Tuesday, November 5, 2013

“ወሬ ነጋሪ” በመሐመድ ይማም

ትችት በኤፍሬም የማነብርሀን
የአንድ ሕዝብ ታላቅነት አንዱና ዋና መለኪያው ወቅታዊ ታሪኩን ለመጪው ትውልድ ማስተላለፍ መቻል ወይም አለመቻሉ ነው። ይህንንም ታሪክ ለመጪው ትውልድ የማስተላለፉን ሥራ ማንም ሳያስገድዳቸው የራሳችን ኃላፊነት ነው ብለው በራሳቸው ተነሳስተው በራሳቸው ወጪ ለትርፍ ሳይሉ የሚፈጽሙ ደራስያን ለሕብረተስባቸው ትልቅ ባለውለታ ናቸው። በተለይ ደግሞ ይህንን ኃላፊነት መውሰዱ ብቻ ሳይሆን ይሉኝታና ፍርሐት ሳይበግራቸው ለአንባብያን የሚያቀርቡትን ታሪክ ሀቀኝነት በማረጋገጥ በታሪኩ ላይ የሚሰጠውን ዳኝነት ሆን ብለው ለሰሚና አንባቢ ውይም ለመጭው ትውልድ የሚተዉ ደራስያን በልዩ ዓይንና ክብር ሊታዩ ሚገባችው ናችው።
በቅርቡ “ወሬ ነጋሪ” በሚል ርዕስ በእንግሊዝኛ ተጽፎ የቀረበውን የመጀመርያ መጽሐፉን ለሕዝብ በማስተዋወቅ ወደ መድርኩ ብቅ ያለው አቶ መሐመድ ይማም፣ ያቀረበውን ጽሑፍ ይዘትና ጥራት ስመለከተው እነኚህን የመልካም ደራሲ መመዘኛዎች በተገቢው ያሟላ ደራሲ ሆኖ አግኝቼዋለሁ።
መሐመድ ይማምን ለመጀመርያ ጊዜ ያወቅኩት በጣም ከረጅም ዓመታት በፊት የድህረ ምረቃ ፕሮግራም በዬል ዩኒቨርሲቲ እንከታተል በነበረ ጊዜ ነው። አብረን በቆየንባቸው ብዙ ዓመታት ስለሱ የማውቀው፣ እንደአብዛኛው የጊዜው ወጣት ኢትዮጵያ እያለ የኢሕአፓ ዓባል የነበረና የደርግ መንግስትን ጭካኔ በመሸሽ፣ አገር ጥሎ የተሰደደ ኢትዮጵያዊ መሆኑን ብቻ ነበር።፣ ስለታሪኩ እንኳን አጥብቄ ሳልጠይቀው ነው የኖርኩት። እሱም ጨረፍ ጨረፍ እያደረገ ከሚያወራልኝ አንዳንድ ታሪኩ በቀር ብዙ ስላለፈው ሕይወቱ ብዙም አጫውቶኝ አያውቅም ነበር። መሐመድ ይማም ትውልዱ ወሎ ሲሆን፣ እንደማውቃቸው ብዙዎች የወሎ ልጆች ባሕርይ ነገርን ብዙ ማክበድ ወይም ማክረር የማይሆንለት፣ ከሰዎች ጋር ተስማምቶ የመኖር ልዩ ስጦታ ያለው፣ ከአፉ በሚወጣ ምንም ነገር ሰውን ማስቀየም የማይችል ስለሆነና በተለይ በፖለቲካ ሀሳብ ልውውጥ ላይ የሌላውን ወገን ሀሳብ በትግስት የማዳመጥና የራሱንም አቋም በረጋና በሰከነ መንፈስ ማስረዳት የሚችል፣ ተገቢ ከሆነም የአቋም ድክመትን በግልጽ ለማሳየትም ሆነ ለራስ ለመቀበል ያለመቸገር ትልቅ ሥጦታ ያለው ሰው ነው። በመሆኑም እስከአሁን አብረን ያሳለፍናቸው የውይይት ጊዜያት በሙሉ ዕውቅት ገንቢ አጋጣሚዎች ናቸው ብዬ አምንባቸዋለሁ።
