Friday, November 1, 2013

“እኔ ወደ ሀገሬ ለመምጣት ከማንም ጋር አልተደራደርኩም”ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ ሰንደቅ ጋዜጣ ከዳዊት ጋር ያደረገውን ቆይታ እንደወረደ እንደሚከተለው



የአውራምባ ታይምሱ ጋዜጠኛ ዳዊት ኢትዮጵያ ከገባ በኋላ በሀገር ውስጥ የሚታተመው ሰንደቅ ጋዜጣ 8 ዓመት ቁጥር 425 የረቡዕ ጥቅምት 20/2006 .. ዕትሙ ከዳዊት ጋር ያደረገውን ቆይታ እንደወረደ እንደሚከተለው አቅርበነዋል። ቃለምልልሱን ያደረገው ጋዜጠኛ ዘሪሁን ሙሉጌታ ነው።

የቀድሞው የአውራምባ ታይምስ ጋዜጣ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ ከሁለት ዓመታት ስደት በኋላ ሰሞኑን ወደ ኢትዮጵያ ተመልሷል። የጋዜጠኛ ዳዊት ወደ ሀገሩ መመለስ የሰሞኑ መነጋገሪያ ጉዳይ ሆኗል።
የጋዜጠኛ ዳዊት ወደ ኢትዮጵያ መመለስ በበርካታዎችም ዘንድ የተደበላለቀ ስሜት እንዲፈጠር አድርጓል።ከመንግስት ጋር ተደራድሮ ነው የመጣውከሚለው ጀምሮበአክራሪ የዲያስፖራ ፖለቲከኞች ጫና ደርሶበት ነውእስከሚለው ድረስ ጉዳዩ በማወያየት ላይ ነው። በሀገሪቱ የፖለቲካ ሂደት ውስጥም ጋዜጠኛ ዳዊት ተሰዶ በድፍረት እንደገና ወደ ሀገሩ በመመለሱም እንግዳ ስሜት እንዲፈጠር ያደረገ ይመስላል። በዚህና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችም ባልደረባችን ዘሪሁን ሙሉጌታ አነጋግሮታል።


ሰንደቅ፡- በቅድሚያ እንኳን ደህና መጣህ። ከሁለት ዓመታት የስደት ቆይታ በኋላ ወደ ሀገርህ ለመመለስ የወሰንክበት መሠረታዊ ምክንያት ምንድነው?

ጋዜጠኛ ዳዊት፡- የመጣሁበት ዋና ምክንያት በስደት ዓለም በጋዜጠኝነት ሙያ መቀጠል የሚያስችል ሁኔታ ስላጣሁ ነው። በስደት ላይ እያለሁ ድረገፅ ከፍቼ በመስራት ላይ ነበርኩ። ስራውም ምን እንደሚመስል ለመገንዘብ ችያለሁ። በተለይ ስደት ላይ ሆነህ የጋዜጠኝነትን ስራ መስራት እጅግ ከባድ ነው። ሥራው ብዙም የልብ የሚያደርስ ስሜት የለውም። ደስተኛም አትሆንም። ዝም ብለህ ስትመለከተው የይስሙላ ነው የሚሆንብህ። በተለይ ሀገር ቤት በነበርክበት ወቅት በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት የነበረውን ሚዲያ ስትመራ ቆይተህ በስደት ላይ ግን የውሸት ወደሚመስል ስራ ስትገባ ዕድሜህንና ጊዜህን ከማባከን ውጪ የምታተርፈው ነገር ስለሌለ ከዚህ በላይ እዛ መቆየቱ ተገቢ መስሎ አልታየኝም። በግሌ ምን ያህል ጊዜ ነው እንደዚህ የምቆየው? ሙያውን እወደዋለሁ፣ በሙያውም መቀጠል እፈልጋለሁ ብዬ እስካመንኩ ድረስ ውስጤ ደስተኛ ሳይሆን፣ መኖር ስላለብኝ ብቻ ከምኖር ብዬ ነው ለመመለስ የወሰንኩት።

