Wednesday, October 1, 2014

ልማት ያለ ነፃነትና ፍትሕ ፋይዳ የለውም

ከይኩኖ መስፍን (ቦስቶን ሰሜን አሜሪካ )
ሙሱና! አፈና እና አድልዎ ከማንም ግዜ በላይ በሰፈነበት ሀገር ዘላቂ ፍትሕ! ዴሞክራሲ! ዕድገትና የህግ የበላይነት ይመጣል ብሎ ማሰብ ከእባብ እንቁላል እርግብ ይወለዳል ብሎ መጠበቅ ነው:: ዛሬ በኢትዮያ ሙሱና እና ዓይን ያወጣ ያገር ሀብት ዘረፋ የስርዓቱን ሁለንትናዊ መገለጫ ባህሪይ ከመሆኑም በላይ የህዝባችንን ንሮና ህይወት እየገደለና እያቀጨጨ ያለው ከኤይድስ በላይ ስር የሰደደ ተላላፊ በሽታ እየሆነ መጥቷል:: ዘረፋውም ሆነ አፈናው ከግለ ሰብ አልፎ ወደ ተቋማዊና የተደራጀ ሌብነት በመሸጋገሩ ኢትዮያ ሕገ መንግስታዊ ዋስትና የሌላት” ፍትሕ አልባ የሆነች ሀገር አድርጓታል::
እኔ የምኖረው በውጭ ዓለም በሰሜን አሜሪካ ቢሆንም በቅርቡ ለግል ጉዳይና ቤተሰቦቼን ለመጠየቅ ወደ ኢትዮያ ሂጄ ስለነበር ለሶስት ወር ያህል አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ቦታዎች ተዘዋውሬ ከተለያዩ አቅጣጫዎች በወሬ የምሰማውን ነገር ሁሉ በአካል ተገኝቼ በቀጥታ በሕብረተሰቡ ዘንድ በመሬት ላይ ያለው እውነታ ምን እንደሚመስል በማየቴ ብዙ ነገሮችን ለመገንዘብና ለመማር ጥሩ ዕድል አጋጥሞኛል::

እኔም “ማየት ማመን ነውና” በቅርብ ተገኝቼ ባንድ በኩል ከህዝቡ አንደበት የሰማሁትንና ያየሁትን እሮሮ በሌላው ገጽ ደግሞ በመንግስት በኩል ያለው ተግባራዊ ምላሽና እንቅስቃሴ ምን እንደሆነ ሰፊው ሕብረተሰብ በተለይም ከሁኔታው ርቆ በውጭ ዓለም በዲያስፓራ የሚኖረው ኢትዮያዊ ወገን ሁሉ ማወቅ አለበት ብዬ ያሰብኩዋቸውን አንገብጋቢ ጉዳዮች በማንሳት አቅሜ የፈቀደውንና አእምሮየን የዘገበውን ያህል በማካተት የተሰማኝን ስሜትና ተሞክሮ ለማካፈል ከዚህ ቀጥሎ ያለው ጠቅለል ያለ ሃሳብ ለማቅረብ ሞክሬያለሁ::

ክፍል አንድ:-
የኢኮኖሚና የማሕበራዊ ፍትሕ ጥያቄ
በስልጣን ላይ ያለው የህወሓት/ኢሕአዴግ ሞኖፓላዊ ፓርቲ በተለያዩ የዜና አውታሮች አማካይነት ለኢትዮያውያን ከዚያም አልፎ ለዓለም ማሕበረሰብ ነጋ ጠባ አሸብራቂ በሆኑት ቃላት እንደሚገልፀው “በልማታዊ መንግስታችን አመራር ስር ኢትዮያ በፈጣን ዕድገት ጎዳና ላይ ነች:: በቅርቡም መካከለኛ ገቢ ካላቸው በማደግ ላይ የሚገኙ ሀገሮች ተርታ ትሰለፋለች:: ህዝቡም የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ስርዓት የልማት ተጠቃሚ ሆነዋል:: በአቶ መለስ ዜናዊ የልማት ራዕይ ድሕነት በቅርቡ ነበር ሆኖ ይቀራል” ወዘተ ወዘተ ሲሉ ይደመጣሉ::
