ልዩ ሀይል እየተባለ በሚጠራው ታጣቂ ሚሊሺያ ከፍተኛ የዘር ማጥፋት፣ አስገድዶ መድፈርና የሰብአዊ መብቶች ጥሰት መፈጸሙን የሚያመለክት ዛጋቢ ፊልም በስዊድን ቴሌቪዥን መለቀቁን ተከትሎ ፣ የክልሉ መንግስት ምክትል ፕሬዚዳንቱን ቃለመጠይቅ በማድረግ አዲስ ዘጋቢ ፊልም ሰርቶ አቀረበ።
የክልሉ መንግስት በለቀቀው አዲስ ፊልም የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አድናቆታቸውን የገለጹበት ክፍል የተካተተ ሲሆን፣ ይህም የፌደራሉ መንግስት ጉዳዩን አያውቀውም በሚል የመንግስት ባለስልጣናት ሲያስወሩት የነበረውን ወሬ ውድቅ ያደርገዋል ሲል በጉዳዩ ላይ አስተያየቱን የጠየቅነው የአጠቃላይ ሂደቱ ዋና ተዋናይ የሆነው ወጣት አብዱላሂ ሁሴን ገልጿል።
አብዱላሂ እንዳለው የክልሉ መንግስት ራሱን ለመከላከል በለቀቀው አዲስ ፊልም ውስጥ፣ የተቀነባበረውን ድራማ በመምራት ከፍተኛ ሚና የተጫወቱትን የክልሉን ምክትል ፕሬዚዳንት አብዱላሂ የሱፍን ቃለምልልስ አካቷል። በፊልሙ ውስጥ ምክትል ፕሬዚዳንቱ በወቅቱ የወሰዱት እርምጃ ትክክል እንደነበር ገልጸዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የስዊድን የመገናኛ ብዙሀን ጉዳዩ በቶሎ ወደ አለማቀፍ ፍርድ ቤት ስለሚሄድበት ሁኔታ ሰፊ ሽፋን ሰጥተው ዘግበዋል።
ጠበቃ ስቴላ ጋርደ አፍቶን ብላድተ ለተባለ ጋዜጣ እንደገለጡት ማስረጃው ለስዊድን አለማቀፍ የወንጀል ምርመራ ጽህፈት ቤትና በስዊድን የጦር ፍርድ ቤት እንደሚቀርብ ገልጸዋል። የስዊድን መንግስት በኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ላይ ክስ ለመመስረት ጉዳዩን እንደሚያጠናው ጋዜጣው ዘግቧል።
ጉዳዩ የስዊድን ጋዜጠኞችን የሚመለከት በመሆኑም ኢትዮጵያ አለማቀፍ ፍርድ የወንጀል ፍርድ ቤት አባል ባትሆንም ጉዳዩ ወደ አለማቀፍ ፍርድ ቤት ሊሄድ እንደሚችል በዘገባው ተመልክቷል።ወጣት አብዱላሂ እንደተናገረው ጠበቃ ስቴላ ጋርደ የተለያዩ አለማቀፍ ድርጅቶችን እያነጋገሩ ጉዳዩን ወደ ፊት እየገፉት ነው።
የስዊድን የጦር ፍርድ ቤት ማስረጃዎችን ለመመርመር ለአርብ ቀጠሮ ይዟል።
No comments:
Post a Comment