ሰንደቅ፡- ምንም እንኳ ሙያዊ ግዴታህን ለመወጣት ከስደት ይልቅ በሀገር ቤት ይሻላል የሚል አቋም እንዳለህ ብትገልፅም፤ ከአንተ ጀርባ የሚነገረው ብዙ ነው። በተለይም በዲያስፖራ በሚገኙ የፖለቲካ ኃይሎች ጋር ግጭት ውስጥ መግባትህ በሰፊው እየተነገረ ነው እናም በዚህ ረገድ የገጠመህ ችግር ምንድነው? ችግሩስ ወደ ሀገርህ እንድትመለስ ተፅዕኖ አድርጎብሃል?

ጋዜጠኛ ዳዊት፡- በእርግጠኝነት የምነግርህ ነገር ቢኖር ተፈጥሯል የተባለው ችግር እኔን ወደዚህ እንድመጣ አላደረገኝም። በመሠረቱ ጉዳዩን ካየነው ከስደት የሚያስመልስ አይደለም። በእርግጥ እኔ ከአሜሪካ መንግስት ጋር አይደለም የተጋጨሁት ወይም ደግሞ በአሜሪካ ብሔራዊ የፀጥታ አደጋ ላይ ያነጣጠረ ወንጀል አልተፈፀመም። በሌላ ወገን ደግሞ በአሜሪካ የሚኖር ስደተኛ ፖለቲከኛ ቅር ስለተሰኘብህ ብቻ ብድግ ብለህ የምትመጣበት ምክንያት የለም። ትልቁ ነገር ከእነዚህ ሰዎች ጋር ያለኝ መሠረታዊ ልዩነት ከፕሬስ ነፃነት ጋር የተያያዘ ጉዳይ ነው። ዋናውም ልዩነት ይሄው ነው። እኔ ከሀገሬ ተሰድጄ ስሄድ በወቅቱ በምሰራቸው ነገሮች ደስተኛ ያልሆኑ የመንግስት ኃላፊዎች ነበሩ። ደስተኛ አለመሆናቸውንም የሚገልፁት በመንግስት የመገናኛ ብዙሃን ነበር። በወቅቱ ዘመቻው ሲካሄድ ሙያው ነፃ መሆን አለበት ብዬ ነፃነትን ፍለጋ ነበር የተሰደድኩት። ስለዚህ 10ሺህ ኪሎ ሜትር ተሰድጄ ነፃነቴ እንደገና የማስረክብበት ምክንያት የለም።
አሜሪካን ሀገር ሄጄ አይነኬና አይደፈሬ የሆኑ ፖለቲከኞች ስላሉ እነሱን መንካት እንደሌለብኝና እነሱ የሚሉትን ብቻ እንድልላቸው፣ እነሱ እንዲፃፍላቸው ብቻ እየፃፍኩ ዝም ብዬ ሰውን ለማስደሰት ብዬ የምኖር ከሆነ የይስሙላ ኑሮ ነው የሚሆነው። ሀገርን የሚያክል ነገር ተሰደህ ጥለህ ሄደህም፣ እንደገና የይስሙላ ኑሮ እንድትኖር የምትገደድ ከሆነ ከጅምሩ መሰደድ አይገባም። ሚዛናዊ የሆነውን የሙያ ግዴታህን ስትወጣ ቅር የሚላቸው ኃይሎች አሉ። እነዚህ ኃይሎች ሰፊ መሠረት ያለው የፓልቶክ፣ የማኅበራዊ ጽረገፅ፣ ብሎግና የመሳሰሉት የመገናኛ ዘዴዎች አላቸው። የአሜሪካ ሕግም እንደፈለጉ እንዲፅፉ ስለሚፈቅድላቸውም የፈለጉትን ነገር መፃፍ ይችላሉ። ስለዚህ በእኔ ላይ የማጥላላት ዘመቻ አካሂደዋል። ማለት ግን ከሀገሬ እንድሰደድ የደረሰብኝን ግልፅ ተፅዕኖ ያህል እነዚህ ኃይሎች ተፅዕኖ አላደረሱብኝም። ስለሆነም በእነሱ ግፊትና ጫና ወደ ሀገር ቤት ለመመለስ አልተገደድኩም።