በየደረጃው የተኰለኰሉ ካድሬዎችና የፓርቲው የአብዮታዊ ዴሞክራሲ አፍቃሪዎችም የሚነግሩን ይህንን ነው:: በአብያተ ትምህርትም ከመዋእለ ህፃናት ጀምሮ እስከ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ያሉት መምህራንና ርእሳነ መምህራን የሚሰብኩትና ለለጋ ወጣቱ የሚያስተምሩት ይህንን ነው::
በህዝብ አንጡራ ገንዘብ የሚተዳደሩ የብዙሃን መገናኛ ጋዜጠኞችና አንዳንድ አፈ ቀላጤ ምሁራንም ሆኑ ከላይ ያሉት ባለስልጣናት የሚያስተጋቡትና የሚሰሩት ተውኔት “በሀገራችን ልማት ተረጋግጧል የሚል ነው:: ከርእሰ ብሄሩ ጀምሮ እስከ ታች ቀበሌና ጎጥ ድረስ ያሉት የአስተዳዳር አካላትም ረሃብተኛውን ህዝብ የሕልም እንጀራ ለማብላት ሲባል ዋና ስራቸው “ኢትዮያ ለምታለች” የሚል ፕሮፓጋንዳ ማሰራጨትና ማስተማር ነው፡፡
ይሁን እንጂ ይህ ሁሉ በቢሊዮን የሚቆጠር የህዝብ ሀብት ወጪ እየተደረገበት የሚተላለፈው የፕሮፖጋንዳ ክምር እና በልማት ስም የሚሰራው ስንክሳር ድራማ በመሬት ላይ ያለው ሓቅ ሊሸፍነውና ሊለውጠው አልቻለም:: እርግጥ ነው በአዲስ አበባና በሌሎች አንዳንድ የክፍላተ ሀገር ከተሞች መጠነኛ ትላልቅ ፎቆች፣ መንገዶች፣ ትምህርት ቤቶች! የጤና ተቋማት፣ እንዲሁም አንዳንድ ግድቦች አልተሰሩም አልልም:: ማንኛውም መንግስት መጠኑን ይለያል ይሆናል እንጂ በጊዜው አንዳንድ ነገር ሰርቶ ያልፋልና:: ነገር ግን ዋናው እና መሰረታዊ ጥያቄው ስንት ፎቅ ተሰራ፣ ስንት ግድብ ተገነባ፣ ስንት ተማሪ ወደ ትምህርት ቤት ሄደ! ሳይሆን በሀገሪትዋ የዜጎች ሰብኣዊ መብትና ነፃነት፣ የሕግ የበላይነት! ማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፍትሕ ሳይረጋገጥ ዘላቂ ልማትና ዕድገት ሊኖር ይችላል ወይ? የዕድገቱንና የልማቱን ባለቤት ማን ነው? በህወሓት ኢሕአዴግ የልማት ፓሊሲ ማን ነው እየለማ ያለው? አሁን ያለው የትምህርት ፓሊሲ ምን ዓይነት ትውልድ ነው እያፈራ ያለው? በአጠቃላይ መሰረቱ የተናደ ቤትና ስርዓት ዘላቂነት ያለው ልማትና ዕድገት ሊያመጣ ይችላል ወይ? የሚሉትንና ሌሎች የህዝቡን የልብ ትርታ የሚነኩ ጥያቄዎች በቅድሚያ መመለስ ያለባቸው ይመስለኛል::
