገኖቻችን ላይ እንደተፈጸመው በተመሳሳይ መንገድ ያስቀጠቀጠ መንግሥት የቀጠቀጠ ፖሊስ የወያኔ ፖለስ ብቻ ነው፡፡
በማንኛውም ታሪክና ወቅት፤የትኛውም ሃገር፤ ዜጎቹ በሰው ሃገር በህጋዊም ሆነ በሌላ ዘዴ ሄደው፤ ጉዳት ሲደርስባቸው፤ በደል ሲፈጸምባቸው በወገንተኛነት ጥብቅና መቆምና የዘጎችን ደህንነት ማስከበርን ቀደምት ሲያደርግና ድርጊቱን ሲኮንን እንጂ የተበዳይ ወገኖች በራሳቸው ሃገር ለወገኖቻቸው ድርጊቱን በመቃወም ሰልፍ ሲወጡ ለበዳይ በመወገን ግፍ እንዲፈጽም ፖሊስንና ደህንነቱን የሚያዝ መንገስት፤ ግፈ ፈጽሙ ብሎ የሚያዝን መንግስት ትእዛዝ ተቀብሎ የራሱን ወገኖች የሚቀጠቅጥ የሚያቆስልና የሚያስር፤ ፖለስና ደህንነትም ታይቶም ተሰምቶም አይታወቅም፡፡
ያንን እኩይ ተግባር ሰምተን ከቁጭትና ከሃዘን ሳንላቀቅ፤ ወገኖቻችንም ተመልሰው ወደ ቤታቸው ሳይገቡ፤ በሳውዲ ያለውም ግፍና ሰቆቃ ገና ሳይቆም፤ ሌላ ጉድ የሚያሰኝ ነገር ደግሞ አጋጠመኝ፡፡ ሪፖርተር የተባለውን የነሱኑ ደጋፊና ምልስ አባል ጋዜጣ፤ አንድ ወዳጄ ገዝቶት ሲያነብ፤ በጨረፍታ አይኔ ሲያማትር፤ ለማመን የሚያስቸግር ዜና አየሁና ወዲያው በካሜራ ያዝኩት፡፡
ይታያችሁ እንግዲህ ሰዉን መሸጡ አልበቃ ብሎት፤ ይሄው እንደምታዩት ‹‹በኢትዮጵያን ይግዙ›› የንግድ ትርኢት……………. የሚል ማስታወቂያ በድፍረት አውጥቷል፡፡ ምናልባት አሁን ጥያቄ ሲያስነሳ የሕትመት ስህተት ነው የሚል ሰበብ ይሰጠው ይሆናል፤ እውነቱ ግን የሰፈረውን አባባልና ‹‹ ምናልባት›› ከሚባል ግንዛቤ ባለፈ የተዘጋጀ ጽሁፍ ለመሆኑ የጋዜጣው ባለቤት አቋም የሚያረጋግጠው ነው፡፡
ባለፈው ሳምንት በድንገት ሰው ቤት እያለሁ ስለ ሙስና፤ ስለሽብር ፓርላማ ውስጥ ዲስኩር ሲደረግ መመርያው ይሰጥ የነበረው ከቴሌቪዥን በሚወጣ የሟቹ አሸብር ዜናዊ ድምጽና ምስል ነበር፡፡ ራዕይ ነዋ!
ይሄው ለዚህ ለሀገር ሽያጭ የንግድ ትርኢት በቃንና አረፍነው፡፡ ይህም የታላቁ ዘረኛ ራዕይ ተግባራዊ ሲደረግ ነው ማለት ነው፡፡
ኢትዮጵያ ለዘላለም በክብር ትኑር !!!
No comments:
Post a Comment