ሰንደቅ፡- በአንተና በውጪ ከሚኖሩ አንዳንድ የዲያስፖራ ፖለቲከኞች መቃቃር የተፈጠረው ከቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ህልፈት ጋር በተያያዘ ነው የሚል ነገር አለ፤ ስለዚህ ጉዳይ ምን አስተያየት አለህ?

ጋዜጠኛ ዳዊት፡- በወቅቱ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ሕመም ጋር ተገጣጥሞ ሊሆን ከመቻሉ ውጪ በቂ ምክንያት መስሎ አይታየኝም። እንደአጋጣሚ የጊዜው መገጣጠም መቃቃሩን አስፍቶት ሊሆን ይችላል። ከዛ በፊት ግን ከሙያ ነፃነት ጋር በተያያዘ በግሌ ቅሬታዎች ነበሩኝ። እኔ ሀገሬን ለቅቄ ስወጣ በነፃነት እሰራለሁ የሚል የፀና እምነት ነበረኝ። እዛ ከሄድኩ በኋላ የገጠመኝ ሌላ ተፅዕኖ ነው። አሜሪካን ሀገር ሁሉንም ነገር የተቆጣጠሩ አካላት አሉ። ፓልቶኮችን፣ ድረገፃችን፣ ብሎገሮችን በጠቅላላ የሳይበር ሚዲያውን የተቆጣጠሩ የፖለቲካ ድርጅቶች አሉ። ስለዚህ እዛ ክበብ ውስጥ ስትገባ የዚያ መስመር አንድ አካል መሆን ነው ያለብህ። አለበለዚያ መኖር አትችልም። እኔ ደግሞ ለየት ያለ አቀራረብ ማቅረብ እንዳለብኝ አመንኩ። በተቻለ መጠን የሚቀርቡ መረጃዎችን ሚዛናዊ አድርጌ ለማቅረብ ነው የፈለኩት። ነገር ግን እዛ ሀገር ሚዛናዊ አድርጎ መረጃን ማቅረብ አይታሰብም። ሚዛናዊነት ወዲያውኑ የኢህአዴግ አባልነት ካርድ ነው የሚሰጥህ። ስለሆነም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ በሕይወት መኖር አለመኖር አንድ ዘገባ ሰርቼ ነበር። በወቅቱ አቶ በረከት ሰምኦንጠቅላይ ሚኒስትሩ ከእንቁጣጣሽ በፊት ይመለሳሉባሉት ጉዳይ ላይ የተለያዩ ፖለቲከኞችን ጋብዤ አወያይቻለሁ። ከነዚህም አንዱ አቶ ያሬድ ጥበቡ የተባሉት ፖለቲከኛ ለየት ያለ አስተያየት ሰጡ። አስተያየታቸውም አቶ በረከት እውነታቸውን ሊሆን ይችላል የሚል ነበር። እናም እኔ ያንን በቀጥታ አስተናግጄዋለሁ። በተመሳሳይ የእነ አቶ ያሬድን ኀሳብ የሚቃረን አስተያየት አስተናግጄ ነበር። እና ከዛ ጊዜ ወዲህ ጥያቄ መነሳት ጀመረ። ጥያቄው ሊነሳ ያስቻለው ሚዛናዊ ዘገባን ሊያቀርብ የሚችል ድረገፅ ባለመኖሩና አካሄዱም እንግዳ ስለነበር ይመስለኛል። በዚያ ምክንያት በርካታ የዲያስፖራ ሚዲያዎች በእኔ ላይ አፍራሽ ፅሁፍ ማሰራጨት ጀመሩ። ከዚያ በኋላ ለእኔ የሰጠኝ ምልክት ትልቅ ነበር።ዘገባዬን እንኳ ሚዛናዊ የማድረግ መብት የለኝም ማለት ነውስል ማሰብ ጀመርኩ። ከሀገሬ ተሰድጄም፣ ከተሰደድኩም በኋላ ዘገባዬን እንኳን ሚዛናዊ ለማድረግ ነፃነቴን አሳልፌ የምሰጥ ከሆነ ትርጉሙ ምንድን ነው? ስል ጠየኩ። እኔ በማምነው ወይም ሌሎች በሚያምኑበት መስረት ነው ያለብኝ ብዬ ማሰብ ጀመርኩ። ከዚያ በኋላ ነው ኢትዮሚዲያን ጨምሮ አፍራሽ ዘመቻ የጀመሩት።

ሰንደቅ፡- ከመሰደድህ በፊት በተወሰኑ የዲያስፖራ ፖለቲከኞች ውስጥ የመረረ ጥላቻና ፅንፈኝነት እንዳለ አታውቅም ነበር ማለት ነው?

ጋዜጠኛ ዳዊት፡- ይሄንን ጥያቄ በሁለት መንገድ ነው የምመልስልህ። የመጀመሪያው በአብዛኛው እዚህ ሆነን ሽፋን የምንሰጣቸው የዲያስፖራ ፖለቲከኞች አሁንም ቢሆን ከእኔ ውሳኔ ጋር መሠረታዊ ችግር አለባቸው ብዬ አላስብም። ለምሳሌ ፕሮፌሰር መሳይ፣ አቶ ያሬድ ጥበቡ፣ እነ ጃዋር መሐመድ ወዘተ እዚህ ሆነን መጣጥፎቻቸውን የምናስተናግድላቸው ሰዎች አሁንም ቢሆን ችግር የለባቸውም። በውሳኔዬም ይስማማሉ። ከብዙዎቹም ጋር በመደበኛም ሆነ መደበኛ ባልሆነ ሁኔታ ተነጋግረንበታል።
ብቸኛው ችግር ያለው ግን ስደት ላይ መሠረታቸውን የጣሉ የፖለቲካ ድርጅቶች አሉ። እነሱን የሚደግፉ በጣም የሚጮኹ ቁጥራቸው በጣም ትንሽ የሆነ ነገር ግን እንደአጋጣሚ ሆኖ እነዚህ ኃይሎች የሳይበር ሚዲያውን በመቆጣጠራቸው ድምፃቸውን በከፍተኛ ደረጃ የሚሰማ ነው። እነዚህ ኃይሎች ደግሞ ቀኝ ዘመም አቀነቃኞች ናቸው። የእኔ ችግር ከእነሱጋ ነው። እዚህ በነበርኩበት ወቅት ከእነዚህ ኃይሎች ጋር ያለኝ ልዩነትን በከፋ መልኩ የመገንዘብ ዕድል አልነበረኝም። ሁልጊዜ ለሰብአዊ መብት መከበር፣ ለፕሬስና የፖለቲካ ነፃነት መኖር ሁላችንም እንለፋለን። እነዚህም ሰዎች በቅንነት ለእነዚህ መሠረታዊ የሰው ልጅ እሴቶች መኖርና መከበር የሚታገሉ ይመስለኝ ነበር።
ነገር ግን አሜሪካ ከገባሁ በኋላ ሁሉም ለእነዚህ መሠታዊ መብቶች መኖርና መከበር ላይ ነው ወይ የሚታገለው የሚለው ጥያቄ ፈጥሮብኛል። በእነዚህ ጥያቄዎች ተሸፍነው የሚቀርቡ ሌሎች ጥያቄዎች አሉ። በተለይ ከዘርና ከማንነት ጋር በተያያዘ የሚያነሱት ጉዳዮች አሉ። ተመልሶ እንዲመጣ የሚፈልጉት ነገር ያለ ይመስለኛል። ይሄንን ማራመዳቸው መብታቸው እንደሆነ እገነዘባለሁ። ነገር ግን ሚዲያ አለኝ ብለህ መወራት የሌለባቸው ጉዳዮች ደግሞም አሉ።