በዚህ ዓመት ስኔ ወር አካባቢ ይመስለኛል ከመሐመድ ጋር ብዙ ጊዜ በምንቃጠርባት የቢራ ቤት ተገናኝተን ስንጨዋወት፣ በወጣትነቱ ወቅት ኢሕአፓ ውስጥ ስላሳለፋችው ጊዜያት የጻፈው፣ ነገር ግን አቧራ እየጠጣ የሚገኝ ድራፍት እንዳለውና፣ ይህንን ድራፍት ለማሳተም ሃሳብ ያለው በመሆኑ ለጥቂት ጓደኞቹ እንዲያነቡት ሊሰጥ እንዳሰበና እኔም ሀሳብ እነድሰጠው ጠየቀኝ። በተለይ ግን የጽሑፉ ይዘት ሙሉ በሙሉ እውነተኛ ታሪክ በመሆኑ እስከአሁነም ሊያሳትመው ያመነታበት ምክንያት ምናልባት የአንዳንድ በሕይወት ያሉ ሰዎችን ስሜት ሊረብሽ ይችል ይሆን የሚል ፍራቻ ስላደረበት መሆኑን ገለጸልኝ። እኔም እንዲያውም ለወቅቱ አንባቢም ሆነ ለመጭው ትውልድ መጽሐፉ ጠቃሚነት የሚኖረው ሙሉ በሙሉ እውነትን በማቅረብና፣ ዳኝነቱን ላንባቢ በመተው መሆኑን በመግለጽ ካስበው ዓላማ በፍጹም እንዳያፈገፍግ መከርኩት። የሱም እምነት ይኸው በመሆኑ ወዲያውኑ የመጽሐፉን ድራፍት እንዳነብ ላከልኝ።
የመጽሐፉን ድራፍት ማንብብ ጀምሬ ብዙም ወደፊት ሳልሄድ የተረዳሁት ነገር ቢኖር ከሃያ ዓመታት በፊት ጀምሮ የማውቀው ጓደኛዬ በዓይኔ የማውቀው ጓደኝዬ ሳይሆን ልዩና ያሸበረቀ የሕይወት ታሪክ ያለው ሰው መሆኑን ነው። እንዲያውም የማውቀውን ጓደኛዬን የቀድሞ ሕይወት ታሪክ የማነብ ሳይሆን በፍጹም ለማቆም አስቸጋሪ የሆነ ፣የአንባቢን ልብ በሚጽፈው ታሪክ የመስረቅ ጭሎታ ባለው ደራሲ የተጻፈ ልብ ወለድ ታሪክ ማነብ እየመሰለኝ በጣም ባጭር ጊዜ በሳምንት መጨረሻ አንብቤ ጨረስኩትት። ይህንን በአዲስ መልክ ላየው የበቃሁትን ጓደኛዬን በፍጥነት ለማነጋገርና ምን ቢቆርጠው ይህን የመሰለ ታሪክ በድራፍት ይዞ ለዚህ ዘመን ያህል እንደቆየና የዚህ መጽሐፍ መታተም አሁን ላለው ትውልድም ሆነ ለመጭው ትውልድ ትልቅ ውለታ እንደሆነ ላስረዳው በጣም ቸኮልኩ። ወዲያው አግኝቼውም መጽሐፉን ለማሳተም ጊዜ እንዳይሰጥና በምችለው ሁሉ የኤዲት ስራውን ለመርዳት ፍላጎቴን በመግለጽ በሚቀጥሉት ጥቂት ሳምንታት አንዳንድ የቃላትና የመረጃ መስተካክሎች ለማድረግ ፊቃደኛነቴን በመግለጽ የሥራ ውጤቴን አቀረብኩለት። የሌሎችንም አንባብያን ተጨማሪ መስተካክሉች አስገባና ላሳታሚ ልኮት ባጭር ጊዜ ወሬ ነጋሪ ይኸው ለሕዝብ ንባብ በቃ።
