በመስከረም አያሌው
ኢትዮጵያ አፍሪካን መምራት ካለባት የዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት (አይ ሲ ሲ) ወንጀል ፈፅመዋል በተባሉ የአፍሪካ መሪዎች ላይ የመሰረተውን ክስ አስመልክቶ በፍርድ ቤቱ ላይ ያላቸውን አቋም እንዲያርሙ ማድረግ አለባት ሲል የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ (ኢራፓ) አሳሰበ።
ፓርቲው ለዝግጅት ክፍላችን በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው ኢትዮጵያ ከሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች በተለየ ሁኔታ በአፍሪካ ኅብረት የወጡ ሕጐችን በመፈፀም እና በማስፈፀም ረገድ ቀዳሚ ኃላፊነት የሚሰማትና አርአያ ሆና መገኘት ይጠበቅባታል። በመሆኑም አፍሪካን መምራትም ካለባት አፍሪካን ማገዝና የራሷ ድርጅት አድርጋ መሳተፍ ካለባት የአፍሪካውያኑን አቋም በፍጥነት ማረም ይገባታል ብሏል።
የአፍሪካ መሪዎች ከአይ ሲ ሲ አባልነት እንዲወጡ የማድረግ እንቅስቃሴው ለስልጣናቸው ከማሰብ የዘለለ ዓላማ የሌለውና የተጐጂ ዜጐችን ፍትህ የማግኘት መብት ከግምት ውስጥ ያላስገባ በመሆኑ አቋሙን በድጋሚ ተረጋግተው በጥልቀት መመርመር እና መፈተሽ ይገባቸዋል ሲል ፓርቲው አቋሙን አስቀምጧል። አፍሪካ በተደጋጋሚ የሰብአዊ መብት ጥሰት የሚፈፀምባት አህጉር በመሆኗ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ቅድሚያ ተሰጥቶ ሊሰራበት የሚገባ ከመሆኑ አኳያ ዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ለመብት መከበርና ፍትህ ለማስገኘት የሚያደርገው እንቅስቃሴ ሊያስመሰግነው የሚገባ እንጂ ስራው እንዲጓተት ማድረጉ አግባብነት የለውም ብሏል ፓርቲው።
የአህጉሪቱ መሪዎች ለህዝብ መብት መከበር ቆመናል የሚሉ ከሆነ ፍርድ ቤቱን መቃወማቸውን በመተው የተሸሸጉ ወንጀለኞችን ለፍርድ በማቅረብ የተጠቃውን ሕዝብ እና ፍርድ ቤቱን ሊያግዝ እንደሚገባ ፓርቲው ገልጿል። በተጨማሪም መሪዎቹ በሰከነ መንፈስ ተጐጂው ሕዝብ ፍትህ እንዲያገኝ እና መብታቸውን በዘላቂነት የሚከበርበት ሁኔታ እንዲያሰፍን ጠይቋል።
No comments:
Post a Comment