ሰንደቅ፡- የዘርና የማንነት ፖለቲካን ካነሳህ ዘንድ ከተወለድክበት አካባቢ ጋር ተያይዞ የተነሳ ጉዳይ አለና አንተ የትግራይ ተወላጅ በተለይም ቤተሰቦችህ ከአድዋ አካባቢ መሆናቸው አሁን ለተፈጠረው አጋጣሚ መሠረታዊ ምክንያት ሆኗል ማለት ይቻላል?

ጋዜጠኛ ዳዊት፡- ወሳኙ ነገር ይሄው ጉዳይ ነው። እኔ በኢህአፓም ሆነ በደርግ ጭፍጨፋ ወቅት አልነበርኩም። በየትኛውም የኢትዮጵያ የደም መፋሰስ አብዮት ውስጥ አልነበርኩም። እኔ በጋዜጠኝነት ሙያዬ አበረክታለሁ ብዬ ጋዜጣ መስርቼ ገባሁ። ያንንም ተከትሎ ታሰርኩ። ከእስር ከወጣሁ በኋላ ደግሞ ሁኔታዎች አላሰራ ሲሉኝ ተሰደድኩ። በስደት ህይወቴ መሰናክል ገጠመኝ፤ በመጨረሻም ወደ ሀገሬ ተመለስኩ። ከዚህ የዘለለ ሌላ ታሪክ የለኝም።
በእኔ ምክንያትም የጠፋ የሰው ህይወት የለም። በእኔ ምክንያት የተፈፀመ የዘር ማጥፋት ወንጀል የለም። ይሁን እንጂ ያለው እውነታ የተለየ ነው፤ ቀደም ብዬ እንደጠቀስኩልህ። በዲያስፖራ የሚገኙ አንዳንዶቹ የፖለቲካ ታጋዮች ለሰብአዊ መብት መከበር፣ ለሕግ የበላይነት ብሎም ለፖለቲካ ለውጥና የተሻለች ዴሞክራሲያዊት ሀገር ለመፍጠር የሚለውን አጀንዳ በሚዲያ ቢያወሩትም ዋነኛ መሠረታዊ ጥያቄአቸው ግን ሌላ ነው።

ሰንደቅ፡- “ሌላ ነውስትል በምሳሌነት የሚጠቀስ ነገር አለ?

ጋዜጠኛ ዳዊት፡- ሌላ የምልህ አሁን በጥያቄህ ላይ ያነሳህልኝ ጉዳይ የዘር ፖለቲካ አንዱ ነው። አንድ የትግራይ ተወላጅ የፈለገውን ያህል ዋጋ ቢከፍል በአዎንታዊ ጎኑ አይታይም። ይሄንን ስል ሁሉም ናቸው እያልኩ አይደለም። ይሄ ጉዳይ ግን ምንም ነገር ከማይጥማቸው ፅንፈኛዎች ቡድኖች የሚመነጭ ነው። እነዚህ ኃይሎች ምንም ነገር የማይጥማቸው ሙሉ በሙሉ ጨለምተኛ ፅንፍ ውስጥ ያሉ ናቸው። በዚህ ፅንፍ ላይ ትችት ሲቀርብ ምላሹ በቀረበበት ትችት ላይ ሳይሆን በማንነቱ ላይ ነው። እነዚህ ፅንፎች በተፈጥሮ የተሰራላቸው አንድ የቤት ስራ አለ። ይህም ዳዊትን ለማብጠልጠለ የትግራይ ተወላጅ መሆኑ 80 በመቶ የቤት ስራው ተሰርቶላቸዋል ማለት ነው።
የእኔ ከዛ አካባቢ መወለድ እኔን ለማጥቃት ከበቂ በላይ አሳማኝ ሆኖላቸዋል። 80 በመቶ የተፈጥሮው የቤት ስራ ስለተሰራ 20 በመቶ የእነሱ ጥረት ታክሎበት የማጥቃት ዘመቻውን ያካሂዳሉ ማለት ነው። በተጨባጭ የሆነው ነገር ይሄው ነው።