ወሬ ነጋሪ እስከአሁን የኢሕአፓ አባላት ጽፈዋቸው ካነበብኳችውና ተደናቂነትን ካገኙት እንደ ታዎር ኢን ዘ ስካይ በሕይወትተፈራ፤ ምርኮኛ በቆንጂት ብርሃን፣ ዘ ጄነሬሽን በክፍሉ ታደሰና ከመሳሰሉት መጻሐፍት ሁሉ በይዘቱም፣ በሃቀኝነቱም ሆነ፣ በዓላማው በኔ ግምት፣ የሚለይባቸው በርካታ ባሕርያት አሉት። ከነዚህ መጻሕፍት ለወሬ ነጋሪ የሚቀርበው መጽሐፍ ታዎር ኢን ዘ ስካይ ነው። በሁለቱ መጻሕፍት መካከል የቦታ፣ የጊዜ፣ የተሳታፊዎችና የታሪክ ተመሳሳይነትና ትስስር ይታያል ፡፡ መጽሐፉ ግልጽ
እንደሚያደርገውየወሬ ነጋሪ ደራሲ መሐመድ ይማም በመጽሐፉ ውስጥ በሰፊው እንደዘረዘረው በፓርቲው ውስጥ ይጫወት በነበረው አመቺ የጋዜጠኝነት ሚና ሳቢያ፣ ምንም እንኳን ከፍተኛ የኢሕአፓ አባላት መሃል ስለሚካሄደው የመሰረታዊ ፖሊሲ ውሳኔ ከነክፍሉ ታደሰ ያነሰ ዕውቀት ቢኖረውም፣ ካንዳንድ ዋና ተዋንያን ጋር ከነበረው የጓደኝነትና የዝምድና ትስስር የተነሳ ከነሕይወትና ቆንጂት በጣም በበለጠ ስለነግሮች አመጣጥ፣ ምክንያት፤ አዝማሚያና ውጤት የተሻለ ዕውቀት እንደነበረው ያስታውቃል።
መሐመድ በደርግ ዘመንና በኢትዮጵያ የፖለቲካ የመጽሔት ሕትመት ታሪክ ውስጥ የአቅኚነትን (ፓዮኒር) ቦታ የያዘው የጎሕ መጽሔት ጽሑፍ አቅራቢና ጋዜጠኛ ነበር። ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት፣ ደራሲው በእሕአፓ ውስጥ የመሪነት ስልጣን ባይኖረውም፣ ከአንዳንዶቹ የእሕአፓ የመሪነት ስልጣን ከነበራቸው ግለሰቦች ጋር በአጋጣሚ የቀድሞ ጓደኝነት፣ የደም ዝምድናና የጋብቻ ትሥሥር ስለነበረው፣ ክሚከታተሉት የደርግ ሰኪውሪቲ ባለሟሎች ትንሽ ርምጃ ቀደም ለማለት የሚያስችሉት ሁሌም ባይሆን አንዳንዴ ፍንጭና ጥቃቅን መረጃዎች ያገኝ ነበር። ነገር ግን ከክፉ አደጋዎች በብዛት የሚያመልጠው በድፍረቱና በፍጥነት ውሳኔ የመውሰድ ችሎታው እንደሆነ ከታሪኩ እንረዳለን። በተጨማሪም ባለው የስነ ጽሁፍ ችሎታው ሳቢያ ከአነዳንዶች በደራሲው ግምት የመሪነት ቦታ ከነበራቸው ግለሰቦች ጋር የመገናኝት ዕድል ያገኝ ስለነበረ በዓይኑ የሚያየውን ዕውነታና የአንዳንዶቹን መሪዎች የተሳሳተ ግምትና እምነት በቅርብ አይቶ ለማወዳደርና ያየውንና የሰማውን በማቀነባበር ይህ ዕውቀቱ ለኢሕአፓ መውደቅ መሰረታዊ ምክንያቶችን ለመለየትና በግልጽና በማያሻማ ሁኔታ ለቀሪውና ለታሪክ ለማቅረብ አስቸሎታል። በኔ ግምት ይህንን መጽሐፍ እስካሁን ከተጻፉት ሁሉ የተለየ የሚያደርገው ይህ የመረጃ አስተማማኝነቱ ነው። በመሆኑም መጽሐፉ አሁን ላለው ትውልድም ሆነ ለመጪው ትውልድ ትምሕርት አዘል ነው ብዬ አምናለሁ።
