Friday, November 1, 2013

አመፀኛው ንፋስ በልጅግ ዓሊ

አመፀኛው ነፋስ 

ባሰላው ባሰላው እንቢ አለኝ እንዝርቱ፣ 
ከታችም አይደለ ከላይ ነው ጥመቱ። 
የጎንደር ሕዝብ እንጉርጉሮ 

ኦክቶበር 28 እንደ ሃገሩ አቆጣጠር ጠዋት ጉልበተኛ ነፋስ ከባሕር ተነስቶ በደቡብ እንግሊዝ በኩል አድርጎ እያቆራረጠ 
ወደ ሰሜን ተፈተለከ። የባሕሩ ሰይጣን የላከውን ጉልበተኛውን ነፋስ የፈራው አዳሜ ፈረንጅ ሁሉ ተርበትብቶ እኛንም 
በሬዲዮንና በቴሌቪዚዮን ሲያርበተብተን ሰነበተ። 


“ይህንን ቀን ከቆመ የተቀመጠ፣ ከተቀመጠም የተደበቀ ነው የሚያልፈው። ደፍሮ በንቀት ደጅ የቆመ እርሱን አያድርገኝ። 
ይህ አደገኛ ንፋስ ንቆ የሚልፈው ነገር ያለ እንዳይመስላችሁ። ከጉልበቱ ብዛት የቆመውን ዛፍ አንስቶ እላያችሁ ላይ ነው 
የሚከለብሰው። በራችሁንና መስኮታችሁን ጠርቅማችሁ ዘግታችሁ ጠብቁት’’ ስንባል ከረምን። 

አዳሜ ፈረንጅ በእግዜር ሥራ ገብቶ ከባሕሩ ሠይጣን፣ ከነፋሱ ጋር ቀጠሮ የያዘ ይመስላል፡ - “በጠዋት ሊነጋጋ ሲል 
ከእንቅልፍ ሳትነሱ ስለሚደርስ ከቤት እንዳትወጡ፤ ከቤት ከውጣችሁ የባቡርም ሆነ የአውቶቡስ አገልግሎት አታገኙም። 
ይቆማሉ። ሥራም አይታሰብ። እናም ከቤት ዋሉ“ ሲል ምክር አይሉት ተግሳጽ ግራ የሚያጋባ ማስፈራራት ሲነግረን 
ሰነበተ። 

ፈረንጅ ተራቅቆ የለ። ቃሉ ጠብ አላለም። በቀጠሮው ሰዓት ሊነጋጋ ሲል ነውጡ ተደመጠ። ጠብ ያለሽ በዳቦ እያለ፣ 
የሚያስፈራ ድምጽ እያሰማ፣ ያገኘውን ሁሉ እንደ ደረሰ እየደረማመሰ በፍጥነት ወደ ሰሜን ነጎደ። አፈጣጠኑ ምናልባት 
የሚቸኩልበት የጥፋት ቀጠሮ ይኖረው ይሆናል። 
ማን ያውቃል! 

የመስቀል ወፍና የአደይ አበባ፣ 
ቀጠሮ እንዳላቸው መስከረም ሲጠባ፣ 

ማን ነበር ይህንን ስንኝ የቋጠረው? 

የፈረንጅ የክረምት ንጋት አርፍዶ ስለሆነ አረፋፍደን ስንወጣ ጠቡ የከፋው ከዛፋ ጋር እንደነበረ ነበረ የተረዳነው። 
አልፋለሁ አታልፍም ፍልሚያው ለባለ ጉልበት አደላ። ዛፉ ወይ ቆሰሎ ወይ ተሰብሮ ይታያል። ተፈንግሎ መሬት ላይ 
የተዘረረ ብዙ ነበር። 

ጉልበታም ምንጊዜም የሚበረታው በሰላማዊ ላይ ነው። ያ ኩሩ ዛፍ ኩራቱን በድንገት ተገፈፈ። ያ ደግ ዛፍ የበጋውን 
ቃጠሎ እንዳልተገነ ፣ የክፉ ቀን ሰው ባለማግኘቱ የጥቃቱ ሰለባ ሆነ። ዛፉስ በደግ ሥራው መንግሥተ ሰማያት ይገባል። 
ይብላኝ ለኛ በጋውን ዛፉ ሥር ቁጭ ብለን ሃሩሩን ለምናሳልፈው። ይብላኝ ለሰው ፍጡር ከጉልበተኛ ጋር ለሚያብረው። 
ሠፈሩ ድረስ በመጣ ጉልበተኛ ተገንድሶ ሲጠቃ፣ ቆሞ የታዘበው ሁሉ ግን ለዛፉ ወለታ ቢስነቱን ነበር ያሳየው። 