ሰንደቅ፡- ወደ ኢትዮጵያ ከተመለስክ በኋላ ከመንግስት ጋር ተደራድረህ ነው የመጣኸው፤ ከመምጣትህም በፊት ዋሽንግተን በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ትመላለስ እንደነበርም ከኢትዮጵያ የውጪ ጉደይ ሚኒስቴር / ቴዎድሮስ አድሃኖም ጋር የቴሌፎን መልዕክት ልውውጥ አድርገሃል። እንዲሁም ወደ ኢትዮጵያ ገብተህ በሚዲያ ስራ ለመሰማራት ከመንግስት ገንዘብ ተመድቦልሃል የሚሉ አስተያየቶች ተደምጠዋል። እነዚህ አስተያየቶች ምን ያህል እውነት ናቸው?

ጋዜጠኛ ዳዊት፡- መቼም ዘሪሁን ጋዜጠኛ ስለሆንክ መጠየቅ ሊኖርብህ ይችላል። ነገር ግን እኔንጃ ለእንደዚህ አይነቱ ጥያቄ መልስ መስጠት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ አይገባኝም። ስለቁምነገር ብናወራ ይሻለኛል። እንደዚህ አይነት ነገሮች እየተወሩ ነው። ለወደፊቱም መወራታቸው አይቀርም። እኔ ወደ ሀገሬ ለመምጣት ከማንም ጋር መደራደር አያስፈልገኝም። ያም ሆኖ እነዚህን አሉባልታዎች ሐሰት ናቸው።
መከራከሩ በራሱ ለአሉባልታው ክብደት መስጠት ነው ብዬ አምናለሁ። 24 ሰዓት ፓልቶክ ላይ ተቀምጦ ብዙ ነገር ሲፈጥር ለሚውልና ለሚያድር ሰው ለሚፈበርከው ነገር እየተነሱ መልስ ከመስጠት ይልቅ በስራ ማሳየቱ ይቀላል ብዬ አምናለሁ። ከዚህ በፊት ተደራድረው የመጡ ሰዎች ያደረጉት ነገርና እኔ የማደርገውን ነገር ሁለቱንም በማነፃፀር ግንዛቤ ላይ መድረስ ይቻላል ብዬ አምናለሁ። ምክንያቱም ከተደራደርኩና ገንዘብ የሚመደብልኝ ከሆነና የጠቀስካቸው ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣን ከእኔ ጋር ተደራድረው እኔ ወደ ሀገሬ ከተመለስኩ በተደረገልኝ ነገር ስራ መስራት አለብኝ ማለት ነው። ይሁን እንጂ ወደፊት በምሰራው ሥራ እውነትም ተደራድሮ ነበር ወይስ አልነበረም ቢሉኝ ይሻለኛል።

ሰንደቅ፡- በስደትህ የመጨረሻ ፅሁፍ ላይ 1997 ምርጫን ተከትሎ ለእስር ከተዳረክ በኋላ ከቅንጅት አመራሮች ጋር የተሰጠህ ይቅርታ ተነስቶ በሽብርተኝነት ልትከሰስ እንደምትችል ገልፀህ ነበር። አሁንስ ምን ዋስትና አለህ?