አንድ የተገነዘብኩትና ሳልናገር ላልፍ የማልፈልገው፣ መሐመድ ታሪኩን ክሚጀምርባችው የከፍተኛና የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሆኖ ስላሳለፋቸው ጊዜያት ሲናገር ሕይወት ተፈራ ከጻፈችው ታዎር ኢን ዘ ስካይ ጋር መቀራረቦች ስላሉት የእያንዳንዳችን የዚያ ዘመን ወጣቶች ምን ያህል ተመሳሳይ ታሪክ የነበረንና ምን ያህል ነገሮችን ሳናውቀው እንጋራና የልምድ ቅርርቦሽ የነበረን ትውልድ እንደነበርን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። የምናነባቸው መጻሕፍት፤ የምንሰማቸው ሙዚቃዎች፣ የምናስባቸው አስተሳሰቦች ባብዛኛው ዘር ወገንና ሐይማኖት ሳይለዩ አንድ እንደነበርን ያሳያል። ምናልባትም የሀያ ዓመት በዘር የመለያየት የወያኔ ሙከራ ያልተሳካውና፣ ወያኔ እንደሚያስብው ይህን ያህል የተበታተንን ሕዝቦች እንዳልሆን ምስክር የሚሆነው ይህ በሕይወት ተፈራም ሆነ በመሐመድ ይማም መጽሐፍ ውስጥ የምናየው የጋራ ልምዶቻችንናና አስተሳሰቦቻችን ይመስሉኛል።
በተለይ ግን ወሬ ነጋሪን የተለየ የሚያደርገው ደራሲው በመጽሐፉ ውስጥ ከፍተኛውን ሚና የሚጫወት ቢሆንም፣ መጽሐፉ የደራሲው የራሱ ትረካ (አውቶ ባዮግራፊ) ሳይሆን ለተነሳበት ዓላማ ማለትም በትግሉ ሜዳ የወደቁት ጓዶቹ ወሬ ነጋሪ መሆኑን እስከ መጨረሻ ሊገፋበት መቻሉ ነው። በመሆኑም በመጽሐፉ ውስጥ ታሪካቸው የተዘከረላቸው የደራሲው ጓደኞች እያንዳንዳቸው በፍጹም የማይረሱ የመጽሐፉ ተዋንያን መሆን መቻላቸው ነው። ገና ከመጽሐፉ መጀመርያ ላይ የታሪኩን ባለቤቶች ደራሲው ሲያስተዋውቅ በሰዕላዊ ጥብብ በአንባቢው አዕምሮ ውስጥ የማይረሳ ቦታ ይይዛሉ። የመጽሐፉን ዋና ዋና ተዋንያን ደራሲው እንዴት እንዳስተዋወቀ ትንሽ ቀንጨብ አድርገን ብንመለከት፣ በራስ መኮንን ድልድይ ላይ ሳምሶናይቱን ይዞ እየፈራ እየቸረ የሚታየውን ብርሃኑን፣ ጨዋ፣ ደግና መልክ መልካሙን ወልደ አብን፣ የተንጨባረረ አፍሮ ያበጠረውና ጭንቅት የማይሆንለትን ካሳዬን፣ ሲጋራውን ሁሌ የሚያቦነውን መሐመድ አራቢን፡ ስለመልኩ ሁሌ ተጨናቂውን አብርሃምን፣ ውዘተ መጽሐፉ ከጀመረ አንስቶ የት ይገቡ የት ይደርሱ ይሆን እያልን ከነሱው ጋር ሊቆዩ እስከቻሉበት ድረስ እንቆያለን። መጨረሻም “እንኳን ሞታችሁ አልቀራችሁ፣ እንኳን አውቅናችሁ” እንላቸዋለን።