የስርዓቱን የልማት ፓሊሲና አመራር ምን ያህል ትውልድ ገዳይና ሀገር አውዳሚ መሆኑን ለመገንዘብም ሆነ ለማወቅ የግድ የተወሳሰበ ቲኦሪ መተንተን ወይም የፓለቲካ ፈላስፋ መሆን የሚያስፈልገው ጉዳይ አይደለም:: ሀገርንና ህዝብን ማእከል አድረገው ካዩት በያንዳንዱ ቤት ያለው የንሮ ችግር! በየልማት ዘርፉ የሚታየው ዝርፊያ! በወጣቱ ትውልድ ዘንድ የሚታየው ተስፋ መቁረጥና ፍልሰት! በማሕበራዊ ንሮ የሚታየው ምስቅልቅል! በየመንግስት መሥሪያ ቤቱ በየደረጃው የሚታየው አስተዳዳራዊ አድልዎ! በሕብረተሰቡ ውስጥ የሚታየው ፍርሃትና ስጋት ሁሉም ተደማምረው የስርዓቱን አስከፊ ባሕሪይ አፍ አውጥተው የሚናገሩ የህዝቡ እሮሮዎች ናቸው:: አብዛኛውን በቀን አንድ ጊዜ እንኳን መብላት የተሳነው ህዝብ ይዞ ስለ ልማት ማውራት በሕብረተሰቡ ላይ ከመቀለድ በስተቀር ሌላ ትርጉም ሊሰጠው አይችልም:: ችግሩ በዚሁ ፅሑፍ ብቻ ተወርቶ የሚያልቅ ባይሆንም ሁኔታውን ለማወቅ ብዬ በተለያዩ የስራ ቦታዎች ተንቀሳቅሼ ከተመለከትኩዋችው ችግሮች ውስጥ የሚከተሉትን አብነቶች መጥቀሱ ብቻ በቂ ይመስለኛል::
በትምህርት
ትምህርት ላንድ ሀገር የእውቀት ማፍለቂያ መሳሪያ ብቻ ሳይሆን የልማትና የእድገት አንቀሳቃሽ ሞተርም ጭምር ነው:: አብዛኞቹ ያደጉና በፈጣን እድገት ላይ ያሉት ሀገሮች የእድገታቸው ሞሰሶና መነሻ የሆነው ከሁሉም በላይ ነፃ አስተሳሰብ ካለው ሕብረተሰብ የሚመነጭ የሰብኣዊ ዓቅም ግንባታ ላይ ቅድሚያ በመስጠት በቀጣይነት ስለተረባረቡ ነው:: በዓለም ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነ ኢኮኖሚ የሚሸከምና የሚያንቀሳቅስ ሕብረተሰብ (ክህሎት) ለመገንባት ደግሞ ቢያንስ የሞያ ነፃነት፣ ደረጃውን የጠበቀና ከአንድ ፓርቲ ተፅዕኖ ነፃ የሆነ ስርዓተ ትምህርት! በነፃነትና በጤናማ ውድድር ላይ የተመሰረተ የትምህርት ጥራት ማረጋገጥ ወሳኝነት አለው::
ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የትምህርት ስርዓት ግን በተገላቢጦሽ ነው:: ላንድ ሰራተኛ ለመቅጠር መመዘኛው የሞያ ጥራትና ክህሎት ሳይሆን ለድርጅት ያለው ቅርበትና የፖለቲካ ታማኝነት ነው:: የሀገሪትዋ ስርዓተ ትምህርትና ፓሊሲም የሚመነጨው ከዓለም አቀፍ የእውቀት ስታንዳርድ እና ከሀገሪትዋ ነባራዊ ሁኔታ ሳይሆን ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ የጥቂት ሰዎች ሞኖፓላዊ አስተሳሰብ እና እምነት ነው:: ለምሳሌ የትምህርት ቢሮ ሃላፊዎች ሁሉም የፓርቲ አባላት ወይም ካድሬዎች ናቸው፡፡ አስተማሪዎች ከ95 በመቶ በላይ የፓርቲ አባላት ናቸው፡፡ አባል ያልሆኑና በነፃ ህሊና ማገልገል የሚፈልጉ ብቃት ያላቸው ባለሞያዎች ምንም የስራ እድገት እንዲያገኙ አይፈቀድላቸውም ብቻ ሳይሆን በስራ ገበታቸው የመቆየት እድላቸውም በጣም ትንሽ ነው፡፡ በሰበብ አስባቡ እንዲባረሩ እና እንዲጎሳቆሉ ይደረጋል፡፡ እነዚህ ሰዎች በስራቸው የሚተማመኑ እና ብቃት ያላቸው ቢሆኑም ሆን ተብሎ ከህብረተሰቡ እንዲገለሉ እና እንዲሸማቀቁ ይደረጋሉ፡፡ ትምህርት ከጨረሱ በሗላም የተሻለ የስራ ዕድል ለማግኘት! ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለመግባት! ወደ ውጭ ሀገር እስኮላርፕ ለመላክ! የመሳሰሉ ዕድሎች ቅድሚያ የሚሰጣቸው የፓርቲ አባላት! ታማኝና ደጋፊዎቻቸው ናቸው:: ሌሎች ብዙሃኑ ዜጎች ግን በገዛ ሀገራቸው ባይተዋር እና የበዪ ተመልካች ሆነው ከመቅረት ሌላ አማራጭ የላቸውም::
ከትምህርት ጋር ተያይዞ ሌላው በጣም አሳሳቢና አስደንጋጭ ችግር ደግሞ አሁን የድርጅቱን አባላት! ታማኞች የሆኑ ሰዎች! እንዲሁም በየወረዳው የትምህርት ቢሮ የሚሰሩ ካድሬዎች እና ባለስልጣናት ከዛው ከወረዳው ትምህርት ቢሮ ውስጥ የሚቀናጀው የዲግሪ ፕሮገራም ፅሁፍ በመቸብቸብ የሐሰት ዲግሪ እየተሸከሙ የሕብረተሰቡን ሸክም የመሆን አባዜ ነው፡፡ ለአንድ የዲግሪ ፅሁፍ እስከ 500 ብር እንደሚሸጥ አረጋግጬለሁ:: በአንድ የወረዳ ትምህርት ቢሮ የሚሸጠው የዲገሪ ማዘጋጃ ሰነድም ለማስረጃነት ያህል በእጄ ይገኛል፡፡ ስም እና አድራሻ እያቀያየሩና እያባዙ በተሰማሩበት ሁሉ ይቸበቸባል:: ልብ በሉ!! በዚሁ ዓይነት የሐሰት ዲግሪ በተሸከሙ ሰዎች የሚመራው ሕብረተሰብ! የሚማረው ወጣት ትውልድ! የሚቀየሰው የልማት ስተራተጂና ፓሊሲ ምን ያህል ውጤታማ እና ዘላቂነት ይኖረዋል ብላችሁ ትገምታላችሁ?
አዎ!! የዚህ ሁሉ ድምር ዉጤትም በካድሬ ቁጥጥር ስር የተማሩ ወጣቶች ለውጥ ማምጣት ካልቻሉ” አስረኛ ክፍል ጨርሶ ስማቸውን በደንብ መፃፍ ካልቻሉ” ወደ 80 በመቶ አስረኛ ክፍል ማለፍ ካልቻሉ” 20 በመቶው 11 እና 12 ተምሮ እንደገና 50 በመቶ ከወደቀ” በመጨረሻ ሁሉንም መሰናክል አልፎ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ገብቶ ከተማረ በውሗላም ያንድ ፓርቲ አገልጋይ እንዲሆን የሚፈረድበት ከሆነና ተመልሶ ወደ አላስፈላጊ ብክነትና ማሕበራዊ ቀውስ በመግባት የሕብረተሰቡን ሸከም ሆኖ የሚቀር ከሆነ ትምህርት ቤት መመላለሱ ፋይዳ ምንድን ነው?