ዜጠኛ ዳዊት፡- የዚያን ጊዜ ስወጣ ሁለት ነገሮች አቅርቤ ነበር። የመጀመሪያው በግልፅ በመንግስት ሚዲያዎች የሚፃፉ ነገሮች ነበሩ። እነዚህም ነገሮች ለምንድነው ይቅርታው ተነስቶ የማይታሰረው? የሚሉ ነበሩ። እነዚህ ጉዳዮች በግልፅ ሊስተባበሉ በማይችሉ መልኩ ሲንፀባረቅ ታይቷል። በተለይ ኦክቶበር 19 የወጣውን አዲስ ዘመን ጋዜጣን ማየት ይቻላል። ሌላው የመንግስት ባለስልጣናት ቢያስተባብሉም በወቅቱ አስተማማኝ መረጃ ነበረኝ። ይህንንም እንኳ ማሳመን ቢያስቸግር በይፋ በአዲስ ዘመን ላይ ታትሞ የወጡት መረጃዎች በእኔ ላይ ያነጣጠሩ ችግሮች ሊፈጠሩ እንደሚችሉ የሚጠቁም ስለመኖራቸው አጠያያቂ አልነበረም።
አሁንስ ምንድነው ዋስትናህ ላልከኝ ነገር ምንም ሊሆን ይችላል። እኔ አንድ ዜጋ ነኝ። አንድ ድምፅ አለኝ ብዬ ስለማስብ የምችለውን ሁሉ አደርጋለሁ። ሀሳቤን ስገልፅ የመንግስት ኃላፊዎች ቢታገሱኝ ደስ ይለኛል። ነገር ግን ገና ለገና ይታገሳሉ አይታገሱም በሚለው ጉዳይ ላይ ወደኋላ ተመልሶ ከማየት ወደፊት በምሰራቸው ስራዎች የምናየው ቢሆን ነው የሚሻለው። እኔ ሁሌም ተስፈኛ ነኝ። አሁንም ከአቅም በላይ ችግር የሚገጥመኝ ከሆነ እንደገና እሰደዳለሁ ማለት ነው።

ሰንደቅ፡- ወደኋላ ልመልስህና ቀደም ሲል የእናንተ ጋዜጣ ለሕትመት በሚበቃበት ወቅት ከእነ / ብርሃኑ ነጋ ጋር የተለየ ቁርኝት ፈጥሯል በሚል ከፍትህ ሚኒስቴር ማስጠንቀቂያ ተስጥቶህ እንደነበር ይታወቃል። በአንፃሩ ደግሞ በአሜሪካ በነበርክበት ወቅት በድረገፅህ ላይ የእነ / ብርሃኑ ድርጅት ከኤርትራ መንግስት አምስት መቶ ሺህ ዶላር መቀበሉን መዘገብህ ይታወቃል። እነዚህ ሁለት ተቃርኖአዊ አጋጣሚዎችን እንዴት ነው የምትገልፃቸው?

ጋዜጠኛ ዳዊት፡- ቀደም ሲል ከእነ / ብርሃኑ ጋር ስወነጅል ጋዜጠኛ እንደነበርኩና ከማንም የፖለቲካ ድርጅት ጋር ምንም አይነት የጥቅም ግንኙነት እንዳልነበረኝ ነው ስገልፅ የቆየሁት። ሰዎች ግን ይገምቱ ነበር። / ብርሃኑ ገንዘብ መድቦለት ነው የሚሰራው ይሉ ነበር። በእኛ በኩል አባባሉ ስህተት እንደነበር ደጋግመን ስንገልፅ ነበር። ስለዚህ ስህተት መሆኑን ለማሳየት በቂ መረጃ እጃችን ላይ በገባ ሰዓት ምን ያህል ለሙያው ቅድሚያ እንደምንሰጥ እና የጥቅም ግንኙነት የሌለን መሆኑ በበቂ ማስረጃ ያሳየን ይመስለኛል። እንደዚህ አይነቱ ነገር ሁሌም አንደ ጋዜጠኛ ያጋጥማል። በዚያን ጊዜ በመንግስት ከፍተኛ ኃላፊዎች ሳይቀር ጋዜጣችንን የግንቦት ሰባት ጋዜጣ እንደሆነ ፈርጀው አሳድደውኛል። ከተሰደድኩም በኋላ እነዛ የተወነጀልንባቸው የፖለቲካ ድርጅቶች መልሰው ከኢህአዴግ ጋር ሊፈርጁን ችለዋል። ይሄንን ደምረው ስታየው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ባህል የፈጠረው ነገር ነው። እናም ሁሌም ይሄ ነገር ይቀጥላል። ዋናው ነገር ከግንቦት ሰባት ጋር የጥቅም ግንኙነት እንደሌለን የገመቱ ሰዎች ግምታቸው ስህተት መሆኑን እንዲረዱ አድርገናል። አሁንም ያለው ውንጀላም ስህተት መሆኑን ሠርተን እናሳያለን። በዚህ ስራ ውስጥ እስካለህ ድረስ ይሄ ነገር ይቀጥላል።