አንዳንድ ሰዎች ምናልባት ደራሲው በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ባቀረበው ትረካ ላይ ተሞርኩዞ አሁን በኢትዮጵያ ላለው የፖለቲካ ችግር ተመሳሳይነትም ሆነ ልዩነት አስተያየት ቢሰጥ ሊፈልጉና ሊመኙ ይችሉ ይሆናል። ይህንን በሚመለከት ደራሲው ካለፈው ተምረን ወደፊት ይህ እንዳይደገም አጭር ምክር ለኛ ከማቅረብ አይዘልም። ይህ አንዳንድ አንባብያንን ምናልባት ቅር ሊያሰኝና ለምን ግልጽ አቋም አያንጸባርቅም ሊያስብላቸው የሚችል ቢመስልም፣ የመጽሐፉን መሰረታዊ ዓላማ ግን አይቃረንም። “ፈረስ ያደርሳል እንጅ አይዋጋም እንዲሉ”፣ ደራሲው ያለፈውን ጊዜ ድክመት ነገር ግን በመልካም ዓላማና ዘዴ የሚመራቸው ዘዴ ደግሞ ቢያገኙ የኢትዮጵያውያንን የዓላማ ጽናትና ሀሳብን ወደተጨባጭ ውጤት የመቀየር ችሎታ አሳይቷል። ቀሪው አዕምሮ ያለው ከዚህ ስሕተት ተምሮ ድጋሚ ስሕተት ላለመሥራትና ለመልካም ውጤት መታገል ያለበት መሆኑን ብቻ ነው ደራሲው የሚመክረን።
ከኔ ክራሴ ታሪክና ልምድ አንጻር ከወሬ ነጋሪ የተማርኩት ፍሬ ነገር አስካሁን የደራሲውን የመሰለ አንባቢን የሚስብ ወይም የሚማርክ ታሪክ በትንሽ ፍራክሽን ያህል እንኳን የሌለኝ ቢሆንም፣ መቼም በግርግሩ ውስጥ ያለፍኩ በመሆኑ ነገሮችን ከሳጥን ባልወጣ (out of the box) ሃሳብ ሳብጠለጥላቸው ቆይቼ ነበር። በተለይም ኢሕአፓ በፕሮፌሰር ፍቅሬ መርዕድ ላይ ቃታውን ከሳበበት ጊዜ ጀምሮ ለኢሕአፓ መልካም አስተሳሰብ ኖሮኝ የማያውቅና ይህንንም ባገኘሁት አጋጣጥሚ ሁሉ ሳንጸባርቅ ነበር የቆየሁት። ወሬ ነጋሪን ካነበብኩ በኋላ ግን መጽሐፉ ድርጅቱን ከጭፍራው እንድለየውና፣ በድርጅቱ ውስጥ ምን ያህል የኢትዮጵያዊነት ፍቅር የሚያንገበግባቸው መልካም ወጣት ዜጎች እንደነበሩና፣ በግለሰብነታቸው ምን ያህል የሚወደዱ፤ በእምነታቸው ጥንካሬ ምን ያህል የሚያስቀኑ፣ ሀሳብን
ወደ ተጨባጭ ሥራ የመተርጎም ችሎታቸው የጸናና ወሰን እንኳን የማያውቅ ጀግኖች አባላት እንደነበሩት ወሬ ነጋሪ እንዳውቅ ረድቶኛል። ለዚህም ለወሬ ነጋሪ ደራሲ ለአቶ መሐመድ ይማም ጥልቅ ምስጋናዬን አቀርባለሁ።
ወሬ ነጋሪ ን በኢንተርኔት ገብቶ ጉግል በማድረግ አማዞንን ጨምሮ በተለያዩ ድሕረ ገጾች የሚገዛበትን አድራሻ ማግኘት ይቻላል። ገዝታችሁ ብታነቡት ወሬ ነጋሪ ወርቅማ የንባብ ጊዜ እንደሚለግሳችሁ አልጠራጠርም።
ኤፍሬም የማነብርሃን

No comments:

Post a Comment