በጤና እና በሌሎች የመሰረተ ልማት ዘርፎች
ህዝቡ በጤና ዙርያ ያለበት ችግርም በጣም ብዙ ነው፡፡ በአማካይ በየወረዳው ያለው የህዝብ ብዛት ከ150 ሺ እስከ 200ሺ ይደርሳል፡፡ ልክ ከላይ በትምህርት ዘርፍ እንዳየነው ሁሉ የጤና ቢሮ ሃላፊ በሞያው ተመጣጣኝ እውቀት የሌለው የፓርቲ እና የመንግስት ታማኝ ነው፡፡ የሚሰራው ስራም የፖለቲካ ነው፡፡ በጥቂቱ ለ200 ሺ ህዝብ አንድ ዶክተር ማግኘት ወይም መመደብ አልተቻለም፡፡ በዚህ ምክንያት ህዝቡ ወደ ሌላ ቦታ ሻል ያሉ ትላልቅ ከተሞች ሄዶ ለመታከም ደግሞ ከተለያዩ የኢኮኖሚ ችግሮች ባሻገር እዛ ሂዶም ትክክለኛ ህክምና አያገኝም፡፡ በሞያው ማነስ ምክንያትም ለተለያዩ ችግሮች ይዳረጋል:: ለምሳሌ ለበሽታው የተሳሳተ መድሃኒት መስጠት! ጊዜው ያለፈበት መድሃኒት መስጠት! ከአቅም በላይ ገንዘብ መጠየቅ! ለሰሩት ስህተት ተጠያቂ አለመሆን! መንግስት የመደበው መድሓኒት በመንገድ ላይ መሰወር የመሳሰሉ ችግሮች የተለመዱ ሆኗል:: መንግስት በብዙሃን መገናኛ በኩል የሚለው እና በመሬት ላይ ያለው ሃቅ በጣም የተለያዩ ናቸው፡፡
በሌሎች የአገልግሎትና የልማት ዘርፎች የሚታየው እንቅስቃሴም ተመሳሳይ ነው:: ለምሳሌ የኤለክቲሪክ መብራት አላቸው በሚባሉ ከተሞች ቢያንስ በቀን ወደ አራት ገዜ እንደሚጠፋ ነዋሪዎቹ ይናገራሉ፡፡ ችግሩ መብራት መጥፋቱ ብቻ ሳይሆን መቼ ተመልሶ ሊመጣ እንደሚችል እና ህዝቡም ምን ማድረግ እንዳለበት የሚያውቅበት አሰራር የለም፡፡ በዚህ ምክንያት ብዙ የተጀመሩ ስራዎች ይስተጓጎላሉ:: አንዳንድ ምርቶችም ተበላሽተው የሚጣሉበት ጊዜ እንዳለ ይታያል:: አንድ ቀን በዓይኔ ያየሁት ቀላል ገጠመኝ ላንሳ፡፡ የፀጉር አስተካካይ ቤት ነው፡፡ በርካታ ሰዎች ፀጉራቸውን ለመስተካከል ተራ ይዟል:: በዚህ ማሃል መብራቱ ጠፋ እና ሰዎቹ የተወሰነ ጊዜ ከጠበቁ በሗላ ወደየቤታቸው ሄዱ፡፡ የተወሰኑ ሰዎች ደግሞ በጅምር ላይ ስለነበሩ ግማሽ ፀጉር ይዘው እንዴት ቤት መሄድ እንደሚችሉ ተቸግረው እነሱም ሳይቀር ራሳቸው በራሳቸው እየሳቁ ሄዱ፡፡ ይህንን ቀላል ነገር ለአብነት ያህል ጠቀስኩ እንጂ በዚሁ ብልሹ አስተዳደር ምክንያት ተጠያቂነት በሌለበት አኳሃን የሚጉላላው የሰው ብዛት እና የሚባክነው የህዝብና ያገር ሀብት ቤቱ ይቁጠረው፡፡