ሰንደቅ፡- በተሰደድክበት ወቅት ጋዜጣውን በድንገት መዝጋትህና ሰራተኞች መደናገጣቸው ይታወቃል። በሁኔታውም ሰራተኞቹና የጋዜጣው አንባቢዎች አዝነዋል። አሁን ላይ ሆነው ለታስበው የሚፀፅትህ ነገር አለ?

ጋዜጠኛ ዳዊት፡- በወቅቱ የተፈጠረው ነገር ሁሉም ሰው መገመት እንደሚችለው በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ነበርኩ። እናም በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ስትገባ እንኳንስ አንድ ኩባንያ ትዳርህንም ልትበትን ትችላለህ። እኔም ድርጅቱን ስዘጋው ቀዳሚ ተጎጂ ነበርኩ። ስለዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ሲፈጠር ችግሮች ያጋጥማሉ። በዛ ሂደት የሚጎዱ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ። የዛን ጊዜ የተፈጠረው ነገር ከጉዳዩ አስቸጋሪነትና ጉዳዩ ደግሞ ምስጢራዊ በሆነ መልኩ መያዝ ስለነበረበት ነው። የስራ ባልደረቦቼም በዚህ መልኩ ተረድተውኛል ብዬ አስባለሁ።
ሰንደቅ፡- አሁን ከቀድሞ ሰራተኞችህ ጋር ጤናማ ግንኙነት መፍጠር ችለሃል?
ጋዜጠኛ ዳዊት፡- በጣም ጤናማ ግንኙነት ነው ያለኝ። አንዳንዶቹ ኤርፖርት ድረስ መጥተው ተቀብለውኛል። ሌሎቹም ጋር ተገናኝተን ምሳም፣ እራትም ተገባብዘናል። ከአብዛኛዎቹም ጋር ተገናኝተናል። ግንኙነታችንም ከስራ ባልደረባ በላይ ነው። ያለን ትስስር የጓደኝነትም ስለሆነ ያለው ነገር አዎንታዊ ነው። ይረዱኛል ብዬ አምናለሁ።
ሰንደቅ፡- አሁን በምን መልኩ ነው መቀጠል የምትችለው? ቀደም ሲል የነበረውን ጋዜጣ መልሰህ ታሳትማለህ ማለት ነው?
ጋዜጠኛ ዳዊት፡- ለጊዜው በድረገፅ ላይ ነው የማተኩረው። የጋዜጣውን ጉዳይ በተመለከተ ብዙ የሚሰሩ ስራዎች አሉ። የሕግም ጉዳይ አለ። እና ጋዜጣው የአጭር ጊዜ ሳይሆን የረጅም ጊዜእቅድ ነው የሚሆነው። የአጭር ጊዜ እቅዴ ድረገፁን ማጠናከር ነው። በአገር ቤት መረጃ በምስልና ድምፅ አጠናክሮ ማቅረብ ነው። በቀናት ጊዜ ውስጥም ወደ ተግባር ይገባል። ጋዜጣው ግን ምናልባት ከወራት በኋላ ሊሆን ይችላል። የሚጠናም ነገር አለው። ዞሮ ዞሮ አውራምባ ታይምስ በሚለው ጉዳይ ነው መዝለቅ የምፈልገው።

No comments:

Post a Comment