የወደቀው ዛፍ መንገድ ዘግቶ አላፊ አግዳሚውን አንሱኝ እያለ ሲለምን ማንም ዞር ብሎ አላየውም። ማን ደፍሮ ቀና 
ያድርገው? ዛፍን ቀና ማድረግ ቢቻልስ ከዚህ ከጉልበተኛሰ ነፋስ መጣላት አይደል። የሰው ጠባይ ሆኖ ተሸንፎ ለወደቀ 
ማን ያዝናል። ለጉልበተኛ ለንፋስ ያግዛል እንጂ። ማንም ደፍሮ ቀና አድርጎ ሊያቆመው አልሞከረም። እንዲያውም የሞተር 
መጋዛቸውን ይዘው መጥተው እወደቀበት ላይ ቆራርጠው ጣሉት። የነፋሱ አጋዦች ከጉልበተኛ ንፋስ ጋር ወግነው 
ለዘመናት አብሮ የኖረውን ዛፍ ቆራርጠው ከቀየው አስወገዱት። 

ያዘኑ “ይህንን ምስኪን ዛፍ የት ልታደርሱት ነው?’’ ብለው ጠይቀው ነበር። “የት አባቱ ይህ ጨቋኝ ዛሬ ጉድ ሆነ። እዚህ 
እፊታችን ተገትሮ አሻግረን ማዶውን የጎረቤቶቻችንን ኑሮ እንዳናይ እየከለከለን የነበረ አይደል’’ ሲሉ ተመጻደቁበት። 
በወደቀ ዛፍ ምሳር ይበዛበታል ያሉት ደረሰ። “እላያችን ላይ ይወድቃል ብለን ፈርተን ስናሞግሰው የወደድነው መስሎት 
ከነበረ ተሳስቷል። እድሜ ለነፋሱ አሻግረን እንድናይ ፈቅዶልናል። ይህንን ብኩን ፍጡር አቃጥለን ቤታችንን በክረምት 
እናሞቅበታል ’’ አሉ። ወፎቹ ቤታቸው ፈርሶ ሲያዝኑ ሌላው ቤቱን ማሞቂያ እንጨት በማግኘቱ ይደሰታል። 
ሰማዩ ግን አዘነ። አለቀሰም።ሰማይ እንደ ትላንት አዝኖ ሲያለቅስ ታይቶም አይታወቅ። ከልቡ ነበር ያዘነ። ጉልበተኛ 
ከመምጣቱ በፊት የሚያደርሰውን ጉዳት አስቦ ይመስላል ለቅሶውን ከንፋሱ በፊት ነበር የጀመረው። ምርር ብሎ ከማልቀሱ 
የተነሳ እምባውን አጎረፈ።የሰማዩ እንባ ነፋሱ ሽሽት ቤቱን ነቀነቀው። ግን ማን ሰምቶት። ነፋሱም ያገኘውን ሁሉ በጥፊ 
ማጠናገሩን ቀጠለ። እምባውም ጎረፈ። በየሰውም ቤት መግባት ጀመረ። ሰውም በአባራሪው ንፋስ ሳይሆን በተጠቂው 
ዝናብ ተማረረ። 
 አመፀኛው ንፋስ በልጅግ ዓሊ 
 2
ጉልበተኛው ነፋስ ለብዙ ሰዓታት እልኩ አልበረደለትም ነበር። ውጭ ሆኖ በስሱ ሲፎክር ዋለ። አንገታቸውን የደፉትን 
ትንንሽ ቅርጫፎች እየበጣጠሰ ከእናታቸው እየነጠቀ እያሽቀነጠረ እየጣላቸው ነበር። አዳሜ የድሮ የድሎት ኑሮዋን 
ለመመለስ እየተራወጠች ነበር። ያልገባት ሲወድቅ ዝም ብላ የተመለከተችው ዛፍ በበጋው ቃጠሎ ብትፈልገውም 
እንደማታገኘው ነው። ቆራርጦ መውስድ ቀላል ቢሆንም መልሶ መትከልና ማሳደግ ከባድ መሆኑን አልተገነዘበችም። 
እንደው ብቻ ምን እንደሚከተል ሳታውቅ የነበረውን ጉልበተኛ ሲያፈርስ ትተባበራለች። ከጉልበተኛው ጥቅምን ስትሻ 
ከንፋስ በላይ ንፋስ ትሆናለች። ንፋስ ሲያጠፋ አብራ ታጠፋለች። ንፋስ ሲጠፋ አዳሜ ደግሞ ወደሚቀጥለው ንፋስ 
ትሻገራለች። ይህ ለጉልበተኛ ማደር አዳሜን ለመደባት አይደል? 