ሌላው በኢትዮያ ትልቁ የመዝረፊያ ቦታ በመንገድ ስራ! በውሃ ሀብት ልማት! በመሬት ድልድል! በቤቶች ኮንስትራክሽን! በሰፋፊ የግልና የመንግስት እርሻዎች ያለው የፕሮጀክት እንቅስቃሴ ነው:: እነዚህ ፕሮጀክቶች አንዳንዴም “የባለስልጣኖች የሚታለቡ ላሞች” እየተባሉ እንደሚጠሩ በዘርፉ የሚሰሩ ጓደኞቼ ነግረውኛል:: በነዚህ ፕሮጀክቶች ከውጭ በእርዳታና በብድር የሚገኘው ዕዳን ጨምሮ በየዓመቱ በብዙ ቢሊዮን የሚፈሰው መዋእለ ንዋይና በጀት ቁጥር ስፍር የለውም:: በነዚህ የስራ ዘርፎች ቀጥተኛ እጅና ተሳታፊነት ያላቸው ግዙፍ ባለድርሻዎች በዋናነት የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ተቋራጮች (ኮንትራክቶሮች)! ዲዛይኖሮች! ኮንሳልታንቶችና እንዲሁም የመንግስት ተቆጣጣሪዎችና ተጠሪዎች ናቸው::
በነዚህ የልማት ዘርፎችና ፕሮጀክቶች አካባቢ ጎልተው ከሚታዩ መሰረታዊ ችግሮች ውስጥ አንዱና ዋነኛው ማነቆ የባለ ሙያዎች (ብቁ የሰለጠነ የሰው ሓይል) እጥረትና ፍልሰት ነው:: በሌላ አነጋገር ለስርዓቱ ታማኝ ያልሆኑ ብቃት ያላቸው ባለሙያዎችን ከስራው እየገፈተሩ በማባረር በምትካቸው ታማኝና ታዛዝ በሆኑ ካድሬዎች ስለሚተካ በሞያቸው ብቁ የሆኑ ሰዎች ያላቸው ዕድል ሥራ አጥ ሆኖ እየተንሳፈፉ መኖር አሊያም ሳይወዱ ወደ ስደት መፍለስ ነው::
ሁለተኛው ትልቁ ችግር ጥራት ነው:: ጥራት የሌለው ፕሪጀክት ደግሞ የወደፊቱ የትውልድ ዕዳ እንጂ ልማት አይባልም:: ለምሳሌ መንገዶች! ድልድዮች እና የውሃ ቧምባዎች ከተሰሩ ከጥቂት ወራት በሗላ እንደሚፈራርሱ እና መተላለፍያ መሰመሮችን እየተዘጉ ሕብረተሰቡ ለአደጋ እና ለኪሳራ እንደሚዳረግ በግልፅ የሚታይ ነገር ነው:: ለዚህም ነው ሕብረተሰቡ በፌዴራል የሚሰሩ እንደ መንገድ የመሳሰሉ የመንግስት ፕሮጀክቶች የራሱ የሆነ መጠሪያ በመስጠት ሽሮ ፈሰስ ዛሬ ተሰርቶ ነገ የሚፈርስ በሚል የህዝቡ መነጋገሪያ ሆኖ ሲታይ በጣም የሚገርምና የሚቆጭ ነው::
ሶስተኛው ትልቁ ችግር ሙሱና እና ዓይን ያወጣ የሀገር ሀብት ዘረፋ ነው:: ዘረፋው ደግሞ ተራ ዝርፊያ አይደለም:: ዘረፋው አጠቃላይ የስርዓቱን መገለጫ ባህርይ የሆነ ተቋማዊ! ሰንሰለታዊና ድርጅታዊ ይዘት ያለው ሌብነት ነው:: በዚሁ ቀጥተኛ ዝርፊያ የተሰማሩ ደግሞ ከላይ የተጠቀሱት አካላት ናቸው:: ሁሉም በተናጠልም ሆነ በቅንጅት በዝርፊያ የተሳተፉ ስለሆነ አንዱ አንዱን ደፍሮ መቆጣጠርና ስርዓት ማስጠበቅ ወይም በሕግ መክሰስ አይችልም:: ለምሳሌ አብዛኞቹ የውጭ ኮንትራክተሮች የመንግስትን ፕሮጀክቶች ለመስራት ሲቀጠሩ ተወዳድረው በብቃታቸውና በጥራታቸው ተመርጠው ሳይሆን በተለያየ መልኩ የባለስልጣናትን አፍ አጉረሰውና እጅ ጨብጠው ነው ኩንትራቱን የሚያገኙት:: እንደነ ሳሊኒ! ሚድሮክ! የቻይና እና ሌሎች ኮንትራክተሮች በአብነት የሚጠቀሱ ናችው:: የኢትዮያ አንጡራ ሀብት የሆነው ለውጭ ባለሀብቶች እየተቸበቸበ ያለው መሬትም ትልቁ የሙሱና ምንጭ ሆኗል::
ይህ ሁሉ ቅጥ ያጣ ዝርፊያ እየተካሄደ መንግስት ለምን አይቆጣጠርም? ለምን ዝም ይላል? የሚል ጥያቄ እንደሚነሳ እርግጠኛ ነኝ:: ይህ ጉዳይ የራሴም ጥያቄ ስለነበረ መልስ ለማግኘት በተለያየ የሃላፊነት ደረጃ ያሉትንና እንዲሁም እስከ ታች የቀበሌ ነዋሪዎች ድረስ ብዙ ሰዎችን ለማነጋገር ዕድል አጋጥሞኛል:: ከዚህ ሁሉ የተረዳሁትና የተነገረኝ ሙሱና እንደ ክፉኛ ተላላፊ በሽታ ልክፍት መድሃኒት የማይገኝለት ወረርሽኝ በሽታ ሆኗል የሚል ነው:: ይህ ማለት ሙሱና የአገዛዙን ሁለንትናዊ መገለጫና ባሕርይ (ደመ ነብስ) ሆኗል የሚል ነው::
ሙሱናን መቆጣጠር የሚቻለው ደግሞ ሃላፊነት የሚሰማውና ለሕግ ተገዥ የሆነ” ተጠያቂነትና ግልፅነት ያለው መንግስትና የአሰራር መካኒዝም ሲኖር ነው:: በሌላ አነጋገር ህዝቡ ራሱ ስልጣናቸውን መከታ በማድረግ በህዝብና በሀገር ሀብት ላይ የሚቀልዱ! የሚዘርፉና የሚባልጉትን ባለስልጣናት ለመቆጣጠር የሚችልበት ብሎም ወደ ፍርድ የሚያቀርብበትን ነፃ የሚድያ! የፍትሕ! የዳኝነትና የዴሞክራሲ ተቋማት ሲኖሩና ሲከበሩ ብቻ ነው::
ነገር ግን በስልጣን ላይ ያለው መንግስት ራሱን ለመቆጣጠር ቀርቶ የህዝቡን እሮሮና ጥያቄ ለማዳመጥና ለመመለስ የሚያስችል ባህርይ! ብቃት! ጆሮና ዓይን የለውም:: አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ መንግስት ሙሱናን መቆጣጠር ማለት እንደ ራስህን በራስ የመግደል (ሱሳይዳል) ዓይነት አድርጎ ነው የሚያየው:: ዛሬ በሀገራችን ስልጣናቸውን ተገን አድርገው የሚዘርፉ ብዙ ጎበዝ አለቆችና ብድኖች ተፈጠሯል:: ባጠቃላይ ሲታይ ማን ለማን መቆጣጠርና መክሰስ በማይችልበት ሁኔታ ላይ እርስ በርስ በተፋጠጥ ላይ የቆሙ ናቸው:: አልፎ አልፎ ሙሱናን እንቆጣጠራለን በሚል ሽፋን የሚያደርጉት እንቅስቃሴም ተቀናቃኝና ለስርዓቱ ታማኝ ያልሆኑ ዜጎችን ለመምታት የሚጠቀሙበት ስልት እንጂ ስርዓቱን ከስረ መሰረቱ ለማፅዳት እንዳልሆነ ህዝቡ በነቂስ ያውቃል::