ይህ አደገኛ ነፋስ በዚያ ፍጥነቱ አራት ሰው እዚሁ ታላቋ ብርታንያ ውስጥ ገድሎ አልፏል። በሌሎች የአውሮፓ አገሮችም 
ብዙ ብዙ አጥፍቷል። ንብረትም ብዙ ባክኗል። ፈረንጅስ ገንዘብ አለው መልሶ ይገናባዋል። ሃይቲ ላይ እንደደረሰው 
መሬት መንቀጥቀጥ ይህ የተፈጥሮ ችግር ደሃ ላይ ሲደርስ አይጣል ነው። መከራው ለብዙ ዓመታት ይቀጥላል። የሃብታም 
ሃገሮች እርዳታ እንደሆነ ለይስሙላ ነው። እሱስ ለደሃው ከመድረሱ በፊት በአስተዳደር ወጪ እዚያው እተሰበሰበበት 
አይደል የሚያልቅ። 

ዛፉስ አንድ ሞቱን ነበር የሞተው። ከዛፉ ጋር መኖሪያዋ ለፈረሰው ወፍ አዘንኩ። ወፎቹን ስመለከት ጉልበተኛው ንፋስ 
አዱ ገነት ሸገር ላይ ቢመጣ ሊያደርስ የሚችለውን ጥፋት ሳስበው ዘገነነኝ። ተወልደን ያደግንበት ሠፈር ከመሬት ገጽ 
ሲጠፋ አሰብኩት።ያ የዛገ የጣራ ቆርቆሮ ክንፍ አውጥቶ ሲበር ታየኝ። ቆርቆሮውን ያያዘው ባለ ባርኔጣ ምስማር ይህንን 
ጉልበተኛ የሚከላከል አይሆንም። ቤቶቹስ ከተሰሩ ሰነበቱ’ኮ። ግማሹቹ የኮንጎና የኮሪያ ዘማቾች የሠሯቸው ናቸው። ዘመኑ 
የትየለሌ . . . ። 

ቤቶቹ ከፈረሱ እንደ ወፏ መኖሪውን የሚነጠቀውን ነዋሪ አሰብኩት። በክረምት የቤት ማሞቂያ እንጨት አገኘሁ ብሎ 
የሚደሰተውን አስብኩት። ደሃው ሕዝብ በድንኳን ራቅ ተደርጎ ወደማይታይበት ሠፈር ይጣል ይሆናል። መቼም ከዚህ 
ከከተማው እንብርት የሚያስቀምጠው የለም። ከዚያም የዴያስፖራ ጆፌ አሞራ “ኢንቬስተር’’(በየኤምባሲው ተመዝግቦ 
ቁጭ ብሎ የሚጠብቀው ሁሉ) ሎተሪ ወጣለት ማለት ነው። ለወያኔና ለደጋፊ “ኢንቬስተሮች’’ ሰርግና ምላሽ ይሆናል። 
ቤቱ በፈረሰበት ሕዝብ ላይ መሬቱን ለመቀራመት ይጫረቱበት ይሆናል። መቼም ህዝቡ ፕላስ 2. . . ፕላስ 3 . . . ፕላስ 
ገለመሌ . . .የሚባለውን ለመሥራት አቅም የለውም። ሌላው ቢቀር ይህ ኮንደሚኒየም የሚባለው እስከሚሰራ የት 
ይሠፍር ይሆን? 
መቼም ይህንን የጥፋት ዘመን እግዚያብሔር ከላያችን ያንሳልን። ሃገራችንን የአባቶቻችንን ከራማ ይጠብቅል። አላህ ወደ 
ፈተናም አያግባን። ዋቅ ከክፉ ይጠብቀን እንጂ አደጋው ቢደርስ የሚከተለውን ችግር መገመት ይከብዳል። ማን ያውቃል 
እንደተለመደው እርዳታውስ በኢሕአዴግ ድርጅቶች አባልነት ሳይሆን ይቀራል። ሕዝብ መሪዎቹን በማይመርጥበት ሃገር 
መፈክሩ የተገላቢጦሽ ነው። “ካጠገብከው ያምጻል ፣ ካስራብከው አባልህ ይሆናል’’ ነውና። 

ምድረ የእርዳታ ድርጅትም(NGO) ቢሆን ሎተሪ ይወጣለት ነበር። አዲስ የመለመኛ ምክንያት። መንግሥት እነዚህ 
ሆዳም ድርጅቶችን ተንከባክቦ በማያዝ የሰበሰቡትን እርዳታ ራሳቸው እንዲዝናኑበት ያደርጋል። እነርሱም አጻፋውን 
ዴሞክራሲዊ መንግሥት ብለው ይክቡታል። ልከክልህ እከክክልኝ ዓይነት ትብብር። 

ጸሎታችን ከእንደዚህ ዓይነት አደጋ ሕዝባችንን እንዲሰውርልን ነው። ከዚህስ ጉድ ያድነን። የስምንተኛው ሺህ ምልክት 
ከሆነው . . . ሆዳም ከድሃ ላይ ቀምቶ ከሚበላበት . . . መሬት ላራሹ ሳይሆን መሬት ለራሴ ከሆነበት . . . ጉልበት 
ካለው ጋር አብሮ ለመጎልበት ከምንራወጥበት . . . ደካማን ለማጥፈት ወደ ኋላ ከማንልበት፣ ክህደት 
የበዛበት. . . ዘመን . . . ይሰውረን። አሜን . . . 

ለሟቾች ነፍስ ይማር እንላለን። 

ሰለ ሃገራችን ደህንነት የሚያስቡ በሰላም ይክረሙ! 
ለንደን 29/10/13 
በልጅግ ዓሊ 
Beljig.ali@gmail.com 


No comments:

Post a Comment