ሁላችንም እንደሰማነው ከጥቂት ወራት በፊት ሙሱናን ለመቆጣጠር ተብሎ የተጀመረውን የአንድ ሳምንት ሞቅ ሞቅታ እንደ ነበር ይታወሳል:: ህዝቡም በጉጉት ይጠብቅ ነበር:: ነገር ግን የሚፈልጉዋቸውን ጥቂት ሰዎች ካሰሩና ከመቱ በሗላ እርምጃው ባልታወቀ ሁኔታ ወዲያውኑ እንዲቆም እንደተደረገ የሚታወቅ ነው:: እንዲቆም የተደረገበት ዋናው ምክንያት ደግሞ ጉዳዩ እስከ ላይ ድረስ ሰንሰለታዊ! ድርጅታዊ ይዘትና ግንኙነት ስላለውና በዚሁ ከቀጠለ ደግሞ የህወሓት/ኢሕአዴግን ህልውና አደጋ ላይ ስለሚጥል” የአቶ መለስ ዜናዊንና ተከታዮቻቸውን ስምና ታሪክ ስለሚያጎድፍ” እንዲሁም በብዙ ባለስልጣናት ዘንድ ተጠያቂነትን ሊያስከትል ይችላል በሚል ስጋት ለህዝቡ ያዳባባይ ሚስጢር ሆኖ እንዲቀር ተደርጓል::
ማጠቃሊያ
የሞያ ነፃነት በተገደበበት” ነፃ የፍትሕ” የዳኝነትና የዴሞክራሲ ተቋማት በሌሉበት! የሕግ የበላይነትና ተጠያቂነት በጠፋበት” ባጠቃላይ አንድ ፈላጭ ቆራጭ ፓርቲ የሀገሪትዋን ሁለንትናዊ ሰብኣዊ” ማተሪያላዊና አእምራዊ ሀብት ተቆጣጥሮና ገድቦ ራሱ ሕግ አውጪ! ራሱ ሕግ ተርጓሚ! ራሱ ሕግ ፈፃሚና አስፈፃሚ በሆነበት ድሃ ሀገር ምን ያህል ለዝርፊያ የተጋለጠ ሕብረተሰብ እንደሆነ እንኳን ለዜጎችዋ ለዓለም ማሕበርም የሚዘገንን ተግባር መሆኑን መገመቱ አያዳግትም::
ይህንንም ተደጋግሞ የተነገረ ስለሆነ አሁን ባነሳው ምናልባት ለሰሚው የሚሰለች ወይም ለቀባሪ ማርዳት ሊሆን ይችላል የሚል ሃሳብ ነበረኝ:: ነገር ግን የሀገርና የህዝብ ጉዳይ እያዳረ የሚቆረቁር ስለሆነ እንደ ግል ጉዳይ ሰልችቶህ የምትተው ነገር አይደለም:: እኔም ላለፉት ዓመታት በተደጋጋሚ ወደ ሀገር ቤት በሄድኩ ቁጥር መሰረታዊ ለውጥ ያስፈልጋቸዋል ብዬ በማምንባቸው ወቅታዊና ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ በተደጋጋሚ የእርምት ፅሑፍ አቅርቤ እንደነበር አስታዉሳለሁ:: ይሁን እንጂ በተመላለስክ ቁጥር የሚያሳዝን እንጂ የተሻለ ነገር አታይም:: በተለይም ከአቶ መለስ ዜናዊ ሕልፈት በሗላም ምናልባት ካለፈው ስህተታቸው ተምረው የተወሰነ ለውጥ ይመጣ ይሆናል የሚል ግምት ቢኖረኝም አሁን ያለው ሁኔታ ሲታይ ግን የባሰ እንጂ የተሻለ አይደለም:: እንዲያውም በሀገርና በወገን ላይ ለሚደርሰው ጥፋትና ጉዳት ለማን አቤት እንደሚባል አውራ እንደሌለው ንብ መንገዱ የጠፋበት ሁኔታ ሆኖ ነው ያገኘሁት::
ትእዝብቴ በዚህ ብቻ አላበቃም:: በተለይም በመልካም አስተዳደር! በፓለቲካ ምሕዳር! በሀገር ድህንነትና አንድነት ዙሪያ መንግስት እየወሰደ ያለው የቂቢፀ ተስፋና አፍራሽ እርምጃ ምን ያህል መረኑ የለቀቀና የከፋ መሆኑን ተጨባጭ ማስረጃዎችን በማስደገፍ በክፍል ሁለት ፅሑፌ ለማቅረብ እሞክራለሁ
ኢትዮያ ሀገራችን ለዘላለም ትኑር
sgbtsait@gmail.com

No comments:

Post a Comment